አብይን የምደግፈው አዎ ለራሴ ስል ነው! ከፀፀት ለመዳን፤ ከህሊና ወቀሳ ለመትረፍ ስል! ዶክተር አምባቸው መኮንን ከተገደለ በኋላ የተሰማኝን ስሜት እኔ ነኝ የማውቀው። የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆኖ በሀላፊነት በቆየባቸው ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ በውጥረት ተከቦ በርካታ በጎ ስራዎችን አከናውኗል። ጥሩ ስራ ሲሰራ አንድም በጎ ቃል ትንፍሽ አላልኩም ነበር።ኦሮሚያ ክልል ሄዶ ስለልዩ ጥቅም አወራ ሲባል ግን እሱን ለመተቸት ማንም አልቀደመኝም።
አሁን የአምባቸውን ምስል ፌስቡክ ላይ ባየሁ ቁጥር ፀፀቱ ይገርፈኛል። እሱን ተችቼ የፃፍኩትን ፅሁፍ ከፌስቡክ ገፄ አጥፍቸዋለሁ። የጥፋተኝነት ስሜቱ ግን ከህሊናየ ሊጠፋ አልቻለም።
ይህ ፀፀቴ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲደገም አልፈልግም። ዶክተር አብይ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ተዘርዝረው የማያልቁ በርካታ ለውጦችን ያመጡ ቢሆንም ከምስጋና ይልቅ በየቀኑ ትችት ሲያስተናግዱ የሚውሉ መሪ ሆነዋል። (የገቡበትን አጣብቂኝ ዘግይቸ እስከምረዳ ድረስ ላይ ላዩን እየተመለከቱ ከሚተቿቸው ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ። ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ።)
ለመሆኑ ዶክተር አብይ በስንት ጠላቶችና ፅንፈኛ ሀይሎች ተከበው አበሳቸውን እንደሚያዩ አስበንው እናውቃለን?
በአንድ በኩል ከስልጣን የተወገደው ህወሀት የተባለው የሽማግሌዎች ስብስብ ቡድን ወደስልጣን እንደማይመለስ ቢያውቀውም “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል ብሂል ኢትዮጵያን ይበታትንልኛል የሚለውን የጥፋት እቅድ በየጊዜው ሲሸርብና ሲያስፈፅም ይውላል። በሌላ በኩል ኦነግ ሸኔና አባ ቶርቤ የተባሉ አሸባሪ ቡድኖች የመንግስት ሀላፊዎችንና ታዋቂ ሰዎችን እየተከታተሉ ይገድላሉ። ግብፅ በአባይ ግድብ ግንባታ ላይ የአብይን አስተዳደር መፈናፈኛ አሳጥታ ይዛዋለች።
የአንድነት ሀይሉና የአማራ ብሄርተኞች በበኩላቸው “የፊዴራልና የአዲስ አበባ መስተዳድር የሀላፊነት ቦታዎች በተረኝነት በኦሮሞዎች ብቻ ተያዘ” ብለው ጩኸታቸውን ያሰማሉ። “ጊዜው የኦሮሞ ነው” ብሎ የሚያስበው በጃዋር መሀመድ ይመራ የነበረው ፅንፈኛ ቡድን ደግሞ “ሁሉንም ነገር እኛ ካልተቆጣጠርነው ለውጥ የለም” የሚል ድምዳሜ ላይ ስለደረሰ “የአብይ አስተዳደር የነፍጠኛን አሀዳዊ ስርአት ለመመለስ እየሰራ ነው” ብሎ ስሙን ያጠፋል፤ አመፅ ይቀሰቅሳል። እንደ ለማ ሱሴ አይነት “ለውጡ ተቀልብሷል” በሚል ያኮረፉ ሰዎች ደግሞ በመንግስት የሀላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጠው ሴራ ይጎነጎናሉ። “የብሄር ፖለቲካ መታገድ አለበት፤ ህገ መንግስቱም አሁኑኑ ተቀዶ መጣል አለበት” የሚለው ወገን ደግሞ “ነውጥ እንጂ ለውጥ አልመጣም” እያለ በየቀኑ የአብይን ስም ሲያብጠለጥል ይውላል።
እንግዲህ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በነኝህ ችግሮች ሁሉ ተከበው፣ እንደ ገና ዳቦ ከላይና ከታች እየተለበለቡ ነው እያንዳንዱን ቀን የሚያሳልፉት። ግን ለምንድነው በጎውን ነገር የማንመለከተው? ህወሀት ከስልጣን ከተወገደ በሗላ በዶክተር አብይ አመራር አማካኝነት የመጡ ለውጦችን ለመረዳት የተቸገርንበት ምክንያትስ ምንድነው?
ወያኔ በምርጫ ቦርድና በፍርድ ቤት ጉዳይ እንደማይደራደር አለም ያወቀውና ፀሀይ የሞቀው እውነታ ነበር ። ዶክተር አብይ ግን በነዚህ ተቋማት ላይ መአዛ አሸናፊንና ብርቱካን ሚዲቅሳን ሲሾሙ “ለእኔ ያገለግሉኛል” ብለው አስበው እንዳልሆነ ሁላችን የምንረዳው ጉዳይ ነው። በተለይ ብርቱካን በገለልተኝነቷና በጠንካራ አቋሟ ተፈትና ያለፈች ሴት ናት።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሆኖ የተሾመው ዶክተር ዳንኤል በቀለም መንግስት የሚፈፅመውን ወንጀል ሊደብቅላቸው እንደማይችል ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠንቅቀው ያውቃሉ። እነኝህን ሰዎች የሾሟቸው “እኔን ይደግፉኛል” ብለው ሳይሆን ለውጥ በማምጣት ሂደት ውስጥ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ብለው በማመናቸው እንደሆነ ግልፅ ነው።
ክልሎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ችለዋል።የመናገርና የመፃፍ ነፃነት ምህዳሩ እጅግ ከመስፋቱ የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ከመተቸት አልፈው ጠቅላይ ሚንስትሩን እስከመዝለፍ ደርሰዋል።
የግል ሚዲያውም አብይን ካልተቸ በስተቀር የሰላም እንቅልፍ መተኛት የሚችል አይመስለውም። ኦኤምኤን፣ ትግራይ ሚድያ ሀውስ፣ድምፂ ወያነ፣ኩሽ ሚድያ፣ ርዕዮት ሚዲያ፣ አዲስ ስታንዳርድ፣ አዲስ ፎርቹን፣ አባይ ሚድያ፣ ኢትዮ 360 ሚዲያና ጃዋር አስተዋውቆለት ከመቶ ሺህ በላይ ተከታዮችን ያገኘው እንደ ፊንፊኔ ኢንትርሴፕት አይነት አነስተኛና ጥቃቅን የፊስቡክ ገፅ ሳይቀር በየቀኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብይን ሲያብጠለጥሉ ይውላሉ።
የሚያሳዝነው ኢትዮጵያ እንድትበታተን የሚፈልጉት ብቻ ሳይሆኑ “ኢትዮጵያን እንወዳለን” የሚሉት ወገኖች ጭምር በማወቅም ይሁን ባለማዎቅ የዚህ ዘመቻ ተካፋዮች መሆናቸው ነው። በመለስ ዜናዊ የግፍ አገዛዝ ዘመን እንኳን እንደዚህ አይነት የተቀናጀ የሚዲያ ዘመቻ ተካሂዶ አያውቅም።
ጠቅላይ ሚንስትሩን በማጣጣል ረገድ እንደ እኔ አይነቱ ተራው ዜጋም አልቦዘነም። አፄ ምኒልክ ሩህሩህና ትዕግስተኛ መሪ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል። ለዚህም አሁንም ድረስ “እምየ ምኒልክ” ብለን እንጠራቸዋለን። ይገባቸዋል! ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ “መግደል መሸነፍ ነው፤ፍቅር ያሸንፋል” ብለው በፍቅርና በሰላም ተከባብሮ መኖር እንደሚገባ ሲነግሩህ ” ይሄ የሀይማኖት ሰባኪ ነው፤ አገር መምራት አይችልም” ብለህ ታጣጥለዋለህ። ዘግይቶም ቢሆን የአገር ደህንነትን ለማስጠበቅ በወንጀለኞች ላይ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ደግሞ “አምባገነን ሆነ” የሚለውን የወያኔን ዘለፋ ታስተጋባለህ።
ይሄ ሰው ግን አያሳዝንህም? ቴዲ አፍሮ “አያሳዝንም ወይ” እያለ ለአፄ ቴውድሮስ ያቀነቀነውን ዜማ ስንሰማ “በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንዴት የቴውድሮስን አላማ መረዳት አቃታቸው?” ብለን በፀፀት ተውጠን አብረን እናንጎራጉራለን። በተቃራኒው ደግሞ አሁን ከጎናቸው ቆመን ድጋፍ ልንለግሳቸው የሚገባውን መሪ በየቀኑ ስናወግዛቸው እንውላለን።
ግን ግን …ዶክተር አብይ የሰሩት ሀጥያት ምንድነው? እግዚአብሄርን በመፍራታቸውና ኢትዮጵያን በመውደዳቸው? የመጡበትን ጎሳ ለይተው “እንኳን ከዚህ ወርቅ ህዝብ ተፈጠርኩ” ባለማለታቸው? በወረደ ቋንቋ ለሚተቿቸውና ለሚሰድቧቸው ሰዎች መልስ ባለመስጠታቸው? ተጥሎ የተገኘን ልጅ አንስተው በማሳደጋቸው? ትሁት በመሆናቸው? የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታታቸው? የታሰሩ ስደተኞችን አስፈትተው ራሳቸው በሚጓዙበት አውሮፕላን ይዘው በመመለሳቸው? ችግኝ በመትከላቸው? አዲስ አበባን በማስዋባቸው? ሙስና ውስጥ ባለመዘፈቃቸው? አስር አመት የተጓተተውን የአባይን ግድብ ግንባታ አፋጥነው ውሀ ሙሌት በመጀመራቸው? ኢትዮጵያን እናበልፅግ በማለታቸው? እኔ ሊገባኝ አልቻለም።
ይህንን ስል ዶክተር አብይ ፍፁም ናቸው እያልኩ አይደለም። እንደማንኛውም ሰው በንግግርም ይሁን በአሰራር ይሳሳታሉ። የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች ፍፁም እንዳልነበሩት ሁሉ የአሁኖቹም ፍፁም ሊሆኑ አይችሉም። ሰው ናቸውና ያጠፋሉ ፤ይሳሳታሉ። ድጋፋችን የምንሰጣቸው ፍፁም ናቸው ብለን ሳይሆን ትልቋን ስዕል ማለትም ኢትዮጵያን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ህዝቡ ለዶክተር አብይ የሰጠውን ድጋፍ ቀንሶ የነበረው የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዳደር ጃዋር ላይ ያሳይ በነበረው መለሳለስና ማባበል ምክንያት መሆኑን ብዙዎቻችን የምናውቀው እውነታ ነው። ግን በወቅቱ ከነበረው ተጨባጭ ችግር አንፃር እኛስ በጠቅላይ ሚንስትሩ ቦታ ብንሆን ኖሮ ምን የተለየ ነገር እናደርግ ነበር?
የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው አቶ ታየ ደንደአ ሰሞኑን በአንድ ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ጃዋር መሀመድ “ተከበብኩ” ብሎ ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ ለተገደሉ 97 ሰላማዊ ዜጎች ተጠያቂ ተደርጎ ቢታሰር ኖሮ የጃዋርን እስር በመቃወም ሊከሰት የሚችለውን ብጥብጥ መቆጣጠር የሚችል የተቀናጀ የፀጥታ ሀይልና መዋቅር አልነበረም። ሥለዚህ የማይቻል ነገር ነካክቶ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ጠንካራ የፀጥታ ሀይል እስከሚደራጅ ድረስ ፈተናውን በትዕግስት ማለፍ ይጠይቅ ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድም ባለፈው ሳምንት ከኦቢኤን ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የግል ጠባቂዎቻቸውን እንኳን ለመቀየር የተቸገሩበት ጊዜ እንደነበር ገልፀዋል። እንግዲህ ዶክተር አብይ ይህንን ሁሉ ፈተና አልፈው ነው መንግስታቸውን አጠናክረው ህግ ማስከበር የጀመሩት። ታዲያ እኝህ ሰው ድጋፍ አያስፈልጋቸውም?
እኔ በበኩሌ ከላይ እንደገለፅኩት በዶክተር አምባቸው ላይ የፈፀምኩትን ስህተት በጠቅላይ ሚንስትር አብይ ላይ መድገም አልፈልግም። ሰው ተሰባሪ ነው! እግዚአብሄር ክፉውን ነገር ያርቅ እንጂ ዶክተር አብይ አንድ ነገር ቢሆኑ ወይም ከስልጣናቸው ተነስተው አገሪቱ ወድ ትርምስ ብታመራ “አያሳዝንም ወይ” እያልኩ ሳንጎራጉርና በፀፀት ራሴን ስገርፍ መኖር አልፈልግም። ለዚህ ነው “አብይን የምደግፈው ለራሴ ስል ነው” የምለው! “ድጋፍ በሚሻበት ሰአት ለምን ከጎኑ አልቆምኩም?” የሚል የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማኝ አልጋየ ላይ መውደቅና የሰላም እንቅልፍ መተኛት ስለምፈልግ ነው አብይን የምደግፈው!
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
ነፃ ሕዝብ says
መደገፍ መብት ነው ፥ ነገር ግን እርሱ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ እየደረሰባቸው ያለው እጅግ አስከፊ ግድያና ሲቃይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና መቋጫም ያልተገኘለት ሆኖዋል ፥ በእጅጉ የሚገርመው ደግሞ እርሱ ከመጣ በሁዋላ በርካታ ለውጦች እንደተደረጉ በሰፊው ይወራል ፥ ምንድነው ለውጡ ? የፋሽስቱና ነፍሰ-ገዳዩ ህወሃት ሕገ መንግሥት እንዳለ ነው ፥ በህወሃት ዘመን የነበሩ ሰዎች እስካሁንም አሉ ፥ ከህወሃት የቅኝ ግዛት ወደ ኦሮሞ ቅኝ ግዛት ተሸጋገረ እንጂ አንዳችም ለውጥ የለም ፥ እስሩና ሰብአዊ ጥሰቱ ቀጥሎዋል ፥ በየግዜው በርካታ ኢትዮጵያውያን እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ይገኛሉ ፥ ከፋሽስቱና ገዳዩ ህወሃት በባሰ ሁኔታ እጅግ አስከፊና ለመስማት የሚዘገንን የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ እንጂ አቶ አብይ አህመድ አሊ ያመጣው አንዳችም ለውጥ የለም ፥ እንዳውም ከዘረኛውና ሀገር ሻጩ ህወሃት የባሰ የአፓርታይድ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋና ፋሽዝም እየነገሰ ሄዷል ፥ አብይ ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ያለው እጅግ የከፋና የከረፋ አመለካከት ሲሆን ሀገሪቱን ወደ እስልምና ሃይማኖት ለመለወጥ ውስጥ ውስጡን እያሴረና ኦርቶዶክስን እያዳከመ ያለ እጅግ አደገኛ ሴረኛ ሰው ነው ፥ 4 መስጊድ ሲቃጠል በአደባባይ ወጥቶ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል የነበረ አያሌ ቤተ ክርስቲያኖች ሲቃጠሉና የኦርቶዶክስ ተከታይ ወገኖች ሲታረዱ ትንፍሽ ያለው ነገር የለም ፥ አንዳችም የማስተዛዘኛ ቃላት እንኳ ሊወጣው ያልቻለ ፀረ-ኦርቶዶክስ ነው ፥አብይ አፈ ቅቤ ሲሆን ልቡ ግን ጩቤ ነው ፥ በፋሽስቱ ህወሃት ተኮትኩቶና በሴራና ተንኮል ሲጋት የኖረ እኩይ ሰው በጎ ነገር መጠበቅ አብዝቶ ሞኝነት ነው ።
ase abe says
እውነት አንተ ስለ ኦርቶዶክስ ዕምነት ተቆርቁረህ አይደለም ።ግን ድብቅ ሤራና ጥላቻ ወይም ዲጂታል ወያኔ ነህ ። ወያኔ 27 ዓመት ሙሉ በቤተክርስቲያኗና በአማኟቿ ላይ የፈፀማቸውን ግፍና በደሎች የሚዘነጉ አይደለም ። ሁለት ሲኖዶስ አቋቁመው አማኙን ግራ ሲያጋቡ የነበሩ የሀይማኖት አስታርቆና አስማምቶ በአንድ ላይ ተጠቃለው እንዲሰሩ፤ ውጭ ያሉትም ቀሳውስትና ጳጳሳት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረገ (ያውም ያለ ትራንስፖርት ወጪ) ፤ ደርግና ወያኔ ወርሰዋቸው የነበረውን የቤተክርስቲያንዋ ገቢ ምንጭ ህንፃዎችን እንዲመለስላት ያደረገ፤ ቤተክርስቲያኗና በአማኟ መካከል አንፃራዊ ሠላም እንዲኖር ያስቻለ፤ ” ኦርቶዶክስ ሃገር። ነች” ብሎ በአደባባይ የመሠከረው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ነው እንጂ ፋሽስቱ ለገሠ ዜናዊ አይደለም ። የኦርቶዶክስ ጠላት ቢሆን ኖሮ ዝም ብሎ ጉዳችንን ማየት ይችል ነበር።አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ነውና ወግድ ይሁዳ ብዬሃለው ። ከእነ ችግሩም ቢሆን ከባንዳ ወያኔ አብይ ይመረጣል።
Tesfa says
በሲያትል አሜሪካ የኦሮሞ አክራሪዎች ኢትዮጵያ ትውደም፤ አብይ ይውደም፤ አማራ ከኦሮሚያ ይውጣ እና በትልቅ ካሚዪን ቢጫን ተርፎ የሚቀር የስድብ ጋጋታ ሴት፤ ወንድ፤ አዛውንት ሳይሉ አወረድት። የሚገርመው ያው ልክ ወያኔ ያረግ እንደነበረው በደቦ ተደራጅተው ሰው መደባደባቸው እጅግ የሚያስገርም ትዕይንት ነበር። እውነትም አለሙ ሁሉ አብዷል ያሰኛል። እኔ ለኦሮሞ ጽንፈኞች እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ። ከሰፈር አሸባሪነት ወደ አለምአቀፋዊ አሸባሪነት በመድረሳቸው። ይደንቃል። በመሰረቱ ኢትዮጵያ የትግራይ፤ የአማራ የኦሮሚያ መኖሪያ ብቻ አይደለችም። ከ 80 በላይ የሚጠጉ ብሄረሰቦች መኖሪያ እንጂ! ወያኔ የኦሮሚያ ክልል፤ የአማራ ክልል፤ የትግራይ ክልል፤ የአፋር ክልል ወዘተ ስላለ ምድሪቱን ያንተ ዘር ብቻ አድርገህ የምታይ ማንህም ብትሆን ከብት ነህ። አሜሪካ ላይ ቆሞ ሰው በፓለቲካ ሰበብ የሚደበድብ ማንም ይሁን ምንም ከቀንድ ከብቶች አይሻልም። ለዛ ይሆነ ቀልደኛው በሲያትል የደረሰውን ጉድ ከተመለከተ በህዋላ “ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች ከአፍሪቃ አንደኛ ናት የሚለው ሚስጢር የገባኝ አሁን ነው ያለው”. አይ ለነጻነት መቆም እንዲህም ብሎ ነጻነት የለም። ሌላውን እየገፈተሩ የመኖር ናፍቆት!
በወያኔና በኦሮሞ አክራሪዎች የምናየው እብደት ሰማይ ጠቀስ ነው። ማንም ሰው ይህን እንደ ጤናማ የፓለቲካ እይታ የሚያይ ካለ ራሱን መመርመር አለበት። አበራ ለማ ሞገደኛው ነውጤ በሚለው ድራማዊ ነክ ጽሁፉ ላይ ባልፈጸመው የጓደኛው ሞት ሳያውቀው ተከሶ የቀረበው ሰው ጃኛው ፍ/ቤት ሲያዋክቡት ጌታው ” ጤና መሆን ወንጀል ነው እንዴ” በማለት አዞሮ የጠየቃቸው ትዝ አለኝ። ይመስለኛል ለእውነትና ለሰው ልጆች መብት መታገል ህመምተኛ የሚያስብልበት ጊዜ የደረስን ይመስለኛል። በዘሩ እንደ ድር አራዊት ተሰልፎ የሰው አንገት እየቀላና እየዘረፈ ንብረት የሚያቃጥለው ደግሞ እስይ የሚባልበት ጊዜ ላይ ነን።
ዶ/ር አብይ የገደለን እስካልገደለ፤ ቤትና ንብረት የዘረፈና ያቃጠለን ለቅሞ እስካላሰረ ድረስ ይህ የጃዋር ሰራዊት በቋንጭራና በገጀራ የራሱን አንገት እንደሚቀላው ማወቅ አለበት። እኔ ወያኔ አፍቃሪ አይደለሁም። ግን give credit where credit is due በሚለው ህሳቤ ወያኔ በስልጣን ላይ ቢሆን ኑሮ ይህ ሁሉ አይፈጠርም። ተኩሶ ቁም የሚል ዋርድያ ያለው በመሆኑ ይጠራርጋቸው ነበር። በነካ እጄ ወያኔ በግድቡ ዙሪያ ሲወሳ በክፉ እንጂ በመልካም ተወስቶ አይታወቅም። እውነቱ ግን ከወያኔ በፊት የነበሩ ሁሉ አወሩ እንጂ ሃሳብን ወደ ተግባር ለመለወጥ አልቻሉም። ስለሆነም የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እይታ ሊመሰገን ይገባዋል። አባይን የደፈረ ጀግና እሱ ነው። አሁን ወያኔ በመቀሌ የሚሰራውን ክፋት ቢያይ ምን ይል ይሆን? አይ ጊዜ!
ዶ/ር አብይ በእኔ እምነት ሊደገፍ ይገባዋል። ያው በፈጠራ ወሬ እከሌን አስገደለ፤ እከሌን አባረረ፤ ለኦሮሞ አዘነ ወዘተ የሚለው ወሬ ሁሉ ውሃ የማይቋጥር ጭራሽ ውሸት አለዚያም የተጋነነ ጉዳይ ነው። ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤ/ክ አይጠላም። ይህ ውሸት ነው። በእነዚህ 2 አመታት በሰራቸው ሥራ ነው መመዘን ያለበት እንጂ በወያኔ ፤በአማራ ወይም በኦሮሞ አክራሪዎች የተዛባ መስፈርት መሆን የለበትም። የሚያሳዝነው አማራው ጄ/አሳምነውን አስገደለ ይላል። በሥፍራው የነበሩ ሁሉን ነገር ከሥሩ የሚያውቁ ሰውየው ከአመራር ጋር ባለመስማማት ከስብሰባ ሁሉ እየቀረ በህዋላ የአማራ አመራር የሚባሉትን በጥይት ደብድቦ እንደገደለ ግልጽ ነው። የጄ/ ጻረ ገዳዮችም ገደለ ተብሎ የታሰረው ልጅ አይደሉም። ሌላ እንጂ። እረ ስንት ማለት ይቻላል። እናማ እነዚህ የፓለቲካ ደነዞች ሴት ልጅ እየደበደቡ፤ እየዘረፉ፤ እየደፈሩ አስከሬን በመኪያ እየጎተቱ “ኦሮሞ ነጻ ትውጣ” የሚሉን ነገም ዛሬም በሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ላይ ለመቀለድ ብቻ ነው። እነዚህን ሃይሎች ከአሁኑ በህቡዕና በይፋ በሃገር ውስጥና ውጭ እስካልተፋለምናቸው ድረስ ገና ብዙ አሳፋሪ ነገር ይፈጽማሉ። የትግራይ ልጆች ከእነዚህ አውሬዎች ጋር በእርግጥ አብረው ተሰልፈው ከሆነ ታመዋል። ቤ/ክርስቲያን ከሚያቃጥል ድርቡሽ ጋር። አይደረግም። አሰፋ ጫቦ አንድ ጊዜ አንድ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሊመለምለው ጎሳውን ወይም ዘሩን ይጠይቀዋል። እሱም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለት ሲመልስለት ከእጣት እጣት ይበልጣል በማለት ሊያባላን አስቦ የቀረበው የስለላ መረቡ መልማይ አፍሮ ትቶት እንደሄድ ራሱ አጫውቶናል። ግን ያ ጀግና ዛሬ የለም! አይ አንተ ሞት ልፋጩን ትትህ እንዴት የሰውን ህይወት ሊለውጡ የሚችሉ ጀግኖችን ትቀማናለህ? ይብቃኝ!