
በእኛ ሀገር የሚከበሩ የህዝብ በዓላት በህግ የታወቁ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለምአቀፍ ተቋማት እንዲሁም ኢምባሲዎች እና የቆንፅላ ጽ/ቤቶችም የእኛን ሕዝብ በዓላቶች እንዲያከብሯቸው ይጠበቃል። ምክንያቱም በዓላቱን ማክበር ህዝብን ማክበር ከዚያም ሲያልፍ ሀገሪቱ ሉዓላዊ መሆኗን ማረጋገጥ ነውና።
እነዚህ በዓላት የዘመን መለወጫ በዓል (መስከረም 1)፣ የዓደዋ ድል መታሰቢያ ቀን (የካቲት 23)፣ የድል ቀን (ሚያዝያ 27)፣ የዓለም የሠራተኞች ቀን፣ መስቀል (መስከረም 17)፣ ጥምቀት (ጥር 11)፣ የክርስቶስ ልደት(ታህሳስ 29/28) እንዲሁም ቀናቸው በየዓመቱ የሚቀያር ስቅለት፣ ትንሳዔ፣ ፣ኢድ አልአድሃ፣ መውሊድና ኢድ አል ፈጥር ናቸው። በእነዚህ ቀናት እንደሁኔታው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የግል ድርጅቶችና የንግድ ሱቆች ለሕዝብ አገልግሎት ዝግ ሲሆኑ ይስተዋላል።
አንድ ሠራተኛ በነዚህ ቀናት ስራ ባይሰራም ቀጣሪው መስሪያ ቤት /ድርጅት/ ሙሉ ደመወዝ እንዲከፍል ህግ ያስገድዳል። ምናልባትም በስራው ባህሪ ምክንያት አንድ ሰው በእነዚህ ቀናት ውስጥ የሚሰራበት ድርጅት የሚያሰራው ከሆነ በልዩ ቀመር ተጨማሪ ክፍያ ቀጣሪ መስሪያ ቤቱ እንዲከፍል የአሰሪ እና ሠራተኛ ህግ ያስገድዳል። የዚህን ዝርዝር አልሄድበትም። የፅሁፍ ዓላማም አይደለም።
ዛሬ (ጽሁፉ ትላንት የወጣ ነበር) ግንቦት 20 ነው። ኢህአዴግ ደርግን ያስወገድኩበት ቀን ነው ይላል። ኢህአዴግ አሁን መንግስት መስርቷል። ዛሬ የህዝብ በዓል ነው በማለት በተለይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ናቸው። አዲስ አበባ ያሉ አንዳንድ ኢምባሲዎች ቀኑን የህዝብ በዓል አድርገው አገልግሎት እንደማይሰጡ ድረገፃቸው ላይ አስቀምጠዋል። ለአብዛኛው ሰራተኛ የእረፍት ቀን ነው።
ግን ለመሆኑ ግንቦት 20 በህግ የታወቀ ከላይ እንደጠቀስኳቸው ዓይነት ደረጃ ያለው የህዝብ በዓል ነው? ለምንስ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዛሬ ዝግ ሆኑ? ይህንን ለመመለስ ዋነኛ መሠረታችን በ 1967/75 የሕዝብ በዓላትን እና የእረፍት ቀንን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 16/1967 ነው። በዚህ አዋጅ መቼም ደርግ በ1967 ዓ.ም ግንቦት 20፤ 1983 በኢህአዴግ እንደሚወገድ ተንብዮ የህዝብ በዓል ያደርገዋል ተብሎ አይገመትም። (ስለዚህ) አልተካተተምም።
ከ1967 በኋላ የህዝብ በዓላት እና የእረፍት ቀንን በተመለከተ የወጣው ብቸኛ ህግ በ 1988/96 የወጣው አዋጅ ቁጥር 29/1988 ነው። ይህ አዋጅ የበፊቱ ማሻሻያ ነው። ያሻሻለውም አዋጅ 16/1967 አንቀፅ ሶስትን ብቻ ነው። አንቀፅ 3 ደግሞ “የድል ቀን” ስያሜን እና ሚያዝያ 27 መከበር እንዳለበት አድርጎ አሻሽሎታል። ከዚህ ውጭ የማሻሻያ አዋጁ ያለው ነገር የለም። ግንቦት 20ንም እንደ አዲስ በዓል አላካተተም። ታዲያ ግንቦት 20 ከየት መጦ ነው የሕዝብ በዓል የሆነው? ይሄንን አስመልክቶ ከ 1988 በኋላ ህግ ወጥቶ እንደሆን ፈልጌ አላገኘሁም።
በነገራችን ላይ ህግ ስለሌለ ብቻ ሳይሆን እንዲሁ ዝም ብሎ በአመክኖዊ አስተሳሰብ ግንቦት 20 የህዝብ በዓል ሊሆን አይገባውም። ብሄራዊ በዓል እና የድርጅት በዓል መለያየት አለባቸው። ግንቦት 20 የድርጅት በዓል እንጂ ብሔራዊ በዓል አይደለም። ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ለራሱ ማክበር ይችላል። መብቱ ነው። የመንግሥት ተቋማትን እና ህዝቡን ግን በህግ ቋንቋ መዝጋት እና ማስገደድ አይችልም።
ነገሩ እንዳለመታደል ሆኖ እኛ ሀገር የፖለቲካ ፓርቲ እና መንግሥት ተቀላቅለዋል። በአሰራር አንድ ናቸው። መከበር አለበት ቢባል እንኳን ኢህአዴግ ህግ ሳይኖር ግንቦት 20 ይከበር ከሚለን ህግ አውጥቶ አክብሩ ቢል ምን ይሳነዋል። ህጉን በፓርላማ ማፀደቅ ይችላል። ሙሉ መቀመጫ እስካለው ድረስ። ያለምንም ህጋዊ መሰረት ይከበር ማለት ግን ህዝብን በትልቁ እንደመናቅ ይቆጠራል። ሰራተኛውም ማረፍ ስለሚፈልግ ቀኑን በስምምነት ዝግ ያደርገዋል። ይሄ ድርጊት በየዓመቱ ተለመደና ግንቦት 20 ብሔራዊ የህዝብ በዓል ሆኖ አረፈው።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply