እውነትን መናገር ለራስ ነው የሚያምኑበትን ሳይናገሩ ከመኖር ይሰውረን!!!
ከአንድ አመት በፊት ልክ በዛሬዋ እለት ስለ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የማውቀውን ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እስከ ቂሊንጦ በሚል ርእስ አንዲት ጽሁፍ ጀባ ብዬ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ እነ ካሚል ሸምሱ ከቂሊንጦ ቃሊቲ ከዛም ወደ ቤተሰብ ተቀላቅለዋል፤ ደስ የሚያሰኝ ዜና ነው፡፡
በርካታ ጓደኞቼን ስለ ካሚል ሳጫውታቸው በቅድሚያ ግራና ቀኛቸውን ይመለታሉ፣ ይቀጥሉና አንገታቸውን እስቲሰበር ድረስ ወደ ኋላቸው ገልመጥ ይላሉ፣ ይቀጥሉና የአግአዚ ስናይፐር እንዳይመታቸው ይመስል ወይንም ነፍሴን አደራ በሰማይ በሚመስል መልኩ ሽቅብ ያንጋጥጣሉ፣ በመጨረሻም ራሴውኑ በጥርጣሬ አይን ይመለከቱና ስለ ካሚል ሸምሱ ያላቸውን አስተያየት በሹክሹክታ ይነግሩኛል፡፡
ብሽቅ ብዬ ትቻቸው ልሄድ ስልም ምክንያታቸውን ይገልጹልኛል፣ ‹ምን ነካህ አብረውን የተማሩት እነ እከሌ እከሊት እኮ የማእከላዊ ባልደረባ ሆነዋል፣ እነ እንትና እኮ የደህንነቱን መስሪያ ቤት ከሚያሾሩት ውስጥ ይመደባሉ፣ በዛ ላይ ደግሞ ባለትዳርና የልጆች አባት ነኝ› ሲሉ ይደመጣሉ፤ እንዲህ አካባቢያቸውን በአይነ ቁራኛነት ሲከታተሉ ሳይ አዝኜላቸዋለው፤ በአንጻሩ ደግሞ ለመብቱ መከበር ሲል ዋጋ የከፈለውንና ድል ያደረገውን ካሚል ሸምሱን ሳስብ ሀገራችን ሰው እንዳላጣች ማረጋገጫ ይሆነኝና እጽናናለው፡፡
ወዳጄ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የነጻነት ምልክት ሆነሀልና እንኳን ደስ አለህ! ከምትወዳቸው ቤተሰቦችህ ለመቀላቀል እንኳን አበቃህ፤ ከባለቤትህ ጋር ምን ያህል እንደምትዋደዱ አውቃለው፤ ካምፓስ እያለን ባለቤትህ ውጭ አገር ሆና ስትደውልልህ ‹ተራርቀን እስከመቼ?› ተባብላቹሁ የተላቀሳችሁበትን ጊዜ አስታውሳለው፤ ባለቤትህም እንኳን ከልደታ-ቂሊንጦ-ቃሊቲ ከመመላለስ አረፈች፤ አላህ እንኳን አንድ አደረጋችሁ!!!
በነገራችን ላይ ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች መካከል በቀዳማይ ሚኒስትራችን አይተ መለስ ዜናዊ ጥርስ የገባ ሰው ቢኖር ካሚል ሸምሱ ነበር፤ ይህንንም በአፍ ወለምታ የምናገረው ሳይሆን በማስረጃ ነው፤ ካሚል ሸምሱ በተለያየ ጊዜ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ መፍትሄ ለማፈላለግ ባደረገው ጥረት በርካታ ስብሰባዎችን መርቷል፤ ታዋቂው ደራሲ አሌክስ አብርሀም ካሚል በሻሸመኔ ከተማ ተገኝቶ ህገ መንግስቱን የተመረኮዘ ማብራሪያ ሲተረጉም የሚያሳይ ምስል በመጽሀፈ ገፁ ለጥፎ ተመልክተናል፡፡
ካሚል ሸምሱ በተደጋጋሚ የሚናገረው አንድ ኃይለ ቃልም ነበር፣ ‹መንግሥት እኛን ወንጀለኛ ብሎ ለማሰር ማስረጃ ሳይሆን መረጃ የለውም› የምትል ነበር፤ የሰዎችን ሀሳብ የራሳቸው እንደሆነ አድርገው ማቅረብ የሚቀናቸው አይተ መለስ ዜናዊ ፓርላማ ላይ እንደ ጎበዝ ተማሪ ከፊት ወንበር ላይ ተሰይመው፤ ‹ኮሚቴዎቹን ለማሰር ማስረጃ መረጃም አለን› ሲሉ ተናገሩ፤ የካሚል ሸምሱ አነጋገር እንቅልፍ ነስቷቸው እንደነበር ራሳቸውን በራሳቸው አጋለጡ፡፡
ጥርስ ውስጥ የገባው ካሚል ሸምሱ ፌዴራል ፓሊስ፣ የደህንነት መስሪያ ቤቱ፣ ኢቲቪ፣ ማእከላዊ፣ ቂሊኒጦና ቃሊቲን የመሳሰሉ የመንግሰት ተቋማት ተባብረው አብጠርጥሮ የሚያውቀውን ሰብአዊ መብት አንድ ሁለት … እያሉ አራቆቱት፡፡ አሸባሪ ነህ ሲሉም ሮቦት ዳኞች ፈረዱበት፤ ከወህኒም ጨመሩት፤ ጊዜ ለኩሉ እንዲል ጠቢቡ ከፍርግርጉ ጀርባ የነበረውን ካሚል ሸምሱ እውነት ነጻ አወጣችው፤ ምናልባትም አንዳንድ የዋሆች ይህንን የህወኃት ድርጊት ‹ምህረት› ብለው ይጠሩት ይሆናል፡፡
አትሳሳቱ ! ኮሚቴዎቻችን የታሰሩት፣ የተሰቃዩትና የተፈረደበቸወ ጥፋተኞች ሆነው እንዳልሆነ ራሱ ወያኔ አሳምሮ ያውቀዋል፤ እነ ካሚል ሸምሱን ነጻ ያወጣቸውም እውነትን ይዘው እስከ መጨረሻው በመጓዛቸው ነው፤ መሀሪ የሚባል የወያኔ አባል ሊኖር ይችላል፤ ወያኔ ግን መሀሪ አይደለም፡፡
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply