
ለዲ/ን ዳንኤል ክብረት የተሰጠ ምላሽ
ስለ ፈላስፋው ዘረ-ያዕቆብ ሙህራንና ጻህፍት በሁለት ተከፍለው ኢትዮጵያዊ ነው፣ ኢትዮጵያዊ አይደለም በማለት ይከራከራሉ። ኢትዮጵያዊ ነው ከሚሉት ውስጥ ዋናዋናዎች ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ አብርሃም ደሞዝ፣ የኔታ አለማየሁ ሞገስ፣ ፈንታሁን ጥሩነህ፣ ብሩህ አለምነህ ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያዊ አይደለም ከሚሉት ውስጥ ዋናዋናዎች ኮንቲ ሮሲኒ፣ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ ፍስሐ ታደሰ፣ ሰሎሞን አበበ ቸኮል፣ ካሳሁን አለሙ፣ ታሪኩ ውብነህ ይገኙበታል። ሁለቱም ቡድኖች የሚያሳምኑም የማያሳምኑም ሃሳቦችን ይሰነዝራሉ።
ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ አይደለም ከሚሉት ውስጥ ጥልቅ የሆነው እና የሌሎችን (በተለይም የኮንቲ ሮሲኒን) ሃሳብ የሚያንፀባርቀው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ስለሆነ ‘የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ እና ሌሎች’ በሚል ካሳተመው መፅሀፍ የጠቀሳቸውን የኮንቲ ሮሲኒና ራሱ ዳንኤል ክብረት የጨመራቸውን ሃሳቦች በአንድ በኩል እና የኔን አስተያየት እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
- የዘርአ ያእቆብ የዓለም ስሙ ‹ወርቄ› ነው፡፡ ወርቄ የሚል የስም አወጣጦች በአማራው አካባቢ እንጂ በአኩስም አካባቢ የተለመደ ስሞ አይደለም፡፡ ዳ. ኡርቢኖ (መፅሃፉን እንደጻፈው የሚታማው) በደብረ ታቦር አካባቢ ሲኖር የሰማውን ስም መሆን አለበት የተጠቀመው፡፡ አክሱምም ቢሆን አክስም ውስጥ የተወለደበትን ቦታ አካባቢ ግን አይነግረንም፡፡ ኡርቢኖ አክሱም አካባቢ ስለነበረ ነው ይህን የትውልድ ቦታ የመረጠው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ፈላስፋ መኖርን እራሱ ያወቅነው ከአውሮፓውያን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሱ የሚወራ አፈ-ታሪክ እንኳን የለም።
መልስ፦ ዳ. ኡርቢኖ አክሱምም ጎንደርም ስለኖረ የት ምን አይነት የስም አወጣጥ እንዳለ ያውቃል ገ/ኪዳን ማለት አይጠፋውም፣ ቢሆንም አክሱም ውስጥ ወርቄ የሚባል ስም የለም ማለት በአማረኛ ስም የሚጠራ ሰው የለም እንደማለት ነው። ይህ አተያይ በፍልስፍና ከቀላል ፋላሲዎች አንዱ ነው። ግን ለምን ደብዛው ጠፋ? የዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና እንኳን ሊስፋፋ ይቅርና ለሕይወቱም አስጊ ሁኔታ ስለፈጠረበት እየተሽሎከሎከ ከመኖር ውጪ ሃሳቡን የሚያስፋፋበት እንኳ በቂ ሰላም አላገኘም። በድብብቆሽ እያለ ወልደሕይወትን በማስተማሩ ግን ቢያንስ አሁን ወደእኛ ትውልድ ሊደርስ የቻለውን የፍልስፍና መጽሐፍ ማግኘት ችለናል ይለናል ፈንታሁን ጥሩነህ። ራሱ ዘርዓ ያዕቆብም ከእኔ በኋላ የሚመጡ እንዲያውቁኝ ግን እስክሞት ድረስ በእኔ ዘንድ ሸሽጌ የምይዘውን ይህን ጽሑፍ ልጽፍ ወደድሁ ሲል ፍልስፍናው እንደ ግርካዊያን በአደባባይ እንዳላስተማረው ይጠቁመናል፣ በአደባባይ ማስተማር ነበረበት ብየ አልፈርድበትም ማስተማሩ ሞት ይዞበት ቢመጣ ጭራሽ ሳናውቀው እንቀር ነበር።
- ዘርአ ያእቆብ ትርጓሜ መጻሕፍት እንደተማረ ይነግረናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርት ብሉይ፣ ሐዲስ፣ ሊቃውንትና መጻሕፍተ መነኮሳት ናቸው፡፡ ዝርዝር ማቅረብ የሚወደው ዘርአ ያእቆብ ጠቅልሎ ‹መጻሕፍትን ተማርኩ› የሚለውን ለመቀበል አስቸጋሪ ነው፣ ያውም በዐሥር ዓመት፡፡ የሐዲሳት ትርጓሜ ብቻ አምስት ዓመት ይፈጃልና፡፡ ስለ መምህርነቱ ሲነግረን ‹በአክሱም መጻሕፍትን ለአራት ዓመት አስተምር ነበር› ይላል፡፡ የመጻሕፍት አስተማሪ የሚባል መምህር በቤተ ክርስቲያን የለም፡፡ የሐዲሳት መምህር፣ የብሉያት መምህር፣ የሊቃውንት መምህር፣ የመጻሕፍተ መነኮሳት መምህር እንጂ፡፡ ዘርአ ያእቆብ ዳዊትን በነጠላ ያውቀዋል፣ ሐዲስን አንብቦታል፡፡ ዘርአ ያዕቆብ ሊቃውንቱ ከሚታወቁበት ከትርጓሜ ሊቃውንት፣ ከመጻሕፍተ መነኮሳት፣ ከፍልስፍና መጻሕፍት ፈጽሞ አይጠቅስም፡፡ ዘርአ ያዕቆብ ዳዊት ከማወቅ፣ ሐዲስን ከማንበብ የዘለለ የብሉይ ትምህርት የለውም፡፡ ስለዚህም ከብሔረ ኦሪት አሟልቶ መጥቀስ ስላልቻል ሙሴ ሩካቤ ሁሉ ርኩስ ነው አለ ይለናል።
መልስ፦ በእርግጥ የቤተ ክርስቲያንን የትምህርት ደረጃዎች በብቃት ለማለፍ ረዥም አመታት እንደሚወስድ ይታወቃል፡፡ ለእነዚህ ተማሪዎች በትምህርታቸው ረዥም ጊዜ የሚወስድባቸው አንድም የትምህርት ስርዓቱ ሽምደዳ መሆኑና የስራ መደራረብ እና አስተማሪ መጥፋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ስራየ ጉዳየ ብለው የያዙት ተማሪዎች በ10 ዓመት ውስጥ ሊያጠናቅቁት ይችላሉ እንደ ቅዱስ ያሬድ፡፡ አንዳንዴም ታምር በሚመስል መልኩ አንዳንድ ሊቃውንት የትምህርቱን ሰንሰለት በአጭር ጊዜ እንደጨረሱ ይነገራል፡፡ ከዚህ አንፃር ዘርዓ-ያዕቆብ የአዕምሮ መጥቀቱ ከፍተኛ ስለሆነ በ10 አመት ሊያጠናቀው ይችላል፡፡ ለነገሩ ዘርዓ ያዕቆብ 10 አመት የፈጀበት አራቱን ጉባኤያት ለመማር እንጅ ጥቅል አይደለም፡፡ በብሩህ አለምነህ ሂሳብ በ1601 በ9 አመቱ ቄስ ት/ቤት ገባ፡፡ በ1604 በ12 አመቱ ንባብ ቤትን፣ ገበታ ሐዋርያትን እና ዳዊትን ተማረ፡፡ በ1604 የዜማ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ቅኔ እና ሰዋሰው ት/ት ፊቱን አዞረ፡፡ ከአራት አመት በኋላ በ1609 10 አመት ወደ ፈጀው የመፅሀፍ ቅዱስ ትርጓሜ ጥናት ተመለሰ፡፡ አራት አይናው ሊቅ በ1627 አክሱም ላይ የአራቱም ጉባኤያት መምህር ሆነ፡፡ ለ4 አመታት አስተምሮ ተሰደዶ፡፡ እነዳንኤል አልተማረም አላስተማረም የሚሉት በትምህርት ያሳለፈው 17 አመትና በማስተማር ያሳለፈው 4 ዓመት ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ለእኔ የማንሰላሰልና የአዕምሮ ብሩህነቱ ከፍተኛ ለሆነው እና ከመሸምደድ ይልቅ ይዘቱን ለመረዳት ለሚጥረው ዘረዓ-ያዕቆብ 17 አመት ሲበዛበት ነው፡፡ ኢህአዴግ እንኳን ገናናው ደርግን ለመጣል የፈጀበት 17 ዓመት ብቻ አይደል እንዴ! ሌላው የእነ ዲ/ን ዳንኤል ጥርጣሬ ለምን ከተማረ የተማረውን በፍልስፈናው ውስጥ አላስታወሰውም የሚል ነው፡፡ ለ17 ዓመታት የተማረውን ትምህርት እና ለ4 አመት ያስተማረውን አምሮ እንደሚተች በጥቅል ሀሳቡ ነግሮናል በተለይ ወደ አክሱም ተመልሶ እንዲያስተምር በተጠየቀበት ጊዜ የማላምንበትን አላስተምርም፣ የማላምንበትን አስተምሬ ሊቅ ከምሆን ይቅርብኝ ታራ ልሁን ብሏል፡፡ በሀተታው በጊዜው የነበረውን ሰርዓት በጥቅል ነገርን እንጅ በእየ መጽሀፍቱ ምን እንደተማረ እና ምን እንዳስተማረ አልነገረንም፡፡ የሚማረውም ያስተማረውም ያው የተለመደው ስለሆነ (ከአቀራረቡ በስተቀር)፡፡ አራት አይናው የመፅሃፍት መምህር ዘርዓ-ያዕቆብ ሙሴን ሩካቤ ሁሉ ርኩስ ነው ብሏል ያለበት ምክንያት ኦሪቱን በደንብ ስለተረዳው ነው፡፡ የሚገባው ይገባዋል።
- ዘርአ ያእቆብ መጻሕፍት ሲያስተምር ‹ፈረንጆች እንዲህ ይላሉ፣ ግብጻውያን እንዲህ ይላሉ እላለሁ› ብሏል፡፡ ለመሆኑ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የግብጽ ትርጓሜ አለ ወይ? ‹ለግብጻውያን ፈረንጅ፣ ለፈረንጆችም ግብጻዊ እመስላቸው ነበር› ይላል፡፡ ለመሆኑ ግብጻውያን ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ወይ?
መልስ፦ ኢትዮጵያ የምትከተለው ከግብፅ መጥቶ በተስፋፋ ስርዓት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአምልኮት ስርዓቱ ይቅርና የሚመሯት ጳጳሳት እንኳ የሚመጡት ከገብፅ ነበር፡፡ ከዚህን አንፃር የግብፅ ትርጓሜ ማለት የኢትዮጵያ ትርጓሜ ማለት ነው። የኢትዮጵያዋ ተዋህዶ እና የግብፆ ኮፕቲክ የአንድ አፈር አፈሮች ናቸው፡፡ ውሾችን እንደሰው የሚያናግረው ዳንኤል ይህን ሳይረዳው ቀርቶ ሳይሆን ብዙ ሃሳቦችን ለመደረት ሰለፈለገ ነው፡፡ አራቱ ጉባኤያት መጽሀፍት ስለየትኞቹ ሊቃውንት ነው የሚያወሩት ከግብፅ እና በግብፅ በኩል ስለመጡት አይደለምን?
- ‹ወልደ ዮሐንስ የተባለ አንዱ ጠላቴ ሊከሰኝ ሄደ› ይላል፡፡ አንድን የመጻሕፍት መምህር ለመክሰስ የአካባቢው ገዥ አንሶ ነው ወልደ ዮሐንስ ደንቀዝ ድረስ የሚጓዘው? እንደዛሬው መኪና፣ አውሮፕላንና ሌላም መጓጓዣ የለ፡፡
መልስ፦ በኢትዮጵያ ታሪክ ክስን ለንጉስ ማቅረብ የተለመደ ነው። ብዙ ታሪኮችን ብትሰሙ ነገስታቱ ረዳት የላቸውም እንዴ እስክትሉ ድረስ ጥቃቅን ጉዳዮችን የሚያዩበት ጊዜ አለ። በወቅቱ ከፍተኛ፣ መካከለኛ፣ ዝቅተኛ የሚባል ፍ/ቤት የለም። በተቻለ መጠን ሁሉም ጠቅሎ ያለው ነገስታቱ ጋ ነው፡፡ በተለይም እንደ ወለደ ዮሐንስ አይነት የንጉስ ወዳጆች ክሳቸውን ለጭቃ ሹም ማሰማት አይፈልጉም፡፡ ይህን ለመረዳት ወደኋላ የነገስታቱን የፍርድ ይዘት ማጥናት ተገቢ ሆኖ ሳለ ወደ ድምዳሜው መገስገስ አዋጭ አይደለም፡፡
- ዘርአ ያእቆብ ከአክሱም ወጥቶ ሁለት ዓመት ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን የንጉሡ መልእክተኛ ወደ እኔ መጥቶ ንጉሡ ፈጥነህ ወደ እኔ ና ይልሃል አለኝ፡፡ እኔም እጅግ ፈራሁ፡፡ የንጉሡ ሰዎች ይጠብቁኝ ነበርና እሸሽ ዘንድ አልተቻለኝም ይላል። ለእርሱ የአካባቢው ጭቃ ሹሙ አንሶ ነው ንጉሡ መልእክተኛ የሚልክበት? ምንስ ስለያዘ ነው የንጉሥ ሰዎች ከበው የሚጠብቁት? ለአንድ ሰው ሲባልስ የበሽሎ በረሓን ተሻግሮ፣ ላስታን አቋርጦ አምሐራ ድረስ እንዴት የንጉሥ ሰው ይላካል? ፈፋስፋውስ በጠዋት ተነሣሁና ሄጄ ወደ ንጉሡ ገባሁ ያለው እዚያው ቤተ መንግሥቱ አጠገብ የሚኖር ሰው ካልሆነ እንዴት? የማይመስል ነገር ነው፡፡
መልስ፦ እዚላይ እኔ ባነበብኳቸው የዘርዓ ያዕቆብ ሀተታዎች ስህተቶች መኖሩን አልክድም። ወደ መልሴ ልመለስና ዘርዓ ያዕቆብ ወደ እኔ ና አለኝ ንጉሴ ያለበት ምክንያት የተከሰሰው በንጉሱ ነውና ጉዳዩ የሚያይለት ንጉሱ ስለሆነ ነው፡፡
- ዘርአ ያእቆብ ከአክሱም ሸሽቶ ሲወጣ ‹ሦስት ወቄት ወርቅና መዝሙረ ዳዊት ያዝሁ› ይላል፡፡ ሦስት ወቄት ወርቅ ከየት አገኘ? በዚያን ጊዜ የመጻሕፍት መምህራን ቢበዛ እህል፣ ከብትና መሬት ይኖራቸዋል እንጂ ‹ሦስት ወቄት ወርቅ› ከየት ያገኛሉ? በሽሽቱ ወቅት ዘርአ ያእቆብ ወደ ሸዋ ለመሄድ ተከዜን ነው የተሻገረው፡፡ ትልቁን ወንዝ ዓባይን የት ትቶት ነው? መንገዱን በሚገባ አያውቀውም፡፡
መልስ፦ ሦስት ወቄት ወርቅ ማለት 84 (3×28) ግራም ማለት ነው። ሶስት ወቄት ወርቅ! በዘመነ ዘርዓ ያዕቆብ ሀብት የሚለካው በዶለር፣ በፓውንድ እና በብር አልነበረም። ወርቄ ይዞት የሸሸውን 3 ወቄት ወርቅ ሀብታም ነበር የሚያስብልም አይደለም፡፡ የዳንኤል ችግሩ ያም ቢሆን የት ተገኘ ነው፡፡ ዲ/ን ዳንኤል የመምህር ደሞዙ የሚከፈለው በእህል፣ በከብትና በመሬት እንደሆነ ነገሮናል እናማ የሚሰደድ ሰው እህሉን፣ ከብቶቹን ካለውም መሬቱን ሽጦ ያሰደዳል፡፡ ለነገሩ ከዚህ በፊት ከንጉሱ ቀርቦ 5 ወቄት እንደተሰጠ ነገሮናል። ሌላው የዲ/ን ዳንኤል ጥያቄ አባይ አልተጠቀሰም ከአክሱም ነው። ወደ ሸዋ ለሚጓዝ ሰው ተከዜን ሳያቋርጥ አባይ መድረስ ይችላልን? ዲ/ን ዳንኤል ዘርዓ ያዕቆብ አባይን አያውቀውም ይለናል ዘርዓ-ያዕቆብ ግን እንደሚያውቀው ሲነግረን ወደ ጎጃም ተሻግሬ (አባይን ተሻግሬ) መኖር ፈልጌ ነበር ሲል ነግሮናል፡፡ ከተነሳ አይቀር የኔ ጥርጣሬ የመንገዱ ጉዳይ ሳይሆን ዋሻው ሸዋ ክፍለ ሀገር መሆኑ ላይ ነው፡፡ በኔ ግምት ዘርዓ ያዕቆብ ያረፈበት ዋሻ ወሎ ይመስለኛል፡፡ አባይን ተሻግሮት ላይሆን ይችላል፡፡
- ዘርአ ያእቆብ ‹እስልምናን፣ ክርስትናንና አይሁድነትን› የሚተች መስሎ ቢቀርብም ትችቱ ግን በኢትዮጵያውያን ላይ ይከፋል፡፡ ለንጉሥ ሱስንዮስንና ለካቶሊክ አዳልቶ ንጉሥ ፋሲለደስና ኦርቶድክስን በጥላቻ ያነሳል።
መልስ፦ ይህ የተለመደ ነው፡፡ ዘርዓ ያዕቆብ የተመቸውን እያመሰገነ የጠላውን እየተቸ ነው የፃፈው፡፡ በእርግጥ ስለካቶሊክና አይሁዳዊነት እንዲሁም ስለ አፄ ሱስንዮስ የሚገባውን ያህል የተቸ ቢሆንም የትችት በትሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ን ላይ ይጠነክራል፡፡ ዲ/ን ዳንኤልን የከነከነው ይህ ነው። ለምን ቢባል ዘርዓ ያዕቆብ ከካቶሊክ እና ከአይሁዳዊነት ይልቅ ኦርቶዶክስን ያውቃታል፡፡ የአውሮፓ የማህበራዊ ትችት ፈላስፎች ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባህል እና እምነት ሳይሆን በየ ሀገሮቻቸው ስለሚገኙት ቤት እምነቶች ነው የሚጽፉት ዘርዓ ያዕቆብም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ ታላቁ ብዕረኛ ቶማስ ፔይን የሚተቸው በቅርብ የሚያውቃቸውን ቤተ እምነቶች ነው፡፡ ታዲያ ዘርዓ ያዕቆብ ኦርቶዶክስን አብዝቶ የሚነቅፈው ስለሚያውቀት እና ስለሚመለከተው ነው፡፡ ይህኔ ወደ ሌሎቹ ቢያተኮር ኑሮ ኢትዮጵያዊ አይደለም ለማለት ትልቅ ማስረጃ ያደርጉት ነበር እነ ዲ/ን ዳንኤል፡፡
- ዘርአ ያእቆብ የክርስቲያን ሕግ ግን ከጋብቻ ምንኩስና ትበልጣለች ባለች ጊዜ ሐሰትን ተናገረች፤ ከእግዚአብሔር የተገኘች አይደለችምና። ከየትኛው ህግ አምጥቶ ነው የክርስቲያን ሕግ ከጋብቻ ምንኩስና ትበልጣለች አይልምና።
መልስ፦ ዲ/ን ዳንኤል ኦሪቱን ተወው፣ ነበያትንም እንዲሁ፣ መጸሐፈ መነኮሳትን እና ልዩ ልዩ አዋልድ መፅሐፈትን ተዋቸውና ክርስቶስ የተናገረውን ወንጌል ብቻ አስተውለው። ማቴ 19፡16-25 “እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው። እርሱም። ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው። እርሱም። የትኞችን? አለው። ኢየሱስም። አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ጐበዙም። ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው። ኢየሱስም። ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ። እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው። ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና። እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ።” ድጋሜም ማቴ 19፡29 “ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።” ምንኩስና ከማግባት እንደሚበልጥና መቶ እጥፍ እንደሚያሸልም ያስተማረው ራሱ ክርስቶስ ነው። የዳንኤል ክብረት ሀሳብ አቃንቃኞች ሀዋርያው ቅዱስ ጳሎስ ያለውን አልሰማችሁም እንደ እኔ ሁኑ ነበር ያለው።
ፈላስፋው ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በሰፊው የፃፈው ምንኩስና በሰው ልጆች ላይ የጣለውን ጠባሳ ለማስረዳት ነው፡፡ ለፈለስፈው ከተፈጥሮ የሚያፈነግጥ የሀይማኖት ሰርዓት ከእግዚአብሔር አይደለም ይላል ልክ ነው፡፡ ተፈጥሮአችን እንድንጋባ፣ እንድንባዛ፣ እንድንደሰት እንጅ እንድንመነኩስ አይደለም፡፡ ወንጌል ግን ተፈጥሮአችንን ስለኮነነብን ከእውተኛው አምላክ አይደለም፡፡
- ዘርአ ያእቆብ ልጅ የወለደበትን ጊዜ ጥቅምት 11 ቀን 1631 መሆኑን ይነግረናል፡፡ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ ቢሆን ይህ ልማድ አይኖረውም ነበር፡፡ እንኳን ያኔ በዐፄ ምኒልክ ዘመንም የልጆች ልደት አይታወቅም ነበር፡፡ የነገሥታቱ ካልሆነ በቀር፡፡
መልስ፦ ዲ/ን ዳንኤል የማውቀው በነገሮች ላይ እጅግ አሳማኝ ሀሳቦችን እያነሳ ሲሞግት ነው፡፡ በፈላስፍው ዘርዓ ያዕቆብ ላይ ያነሳቸው ሃሳቦች ግን በቀላል አመክነዮ ውደቅ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸውን የተወለዱበትን ቀን አያስታውሱም ማለት ተገቢ ነውን? ተገቢነቱ ይቅርና እውነታውን እንይ ወለጆች የልጆቻቸውን ልደት በማስታወሻ ጽፈው የሚያዙ ነበሩ፣ በቃላቸው የሚያስተውሱትም ነበሩ። ቢያንሰ እንኳን ከነገሮች ጋር ማለት ከድረቅ፣ ከጦርንት፣ ከሌላ ሰዉ ሞት እና ከተለያዩ ማህበራዊ እና ተፈጥሮዊ ክሰተቶች አንፃር የልጆቻቸዉን ልደት ያሰተውሳሉ፡፡ በእርግጥ ልደት የሚከበርላቸዉ ልጆች ነበሩ ለማለት ያከብደኛል፡፡ በኢትዮጵያን ታራክ የሚታወቁ ገለሰቦች ታራካቸዉ የሚጀመረዉ በዚህ ቀን ተወለዱ በሎ ነዉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ልደታቸዉን መመዝገብ ያሰፈለጋዉ ታራክ ሰሪ መሆነቸዉ በልደታቸዉ ቀን ሰለታወቀ ነዉን? በጭራሽ ማንም ሰዉ እንደተወለደ ንጉሰ፣ ሀገር ገዥ፣ ቅዱሰ፣ ወታደር ይሆናል ተብሎ ለህይወት ታሪኩ ሲባል ማሰታወሻ አይያዝም፡፡ በተቻለ መጠን አብዛኛዉ ሰዉ ልደቱን የሚያዉቀዉ ከመላጆቹ ማሰታወሻ ነው፡፡ ወይስ ዘርዓያቆብ ልጀን የወለድኩት የአቶ ጨቡዴ በሬ ገደል የገባ ቀን ነዉ ብሎ ይጻፋ፡፡ ይህ 17 ዓመት ከተማሪና ከተመራመረ ሰዉ አይጠበቅም፡፡ ለነገሩ የልጁን ልደት መጥቀሰ ለምን አሰፈለገ? አጭር መልስ የአፃፃፍ ዘይዴዉ ሰለሆነ ይህን ለመረዳት ሀተታዉን ደግም ማንበብ ነዉ፡፡
- ከሳሹ ወልደ ዮሐንስ ዘርአ ያዕቆብን እንፍራንዝ ድረስ ይከታተለዋል፡፡ ዘርአ ያዕቆብ እንፍራንዝ ውስጥ ከሀብቱ ዘንድ ተጠግቶ በጽሕፈትና በድጉሰት ነበር የሚኖረው፡፡ ያንን ያህል የታወቀና ተጽዕኖ ፈጣሪ አልነበረም፡፡ ታድያ ወልደ ዮሐንስ ለምን ይከታተለዋል? ሁለቱም እዚያው ደንቢያ ውስጥ የሚኖሩና ቀድመው የሚተዋወቁ ሰዎች ካልሆኑ በቀር፡፡ ዘርአ ያዕቆብ እንደሚለው ወልደ ዮሐንስ አኩስማዊ ነው፡፡ በኋላ ግን በደንቢያ አድባራት ላይ ተሾመ፡፡ ነገሥታት በባህላቸው አብዛኛውን ጊዜ ሰውን የሚሾሙት በተወለደበት ቦታ ነው፡፡ እናም ወልደ ዮሐንስ የዚያው የደንቢያ ሰው ቢሆን ነው ደንቢያን የተሾመው፡፡ ስለዚህ ፈላስፋው ዘርአ ያዕቆብ ይኖር የነበረው ማኅደረ ማርያም አጠገብ ሳይሆን አይቀርም እናም አክሱማዊ ነኝ ማለቱ ዋሽቷል፡፡
መልስ፦ ይህ ሀሳብ መሰረት ያለዉ መከራከርያ ነዉ፡፡ ትችቱን ዘርዓ -ያቆብ ኢትጵያዊ ነዉ የሚሉትም የጋሩታል በተለይ ፕ/ር ጌታቸዉ ሀይሌ፡፡ ይህ መከራከርያ ለኔም ግራ ገብቶኛል፣ እሰከአሁን የዘረዘረኳቸዉ እና ቀጣይም የምዘርዝራቸዉ የሀሳብ ደርቶውች ናቸዉ፣ ይህኛዉ ግነም ፈታኝ ነዉ፡፡ እንደ ማንኝዉም ግለሰብ ግምቴን ማሰቀመጥ ግን ግድ ይሆንብኛል። አንድም ምን አልባት ከሳሹ ወልደ ዮሀንሰ የእንፍራዝ ተወላጅ ቢሆንሰ፡፡ ተዲያ ትግራይ ምን ወሰደዉ እንደትሉኝ ቄሶች ከቦታ ቦታ መዘዋወር ልማዳቸዉ ነውና በተለይም ተረጋጋግተዉ እሰኪቀመጡ፡፡ ዘርዓ-ይዕቆብ ከአክሱም ከህናት አንዱ ማለቱ አክሱምዊ ከህን ማለቱ አይመለኝም፡፡ ከጎጃም ተነሰቶ ጎንደር የከተመ ካህን የጎጃም ካህን አይባልም። ካህናት የሚጠሩት በሚያገለግሉት ደብር ሰም ነዉ፡፡ የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ካህናት፣ የደብረ ብርሀን ስላሴ ቤ/ን ካህናት ከየትም ይምጡ። ሁለትም ምን አልባት ወልደ ዮሀንሰ የአክሱም ሰዉ ሁኖ ሳለ ባልተለመደ ሁኔታ በደንቢያ አካባቢ ቢሾምስ፡፡ ወልደ ዮሀንስ የትም ይሁን የት የዘርአያእቆብን ምንፈቅና ደርሰበታል፡፡ ሰለዚህ በምንኛዉም አጋጣሚ፣ መክሰስ ይፈልጋል፡፡ በንጉሱ ፊት ባሰቀረበዉ ጊዜም ዋሽቶ ተለቀቀ እንጂ የሞቱን ፅዋ ሊጠጣ ነበር፡፡ ንጉሱ በፈለሰፈዉ ንግግር ሰለተደመሙ ከማሰር ይልቅ 5 ወቄት ወርቅ ሰጥተዉ ሸኙት። ሱሰንዮሰ ፈላስፋዉን አሰቀርቶ እየተመከከሩ ሀገሪቱ ቢያቀኗት ኑሮ ሱሰንዮሰ እንደ ታላቁ አሌክሳንደር ዘርዓ-ይዕቆብም እንደግሪክ ፈላሰፎች ይሆኑ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ግንኙነቱ በአጭር ከሸፈ። ዘርአ-ያቆብና ወልደ ዮሀንሰ ትዉልድ ቦታቸዉን በተመለከተ በሀተታዉ ግልፅ ያላሆነ መሆኑ እና ብዙ ተመራማሪዎች ጥርጥሬያቸዉን መግለፅቸዉ ሙሉ ሀተታዉን ዋጋቢስ አያደርገዉም፡፡ ቢያንሰ ሁለቱ ግለሰቦች የደንቢያ ሰዎች መሆናቸዉና አለመሆናቸው ሰለልተረጋጋጠ፡፡ የደንቢያ ሰዋች እንኳ ቢሆኑ አዉሮፓዊያንም ቢሆኑ እኛ እምንፈልገዉ ፍልስፍናዉን ነዉ፡፡
- ዳ. ኡርቢኖ ለዲ አባዲ የላከውና በግእዝ የጻፈው የገንዘብ መጠየቂያ ደብዳቤውና በሐተታ ዘርአ ያዕቆብ ላይ ዘርአ ያዕቆብ ሀብቱን ድግፍ የጠየቀበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ በደብዳቤውና በመጽሐፉ ውስጥ ተመሳሳይ የግእዝ ቃላት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ‹ፍሬ ጻማየ› የሚለው አገላለጥ በሐተታ ዘርአ ያዕቆብ ሁለት ጊዜ፣ በሐተታ ወልደ ሕይወት አንድ ጊዜ ይገኛል፡፡ በዳ. ኡርቢኖ ደብዳቤም ይሄው አገላለጥ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በ1852 በመጋቢት ወር ርዳታን አስመልክቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‹ሀብታም በከብት ደኃ በጕልበት› የሚል ገለጣ ተጠቅሟል፡፡ ይህ አባባል ለአንቶኒዮ ዲ. አባዲ. በ1853 በተላከው የ‹ሐተታ ዘርአ ያእቆብ› ቅጅ የላቲኑ ደብዳቤ ላይ ይገኛል።
መልስ፦ ይህ ኡርቢኖ ለአለቃዉ ዲ አበዲ ገንዘብ እንዲሰጠዉ እና እርዳታዉ እንዳይለየዉ የሚማፀንበት ደብዳቤዎች ከሀተታ ዘርአ-ያቆብ ጋር መመሳሰል ያዉም በቃላት ደረጃ፣ እንዲይመዉ የሚገረመዉ ኡርቢኖ ጌታዉን ዲ. አበዲን እና ደብተራዉ ዘርአ ያቆብ ጌታዉን ሀብቱን እርዳታ የጠየቁበት መንገድ ቢለያይ ነዉ፡፡ የሚለምን ሰዉ መለማመጥድ አለበት ይህን ሁለቱንም አድርገዉታል፡፡ በቅዱሰ ገብርኤል ቀን ስለቅዱሰ ገበርኤል ብለዉ የሚለምኑ ሰዋች አንድ ሳይሆኑ አንድ አይነት ሀሳብ ሰላላቸዉ ነዉ፡፡ የቅዱሰ ገበርኤል ቀን ሰለቅዱሰ ጊዮርጊስ እያለ ቢለምን ብዙ ላያገኝ ይችላል፡፡
- ዳ. ኡርቢኖ በኢትዮጵያ የመጻሕፍትህ ጠባቂ፣ አንባቢ፣ ጸሐፌና ተርጓሚ ሲል የገለጠበት መንገድ ራሱን ከሚሲዮናዊነቱ ይልቅ በእነዚህ መስኮች አሠማርቻለሁ ብሎ እንደሚያስብና አለቃው ዲ. አባዲም በዚህ መንገድ እንዲያስበው እንደሚፈልግ ያሳያል፡፡ ዘርአ ያእቆብም ተመሳሳይ ሞያ ነበረው፡፡
መልስ፦ ኡርቢኖ እና ዘርአ ያኦቆብ ተመሳሳይ ሙያ የላቸዉም፡፡ ምን አልባት ሁለቱም ሙይ ቀይረዋል። ኡርቢኖ ለሚሶናዊነት መጥቶ አሳሽም ነበር አሉ እንደሚባለዉ ብዙ ሚሶናዉያን እንደሚያደርጉት መፅሀፍ ሲዘርፍ ኑሯል፡፡ ሚሶንያዊነቱንም እስከ መዘንጋት ድረሶ ነበር ሲል በወቅቱ የነበረ ሚሶናዊ መስክሮበታል፡፡ ዘርአ ያዕቆብ ደግሞ ተማረ ተመራመረና መምህር ሆነ ከዚያም ተባረረ፡፡ መምህርነቱም ለወልደ ህይወት እንጂ ለሌላ አለነበረም፡፡ ለወልደ ህይወትም እሱን ብቻ እዳስተማረዉ ሲገልፅ መምህሬ ይለዋል መምህራችን አላለዉም፡፡ ዘርአ-ያዕቆብ ከፍልስፍና እና ከመምህርነት ይልቅ ያደላዉ ለገበሬነቱ ነበር፡፡ ስለዚህ ዘርያ-ያዕቆብ ገበሬ ነበር፡፡ ኡርቢኖ ደግም መፅሀፍ አሳሽ ታዲያ ምን ሞያ ነዉ የሚይገናኛቸዉ፡፡ ሞያ መቀየራቸዉ ከሆነ ያመሳሰላቸዉ ሞያ የማይቀይር ማን ነዉ እባካችሁ?
- ዘርአ ያዕቆብና ዳ. ኡርቢኖ የተወለዱት በተመሳሳይ ቀን ነው፡፡ ዘርአ ያዕቆብ የተወለደው በነሐሴ 25 ቀን 1592 ነው፡፡ ኡርቢኖ ደግሞ በኦገስት 30 ቀን 1814፡፡ ይህ እንዴት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል? የዳ. ኡርቢኖ እና የወርቄ የክርስትና ስም ተመሳሳይ ነው፡፡ ወርቄ የክርስትና ስሙ ‹ዘርአ ያእቆብ› ሲሆን የዳ. ኡርቢኖ ደግሞ ‹Jacques – ያዕቆብ ነው›፡፡ የመጽሐፉ ቀዳማዊ ስም ‹ሐተታ ያዕቆብ ወይም መጽሐፈ ያእቆብ› ነበር። ዳ. ኡርቢኖ በኋላ የሐተታ ያዕቆብ ጸሐፊ የኢትዮጵያ የክርስትና ስም ቅርጽ ያለው ስም ዘርአ ያእቆብ ብሎታል፡፡
መልስ፦ በእርግጥ በፓወር ግእዝ ካላንደር ኦገሰት 30 ቀን 1814 ስተረጎመዉ 25/12/1806 ዓ.ም ይሆናል፡፡ ድንቅ ግጥጥምሽ ነዉ፡፡ እኔና ዲ/ን ዳንኤል የተወለድንበት ቀን ተመሳሳይ ቢሆን ችግሩ ምንድን ነዉ? ምን አለባት ኮኮብ ቆጣሩዎች ትርጉም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ የሁለቱ ሰዎች ነሀሴ 25 ቀን መወለድ የዚህን ያህል የሚያናጋ ትንታኔ አይመሰለኝም፡፡ ሁለት ሰዋች በተመሳሳይ ቀን የመወለዳቸዉን ጉዳይ በእስታስቲክስ ፕሮባብሊቲ (statistical probability) ማሰረዳት ቀላል ነዉ።
ሂሳቡን ተወትና ኡርባይ የልደቱን ቀን እንዲሁም ያአቆብ የመለዉን የክርሰትና ሰሙን በድብቅ ፁፍ የወርቄ ፈልሰፈና ነዉ ያለበት ምክንያት ምንድን ነዉ፡፡ ምን አልባት ከአለቃዉ ከኢ. አበዲ ገንዘብ ለምግኛት ሲሊ ይሆናል አይመሰለኛም ይልቅ ገንዘብ የሚያሰገኛዉ በራሱ ሰም ቢያሰትመዉ ነበር።
- ዘርአ ያዕቆብ ወደ እንፍራንዝ መጥቶ በሀብቱ ቤት መኖር ሲጀምር መልከ ጥፉ፣ ጠባየ መልካምና ልቡና ብሩኅ የሆነች የሀብቱን አገልጋይ ኂሩትን አገባ። ከእርሷም ልጅ ወለደ፡፡ ስለ ፈላስፋው ሚስት ኂሩት የተሰጠው ገለጻ ዳ. ኡርቢኖ ስለ ቤት አገልጋዩ ሴት (ዕቁባቱ ጭምር) ከሚሰጠው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
መልስ፦ እንዴ ሰወች የሚወዳቸዉን አጋራቸውን የሚገልጱበት መመሳሰሉ ችግሩ ምድን ነዉ፡፡ ያፈቀረ ሁሉ የኔማር ‘የኔማር’ የሚለዉ ዘፈን አሰር ጊዜ ቢዘፈን ምን እንዲህ አሉ ያስብላልን? ሰዎች በተመሳሳይ ክሰተት ተመሳሳይ ሀሳብ ሊያሰቡ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ 100 አባዉራዎችን መርጠን ሚሰቶቻችሁን ግለጿቸዉ ብንላቸዉ አብዛኛዉን በይዘት የሚመሳሰል መልስ ይሰጡናል። የኡርቢኖ እና የዘርአ ያዕቆብ ሴቶች መልክ ጥፉ የሆንበት ምክንያት ይቅርታ ይደረግልኛና በወቅቱ አጠራር ባርያ (ጥቁር ድሃ አገልጋይ) ይመስሉኛል፡፡ ለምን ብትሉ የዘርአ-ያቆብ ሂሩት በሀብቱ ቤት ስትገዘገዝ የኖረች ድሀ ስትሆን የኡርቢኖዋ ደግሞ ኡርባኖ እራሱ ይታማል እንጅ እንደዕቁባቱ አይቆጥራትም፡፡ ዕቁባቷ እንደሆነ እንዲጠረጠር ያደረገውም ደጋግሞ ስለሚያመስግናት ነው፣ የፆታዊ ፍቅር ያለበት ስለሚመስል ነው፡፡
- ዘርአ ያእቆብ ከአኩስም የመጣበትና ዳ. ኡርቢኖ ከአኩስም የመጣበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ኡርቢኖ በ1847 ወደ ትግራይ መጣ፡፡ ከአክሱም በ1849 ወደ ተድባበ ማርያም (አምሐራ) መጣ፡፡ ከአምሐራ ጎጃም ገብቶ፣ በመጨረሻም በ1850 ጎንደር ሠፈረ፡፡ ዘርአ ያዕቆብም ከአኩስም ወደ አምሐራ መጣ፣ በዚያም ሁለት ዓመት ተቀመጠ፡፡ በኋላም ወደ ጎንደር መጣ፡፡ የእነዚህ ሁለት ታሪኮች መገጣጠም እንዴት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል?
መልስ፦ መገጣጠሞች ሲበዙ ለምን እንድንል ያስገድደናል፡፡ ቢሆንም ከመደምደማችን በፊት ለምን ተገጣጠሙ ማለት አለብን፡፡ ዘረዓ ያዕቆብ አክሱም አድጎ ወደ አምሐራ ተሰደደ፣ ከስደቱ መልስ በጎንደር ደንቢያ እንፍራንዝ ኖሯል፡፡ ኡርባኖ በበኩል እንደ ሌሎች ሚሶናዊያን በአክሱም በኩል ገብቶ በአምሐራ በጎጃም በጎንደር ተዛዙሯል፡፡ ታዲያ ኡርባኖ ከዘረዓ ያዕቆብ ጋር ላለመመሳሰል በኡጋዴን በኩል መምጣት ነበረበት ትላላችሁ?
- የሐተታ ዘርአ ያዕቆብና ፍልስፍና ከዳ. ኡርቢኖ ደብዳቤዎች ጋር ይዘታዊ መመሳሰል አላቸው። ዳ. ኡርቢኖ በግንቦት 1854 ለአንቶንዮ ዲ. አባዲ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሰውን የዚህ ዓለም ማዕከል አድርጎ የሚያይበትን አመለካከቱን አንጸባርቆ ነበር፡፡ ይህም አስተሳሰብ በሐተታ ዘርአ ያእቆብ ላይ በዚያው መልኩ ይገኛል፡፡ ዘርአ ያዕቆብ ተፈላስፎ የእግዚአብሔርን መኖር ያመነው ‹ፍጡር ያለ ፈጣሪ ሊኖር አይችልም› ከሚለው ሐሳብ ተነሥቶ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ደግሞ በካቶሊክ ትምህርት ቤቶች በስፋት ይሰጥ የነበረው የቶማስ አኩዊኖስ ፍልስፍና ነው፡፡ ዳ. ኡርቢኖ ወደ ግእዝ በተረጎመው በቅርጣግና ሌሊቶች (The Carthage Nights) እና በሐተታ ዘርአ ያእቆብ መካከል ተመሳሳይ የሆኑ የሰዋሰው አገባቦችና አገላለጦች አሉ፡፡
መልስ፦ መልካም ኡርቢኖ በኢትዮጵያ ባህልና በዘረዓ ያዕቆብ ፍልልስፍና ተፅዕኖ ስለወደቀ ተመሳሳይ ይዘት ያለዉ ደበዳቤ ቢፅፉ አይገርምም፡፡ በተለይም ወደ መጨረሻዉ ኡርቢኖ አኗኗር ፈላስፋዉ ተፅዕኖ ስላደረገበት የሚፅፈዉ ደብዳቤ ከአንድ ሰባኪ መነኩሴ የማይጠበቅ ፍልስፍና አንፀባርቋል፡፡ ኢትዮጵያ ዉሰጥ ለመኖር ስሊም ካቶሊክ አይደለሁም ያለበት ጊዜም ነበር። ፈጡር ያለፈጣሪ ሊኖር አይችልም ማለት ትልቅ ፍልስፍና የሚያሰፈልገዉ አይደለም፡፡ ስለ ቶማስ አኩዊኖስ የማያዉቅ አንድ ሰዉ ስለፈጠሪ ምን ማሰረጃ አለህ ቢባል አጭር መልሱ ፈጥረት ሰለአለ ነዉ፡፡ ሌላዉ ኡርቢኖ በተገጎመዉ ” The Carthage Nights” እና በሀተታ ዘርአ ያቆብ በካከል ተመሳሳይ ሰዋሰዉ መኖሩን ከመመርመራችን በፊት ” The Carthage Nights” ስለ ምንድን ነዉ የሚያወራ ስለ እስላማዊ አስተምሮ ትችት ነው ይባላል። ታዲያ ሁለቱም የትችት መፅሀፍት እንደመሆናቸዉ ተመሳሳይ ቃላትን አልፎ አልፎ ቢጠቀሙ የሚያሰደንቅ ነገር ነዉን?
ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ስለፈለኩ ብቻ ኢትዮጵያዊ ነው ብየ መደምደም ይከብደኛል። ችግሩ ጥልቅ ምርምር ተደርጎ መታወቅ አለበት። ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ባይሆንም እንደ ጉዱ ካሳ አይነት በማህበረሰቡ፣ በሊቃውንትና በነገስታት ሲገፋ ሲደፋ የኖረውን እሳቤ ስለሚውክል ማንነቱ እዚ ድረስ አያስጨንቀኝም። ይልቅስ ይሚቆረቁረኝ ያን የመሰለ ፍልስፍና ማንም ይጻፈው ማን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተጻፈ መጠቀም ሲኖርብን ሃሳቡን ማሳደዳችን ነው። ሰየው ስለመሰደዱ በትክክል አላውቅም (ማንም አያውቅም) ሃሳቡ ስለመሰደዱ ግን እርግጠኛ ነኝ። ለእኔ ዘርዓ ያዕቆብ ምን አልባት እውነተኛ ሰው ካልሆነ እውነተኛ ሃሰብ ነው።
የ17 ክ/ዘመን ድንቅ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብ በሚያሳዝን የሲቃ ድምጹ ዘመን በማይሽረው ሀትታው እንዲህ ይላል፦
‘‘ከሁሉ ሰው፤ ከፈረንጆቹና ከግብፃዊያን ጋር እስማማለሁ፡፡ እኔ በሃገሬ መፅሃፍት ሳስተምር ብዙዎቹ ጓደኞቸ ጠሉኝ፡፡ በዚህ ዘመን የባልንጀራ ፍቅር ጠፍቶ ነበርና ቅናት ያዛቸው፡፡ ከአክሱም ካህናት አንድ ወልደ ዮሃንስ የተባለ ጠላቴ የንጉስ ወዳጅ ስለነበረ ወደ ንጉሱ ( አፄ ሱስንዮስ) ገብቶ እንደዚህ አለው፡፡ ‘ይህ ሰው ህዝብን ያሳስታል፡፡ ስለሃይማኖታችን (ኦርቶዶክስ) እንነሳና ንጉሱን እንግደለው (ካቶሊክ ስለነበር)፣ ፈረንጆቹንም እናባራቸው ይላል’ እያለ ይሄን እና ይሄን በመሰለ ውሸት ከሰሰኝ፡፡ እኔም ይህን አውቄ ገና ለገና (ንጉሱ) ይገድለኛል ብዮ ፈርቼ የነበረኝን ሶስት ወቄት ወርቅና የምፀልይበትን መዝሙረ ዳዊት ይዠ በሌሊት ሸሸሁ፡፡ ወዴት እነደምሄድ ለማንም አልተናገርኩም፡፡ ወደተከዜ በረሀ ገባሁ፡፡ በነጋታውም ራበኝ፡፡ ከሀብታሞች ገበሬዎች እንጀራ ለመለምን እየፈራሁ ወጣሁ፡፡ ሰጡኝና በልቼ እየሮጥኩ ሄድኩ፡፡ እንዲህ እያልኩ ብዙ ቀን ቆየሁ፣ በኋላም ሰው የለለበት በርሃ አገኝሁ፡፡ መልካም ዋሻም አገኘሁና ሰው ሳያየኝ በዚህ ዋሻ እኖራለሁ ብየ ወሰንኩ፡፡ ቁጥር የሌለው ክፋታቸውን አውቄ ከሰዎች ጋር መኖር ጠላሁ፡፡ ሌሊት መጥተው የበርሃ አራዊት እንዳይበሉኝም በድንጋይና በአሽዋ አጥር ዋሻየን አጠረኩ፡፡ እሚፈልጉኝ ሰዎች ወደኔ ቢመጡ የማመልጥበት መውጫ አዘጋጀሁ፡፡ ሱስንዮስ እስኪሞትም ድረስ በዚያ ሁለት ዓመት ቆየሁ፡፡’’ ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ ምዕራፍ፦2
ወርቄ ማለት የመናገር ነፃነቱን ተነፍጎ ራሱን ደብቆ የኖረ ታልቅ የማለዳ ኮከብ ነበር። ብዙ ሰዎች ተመሳስለውና መስለው የመኖርን ጥበብ የሚማሩት ከሰው ጋር የመኖር ህልውናቸውን ላለማጣት ሲጥሩ ነው። ከተለምዶ አኗኗር ጋር መመሳሰል ካልቻሉ መከራውን ችለው፣ ነፃነታቸውን አውጀው ፈላስፋ ይሆናሉ። ህዝብ በጀምላ የሚያስበውን እያሰቡ ፈላስፋ መሆን ይከብዳል፣ ወጣ ማለት አላባቸው መጠየቅ፣ መጠራጠር የሚባል ነገር አለና። ወርቄን የጨለማ አበጋዞች መከራ አጸኑበት፣ ከስራው እና ከሀገሩ አባረሩት፣ ፍልስፍናውም ወደ ህዝቡ ልብ ሳይደርስ ቀረ። ለቁጭት ይሆነን ዘንድ ሀተታውን ፅፎ አስቀረልን። ዶ/ር ጌታቸው ሐይሌ ደግሞ ከግዕዝ ወደ አማርኛ ‘ሐተታ ዘዘርአ ያዕቆብ በሚባል ስም የሚታወቀው የወርቄ የሕይወት ታሪክ’ ብሎ ተረጎመልን።
የሚያሳዝነው ዛሬም የወርቄን ድምፅ ለመስማት ወንጌሉን (ሀተታውን) ለማንበብ የምንፈልግ አይምመስልም። ጠቢብ በሃገሩ አይከብርም መስለኝ የራሳችንን ጥለን የውጮቹ ህልመኞች የጻፉትን ድርሰት ተሸክመን እንገዳገዳለን። ያም ሆነ ይህ ወርቄ ማለት በምእራቡም በምስራቁም የተነሱትን የፍልስፍና ጥያቄዎችን እና መልሶቻቸውን ይዞ ብቅ ያለ አማኝ (ምን አልባት ክርስቲያን) ፈላስፋ ነበር። ወርቄ በሀተታው ያነሳቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች፣ መልሶች፣ መርሆች እና አስተሳሰቦች ውስጥ ዋና ዋናዎቹን እንይ፦
- በአርያም የሚያውቅ አለን? አዋቂስ አድርጎ የፈጠረኝ ማነው? በዚህስ አለም እኔ እንደምን መጣሁ? እኔ በገዛ እጄ ተፈጠርኩን?
መልስ፦ እኔ በተፈጠርኩ ጊዜ አልኖርኩም፡፡ አባት እናቴ ፈጠሩኝ ብልም እንደገና ወላጆችና የወላጆችን ወላጅ፣ወላጅ የሌላቸው በሌላ መንገድ ወደዚህ ዓለም የመጡትን እንደኛ ያልተወለዱትን የፊተኞቹ ድረስ ፈጣሪያቸውን እፈልጋለሁ፡፡ እነርሱም ቢወለዱ የፈጠራቸው አንድ ህላዌ አለ ከማለት በቀር የጥንት መወለጃቸውን አላውቅም፡፡ ያለና በሁሉም የሚኖር የሁሉ ጌታ ሁሉን የያዘ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዓመቱ እማይቆጠር እማይለወጥ ያልተፈጠረ ፈጣሪ አለ አልኩ፡፡
- በመራቃቸው ደቃቃዎች የሚመስሉ ከዋክብትን ቁጥራቸውን፣ እርቀታቸውን፣ ታላቅነታቸውንስ የሚያውቅ ማነው?
መልስ፦ ጥያቄውን ማንሳቱ በቂ ነው። የጊዜው ቴክኖሎጅ ስላልፈቀደለት ጥያቄውን በዝምታ ማለፍ ነበረበት።
- በእውነት (ፀሎቴን) የሚሰማኝ እግዚያብሔር አለን? ኧረ እግዚያብሔርስ ያውቃልን? ጆሮን የተከለ አይሰማምን? በእውነት እንድሰማበት ጆሮ የሰጠኝ ማነው?
መልስ፦ ፈጣሪስ አለ፡፡ ፈጣሪ ባይኖር ፍጥረት ባልተገኘ አልኩ፡፡ እኛ ብንኖር ፍጡራን እንጅ ፈጣሪዎች አይደለንም፡፡ የፈጠረ ፈጣሪ አለ እንል ዘንድ ይገባናል፡፡ ይህም የፈጠረን ፈጣሪ አዋቂና ተናጋሪ ካልሆነ በቀር ከዕውቀቱ በተረፈ አዋቆዎችና ተናጋሪዎች አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ሁሉን ፈጥሯል ሁሉን ይይዛልና እርሱ ሁሉን ያውቃል፡፡ ፈጣሪየ ወደ እርሱ ስፀልይ ይሰማኛል ብየ ሳስብ ትልቅ ደስታ ተደሰትኩ፡፡ በትልቅ ተስፋም እየፀለይኩ ፈጣሪየን በሙሉ ልቤ ወደድኩት፡፡ ጌታየ ሆይ አንተ ሃሳቤን ሁሉ ከሩቅ
ታውቃለህ አልኩት፡፡ እኔ ሳልፈጠር ሀሳቤን ያውቃልና ፈጣሪየ ሆይ እውቀትን ስጠኝ አልኩ፡፡
- እግዚያብሔር የሰዎች ጠባቂ ከሆነ ለምን ፍጥረት እንዲህ ከፋ? በቅዱስ ስሙ ሲበድሉና ሲረክሱ የሚያውቅ ከሆነ እንዴት የሰዎችን ክፋት ዝም ይላል?
መልስ፦ ከፀሎት በኋላም ስራ ስለሌለኝ ሁልጊዜ ስለሰዎች ክፋትና ሰዎች በእርሱ ስም ሲበድሉ፣ ወንድሞቻቸውን ጉደኞቻቸውን ሲያባርሩ እና ሲገድሉ ዝም በማለቱ ስለፈጣሪ ጥበብ አስብ ነበር፡፡ ሃይማኖታቸውን ከመሰረቱ አመፃ እየሰሩ ከንቱ ያስተምራሉ፡፡ በከንቱም ክርስቲያኖች ተባሉ። እየሱስ ክርስቶስ ግን ከሁሉ አስቀድሞና ከሁሉ በላይ ክርስቲያኖችን እርስ በርሳቸው እንዲፋቀሩ አዟቸዋል፡፡ ይህ ፍቅር የተባለው ግን ክርስቲያኖች በተባሉት መካከል ፈፅሞ ጠፋ፡፡ ሁሉ ወንድሞቻቸውን ይበድላሉ፡፡ እርስ በርሳቸው እንደ እህል አበላል ይዋዋጣሉ፡፡ እኔም ሀይማኖቴን አመንዝራና ዋሾ መሆኑዋን ካወኩ በኋላ ስለርሷ (እና) በዝሙት ስለተወለዱ ልጆቿ አዘንኩ፡፡ እነሱ በጠብ፣ በማሳደድ፣ በመማታት፣ በማሰር፣ በመግደል ወደዚህ ዋሻ ያባረሩኝ ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን የሀገራችን ሰዎች የወንጌልን ፍቅር ወደ ጠብና ሃይል ወደ ምድራዊ መርዝ ለወጡት፡፡ በሐሰትም ክርስቲያኖች ይባላሉ፡፡
- የኔ ሃይማኖት ለኔ ትክክል እንደሚመስለኝ እንዲሁ ለሌላውም ሃይማኖቱ እውነት ይመስለዋል፡፡ታዲያ እውነት የሚፈርድ የት አገኛለሁ?
መልስ፦ ግብፃዊያኖች ደግሞ (ኦርቶዶክሶች) እንዲህ እንዲህ ይላሉ እላለው፡፡ እኛም ብንመረምር ይህን ሁሉ እናውቃለን እላለሁ እንጅ ይህ መልካም ነው ይህ ደግሞ ክፉ ነው አልልም፡፡ ግብፃቹ የፈረንጅ፣ ፈረንጆቹ ደግሞ የግብፃዊያኖቹ እመስላቸዋለው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ጠሉኘ፡፡ ብዙ ጊዜም ወደንጉሱ ከሰሱኝ፡፡ እግዚያብሔር ግን አዳነኝ፡፡ በጣም አላወኩምና የተማሩና ተመራማሪ ሰዎች እውነቱን እንዲነግሩኝ ሄጄ ልጠይቃቸው ብየ ብዙ አሰብኩ፣ እንደገናም ሰዎች በየልባቸው ያለውን ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ይመልሱልኛል ብየ አሰብኩ፡፡ ሰው ሁሉ የኔ ሃይማኖት እውነተኛ ናት ይላል፡፡ በሌላ ሃይማኖት የሚያምኑ ሐሰተኞች የእግዚያብሔር ጠላቶች ናቸው ይላል፡፡ ዛሬም ቢሆን ፈረንጆች ሃይማኖታችን መልካም ናት፣ ሃይማኖታችሁ ግን መጥፎ ናት ይሉናል፡፡ እኛም መልሰን እንዲዚህ አይደለም የናንተ ሃይማኖት መጥፎ የኛ ሃይማኖት ግን መልካም ናት እንላቸዋለን፡፡ እንደገናም የእስልምና፣ የአይሁድ አማኞችን ብንጠይቃቸው እንዲሁ ይሉናል፡፡ በዚህም ክርክር ፈራጅ ማን ይሆናል፡፡ ሰዎች ሁሉ እርስ በእርሳቸው ወቃሾችና ተወቃሾች ሆነዋል፡፡ አንድ እንኳን ከሰው ልጅ የሚፈርድ አይገኝም፡፡
- ዋሾ ሰው ሐሰተኛ መንገድ ሲያገኝ እዉነት አስመስሎ ሀሰት ይናገራል፡፡ ሊመረምሩ የማይፈልጉ ሰዎች እውነት ይመስላቸውና በእርሱ ሃይማኖት ያምናሉ፡፡ እስኪ ህዛባችን በስንት ውሸት ያምናል? እነዚያስ የፊተኞቹ ገንዘብና ክብር ለማግኝት ካልሆነ በቀር ስለምን ዋሹ?
መልስ፦ በሃሳብ ከዋክብትና በሌላም አስማት፣ አጋነንት በመሳብና በመርጨት፣ አስማት በማድረግ፣ በጥንቆላ ሁሉ ያምናሉ፡፡ ይህንን ሁሉ መርምረው እውነቱን አግኝተው አያምኑም፡፡ ነገር ግን ከአባቶቻቸው ሰምተው ያምናሉ፡፡ እንዲሁም ህዝብን ሊገዙ የሚፈልጉ ሁሉ እውነት እንነግራቸኋለን እግዚያብሔር ወደናንተ ላከን ይሏቸዋል፡፡ ህዝቡም ያምናል፡፡ ከነርሱም በኋላ የመጡት እነርሱ ሳይመረምሩ የተቀበሏትን ያባቶቻቸውን እምነት አልመረመሩም፡፡ ከዛ ይልቅ ለእውነት ለሃይማኖታቸው ማስረጃ ታሪክን፣ ምልክቶችን፣ ተዓምራትን እየጨመሩ አፀኑት፡፡ እግዚያብሔርንም የሐሰኞች ተካፋይና የሐሰት ምስክር አደረጉት፡፡ ሙሴ ፈቃዱንና ሕጉን ልነግራችሁ ከእግዚያብሔር ዘንድ ተልኬ መጣሁ ይላል፡፡ ከርሱ በኋላ የመጡት በግብፅና በደብረሲና እንዲህ ተደረገ እያሉ ታሪክን፣ ተዓምራትን እየጨመሩ የሙሴን ነገር እውነት አስመሰሉት፡፡
- በቅዱስ መፅሃፍት የተፃፈ ሁሉ እውነት ይሆን? የእግዚያብሔርን ስራ የሰው ምስክር ሊያስተካክለው ይቻለዋልን? እንግዲያስ ትንሹና ምስኪኑ ሰው ለሰው ጥበቡንና እውነቱን እንድገለፀለት ከእግዚያብሔር ዘንድ ተልኬ መጣሁ እያለ ስለምን ይዋሻል?
መልስ፦ የሙሴ መፅሃፍ ከፍጥረት ሕግ ሰርዓትና ከፈጣሪ ጥበብ ጋር አይስማማም፡፡ ከውስጡ የተሳሳተ ጥበብ ይገኛል፡፡ በፈጣሪ ፈቃድና በፍጥረት ህግ የሰው ልጅ እንዳይጠፋ ልጆችን ለመውለድ ወንድና ሴት በፍትወተ ስጋ እንዲገናኙ ታዟል፡፡ ይህም ግንኙነት እግዚያብሔር ለሰው በሕገ ተፈጥሮ የሰጠው ነው፡፡ እግዚያብሔር ዘንድ እርኩሰት ሊገኝ አይችልም፡፡ ሙሴ ትክክል ነው አልልም፡፡ ነገር ግን የወሲብ ስርዓት የተፈጥሮ ስርዓት እንደሆነ ምንኩስና ግን ልጆች ከመውለድ ከልክሎ የሰውን ፍጥረት አጥፍቶ የፈጣሪን ጥበብ የሚያጠፋ እነደሆነ ልቦናችን ይነግረናልና ያስረዳናል፡፡ የክርስቲያን ሕግ ምንኩስና ከወሲብ ይበልጣል ብትል ሐሰት ትናገራለችና ከእግዚያብሔር አይደለችም፡፡ እንዲሁም መሐመድ የማዛችሁ ከእግዚያብሔር የተቀበልኩትን ነው ይላል፡፡ መሐመድን መቀበል የሚያስረዱ ተዓምራት ፀሐፊዎች አልጠፉምና ከሱም አመኑ፡፡ እኛ ግን የመሐመድ ትምህርት ከእግዚያብሔር ሊሆን እንደማይችል እናውቃለን፡፡ የሚወለዱ ሰዎች ወንድና ሴት ቁጥራቸው ትክክል ነው፡፡ በአንድ ሰፊ ቦታ የሚኖሩ ወንድ ሴት ብንቆጥር ለእያንዳንዱ ወንድ አንዲት ሴት ትገኛለች እንጂ ለአንድ ወንድ ስምንት ወይም አስር ሴቶች አይገኙም፡፡ የተፈጥሮ ህግም አንዱ ከአንዲት ጋር እንዲጋቡ አዟል፡፡ አንድ ወንድ አስር ሴት ቢያገባ ግን ዘጠኝ ወንዶች ሴት የሌላቸው ይቀራሉ፡፡ ይህም የፈጣሪን ስርዓትና ሕገ ተፈጥሮን የጋብቻንም ጥቅም ያጠፋል፡፡ አንድ ወንድ ብዙ ሴቶች ሊያገባ ይገባዋል ብሎ በእግዚያብሔር ስም ያስተማረ መሐመድ ግን ትክክል ነው አልልም፡፡ ከእግዚያብሔር ዘንድ አልተላከም፡፡
ወቀሳውን ይቀጥላል፦
በእሁድ ቀንና በበዓል ቀናት በአስፈላጊው ልክ የበላ እንዳልበደለ እንዲሁ በአርብ ቀንና ከፋሲካ በፊት (በአብይ ጾም) ባሉት ቀናት ለክቶ የሚበላ አልበደለም፡፡ እግዚያብሔር ሰውን በሁሉ ቀንና በሁሉ ወራት ካስፈላጊ ምግብ ጋር አስተካክሎ ፈጥሮታል፡፡ አይሁድ፣ ክርስቲያንና እስላም ግን የፆምን ሕግ ባወጡ ጊዜ ይህን የእግዚያብሔር ሥራ ልብ አላሉም፡፡ እግዚያብሔር ፆምን ሰራልን እንዳንበላም ከለከለን እያሉ ይዋሻሉ፡፡ ከጋብቻ ይልቅ ምንኩስናን ይበልጣል ብለው የሚያምኑ እነርሱ በፈጣሪ ስራ ፅናት ወደ ጋብቻ ይሳባሉ፡፡ ፆም ነፍስ እንደሚያፀድቅ የሚያምኑ እነርሱ ደግሞ እረሃብ በበዛባቸው ጊዜ ይበላሉ፡፡ ገንዘቡን የተወ ፍፁም እንዲሆን የሚያምኑ በገንዘብ ለሚያገኙት ጥቅም ወደ ገንዘብ መፈለግ ይሳባሉ፡፡ ብዙዎች የሀገራችን መነኩሴዎችም እንደሚደርጉት ከተውት በኋላ እንደገና ይፈልጉታል፡፡ እንደዚሁ ዋሾዎች ሁላቸው የተፈጥሮን ሥራ ሊያፈርሱ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ደካማነታቸውን ያሳያሉ እንጂ አይችሉም፡፡ ፈጣሪም ይስቅባቸዋል፡፡ የፍጥረት ጌታም በላያቸው ይሳለቅባቸዋል፡፡
- አማኝ ሳልሆን አማኝ እመስላለሁ፡፡ በእግዚያብሔር ዘንድ ይህ ያስቀጣኝ ይሆን?
መልስ፦ እኔም ለሰዎች ክርስቲያን እመስላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በልቤ እርሱ እንዳስታወቀኝ የሁሉ ፈጣሪና የሁሉ ጠባቂ በሆነ በእግዚያብሔር ካልሆነ በስተቀር በማንም አላምንም፡፡
ዋቢ መፅሃፍት
- ዳንኤል ክብረት፣ የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ እና ሌሎች፣ 2011
- ጌታቸው ሐይሌ፣ ‘ሐተታ ዘዘርአ ያዕቆብ በሚባል ስም የሚታወቀው የወርቄ የሕይወት ታሪክ’
- ብሩህ አለምህ፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ 4ኛዕትም፣ 2010
በመ/ር አበባው አሰፋ abebawacc3368@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
የዲያቆኑ «የዘርአ ያእቆብ የዓለም ስሙ ‹ወርቄ› ነው፡፡ ወርቄ የሚል የስም አወጣጦች በአማራው አካባቢ እንጂ በአኩስም አካባቢ የተለመደ ስሞ አይደለም፡፡» በሚል ክርክር ዘራያቆብ «ኢትዮጵያዊ አይደለም/ሊሆን አይችልም» የሚል ማጠቃለያ ላይ መድረስ የመጨረሻ የማይመስልና መሃይማዊ ትንተና ነው፡፡ የትግራይ ሰው ዋሽራ ድረስ ሄዶ ዜማ ይማራል፡ የደ/ታቦሩም ዲያቆን አክሱም ሄዶ ቅኔና ዜማን ይማራል፡፡ እናም በተወለደበት ሳይሆን በተማረበት ልምዲ፡ ወልዶና ከብዶ ሊኖር ይችላል፡ በዚህ መልኩ ኡእሄደው ወርቄ አክሱም ላይ ሲኖር ኢገኝ፡ ስሙ የአማራ ነውና ወርቄ ወርቄ ሊጆን አይችልም የሚሉ ክርክር ባዶ ነው፡፡ እና «ኡርቢኖ አክሱም አካባቢ ስለነበረ ነው ይህን የትውልድ ቦታ የመረጠው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡» ብሎ መተቸት ምሁራዊ ትችት አይደለም፡፡ በጣም የሚገርመው «ኢትዮጵያውያን ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ፈላስፋ መኖርን እራሱ ያወቅነው ከአውሮፓውያን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሱ የሚወራ አፈ-ታሪክ እንኳን የለም።» የሚለው የዲያቆኑ ሃሳብም ውሃ አይቋጥርም፡፡ ምክ፡ አንድ ወርቄ/ዘራያቆብ በአንድ መንደር ቢበዛ ወረዳ ውስጥ ባለ ሰው ብቻ ቢታወቅ ነው፡፡ እንደ አለቃ ገ/ሃና አይነቱና በተለያዩ ዘመናት የተነገሩ ቀልዶችን ሁሉ ለአለቃ ገ/ሃና እየተሰጡ ስማቸው እንደገነነው አለቃ፡ የወርቄ በአፈታሪክ እንኳን አለመታወቅምና ወርቄ ብሎ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ሊኖር አይችልም የሚል ክርክር ጎደሎ ነው፡፡ ይህን ጽሁፍ ያቀተበልንን አበባውን አደንቃለሁ፡፡ በሌላ ሪቪው ተመልሼ እመጣለሁ፡፡
ወንድሜ ቢለው ሰይጣንን አብዝቶ ገረመው አይደል?
አትድከም ወንድሜ፤ ዘረዓ ያቆብ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ዓፄ ሱሴኒዮስ ህዝቡን ወደ ካቶሊክ እምነት እንዲገባ የሚያደርገውን ክህደት በመቃወሙ ዓፄው ሲያሳድደው ከአክሱም ሸሽቶና በየሸለቆው ተሽሎክሉኮ ደንቢያ- ጎንደር- ገብቶ የኖረ፤ የዓፄው ልጅ እንደሱው አባቱን ይቃወም የነበረው ንጉሥ ፋሲለደስ እንደ ወንድሙ ተንከባክቦ ያኖረው፤ ሚስት ታጭቶለት አግብቶና ልጆች ተክቶ ያለፈ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ስለመሆኑ ኡንዳች ጥርጣሬ አይግባህ…… ሠላም።