5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከሀዲው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን በክልልና በዘር ከመከፋፈል አልፎ ጎረቤት ሀገራትን ጭምር በጎሳና በዘር ሲያባላ እንደነበር ተናግረዋል።
“ሶማሊያ ስንሄድ እኛ እኮ እናንተን አናምናችሁም፤ በክልልና በጎሳ ከፋፍላችሁ የምታባሉን እናንተ ናችሁ፤ የእናንተ መንግስት ነው ይህን የሚያደርገን፤ በጣም ነው የምንጠላችሁ” በማለት ሳይደብቁ ኢትዮጵያን ይወቅሱ ነበር ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
“በተመሳሳይ ደቡብ ሱዳን ስንሄድም አሁን ላይ በሀገራችን እየተባላንበት ያለው ጉዳይ የእናንተው ውጤት ነው” በማለት ኢትዮጵያን እንደሚወቅሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
“በኢጋድ ውስጥ ስዩም መስፍን የሚባለውን ሰውዬ መድባችሁ ከፋፍሎን አባልቶን ሄዷል” በሚልም በግልጽ የጁንታው አባላት በጎረቤት አገራት ላይ የሰሩትን የከፋፋይነት ሴራ ለመንግስት እንደሚናገሩ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት።
ዶ/ር ዐቢይ ይህንን በተናገሩ ማግስት ከሃዲው የህውሃት ቡድን ለደቡብ ሱዳን ህዝቦች ሰላም ማጣት እጁ እንደለበት በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ገልጸዋል።
አምባሳደር ጄምስ ፒታ ሞርጋን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ድርድር በከሃዲው የህውሃት ከፍተኛ አመራር አማካኝነት በመደረጉ ለሱዳን ህዝብ አንዳችም ውጤት አላስገኘም።
የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ሂደትን በከሃዲው የህውሃት ቡድን አባል በሆኑት አቶ ስዩም መስፍን አሸማጋይነት ድርድሩ ቢደረግም፤ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ባለው የህወሃት የተዛባ አስተሳሰብና አድሏዊ አቋም ከውጤት መድረስ አለመቻሉንም አምባሳደሩ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ሂደት ላይ የከሃዲውን የህወሃት አፍራሽ ሴራን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር መግለጻቸውን አስታውሰው፣ እ ኤ አ በ2015 በሱዳን ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካካል በአዲስ አበባ የሰላም ስምምነት ቢፈረምም፣ በአደራዳሪው የጁንታው መሪ ስዩም መስፍን በወሰደው ግልፅ አድልዎ እውን እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በወቅቱ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለግጭቱ የታሰበውን መፍትሄ አላመጣም ብለዋል አምባሳደሩ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዳስደሰታቸው በመግለጽ ለደቡብ ሱዳን መንግሥት ከለላ መሆኑን ያብራሩት አምባሳደሩ ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የቆየውን መልካም ግንኑነት ይበልጥ ለማጠናከር የህወሓትን መጥፎ ፍላጎት ማጋለጥና ከሕዝብ እንዲነጠል ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
“ደቡብ ሱዳን በአንድ አመራር ታምናለች፣ እሱም የአብይ አህመድ መንግስትና አመራር ነው” ያሉት አምባሳደር ሞርጋን ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር አንጋፋ ነፃ ሀገር እንደመሆኗ ውስጣዊ ችግሮቿን በሰላማዊ መንገድ የመያዝና የመፍታት ልምድና እውቀት ያላት ሀገር ናት ብለዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም የሁለቱ አገራት ግንኙነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በህዝብ ለህዝብ ድንበር ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው አህጉራዊ ና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዛቸውን ገልፀዋል።
ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ተግዳሮት እንደምታልፍ እና የልማት ፕሮጀክቶ በተረጋጋና በተቀላጠፈ ሁኔታ እንደምትቀጥል ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። (ኢ.ፕ.ድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply