* ገና ከጅምሩ የመፈረካከስ አዝማሚያ እየታየባቸው ነው
በኢትዮጵያ ውስጥ በነጻ አውጪነትና በብሕር ድርጅትነት የሚታወቁ ሙሉ በሙሉ የተካተቱበት አዲስ የፓርቲዎች የምክክር ቤት (caucus) መቋቋሙ ተገለጸ። በስም ከተዘረዘሩት የምክክር ቤት አባል ድርጅቶች ውስጥ ከአፋር ሁለት፣ ከኦሮሚያ ሁለት፣ ከትግራይ አረና፣ የወላይታና የዶንጋ ሕዝቦች ይገኙበታል። በርካታዎቹ በምርጫ ሕዝብ ድምፅ የነፈጋቸው ሲሆኑ በፓርቲ ደረጃ መድረክ ሲገኝ፣ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ አዲስ አበባ ላይ አንድ ድምጽ ያገኘው ሕብርም አለበት። ስብስቡ ገና ከጅምሩ የመፈረካከስ ሁኔታ እየታየበት እንደሆነ ተገለጸ።
መንግሥት ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ጋር ሙሉ ውጊያ ገብቶ በነበረበት ወቅት ጡንቻ ያበቀሉ ያላቸውን እያጸዳና የሕግ ማስከበር እያካሄደ ነው በሚባልበት ወቅት ላይ፣ በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልል ይቀሰቀሳል የተባለው ውጊያ እንዳይነሳ ተደርጎ አከርካሪው እየተሰበረ ባለበት ወቅት ይህ ኅብረት መመስረቱ በርካቶችን ከጅምሩ አወያይቷል።
ትህነግ የፌደራል ኃይሎች ሲል መሥርቶት ከነበረው ጥምረት ጋር በግልጽና በኅቡዕ ግንኙነት እንዳላቸው በስም ሲጠቀሱ የነበሩ ፓርቲዎችን ያካተተው የምክክር ቤት ትህነግን በስም አላካተተውም። ከኦሮሚያ ኦፌኮን ኦነግ አባላት ናቸው። የኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚ የሆነው ጃዋር መሐመድ ይህንን የምምክር ቤት ዜና “ሰበር” ብሎ ከዘገበው ኡቡንቱ ጋር የመጀመሪያ ውይይት ሲያደርግ “ከማንም ጋር ለሰላም እሠራለሁ” ማለቱ ይታወሳል። ኅብረቱም ይፋ የሆነው ጃዋር ለፖለቲካ ሥራ ወደ ጀርመን ማቅናቱን ተከትሎ መሆኑም “ግጥምጥም” ወይስ በዕቅድ የተሠራ አስብሎታል። ከዚህ በፊት በትግራይ ትህነግ የፌዴራሊስት ኃይሎች ብሎ በሰበሰባቸው ወቅት ጃዋር እነ በቀለ ገርባን ልኮ እርሱ አዲስ አበባ ነበር የሰነበተው።
ብልጽግና የአገራዊ የምክክር መድረኩ ፓርቲው በተመረጠበት የኮንትራት ዘመኑን አስመልክቶ የሚነጋገረው ነገር እንደሌለ ማስታወቁ አይዘነጋም። የምክክር ቤት የተባለው የአስር ፓርቲዎች ስብስብ ገና ከጅምሩ ያስቀመጣቸው ሃሳቦች ቀደም ሲል እነ ልደቱ “የሽግግር መንግሥት” ከሚሉት አካሄድ ጋር መዛመድ እንደሚታይበት ዜናውን ተከትሎ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። መድረኩ ነጻ አውጪ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ካካተተ ለምን ትህነግን እና ኦነግ ሸኔን እንደዘለለ ግልጽ አለመሆኑም ተመልክቶበታል። ሆኖም ትህነግ በአረና፤ ሸኔም በኦነግ ተወክሏል የሚሉም አሉ። (Ethio 12)
እንደ ዑቡንቱ ዘገባ በሀገራዊ የምክክር መድረክ አካሄድ ላይ መሠረታዊ ቅሬታ አለን ያሉ 10 የሚደርሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓትን የሚያስገኝ ሀገራዊ ውይይት አማራጭን ለማቅረብ የሚያስችል የምክክር ቤት (Caucus) አቋቁመናል” ሲሉ በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
የምክክር ቤቱን የመሠረቱት ፓርቲዎችም
1- መድረክ
2- ህብር ኢትዮጵያ
3- የአፋር ህዝብ ፓርቲ
4- የአፋር ፍትህ እና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
5- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)
6- የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ
7-የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር
8- የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ
9- ዓረና ትግራይ
10- የዶንጋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መሆናቸው ተገልጾዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደዚህ ዓይነት ጥምረት ሲመሠረት የሥልጣን ጥያቄን ተከትሎ የሚያስነሳው ውዝግብ ኅብረቱ ሩቅ ሳይሄድ እንዲፈርስ የሚያደርገው መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል። ከዚህ ሌላ አመራር፣ የበጀት አመዳደብ፣ ውክልና፣ በአሸባሪነት የተመዘገቡ ወንጀለኛ ድርጅቶች የመካተታቸው ጉዳይ፣ የአማራ ውክልና አለመኖር፣ ወዘተ ገና ከጅምሩ ኅብረቱ ርቀት ሳይሄድ ባጭር የሚያስቀሩት አቀንጭራዎች ሆነው ብቅ እያሉ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ ያሳባሰብነው ይዘን እንቀርባለን።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
gi says
የኣሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ ነው። የፓርቲ ብዛት ለስልጣን ካለ ፍላጎትና ጥማት የሚመነጭ እንጂ ሌላ አዲስ ነገር ለሕዝብ ስላላቸው አይደለም። ለሕዝብማ መልካም ነገር ቢኖራቸው ሕዝብ በደገፋቸው በመረጣቸው ነበር። እንደ ኣሜሪካ ለመሆን ሲዳክሩ ሕዝብ ያላወቃቸው ለም ኣለኝ በሰማይ ናቸው። ኣለን ለማለት ከሆነ ይሞክሩት።