
የኖቤል ኮሚቴ ሊቀ መንበር ቤሪት ራይስ አንደርሰን ለጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ሽልማት ከመስጠታቸው በፊት ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚንሥትሩ ለሰላም ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ ሰላምና ዲሞክራሲን ለማስፈን በርካታ ርምጃዎችን መውሰዳቸው እንዲሁም በካቢኔያቸው አምሳ በመቶ ሴቶችን መሾማቸዉ ተመስግኗል። በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሰላም ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ሣኅለ-ወርቅ ዘውዴ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ማአዛ አሸናፊ ሴቶች መኾናቸውን ሊቀመንበሯ አመስግነዋል።
ሽልማቱም የተሰጠው፦ ሰላም እና ብልጽግና በኢትዮጵያ ለማስፈን ዓልመው መነሳታቸው ሊቀመንበሯ ገልጠዉ የኖቤል ኮሚቴዉ ዕውቅና ሰጥቶታል። በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት ሰላም እንዲሰፍን ጠቅላይ ሚንስትሩ ላበረከቱት አስተዋጽዖም በኮሚቴው ተመስግነዋል።

ኤርትራ እና ጅቡቲ ሰላም እንዲፈጥሩ ጥረት መደረጉ፤ በደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ሰላማዊ መፍትኄዎችን እንደ አማራጭ መወሰዳቸው ተወድሷል። «ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛ ናት» ያሉት የኖቤል ኮሚቴ ሊቀ መንበር ቤሪት ራይስ አንደርሰን፤ «የመጀመሪያው ሆሞ ሴፒያን የፈለሰው ከእርስዎ [ጠ/ሚ ዐቢይ]ሀገር ነው፣ በዚህም እኛ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን» ብለዋል። ኢትዮጵያ በአዉሮጳዉያን ቅኝ አለመገዛትዋ፤ የአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫ መኾኗ ከመድረኩ ሲገለጥም ሞቅ ያለ ጭብጨባ ከታዳሚያን ተሰምቷል።
(DW)
Leave a Reply