
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል እንዲሁም የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ላይ የአሠራር ለውጥ ማድረጉን ተናገረ።
እነዚህን አገልግሎቶች ለማግኘት የሽያጭ ዋጋ ወይም የብድሩ ገንዘብ አከፋፈልን በተመለከተ ክፍያው መፈጸም ያለበት፦
- በሽያጭ ውል ጊዜ የሽያጭ ዋጋው ባንክ ከሚገኝ የገዢ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ሻጭ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ (Transfer) መሆን አለበት፣
- በብድር ውል ጊዜ የብድሩ ገንዘብ ባንክ ከሚገኝ የአበዳሪ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ተበዳሪ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ (Transfer) መሆን አለበት ሲል የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ለሸገር ነግሯል።
ይህ አሰራርም ከነገ መስከረም 7፣2013 ይጀመራል ተብሏል።
በተጨማሪም ህገወጥነትን ለመከላከል ሲባል የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በስጦታ የማስተላለፍ ውልን አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን ኤጀንሲው እወቁልኝ ብሏል።
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አሰራሩን የለወጠው ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀስ ጥሬ ገንዘብን ሥርዓት ለማስያዝ፣ ህገወጥነትን ለመከላከልና ዘመናዊ አሰራርን ለማስፈን ነው ብሏል። (ንጋቱ ሙሉ ከሸገር 102.1 እንደዘገበው)
ጎልጉል የድገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply