• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ሥራ በኢትዮጵያ

January 1, 2014 09:16 pm by Editor Leave a Comment

በሀገረ ሐበሻ ፤ ክቡር ነበር ሥራ
የሥራ ባሕሉ ፤ ነበረ ጠንካራ
በዓለም መድረክ ላይ ፤ ያደረገው አውራ
ኃያል ጉልበተኛ ፤ እጅግ የሚፈራ
የግዛት ሀገሩን ፤ በምዕራብ ምሥራቁ
አስፋፍቶ ያስያዘው ፤ እያስገበረ ዕንቁ
ዛሬ ግን ስናየው ፤ ያ አውራ ሐበሻ
የቀን ጎደሎ ገጥሞት ፤ ነክሶት ክፉ ውሻ
እዚህ ሀገሩ ላይ ፤ ከእሱው መዳረሻ
ከቶ የማይነካውን ፤ ብዙ የሥራ ድርሻ
ይህ ጨዋ የጨዋ ዘር ፤ የጌታ ልጅ ጌታ
የሎሌ የባሪያ ነው ፤ ያለውን ገበታ
ርቆ ይሄድና ፤ ከሩቃኑ ጓዳ
ተደብቆ ከወገን ፤ ታይቶ እንዳይከዳ
ያለዕረፍት ይሠራል ፤ ተግቶ አስንቆ ባዳ
መጥቶ የማይነግረንን ፤ ሳያፍር ሳይጎዳ
ባሪያው ከነበሩት ፤ ካሳያቸው ፍዳ ፡፡
ሥራን ወዶ ማክበር ፤ ሠርቶም ሀብታም መሆን
ከጥንት ጀምሮ ፤ ነበር ባሕላችን
ወደ ኋላ ግና ፤ የአውሮፓ ሚሲዮኖች
አዩትና አቅሙን ፤ የሕዝቡን እሴቶች
የጎጆ ኢንዱስትሪው (ምግንባቡ) ፤ የያዘውን ቦታ
ነገ እንደሚሆነን ፤ ለሀገር ሆኖ አለኝታ
ሊመጥቅ እንደሚችል ፤ በኪነ ብጀታ (በቴክኖሎጂ)
ስለታወቃቸው ፤ ክፋትን ሸረቡ
ያን የሚሠሩትን ፤ ትጉዎችን ከሕዝቡ
ነጥሎ ለማጥፋት ፤ ከኅብረተሰቡ
እንደዚህ እያሉ ፤ ሰበኩ ከተቡ
እኛ በሀገራችን ፤ ይሄን የሚሠሩ
ብረት የሚያቀልጡ ፤ ሸክላንም ከአፈሩ
በቡዳ ዓይን በልተው ፤ እያስለፈለፉ
ብዙ ሕዝብ እየፈጁ ፤ ሆነው የሚያጠፉ
እነሱን ሰብስበን ፤ ካጠፋን በኋላ
ነው ሰላም ያገኘን ፤ የኖርነው በተድላ
እናንተም እንደኛ ፤ ካላደረጋቹህ
ጤና አይሰጧቹህም ፤ ካልመነጠራቹህ
ብለው ሰበኩና ፤ ወደ ሕዝብ በመግባት
የጥፋቱን ሴራ ፤ መርዘኛውን ስብከት
ቀጥቃጭ ሸክላ ሠሪን ፤ ቡዳ በማሰኘት
ከሰው እንዳይደርሱ ፤ እንዲያልፉ በግዞት
አድርገው በማጥቃት ፤ በእርኩስ ምቀኝነት
ከእድገት ገቱንና ፤ አበቁን ለውድቀት
እነዚህ እርጉሞች ፤ በዚህ ሳይበቃቸው
የቀረውን ሥራ ፤ ተግቶ ለሚሠራው
እኛ በሀገራችን ፤ ይሄን ዓይነት ሥራ
የሚሠራ ሁሉ ፤ ነው ከባሪያ ጎራ
ጨዋ የጨዋ ልጅ ግን ፤ እንደዚህ ዓይነቱን
ቢሞት አይነካውም ፤ በዘሩ የሌለውን
ያዛል እንጅ ያሠራል ፤ባሪያ አገልጋዩን
እያሉ ስሜቱን ፤ ሲያጠቁት ክፉኛ
ኃያል ያረገንን ፤ ብርቱ ባለሻኛ
ባለ ሠይፍ አለቃ ፤ የዕቡያን ዳኛ
እውነት መሰለውና ፤ ስለተታለለ
ያ ክብር ዐቢይ ሀብቱ ፤ እጅግ ተጃጃለ
ሥራን ንቆት ቀረ ፤ ላለመባል ባሪያ
ሴራቸውም ሠምሮ ፤ ደኸየች ኢትዮጵያ
ያኔ ለተሠራበት ፤ ሸር በእነዚያ ውሻ
አቶለት መፍትሔ ፤ ቸግሮት ማርከሻ
ዛሬም ይቸገራል ፤ እንጃ መጨረሻ ፡፡
የዚህ ክፉ ሴራ ፤ አደጋው ታይቷቸው
የዐፄ ፋሲል ልጅ ፤ ዮሐንስ አንደኛው
ሳይጸና ለማረም ፤ ስር ሰዶ ሳይወረው
ልምሹ ሽባ አድርጎ ፤ ሐበሻን ሳይነቅለው
ንጉሥ ሆነው ሳለ ፤ ሳይኖር የቸገራቸው
የሥራን ክቡርነት ፤ ለማሳየት ብለው
ከቤተመንግሥቱ ፤ ኢምንትን ሳይነኩ
በላብ እያደሩ ፤ በሥራ ሊማርኩ
ሰሌን እየሠሩ ፤ ሥራ እየሰበኩ
ከቶም ላለመንካት ፤ የደሀን ግብር እንኩ
ከዚያ በሚያገኙት ፤ እየተዳደሩ
መሥራት እንደሆነ ፤ የጨዋ ዘር ግብሩ
እሳቸው ንጉሡ ፤ ሠርተውም ቢያስተምሩ
በካህንነታቸውም ፤ ሊሠራ የማይወድ
አይብላ የሚለውን ፤ የአምላክን ቃለ ፍርድ
ለአዳምም ያለውን ፤ ጥረህ ግረህ ብላ
ሰብከው እያሰበኩ ፤ ቢተጉም በመላ
ሊነቀል አልቻለም ፤ ያክፉ አሜኬላ
ዐፄ ቴዎድሮስም ፤ ጀግናው ስመ ጥሩ
ንጉሥ ሆኖ እያለ ፤ ባለዝና ኩሩ
ጫማ እንኳን ሳይመኝ ፤ እየሄደ በእግሩ
ዶማውን ጨብጦ ፤ በእጁ እየቆፈረ
የሥራን ክቡርነት ፤ ቢያሳይ እየታተረ
ብዠታ ሴራውን ፤ ሊያጠፋ እየጣረ
መሪ ቃል አውጥቶ ፤ ነዶ እየፎከረ
ታላቅ እንደነበርን ፤ በዓለም ትናንትና
ታላቅ እንሆናለን ፤ ዛሬም እንደገና
እያለ ተቃጥሎ ፤ ባለው ፍቅር ለሀገሩ
አባብሎ በመላ ፤ እሽ ያለለት ለታ
እንቢ ሲለው ደሞ ፤ ሳይወድ በግዴታ
በቆራጥ አመራር ፤ ቢለውም ከምሩ
ሳይነቀል ቀረ ፤ የሰይጣን ምክር ስሩ
ሌሎችም ትጉሐን ፤ ብዙ ቢሞክሩ
አሁንም አልጠፋም ፤ ያ የእንክርዳድ ዘሩ
ከዐፄ ዮሐንስ በላይ ፤ ሰባኪ አንደበቱ
ከዐፄ ቴዎድሮስ በላይ ፤ ቆራጥ ክንደ ብርቱ
ከቶ ማን መቶለት ፤ ይማራል በእውነቱ ?
ምከረው ምከረው ፤ እንቢ ካለ ግና
መከራ ይምከረው ፤ እንዳለው ሳተና
ምናልባት ይማራል ፤ ሲታሽ በመከራ
ግን ከዚህ የከፋ ፤ ምን መጥቶ ሊገራ ?
ነው ወይስ ተምሯል ? አውቋል ያንን ሴራ ?
ተሰብሮ መውደቁን ፤ ማውደሙን አደራ ?
የኛ የሥራ ባሕል ፤ የነበረው ድሮ
ርእሰ ኃያላን ፤ እያለን ጀምሮ
ገና በኦሪቱ ፤ በአምላክ አስተምህሮ
የበዓል ቀናት ተብለው ፤ የማይሠራባቸው
ከወር እስከ ዓመቱ ፤ ነበሩ ተለይተው
በሐዲስ ኪዳንም ፤ እንደ ጥንቱ ሁሉ
የበዓላት መከበር ፤ በሐዲስም ቀጠሉ
ነገር ግን ሥርዓቱ ፤ እንደ ጥንቱ ሳይሆን
የተለየ ሆኗል ፤ ስናይ አከባበሩን
የሐዲስ ኪዳኑ ፤ በበዓል ቀናቱ
ሥራ እንዳይሠራ ፤ ቢልም እንደጥንቱ
ለይቶ ባወጣቸው ፤ ከወሩ በአምስቱ
ቀኖናዊ በሆነው ፤ አስተምህሮቱ
በአከባበሩም ላይ ፤ ታይቷል ልዩነቱ ፡፡
ሕይዎት የምትቀናው ፤ ሥራ ባሉት ብቻ
ከቶ አይደለምና ፤ የችግር ቁልፍ መፍቻ
በእነዚህ በዓላት ፤ የታዘዘው ተግባር
ሕይዎት የሚያቀና ፤ ብዙ አለው ቁምነገር
በማኅበራዊው ፤ ሕይዎት መስተጋብር
የታመመ ያዘነን ፤ ገጥሞት እክል ችግር
የታሰረን ወገን ፤ ታርዞ የተራበን
ደካማ ወገን አልባን ፤ ድጋፍ የሚያሻውን
መጎብኘት መጠየቅ ፤ እርገው የታዘዘውን
ለመገንባት ፍቅርን ፤ ሰ ብ አ ዊ ነ ትን
በጋብቻ ሕይዎት ፤ ለሦስቱ ጉልቻ
ለሚተሳሰሩ ፤ መሥርተው ጋብቻ
ሽምግልናው ምክሩ ፤ እንዲሠምር በእሽታ
በሌላውም ጉዳይ ፤ በተለያየ ቦታ
በጥል በክርክር ፤ ላጣም ሰላም ፋታ
ማስታረቅ ማስማማት ፤ ወጥቶና ወርዶ
ጥላቻን አጥፍቶ ፤ አፋቅሮ አዋዶ
ወደ አምላክ ቤት ሔዶም ፤ ቃለ እግዜርን መስማት
ሰብእናን ማነጽ ፤ ምግባርን ማቃናት
ክብር ምስጋናን ማቅረብ ፤ ማወደስ በጸሎት
ለቀለሱት ትዳር ፤ ለተወለዱ ልጆች
በቂ ጊዜ መስጠት ፤ እንዳይጎዱ በአንዳች
ዕቅድንም መንደፍ ፤ ነገ ለሚሠራው
መምከር ማደራጀት ፤ ገብቶ በጎደለው
ይሄን ይሄንና ፤ እንዲህ የመሳሰለው
ጉዳይ ይከወናል ፤ በዓል ቀን በሆነው
ኑሯችን በሥርዓት ፤ እንዲሆን ዐቅድ ያለው ::
እንዲህ አርጎ አበጃጅቶ ፤ ኑሮውን ሲገፋ
ሥራውን ሲሠራ ፤ አጥቶ ሳይከፋ
ያው ወደኋላ ግን ፤ ገጠመው ደንቃራ
በቅኝ ግዛት ሰላይ ፤ ተተብትቦ ሴራ
ከወደ አውሮፓ ፤ ክፋትን ሸርበው
ሰተት ብለው ገቡ ፤ ቅን አሳቢ መስለው
እንዲያው ግን በሞቴ ፤ ምንድን ነው ያረግናቸው ?
ጥርስ የነከሱብን ፤ የዚህን ያህል ከፍተው ?
እነዚያ እኩያን ፤ ካመጡብን ዕዳ
ከዋናዎቹ አንዱ ፤ ሀገርን የጎዳ
መቀመቅ ያገባን ፤ ያስቆጠረን ፍዳ
የነጻነት ጥቅሟን ፤ ዋጋ እያደባዩ
ከሥራ አጣልተው ፤ ከሀብት እያደኸዩ
መቋቋም እንዳንችል ፤ ሲወረን እኩዩ
ለባርነት ግዛት ፤ ሲያመቻቹን ቆዩ
ከሚሲዮን ልሳን ፤ ጤና አለ ብላቹህ
ጆሮ ልባቹህን ፤ ከፍታቹህ ሰጥታቹህ
እመቀ እመቃት ፤ ዘቅጣቹህ ገባቹህ
ይሄም ሁሉ አልፎ ፤ ዛሬም እንደገና
ሚሲዮን ለሀበሻ ፤ ብለህ ያስባል ቀና
ጆሮና ልብህን ፤ ከፍተህ ሰተሀልና
ደሞ ልትቆጥር ነው ፤ ሌላ የአሳር ዙር ገና
ሥነ ልቡናውን ፤ እያወሳሰቡ
በሳይካትሪ ቁማር ፤ ግራ እያጋቡ
ስንቱን የተማረ ፤ ንክ ፉዞ አደረጉ
ስንቱን ቀለዱበት ፤ እንዲያ እንደፈለጉ
ለሀገር ለወገን ፤ አርገው እንዳይሠሩ
ሰብአዊ ልማቷን ፤ በገፍ አከሰሩ
ፖለቲካም ገብተው ፤ በሀገር ልጆች መሀል
በፈለጉት መንገድ ፤ ጠምዝዘዋቸዋል
ሰላምና አንድነት ፤ ለመቸም እንዳይኖር
ቁልፍልፍ አድርገው ፤ ታንፈታው በማሰር ፡፡
እንኳን ሊቀበሉት ፤ ሊሰማ የሚያስነውር
በቅድስት ኢትዮጵያ ፤ በእግዚአብሔር ምድር
ባሕልን የሚቃረን ፤ ሃይማኖትን ጭምር
እንኳን በሃይማኖት ፤ በዓለማዊ ላሉ
ከቶ የማይታሰብ ፤ ይሁን ለመባሉ
ሰዶማዊነትን ፤ ተቀበሉ እያሉ
ከሰይጣን እንደሆኑ ፤ በይፋ ያሳያሉ
አእምሮ ያለው ሰው ፤ ይሄን ጊዜ እንኳን
ነቄ ብሎ አይወጣም ? ጣጥሎ አጋንንትን ?
ዓላማ ግባቸው ፤ ዐውቆ ምን እንደሆን
ሃይማኖት የሚሉት ፤ እነደሆነ ሽፋን
ዛሬ በዚህ ጊዜ ፤ ያልነቃ ጭንቅላት
መቸም አይባንንም ፤ ምንም ቢያደርጉት ፡፡
ይህ የዋህነት ነው ? ወይንስ ጅልነት ?
በሚሲዮን ሴራ ፤ ደርሶ እያለ ሞት
አእምሮ ያለው ሰው ፤ የሚያስብ ጭንቅላት
የሚከነክነው ፤ የሀገሩ ውድመት
የሚቆረቁረው ፤ የሥልጣኔው መጥፋት
ይመስዮንናል ? ለማገልገል ጠላት ?
ራሱን ለመንቀል ፤ በሰይጣን እጆች ጣት ?
በየትኛው መጽሐፍ ፤ በምን ምስክርነት ?
እሱ ካንተ ይልቅ ፤ ለአምላክ ኖሮት ቅርበት ?
ደሞ እምንህ ደርሶ ፤ የትና መቸ ዐውቆት ?
ከነ መኖሩ እንኳን ፤ መጽሐፉ ያልጠቀሱት
ማን ይናገር ሲባል ፤ ያየ የነበረ
ማንስ ደሞ ያርዳ ፤ እንዳልክ የቀበረ
አንተ ለሱ ተርፈህ ፤ ትሰጣለህ እንጅ
ምን ጎሎህ ምን አተህ ? ትቀበል ከእሱ እጅ ?
ምን ዓይነት አዚም ነው ? ምንስ ዓይነት አስማት ?
እንደዚህ የሚያፈዝ ፤ የሚያደነዝዝ ሞት
ማስተዋል የሚነፍግ ፤ የሚያቅት ለመንቃት ?
አደንቁሮ የሚገል ፤ የደመነፍስ ሕይዎት
ቀድሞስ እውነት መስሎህ ፤ ሳታውቅ ተታለህ
ዛሬ ምን ሆነህ ነው ? እንዲህ መጃጃልህ ?
ማንነትህን ሳይቀር ፤ ሲነቅለው ከልብህ
ሸሩ ሳይታይህ ፤ ፈዘህ ምርዝ መጋትህ ?
አንድ ጊዜ እንቅፋት ፤ ደጅ መንገዱ ላይ
ያደናቀፈው ሰው ፤ ደግሞ እሱው ድንጋይ
ቢያነቅፈው እንደገና ፤ ድንጋዩ እራሱ ነው
ተብሎ እንደተባለው ፤ ንቃት የጎደለው
ሆነህ ቀረህለት ? ሁሌ የሚያጃጅለው ?
መቸ ነው የምትነቃው ? ምንስ ቢያደርግብህ ?
ባዶ እጅህን ቀርተህ ፤ ሁሉን ነገር አተህ
የዛኔ ብትነቃ ፤ ምን ትፈይዳለህ ?
ምንም ምን ለማድረግ ፤ ዕድሉ እኮ አይኖርህ
ንቃ ንቃ ንቃ ፤ እባክህን ንቃ
እንደ የእርግማን ልጅ ፤ አትልመድ ሰቆቃ
ደንበር ብለህ ተነሥ ፤ ሁሉንም በል በቃ
ሀገርህን ማየት ፤ አትሻም ወይ ልቃ ?
በቀድሞው ቦታዋ ፤ እንደገና ታውቃ ?
እስከመቸ ታስራ ፤ እስከመቸ ወድቃ ?
ኢትዮጵያና አፍሪካ ፤ የሆኑት መጻጉ
በአውሮፓ ሚሲዮን ፤ ነው ስለተወጉ
ታሪክ ይንገራቹህ ፤ ሀቁን ብትፈልጉ
ይሄ የሰይጣን አዚም ፤ የማይለቅ ከሆነ
በአፍሪካ ኢትዮጵያ ፤ እየተኮነነ
የመርዝ መርፌውን ፤ መውጋት ከቀጠለ
ዛሬም እንደቀድሞው ፤ ጠልቆ እየሰለለ
ፀሐይ ላትወጣ ነው ፤ ጨለማም ገነነ
ደኅንነትም አይኖር ፤ ሞት ከሠለጠነ
ሰይጣን ከነገሠ ፤ ሴራው ከሰፈነ

ጥር 2003 ዓ.ም.

amsalugkidan@gmail.com

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Literature Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ወርቁ አይተነው የሸሹት ከዝርፊያ፣ ውንብድናና ዕዳ ጋር በተያያዘ ነው September 21, 2023 02:38 pm
  • ወደ አማራ ክልል ሊተላለፍ የነበረ መሣሪያና ሰነድ ተያዘ September 19, 2023 04:35 pm
  • በትግራይ መርዶ በይፋ ሊታወጅ ነው September 19, 2023 04:22 pm
  • ጃርቶች ለምን ይጮኻሉ? September 19, 2023 04:37 am
  • “ዐቢይ ግድቡን ሸጦታል” ጌታቸው ረዳ September 11, 2023 10:18 am
  • አቶ አገኘሁ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ዋጋ እንደሚከፍሉ ተሰማ September 10, 2023 06:52 pm
  • ለዋዜማ ሬዲዮ “ኢትዮጵያን ቋሚ የውሀ ባለ እዳ” ያደርጋል ያላችሁት ረቂቅ ሰነድ የታለ? September 10, 2023 01:58 am
  • ወደር የሌለው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና! ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም September 8, 2023 02:31 pm
  • የትግራይ መፍረስ በርዕሰ መስተዳደሩ አንደበት September 8, 2023 02:49 am
  • ከያቤሎ አዲስ አበባ የተላከ ኮንትሮባንድ ጉለሌ ተያዘ September 7, 2023 01:40 pm
  • “እንኳን ተለያይተንና እርስ በርስ ተባልተን በአንድነት ቆመንም ወጀቡን መሻገር አቅቶናል” September 7, 2023 01:31 am
  • ራሱን መሪ አልባ የሚያደርገው አማራ ክልል August 24, 2023 11:50 pm
  • ጀብደኛው August 24, 2023 10:06 am
  • ጎንደርና ባሕር ዳር ከተሞች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው ተመልሰዋል August 13, 2023 10:55 pm
  • ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል አስመረቀች August 13, 2023 10:26 pm
  • ሪፖርተር የፓርላማ ወንበር አስልቶ የአስቸኳይ አዋጁ በፓርላማ እንዳይደገፍ አቅጣጫ አመላከተ August 13, 2023 09:11 pm
  • ወደ ኤርትራ በኮንትሮባንድ የሚሻገሩ ቆሳቁሶች እየተያዙ ነው August 11, 2023 12:52 pm
  • የአማራ ክልል ትልልቅ ከተሞች ተኩስ ዓልባ ሆነው ውለዋል August 10, 2023 04:31 pm
  • “አንድ ሰው ለመግደል ኅንፃውን ማቃጠል” የኢ-ዲሞክራሲና ጽንፈኛ ኃይሎች ቅዠት፤ (ክፍል ሁለት) August 10, 2023 09:44 am
  • “አርበኛ” መሳይ – “የድል ዜና” ሳይበርድ 50ሺህ ዶላር በጎፈንድሚ August 10, 2023 09:08 am
  • በሕዝቡ ድጋፍ ከተሞች ከዘራፊው መንጋ ሥጋት ነጻ መሆናቸው ይፋ ሆነ August 9, 2023 11:47 am
  • ትህነግ አራተኛውን ሞት ሞተ  August 8, 2023 05:47 pm
  • “ሃሳብ ሲነጥፍ ነፍጥ አንግቤ እዋጋለሁ” የሚሉ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል – የመከላከያ ሠራዊት August 1, 2023 09:25 am
  • ደቡብ አፍሪካ የመሸጉ ወንጀለኞች ለሕግ ተላልፈው ሊሰጡ ነው July 31, 2023 09:27 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule