
ባለፈው ሳምንት ስለ ልደት በዓል በቤተ ክርስቲያናችን አውደ ምህረት ላይ የቀረበውን በቪዲዮ የተመለከቱ ወገኖች፤ “ኢትዮጵያ በወያኔ እጅ ከመውደቋ በፊት ከጌታችን ልደት በዐል ጋራ ተያይዞ ህዝቡ ገና በሚል ስም የሚጫወተው ጨዋታ ነበረው። ሊቃውንቱ ስለገናው ጭዋታ የሚሉት ነገር ካለ አካፍለን” ብለው ጠይቀዋል። ራሴ እየተጫወትኩት፤ በቅኔውና ባብነቱ ትምህርት እየተማርኩትና እየሰማሁት ያደኩበት ስለሆነ በወያኔ ዘመን ተወልደው ስለ ገናው አመታዊ ጨዋታ ምንም ለማያውቁት ባህላቸውንና ወኔያቸውን ለተዘረፉትና ለጠየቁኝ ኢትዮጵያውያን ከሞላ ጎደል አቅሜ የፈቀደልኝን ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ከክርስቶስ ልደት ጋራ ተሳስሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገር ከዳር እስከዳር ህዝብ ሲያንቀሳቅ (ሲያቆራቁስ) የነበረ የገናን ጨዋታ የመሰለ ህዝባዊ ነገር ይቅርና፤ ባንዲት መንደር የምትታይ ትንሽ ጥንታዊት ነገር፤ ያለ ምንም መነሻ የመጣች አይደለችም። ከኛ በፊት የነበሩት ሊቃውንት አባቶቻችን ይህንን ተገንዝበው እያንዳንዷን ጥንታዊት ነገር በጥንቃቄ እያጠኑ፤ ለሀገር ግንባታ ለህዝብ አንድነት እንዲጠቀም አርገው በመስራት ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሻገሩ ኢትዮጵያን በመጠበቅ እስከወያኔ ዘመን አድርሰዋታል።
በወያኔ ዘመን ግን በጥራዝ ነጠቅነት፤ በራስ ክብር ወዳድነት፤ በጥቅምና በባዶ ጭንቅላት እየተገፉ በድፍረት በመቅለብለብ የሚገሰግሱ ሰዎች በየጎራው በየደብሩ ተሰልፈው ሊቃውንቱን እየደመሰሱ ራሳቸውን ሰየሙ። እነዚህ የተሰየሙት ሰርጎ ገቦች የአገር ጠላትና የማርያም ጠላት እያደረጉ በሊቃውንቱና በተሰሩት ጠቃሚ ቅርሶች ላይ ዘመቱ። ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ስለጥንቱ ትምህርትና ታሪክ የሚናገሩትንና የሚመሰክሩትን ሁሉ እንዲታፈኑ እንዳይሰሙ ጭራሽ እንዲጠፉ ዘመቱባቸው። የገናው ጨዋታም ከሚመሰክሩለት ሊቃውንት ጋራ አብሮ የተዘመተበት እና ከኢትዮጵያ አካላዊ ቅርጿና ለዛዋ ጋራ የፈረሰና የተመታ ይመስለኛል።
ገና የምንለው ጨዋታችን hockey ከሚባለው ከበፈረንጆች ጨዋታ ጋራ ይመሳሰላል። በፈረንጁ ዓለም ጨዋታው ከእስፖርት ክፍል እንዳንዱ ሆኖ እንደሚታወቅና በክብር ተጠብቆ ለትውልድ በመተላለፍ ላይ እንደሆነ ከኔ የበለጠ ሁሉም በማጥፋት ላይ ያሉት ወያኔወች ሳይቀሩ ያውቁታል።
hockey የሚባለው የፈረንጆች ጨዋታ ball & crooked ከሚባሉት መሳሪያወቻቸው፤ እኛ ገና የምንለው ጠማማ ብትርና ጥንግ ከምንላት ጋራ ይመሳሰላሉ። ፈረንጆች hockey ለሚሉት ጨዋታቸውና ball & crooked ለሚሏቸው መሳሪያወች ምን ትርጉም እንደሚሰጧቸውና፤ ጨዋታውንም እንዴት እንደጀመሩት አላውቅም። ፈረንጆች ከኛ ይውሰዱት እኛ ከፈረንጆች እንገልብጠው አላውቅም።
ያም ሆነ ይህ የገናው ጨዋታ ረዥም ዘመን ስለቆጠረና ወደቅርስነትም ስለተሻገረ በሁለት መንገዶች፦ ማለትም በcultural anthropology እና በcultural theology ሊጠና ሊተረጎም የሚችል ይመስለኛል። ከcultural theology ጋራ ያገናኘሁበት ምክንያት ከጌታችን ልደት ጋራ ተሳስሮ የመንፈሳዊ ባህል ገጽ በመያዙ ነው።
በአገራችን በዓሉ እጅግ ገኖ የሚታወቀው ልደት ከሚለው ይልቅ ገና በሚለው ነው። በዓሉን ለመቀበል የሚደረገው ዝግጅት ጾም ነው። ከጾሙ ጎን ሌላው ትልቁ ዝግጅት የገናው ጭዋታ ነው። ጨዋታውን እኔም ባደኩባት መስክ ተሳትፌዋለሁ።
ጨዋታውን ሊቃውንት አበው የህብረተ ሰብን ስነባህርይ እንዲገልጽ አርገው ከህዝብ ስነ ልቡና ጋራ አዋህደውታል። ህብረተ ሰባዊ ለዛና ስነ ልቡና የያዘውን የገናን ጨዋታ እንደቅርስ ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ሲገባ፤ ባጭር ዘመን እስከመረሳት ደርሶ እንዴትና ለምን ነበር?ንገሩን በሚል ጥያቄ መቅረቡ እጅግ የሚያሳዝን ነው።
ፈረንጆቹ ሥጋዊ አካላቸውን ለሚጠብቀው ለስፖርት ብቻ ሲሉ ለጨዋታው hockey የሚል ስም ሰጥተው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሲያደርጉ፤ የኛ አባቶች ለሰውነት ብቻ ሳይሆን፤ የሰሩትን፤ “ሃይማኖትየኒ ዐቀብኩ” (1ኛ ጢሞ 4፡7᎗8)ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ባሳየው መንገድ፤ ለዘላቂው ስነ ባህርይ እጅግ እንዲጠቅም አርገው የሰሩልን፤ እምነቴን ሞራሌንና ጠቅላላ ስነ ባህርየን ጠበኩት እያልን እንድንኮራበት ነበር። ወያኔወች ይህንን በማፍረሳቸው ጭራሽም እንዲዘነጋ በማድረጋቸው በትውልድ በሀገር ላይ ጥፋት ፈጸሙ እየተባሉ ከሚከሰሱት ከወራሪዎች ከጣሊያኖች የባሱ እጅግ የከፉ ናቸው ብንል በሽተኛ ካልሆነ በቀር ጤነኛ የሆነ ሰው ውሸት ነው ሊል የሚችል አይመስለኝም።
እነ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ወራሪውን ጠላት ተፋልመው ካስለቀቁ በኋላ “ወጣት ተመልከት እንዳትሳሳት” እያሉ የመከሩን ከምዕራቡ የምንቀበለውን ትምህርት የራሳችንን የበለጠ እንድንረዳበትና ለበለጠ እድገት እንድንጠቀምበት እንጅ፤ እርስ በርሳችን እየተመቀኛኝን ለመጠፋፋት በምናደርገው በቂምና በበቀል የገና ጨዋታውን የመሳሰሉትን በየትም የማይገኘውን ቅርሶች ነቃቅለን ጥለን ኢትዮጵያን እዚህ ለማድረስ አልነበረም።
እነ መላከ ብርሀን አድማሱ “ወጣት ተመልከት እንዳትሳሳት” እያሉ የመከሩንን ከመስማት ይልቅ በባእድ ተንኮለኞች ትምህርት በተወረረና በተመረዘ ጭንቅላት የሰከሩ አንዳንድ ተወላጆች ለህዝብ መጎዳት እንቆረቆራለን እያሉ በሚያስመስልና የህዝብ ልብ በሚሰርቅ ንግግራቸው ህዝቡን እያታለሉ ፈጣሪ ይቅር የማይለውና ተፈጥሮ የማይረሳው በደል በህዝባችንና በአገራችን ፈጽመዋል። አሁንም እየፈጸሙ ናቸው። ከጎንደር ከጎጃም ከወሎ ለመላው ህዝብ የቀረበውን ህዝባዊ ጥሪና ከኦሮሞው ከውራጌውና ከወላይታው ከጋምቤላው የተመለሰውን ህዝባዊና ብሔራዊ ተሰጥኦ ለመቀበል አቅመ ቢስ የሆኑ ለመስማት የደነቆሩ ተማርን የሚሉ ጅሎች አሁንም ሲጃጃሉ ይታያሉ። ህዝቡ እንደነቃባቸውና እንደታዘባቸው የማይረዱ እርቃናቸውን መቆማቸውን የማይገነዘቡ ግብዞች ናቸው።
በተለይ፦የኢትዮጵያን አካላዊ ቅርጿን ያሳጣ ድንበሯን የቆረሰ ህዝቧን በቋንቌ ከፋፍሎ በጠላትነት እያሰለፈ በማፋጀት ላይ ያለው ወያኔ፦ “የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 አመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርሀ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው” ብሎ በቀየሰው የጥፋት መርሆ ለ27 ዓመታት እስከ ዚች ደቂቃ ድረስ ሲያፈርስ የኖረው የገናን ጨዋታ የመሳሰሉትንና ሌሎችን ኢትዮጵያ ነክ የሆኑትን ለአገር ለህዝብ ቤዛ የሆኑትን ሁሉ ቅርሶች እያደነ ማጥፋቱ፤ ወያኔ አገሪ አጥፊ እንደሆነ በግልጽ የሚያስረዳ ነው። በገና ጨዋታችን ያለው ጽንሰ ሀሳብ ወያኔ ካጠፋቸው ቅርሶች ጋራ በሙሉ ተካተው በተረጋጋ ጊዜ በጽሁፍ ተዛጋጅቶ ለትውልድ እንደሚቀርብ ተስፋ አደርጋለሁ።
ቃል ኳሄላ የመከነ ነባር ቃል ነው፤ የሚወልድ ግስ አይደለም ከየት ሰርጎ እንደገባ አላውቅም። ጥንግ የምትለው ግን፦“ያመነድቡኒ ወያጸነግ(ጵ)ውኒ አዕጽምትየ” (መዝ 41፡9) ። ከሚለው ሀረግ እንደተወሰደች ይናገራሉ። ሙሉ አረፍተ ነገሩ፦ “ለምንት ተሀድገኒ ወለምንት ትኩዝየ አንሶሱ፤ ሶበ ያመነድቡኒ ወያጸነጵኡኒ (ያጸነግኡኒ) አእጽምትየ ጸላእትየ” (መዝ 41፡9)። የሚለው ነው። ይህም ማለት፦ ይቃለቡኛል፤ ከለብ ወደለብ ይለጉኛል፤ ያጠነጉኛል ”
ጥንግ የምትባለው ቃል ከዚህ ሀረግ እንደተወሰደች ያብነቱ መምህራን አበው ይናገራሉ። ታዲያ ጥንግ ማለት እየተለጋች እየተጠነጋች ከለብ ወደለብ“ትኩዝየ አንሶሱ” የሚቃለቧት ማለት ነው። በባንቱ ጎል ሲባል ሰምቼ አላውቅም። ጎል የሚባለውን ቃል የሰማሁት አዲስ አበባ ነው። ያም ሆነ ይህ በቁርቁስ ተጀምሮ በሆታ የሚያልቀው የገናው ጫወታ፤ የሚካተቱት መሳሪወችና የተጫዋቾች ባህርያት በቅኔው፤ በምስጢራተ መጻህፍትና በማህበራዊ ግንዛቤ ትኩረት የላቁ አባቶቻችን የሚገልጹበት መንገድ Ethiopic (cultural)theology ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ይመስለኛል” በማለት በከንሳስ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ የቀረበውን ትምህርት እንድትከታተሉት ከዚህ በታች ቪዲዮውን አቀረብንላችሁ።
በቀሲስ አስተርአየ ጽጌ nigatuasteraye@gmail.com
ታህሳስ ሁለት ሽ አስር ዓ.ም.
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply