ከጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በሳዑዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን የኃይል ጥቃት ለማውገዝ በአዲስ አበባ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠራ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አባል ፓርቲዎች ትናንት በመድረክ ጽ/ቤት በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ በሳዑዲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሳዑዲ ፖሊስ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈፀሙን፣ አልፎ ተርፎም እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን በመግለፅ ሁኔታውን አውግዟል።
የችግሩ ክብደትና አሳዛኝነት በመቀጠሉ ድርጊቱን በመግለጫ ከማውገዝ ባለፈ ሁኔታውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመቃወም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከመድረክ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በኋላ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንዳረጋገጡት መድረክ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ከሚያወጣው የተቃውሞ መግለጫ ጎን ለጎን ሰላማዊ ሰልፍ እንዲጠራ መወሰኑን ተናግረዋል። ሰልፉን ለማካሄድ ለአዲስ አበባ የሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ክፍል ለማሳወቅ ደብዳቤ እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልፀዋል። ኅብረተሰቡም ድርጊቱን ለማውገዝ ከፓርቲዎቹ ጎን በመቆም የተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ ጥሪ አድርገዋል። የሰልፉ ቀንና ቦታ በአጭር ቀናት ውስጥ ለሕዝቡ እንደሚገለፅም አያይዘው ገልፀዋል:: የሰንደቅ ዜናዎች (በዘሪሁን ሙሉጌታ)
Leave a Reply