በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውጭ ግንኙነት ትብብር እና ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ አጭሶ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፣ በኢትዮጵያ የፈለገ ጥሩ ሃሳብ፣ ጥሩ አመለካከት ይዘህ ብትመጣ አንተን ለመቃረን ብቻ ሌላ ኃይል ተደራጅቶ ይጠብቅሃል። ይህ ማደም፤ ሴራ ነው። ይህ የሴራ ፅንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ አሁን ገዝፎ ወጥቷል።
“የፈለገ ጥሩ ሃሳብ፣ ጥሩ አመለካከት ይዘህ ብትመጣ አንተን ለመቃረን ብቻ ሌላ ኃይል ተደራጅቶ ይጠብቅሃል”። ይህ የሴራ ፅንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ አሁን ገዝፎ መውጣቱን ዶክተር ደመቀ ይናገራሉ።
መልካም ነገር ይዘህ ስትመጣ የአንተን መልካም ነገር የሚያኮላሹ፣ ከግብ እና ከዓላማህ የሚያጨናግፉ በርካታ ሕጋዊም ሆነ ሕገ ወጥ አደረጃጀቶች በሀገሪቱ እንዳሉ ያመለከቱት ዶክተር ደመቀ፣ እነዚህ ነገሮች ሆን ተብለው የሚደረጉ ካልበላሁ ልድፋው ዓይነት የአስተሳሰብ መሰረት ያላቸው ናቸው ብለዋል። ካልበላሁ ልድፋው ለየትኛውም ችግር መፍትሔ አምጥቶ እንደማያውቅም አመልክተዋል።
መልካም አስተሳሰቦች ስር እንዲሰዱና ግባችንን ማሳካት እንድንችል የሁሉንም ሰው ቀና ትብብር እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣ የሁሉም ሰው አስተሳሰብ የአመለካከት መገራትን እንደሚፈልግ አስታውቀዋል። የተለያዩ አመለካከቶች ይኑሩ፣ እንከራከር፣ እንወያይ፣ በጥሩ መንፈስ መከራከር መልካም ነው ብለዋል።
ክርክር ጥሩ የሚሆነው መልስ ለመሰጣጠት ብቻ ሳይሆን ራስን ለማነፅ፣ ክፍተቶችን ለመሙላት፤ የተከራካሪህንም ክፍተቶች ለመሙላት የምታደርገው ዴሞክራቲክ የሆነ እና የሰለጠነ ክርክር መሆን ሲችል እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህን ዴሞክራሲያዊ የሆነ ለመገነባቢያ የሚረዳ የክርክር ባህል ማዳበር እንደሚገባ አመልክተዋል። በእኛ ሀገር ግን እየሆነ ያለው ክርክር ለማጥቃት እና ለመከላከል እንደሆነም ገልጸዋል።
በኛ ሀገር የፖለቲካ ባህል ሀገር ሊገነባ የሚችል ሃሳብ ይዘህ ብትመጣ ከአንተ በተቃራኒ በመቆም ምንም ሳያዳምጥህ መልስ የሚሰጥህ ወይም ስትናገር የሚያዳምጥህ አንተን ለማጥቃት ወይም የአንተን ሃሳብ ለማኮላሸት ነው የሚሉት ዶክተር ደመቀ፣ ይህ ወደአሰብነው ግብ እንዳንደርስ እንደሚያደርገን ጠቁመዋል። እከሌ በዚህ ጎራ ተሰልፏል።
ስለዚህ ከሱ ጋር ላለመሰለፍ በማለት ሆን ተብሎ ከሱ ጋር ላለመሆን የሆነ ስንጥር እየሰነጠረ በተቃራኒህ ይቆማል። አንድ ከምሆን ሞቼ እገኛለሁ ይልሃል፤ ይህ የፖለቲካ ባህል የትም እንደማያደርሰን አመልክተዋል።
ይህ ዓይነት አካሄድ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሁን እየበዛ እንደመጣ ያመለከቱት ዶክተር ደመቀ፣ ከዚህ የተነሳም ግባችን ላይ እንዳንደርስ ፅንፍ የረገጡ ኃይሎች የአንዱን መብት፣ የመኖር ህልውና፣ ባህል፣ ወግ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ከግንዛቤ ሳያስገቡ እኔ ብቻ በሚል አስተሳሰብ ከምንጊዜውም በላይ ጎልተው መምጣታቸውን አስታውቀዋል።
“ይህን በዓለም ታሪክ ስንቃኝ የቡድን አስተሳሰብ (the we group, the they group) የእኛ ቡድን የእነሱ ቡድን፤ ከእኛ ለእኛ ወገን የእኛ ቡድን የሚጠቀመውን ነገር የእነሱ ቡድን እንዳይጠቀመው እናድርግ። የእኛ ቡድን የማያሳካውን ግብ የእነሱ ቡድን እንዳያሳካ እናድርግ የሚባል ሴራ በዓለማችን ላይ ከባባድ እልቂቶችን አስከትሏል” የሚሉት ዶክተር ደመቀ፣ የአንደኛውም ሆነ የሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ውጤቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
“ለብዙ የአይሁድ ማህበረሰቦች በአውሮፓ እንዲታረዱ ምክንያት ሆኗል። ጭፍን በሆነ ጥላቻ መሰላል (ደረጃ) አስቀምጦ እነዚህ፣ እነዚህ ሰዎች መወገድ አለባቸው ብሎ ማሰብ በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አይተናል። በኢትዮጵያም ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አልገባም ማለት አይቻልም። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰዎች በእሳት ሲቃጠሉ አይተናል። ይህ በጣም አጸያፊ ተግባር ነው። ጭፍን ጥላቻ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ወደ እልቂት እንዳያመራን ዋልታ እረገጥ አመለካከቶችን ማስቀረት፣ መቁረጥ፣ መከራከርም ይኖርብናል ብለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply