የአማራ ክልል መንግስት የመንግስት ተሸከርካሪ አያያዝ፣ አጠቃቀምና የንብረት አስተዳደር መመሪያ ሰሞኑን ማሻሻሉን ይፋ ቢያደርግም የከፍተኛ አመራሮች ሹፌሮች በበኩላቸው የተሻሻለው መመሪያ የኛን ሕልውና የሚፈታተን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጡ።
የክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሰሞኑን ለክልሉ ቢሮዎች በላከው ደብዳቤ ከመስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ወይም የሥራ ኃላፊዎች ለሥራ ጉዳይ ክልሉን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ የሚመሩትን ተቋም ተሸከርካሪ ይዘው እንዳሄዱ እያሳሰበ በተማከለ መንገድ በከተማው በሚዘጋጁ ተሸከርካሪዎች መጠቀም እንደሚችሉ አብራርቷል።
በተማከለ መንገድ በሚዘጋጁ ተሸከርካሪዎች መጠቀም የሚችሉ የሥራ ኃላፊዎች ብሎ የተሻሻለው መመሪያ የጠቀሳቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ ም/ርዕሰ መስተዳድርና በዚህ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች፣ የክልሉ ም/ቤት አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የካቢኔ አባላት የሆኑት የቢሮ ኃላፊዎች፣ ዋና ኦዲተር፣ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች የዞን ዋና አስተዳዳሪዎችና የሜትሮፖሊታን ከተማ ከንቲባዎችን ነው።
የተጠቀሱት ኃላፊዎች አዲስ አበባ ለሚደረጉ ማንኛውም ስብሰባዎች ወይም ሌሎች ሥራዎች ወደ አዲስ አበባ በአይሮፕላን የሚሄዱ ከሆነ ከአይሮፕላን ማረፊያ የሚቀበላቸውና በቆይታቸው ወቅት በማዕከል አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁ ተሸከርካሪዎችን ወይም በቀን 1200 ብር ያልበለጠ የመኪና ኪራይ በሕጋዊ ደረሰኝ መጠቀም እንደሚችሉ ያተተው መመሪያው ለከተማ አገልግሎት ተጨማሪ ተሸከርካሪ ማንቀሳቀስ እንደሌለባቸው አስረድቷል።
የተሽከርካሪ ስምሪትና የማስተዳደሩን ተግባር ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሥልጣን የሰጠው ይኸው መመሪያ በክልሉ የካቢኔ አባላት የሆኑ ቢሮዎች ምክትል ቢሮ ኃላፊዎችና በምክትል ቢሮ ደረጃ የተሾሙ ሹማምንቶች ወደ አዲስ አበባ በአይሮፕላን የሚሄዱ ከሆነ በማዕከል በተዘጋጁ ተሸከርካሪዎች መጠቀም የማይችሉ ከሆነ በቀን ከብር 600 ያልበለጠ የመኪና ኪራይ በመጠቀም በህጋዊ ደረሰኝ ማወራረድ እንደሚችሉ ያትታል።
በመመሪያው የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ተላልፎ የተገኘ የሥራ ኃላፊ ከተፈቀደለት የገንዘብ መጠን በላይ ያለውን ወጪ በግሉ እንደሚሸፍንና በመመሪያው ከተፈቀደው ውጪ ሂሳብ ያወራረደ የመ/ቤቱ የግዥ፣ ፋይናንስና ንብረት አስተዳደርም ተጠያቂ እንደሚሆን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የከፍተኛ አመራሮች ሹፌሮች በበኩላቸው እንደገለጹት የተሻሻለው መመሪያ የአሽከርካሪዎች የሥራ ሁኔታ ያላገነዘበና ለይስሙላ የወጣ መመሪያ እንደሆነ አውስተው “እኛ ከመንግስት የሥራ ሰዓት ውጭ ከኃላፊዎች ጋር እስከ ምሽት እያመሸን፣ ቤተሰቦቻቸውን እያመላለስንና የቤት ወጪያቸውን እየገዛንና ለምናደርስበት የትርፍ ሰዓት አገልግሎት አበል ሊታሰብልን ይገባል” ብለዋል።
የወጣው መመሪያ እርስ በርሱ የሚቃረን ነው ያሉት የኃላፊ አሽከርካሪዎች ለኛ ሳይታሰብ ስልጣን ላይ ላሉ አመራሮች ብቻ መታሰቡ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸው የክልል የኃላፊ ተሽከርካሪዎች አገሪቱ መዲና እንዳይደርሱ እያሳወቀ በዚህ መመሪያ ላይ የሥራ ኃላፊነታቸውን መሠረት በማድረግ የከተማና የመስክ ስምሪት የሚሰጡ ሁለት ተሽከርካሪዎች ለኃፊዎች ሊመደብ እንደሚችል ማተቱ መመሪያው የተሻሻለበትን ዋና ዓላማ አያመለክትም ብለዋል።
አያይዘውም በደላችንን የሚሰማን መንግስት ስሌለለ በደላችን የምንወጣበት ዘዴ አናጣም፣ ተያይዘን እናልቃለን ሲሉ ብሶታቸውን በየተቋሙ በምሬት እገለጹ ነው።
ለዝግጅት ክፍላችን በውስጥ መስመር የደረሰን መረጃ ነው። መረጃውን ከሌላ ወገን ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
Leave a Reply