- የአድዋን በዓል አከብራለሁ ብዬ ሄጄ፤ አፄ ምኒልክ ሲሰደቡ ሰምቼ ተመለስኩ
ምሁር ባልባልም በቃ! አልጸጸትም፣
ፊደል ቢሸከሙት አያደርስም የትም።
አሮጌ ልብስ ነው አስቀያሚ ኮተት፣
ማስተዋል ካነሰው ቢከመርም ዕውቀት።
(የረቡዕ ግጥም ፫ኛ ዓመት፣ ወለላዬ)
የስዊድን ሶሻል ዴሞክራት ተቀጥላ የሆነው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ማኅበር የአድዋን ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ዝግጅት አድርጎ ነበር፤ እሁድ ማርች 5 ቀን 2017። በዝግጅቱ ላይ እንድገኝ ጥሪ ደርሶኝ ከተካፈሉት ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። ዝግጅቱ በቪድዮ ክሊፕ እንድናዳምጣቸው የተመረጡልን ሰዎች ሲኖሩት፣ በአካል የተገኙ እንግዳም ነበሩ። ክሊፑን በስክሪን እያየን ካዳመጥናቸው አንዱ “The Battle of Adwa” የተባለውን መጽሐፍ የጻፉት ፕሮፌሰር ዮናስ ሬይሞንድ ሲሆኑ፣ ስለ መጽሐፋቸው ከኢጣሊያ የታሪክ ተመራማሪ ከጆን ዌልሽ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ይገኝበታል። ሁለተኛው ደግሞ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሚስተር ታቦ ምቤኪ፣ በስድስተኛው የዓለም አቀፍ አፍሪካ ኮንግሬስ ላይ ስለ አድዋ ያሰሙት ንግግር ነበር።
የፕሮፌሰር ዮናስ ቃለምልልስም ሆነ የፕሬዝዳንት ምቤኪ ንግግር የአድዋ ድል በዓልን በሚያረካ ሁኔታ ያንጸባረቀና የታሪክ ምስክርነትም የሰጠ ነበር። ዮናስ ሬድሞንድ ምን ያህል መጽሐፉን ለመጻፍ በምርምር እንደደከሙ ለማወቅ ስንችል፤ በሰጡትም ትንታኔ እጅግ የሚያረካ ሆኖ አግኝተነዋል።ምቤኪም የአድዋ ድል አፍሪካዊ ክብር ሆኗቸው፣ ድሉን በተመለከተ ንግግር ማድረግ መቻላቸው ሌላው ልባችንን በኢትዮጵያዊነት ኩራት የሞላን አጋጣሚ ሲሆን፣ ንግግራቸውም እውነተኛ የጀግኖች አባቶቻችንን ተጋድሎ የሚያስታውስ ነበር።
ጉድ የፈላው በአካል የተገኙት ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ መናገሪያውን ከጨበጡ በኋላ ነበር። ፕሮፌሰሩ በስክሪን የቀረቡትን የሁለቱን ሰዎች ንግግር ማዳመጣቸውን ገልጸው፤ “እኔ ከነሱ በኋላ እንድናገር መቅረቤ ግራ አጋብቶኛል” በማለት ነበር ወደ ዋናው ንግግራቸው የገቡት። ስለ ሁኔታውም ሲያብራሩ፤ “እኔ ያለኝ ወይም የማውቀው የአድዋ በዓል ታሪክ ከነሱ የተለየ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ምቤኪ ከኔ ጓደኛ ከማሞ ሙጨ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያጠናውን ይዞ ነው የቀረበው” ብለዋል። “ምቤኪ ከማሞ ሙጨ የተማረውን በትክክክል ይዞ ማስተላለፍ ችሏል፤ ከኔ ቢማር ደግሞ የበለጠ እውነተኛ ታሪክ ማወቅ በቻለ ነበር” በማለት ሁለቱንም ተናጋሪዎች እና ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨን አጣጥለዋል።
እሳቸው ወደሚያውቁት የአድዋ ድል ታሪክ ሲገቡም፣ አንኳር አድርገው ያቀረቧቸው ነጥቦች አጠር ባለ መልክ የሚከተሉት ናቸው፤
- የአፄ ምኒልክን የአመራር ደካማነት፣ የተላበሱትም ዝና ከሠሩት በላይ የተጋነነ ስለመሆኑ፤
- ራስ መኮንንም ከአፄ ምኒልክ የተሻሉ እንዳልነበሩ፤
- እቴጌ ጣይቱ አርቆ አስተዋይ እንደነበሩ፣ ነገሮችን የመፍታት ብቃታቸው ጠንካራ እንደነበር፤
- በጦርነቱም ጊዜ የሳቸው (የቴጌ ጣይቱ) ብልህ አመራር ባይኖር የጦርነቱ ሁኔታ አሁን የያዘውን መልክ ይለወጥ እንደነበር፣ ይህንንም ሊረዱ የቻሉት ከኢትዮጵያ ወደ ጣሊያን በዚሁ ጉዳይ የተላለፉ መልክቶች በመኖራቸውናያም አስተማማኝ መረጃ ስለመሆኑ፤
- የአድዋ ድል በዕድል ወይም በአጋጣሚ የተገኘ ድል ስለሆነ፤ ይሄን ያህል መጋነን እንደማይገባው፤
- የተገኘው የድል ትርፍም እጅግ ጎልቶና ተጋኖ የተነገረለት እንደሆነ፤
- በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያዊ የታሪክ ጸሐፊዎች ይልቅ እውነተኛውና ትክክለኛው ታሪክ ሰፍሮ የሚገኘው በጣሊያን ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሆነ፤ የነሱን ጽሁፍ ያላካተተ ታሪክ ዕውነተኛነቱ የሚያጠራጥር እንደሆነ፣ በአበሻው የሚነገረው ታሪክ በቃል ካንዱ ወዳንዱ የተላለፉ መረጃ የጎደላቸውናቸውየሚሉ ነበሩ።
ይኽንን በስፋት ሲያስረዱ አስተማሪዬም ወዳጄም የነበረው ሮቢንሰን የተባለ የታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ በአድዋ ጉዳይ መጽሐፍ የፃፈ ቢሆንም፤ የመጽሐፉ ገጽ አብዛኛው የያዘው ስለ ምኒልክ ብቻ ሲሆን፤ ስለ እቴጌ ጣይቱ የጻፈው ምንም ነገር የለም። ፀሐፊ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴም እዛው ሆነው ያዩትንና የሰሙትን ብቻ የጻፉ ስለሆነ፤ የሁለቱም ጽሁፍ ሁሉን ጉዳይ ያላሟላ ውስን ታሪክ የያዘነው ብለዋል።
አፄ ምኒልክን ሲወቅሱ ደግሞ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣልያን ኢትዮጵያ ላይ አንድ ሁኔታ ከደረሰ የሚይዙትን የኢትዮጵያ ግዛት በመከፋፈል ሲስማሙ አፄ ምኒልክ ይሄን እያወቁ ዝም ብለው አልፈዋል። አፄ ዮሐንስ ጣሊያንን አናስገባም ሲሉ፤ ምኒልክ ግን ከጣሊያን መሳሪያ ለመቀበል አፄ ዮሐንስን ላለመርዳት ውል ተዋውለው መሳሪያ ወስደዋል። ይህ ሁኔታ ሲታይ ከሁሉ ነገር ይልቅ ለሥልጣናቸው ይጓጉ እንደ ነበር ማስረጃ ነው ብለዋል።
“አፄ ዮሐንስ ሲሞቱም ጣሊያኖች ኤርትራ እንዲገቡ ፈቅደው ለጣሊያን አስመራን የሰጡ ናቸው። ስለዚህ በትግሬ ዓይን ሲታይ ጣሊያንን ያስገቡ እሳቸው ሲሆኑ፤ የውጫሌን ውልም በተመለከተም የአንቀጽ 17ን ጉዳይን ሲወላውሉ የቆዩና ምንም ማድረግ ያልቻሉ መሪ” በማለት የምኒልክን ደካማ መሆን አጉልተው ለማሳየት ሞክረዋል።
አፄ ምኒልክ ደካማና ወላዋይ ነበሩ የሚለው አባባላቸውን በዚህ ብቻ አላቆሙም። ጣሊያን ምሽግ ለመሥራት በማሰብ ጊዜ ለመግዛት ስምምነት ለማድረግ ሲጠይቅ ስምምነት አድርገው ምሽግ እንዲሠራ ጊዜ ሰጥተዋል። በኋላም ማስለቀቅ ሲያቅታቸው ራስ መኮንን ይሄንን ያደረከው አንተ ነህና ተወጣው በማለት ብዙ ሰው እንዲገደል ምክንያት ሆነዋል። ጦርነቱም ይጀመር ብለው አዋጅ አውጥተው ከዘመቱ በኋላ ያስከተሉት አንድ መቶ ሺህ ጦር ትግራይ ውስጥ ብዙ በመቆየቱ ጦሩ እንዲመለስ ፈልገው ነበር ሲሉ ከሰዋቸዋል።
ጣልያን ወደ ጦርነቱ ቦታ ሲንቀሳቀስ በሦስት ቦታ ሠራዊቱን ከፍሎ በኋላ ለመገናኘት እቅድ ያወጣ ሲሆን፣ ያ እቅድ ሳይሳካለት በመቅረቱ ኢትዮጵያ ልታሸንፍ የቻለችው በዚህ ዕድል በመጠቀም ነው። ይህ ዕድል ባይገኝ ኖሮ የጦርነቱ መልክ ሌላ ይሆን ነበር፤ እንደውም ማኽል የነበረው ጦር ገፍቶ በመሄድ ጥቃት ሰንዝሮ ስለነበር፣ የኢትዮጵያ ጦር ማፈግፈግ ጀምሮ ነበር። በዚህ ጊዜ ምኒልክ የት እንደገቡ አይታወቅም፤ ጣይቱ ጦሩን አበረታተው እንደገና የመጣውን ጦር እንደመለሱት ማሸነፍም እንደቻሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ንግግራቸውን ያጠቃለሉት፣ “ጦርነቱን ኢትዮጵያ ያሸነፈችው በዕድል ነው። የተገኘውም ዕድል አንዱ የጣይቱ በዛን ዘመን ላይ መገኘት፤ ሁለተኛው ደግሞ የጣሊያን ሠራዊት ባወጣው እቅድ መሰረት አለመገናኘቱ ነው” በማለት ነበር።
ይህ ከብዙ በጥቂቱ ከትንተናቸው የተቀነጨበ ሲሆን፣ ንግግራቸው የአድዋን በዓል የድል ብስራት እንዲያንጸባርቅ የተጋበዘ የአበሻ ደም ያለው ሰው ንግግር ሳይሆን፤ በመሸነፉ የተበሳጨ የጣሊያን ሠራዊት አዛዥ ቁጭትና ንዴቱን የገለጸበት አይነት መስሎ የሚታይበት ነበር። ይህም በመሆኑ ንግግራቸው ተቀባይነት ከማጣቱም በላይ ቁጣን ቀስቃሽም ሆኗል። ዕድሉን ያገኙ ተናጋሪዎችም በንግግራቸው የታሪክ መዛባት እንዳለበት፣ ድሉም የተገኘው በዕድል ሳይሆን እቅድ ባለው አመራር እንደሆነ አስረድተዋል። በዚሁ ዙሪያም ለፕሮፌሰሩ ጥያቄዎች ቢቀርብላቸውም በጣሊያን መዛግብት ሰፍሮ እንደሚገኝ ከመግለጽ ውጪ አጥጋቢ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም።
በበኩሌ በዚህ በአድዋ የድል ቀን አከባበር ላይ እንድገኝ ተጠርቼ የሰማሁት ስድብና ማንቋሸሸ ያልጠበኩት በመሆኑ አስደንግጦኛል። የተዋረድኩና የቀለልኩም አይነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል። በሌላ በኩል ደግሞ መማር ያውም ፕሮፌሰርነት ደረጃ መድረስ እንደዚህ ታሪክን የሚያዛባና የሚናገሩትን እንኳን አስተካክሎ ማስቀመጥ ካላስቻለ፣ ሕዝብን ካስናቀ፤ መሪን ካዋረደ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? የሚል ትዝብትም ፈጥሮብኛል። እንደማስበው ከሆነ ፕሮፌሰሩ ወይ የመጡበትን ዓላማ አያውቁም፤ አልያም እሳቸው የሚፈልጉትን ለመናገር ብቻ የፈለጉ እንጂ ስለ አድዋም ሆነ ስለታሪክ የተጨነቁ አይመስሉም።
በሌላ አነጋገር የሳቸውን ሁኔታና አባባል ስናየው፤ አንድ ሰው እቤቱ የአቅሙን ድግስ አድርጎ የኔ የሚላቸውንም እንግዶች ጠርቶ፤ የዛሬው ቀን አባቴ ከጠላት ጋር ገጥመው ያሸነፉበት ቀን ነውና ደስታዬን አብረን እንድናሳልፍ ነው የጠራኋችሁ ብሎ ለተሰበሰበውሲናገር፤ ከተጠሩት ማኽል አንዱ ተነስቶ “ኤዲያ የአባትህን ድል እንደ ድል ቆጥረህ ይሄን ሁሉ ማድረግ ባልተገባህ ነበር፤ ድሉ እስከዚህ መጋነን የሚገባው አይደለም። እንደውም እንደ አባትህ ወላዋይነትና ደካማነት ቢሆን ኖሮ ዕድሉ ሽንፈት ነበር። እናትህ ብልህ ስለሆኑ ዕድልም ስለቀናቸው ነው ያሸነፉት። ይህንንም ካንተ አባት ጠላቶች ከጻፉት ልረዳ ችያለሁ” ብሎ እንደማለት የሚቆጠር ፈር የለቀቀ ዘለፋነው።
ያገሬ ሰው በጨዋታ ማኽል ከአርዕስቱ ውጪ ወጥቶ ሰው ሲዘላብድበት አቶ እከሌ ኧረ ይበቃሃል “ምንድነው አፍ እንዳመጣ መናገር እጅ እንደቆረሰ መጉረስ” ብሎ ያስቆም ነበር። እኛ ግን ይሄን ለማለት እንኳን ዕድል እንዳናገኝ ያለንበት ሁኔታና አጋጣሚው ሳይፈቅድልን ቀርቶ እንደተሸማቀቅን አድምጠን እንደተሸማቀቅን ወጥተናል። ፕሮፌሰሩ በደስታ ሲፍነከነኩ እኛ አንጀታችን ተቃጥሎ ውሎ እንደተቃጠልን አድረናል።
በመሰረቱ ስለ አድዋ ድል ለመናገር ምኒልክን መስደብ ምን አመጣው? ለእቴጌ እርስዎ መጽሐፍ ስለጻፉላቸው እሳቸውን ለማመስገን ምኒልክ መበሻቀጥ ይገባቸዋል ወይ? የአድዋ ድልም እስከዚህ የሚያኮራ አይደለም በዕድል የተገኘ ድል ነው ማለትስ ብልህነት ነው? እዚች ጋ ሽቅብም ቢሆን እያየሁ ምክር ቢጤ ልስጥዎት፤ ምንም አድርገው ሆነ የገቡበት ገብተው አለስልሰውም ሆነ አቃንተው ምኒልክን ያዋረዱ ፕሮፌሰር ከመባል ይዳኑ! አለበለዚያ ግን ዛሬ የተናገሩት ንግግር እንዲሁ ተሰምቶ የሚቀር አይሆንም፤ ነገ ምኒልክ በተነሱ ቁጥር ስምዎ እየተነሳ መዘባበቻ መሆንዎ አይቀርምና አስቡበት።
እቴጌ ጣይቱ የፈጣን አዕምሮ ባለቤት እንደነበሩ እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙ ጸሐፊዎችና በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ሁሉ የመሰከሩላቸው መሆኑን ማንም አይክድም። በዚህም እንኮራባቸዋለን። እቴጌ የነበሩበት ደረጃ፣ የታሪክ አጋጣሚውም ስማቸው እንዲገን ማድረጉ አልቀረም እንጂ፤ ኢትዮጵያ ብዙብልህ ሴቶችያፈራች አገር ናት። ሴቶች ደግሞ በተፈጥሮ ለመላ እና ለዘዴ ከወንድ ይልቅ ፈጣን እንደሆኑ በማያጠራጥር ሁናቴ የታወቀ ነው። እርስዎም ተሳሳቱ እንጂ ባለቤትዎን (ካለዎት) የተጠሩበትን ሁኔታ ገልጸው ምን እንደሚናገሩ ቢጠይቁ ኖሮ ከዚህ የተሻለ አቀራረብ ይዘው እንዲገኙ በመከርዎትነበር።
ለማንኛውም የተናገሩትን በዝርዝር ከላይ ስላቀረብኩት እኔ ሳልሆን የታሪክ አዋቂዎች፣ በተለይም ስለአድዋ ጠንቅቀው የሚያቁ ምሁራን ታሪኩን አስተካክለው በማቅረብ እንደሚያርምዎት አልጠራጠርም። ሌላም ጥሪ አለኝ፤ የፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/ሥላሴን መጽሐፍ ያነበብክ፣ የተማርክ፤ የፀሐፊ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴን የአድዋ ታሪክን ሰነድ የመረመርክ፤ የፕሮፌሰር የባህሩ ዘውዴን፣ የጳውሎስ ኞኞን፣ የተክለ ፃዲቅ መኩሪያ፣ የብላቴን ጌታ ህሩይ ወ/ሥላሴን መጻሕፍት አብጠርጥረህ የምታውቅ ሁሉ፤ “የፈጠራ ወሬ፣ የውሸት ታሪክ ነው የምታውቀው” ተብለልሃል፤ ታሪክ ተለውጦ ቀርቧል። ንጉሥ ምኒልክ ወላዋይ ተብለውልሃልና ውለህ ሳታድር መልስ ስጥ። ጥቁር ሆኖ ምኒልክን የሚያንቋሽሽ፤ ባርነት የመረጠ ብቻ መሆኑን ያላወቀ ምሁር ተነስቷልና ዝም አትበል። ፀሐፌና ጋዜጠኛ ከያለህበት ውጣ! ብዕርህንም ምዘዝ! እቴጌ ጣይቱን ለማጉላት ምኒልክ የሚሰደቡበት ምክንያት እንደሌለ ተናገር።
ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሪቦ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ዶክቶር ሹመት ሲሻኝ ምስክርነታችሁን ስጡ! ራስ መንገሻ ዮሐንስ እቴጌ ጣይቱ ብቻቸውን ሲታገሉ የት ነበሩ? ራስ ሚካኤል አሊ በጦርነቱ ጊዜ የት እንደገቡ አይታወቅም ወይ? ራስ ወሌ ብጡል ጦራቸውን የት ይዘው ጠፍተው ነው ጦርነቱ በዕድል የተገኘው? ራስ አባተ ቧ ያለው የሚነግርላቸው ሁሉ ውሸት ነው ወይ? ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ያ ሁሉ ግጥም ያሁሉ ዘፈን ከምኒልክ ስም ጋር እየተነሱ የሚወደሱት ተጋኖ እንጂ አልተዋጉም ወይ? እነ ባራቶሪ እነ ደቦር ሜዳ እነ አሪሞንዲ እነ ማቲዎስ … የተባሉ የጣሊያን ጦር አዛዦች በዕድል ነው ወይ የተሸነፉት? በድል ነው ወይ የተማረኩና የፈረጠጡት? እውነቱን ንገሩን! ታሪክ ተወላግዷልና አቃኑ! ይቺ ብረዛ፣ ይቺ ድለዛ፣ ይቺ የታሪክ ቡርቦራ እንዳትሰፋ ኃላፊነት አለባችሁና ዝም አትበሉ።
ፕሮፌሰር ሆይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህንን ያጣመሙትን ታሪክ አቀርቅሮ እንደማያልፍ እወቁ። እፊት ለፊታችን ታሪካችን ሲታጠፍ ዝም ብንል ከርስዎ በላይ ተወቃሾች ያደርገናል። የህሊና ወቀሳ ተሸካሚዎች አስኹኖም ያስቀረናል። ስለ አፄ ምኒልክና ስለአድዋ ድል የሚያትቱ ብዙ የታሪክ መረጃዎችና አሁንም ታሪክ አዋቂዎች እንዳሉ አይዘንጉ። “ወርቁ ቢጠፋ እንኳን ሚዛኑ አልጠፋም” የታሪክ ፍቅፈቃ ሙከራዎችዎን ያቁሙ። ለመሆኑ አፄ ምኒልክ በአድዋ በተቀናጁት ድል የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ፣ ምኒልክ በሌሉበት የአፍሪካና የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ መሪ አድርጎ መምረጡን ያውቃሉ? ወይስ አያውቁም? ይሄንንስ ያገኙት በዕድል ይሆን?
እውቁ የታሪክ ተመራማሪ ጆርጅ በርክሌይ “የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፋቸው የአድዋ ጦርነትን ሀቅ ከሙሉ መረጃው ጋር ጽፈውት ይገኛል። ያንን ማንም ሊሰርዘውና ሊደልዘው አይችልም። ጀኔራል አርቤርቶ የተባለው የጦር አዛዥ መማረኩ፣ ጀኔራል ባራቶኒ ሸሽቶ ማምለጡ በዕድል የተገኘ ድል ላለመሆኑ ምስክር ነው። ጦርነቱ የተካሄደው በተቀነባበረ የጦር እቅድ፣ በወታደራዊ መረጃ፣ በዲፕሎማሲ ሥራና በፖለቲካ ጥበብ ነበር።
በወቅቱ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን አገራዊ ክብርና ጥቅም ህልውናና ልዕልና በውድ ካልሆነ ደግሞ በግድ ማስጠበቅ ይገባቸው ስለነበር፤ ይሄም የአንድ መንግሥት ዋንኛ ግዴታና ኃላፊነት በመሆኑ በድፍረት የመጣባቸውን የጠላት ጦር በጦርነት ከመግጠም ውጪ አማራጭ እንደሌለው አውቀው አስፈላጊውን ጊዜ በመምረጥ ጦርነት መግጠማቸው በፖለቲካ ጥበብ ብልጫ ወይም ድል ነው።
በወታደራዊ መረጃ (Military Security intelligence) በኩል ደግሞ በባሻዬ አዋሎም ሀረጎት አማካኝነት በተገኘ መረጃ በመታገዝ ሠለጠነ የተባለውን የአውሮፓ ኃይል ለማሸነፍ አስችሏል።ጣልያኖች ከመሸጉበት እንዲወጡ በማድረግ ባልፈለጉት ቦታና ባልመረጡት ጊዜ ወደ ጦርነት እንዲገቡ ተደርጎ ለሽንፈት እንዲበቁ ያደረጋቸው ወታደራዊ መረጃ በመኖሩ ነው።
ወታደራዊ ሳይንስ (Military Science) በተመለከተም ለጦርነት የተንቀሳቀሰ ሠራዊት በአንድ ቦታ ሰፍሮ ጦርነቱ እስኪጀመር ብዙ ጊዜ መቆየት ወታደራዊ ሥነልቦናውን (Military Psychology) እንደሚጎዳው በማወቅ፣ ስሜቱ እንዳይቀዘቅዝና በሎጆስቲክ አኳያ እንዳይጎዳ፣የውጊያ ዝግጅቱም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ ስንቅም ጨርሶ እንዳይፈታ፤ ቶሎ ወደ ጦርነት መግባት እንደሚገባ በማሰብ ጦርነቱን ለመጀመር ጣሊያኖች ወደ መሸጉበት ከመሄድ ይልቅ እነሱ እንዲመጡ የተሳሳተ መረጃ እንዲደርሳቸው በማድረግ፤ ጠላት በወታደራዊ ሳይንስ በመበለጡ ለሽንፈት ሊጋለጥ ችሏል።
በዲፕሎማሲ በኩል ደግሞ አውሮፓ ውስጥ በተቀመጡት በራስ መኮንንና በግራዝማች ዮሴፍ በኩል ይሠራ ስለነበር፤ እጅግ አኩሪ ድል ተገኝቷል። ኢትዮጵያውያን ያልሠለጠኑ በመሆናቸው በያዟቸው ምርኮኞች ላይ ሰብዓዊነት የጎደለው ደርጊት ይፈጽማሉብለው የአውሮፓ ጋዜጦች ይጽፉ ስለነበር፤ ግራዝማች ዮሴፍ ይሄን በማስተባበል ምርኮኞቹ ሰብዓዊክብራቸው ተጠብቆላቸው እንደተያዙ በመጻፍይገልጹ ነበር። እንደውም አውሮፓውያን እንደፈሩት ሳይሆን፤ ምናቸውም ሳይነካና ሳይጎድል ወደ አገራቸው እንዲገቡ በመደረጉ፤ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥልጣኔ እንዳላት ልታስመሰክር ችላለች። ከአንድ መቶ ዓመታትም በላይ ከብዙ አገሮች ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች ይታወቃል።
ይህን የመሰለ የሚያኮራ ታሪክ ያለው ድልና በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ አንጸባራቂ የነጻነት ብርሃን የሆኑትን የአፄ ምኒልክን ታሪክ የሚያውቅ፤ የነጻነትን ጥቅምም የተረዳ ሰው የድሉን ትንሽነት፣ የምኒልክን ወላዋይነት ሲነገረው ምን ያህል እንደሚያዝን፣ እንደሚቆጣና እንደሚበሳጭ ለማንም ግልጽ ነው። እኔም የአድዋን የድል በዓል ለማክበር ሄጄ የደረሰብኝ ይሄ ነው። ከሁሉም ከሁሉም የከነከነኝን በድጋሚ ጠይቄ እንለያይ። እንደው እውነት! ኧረ ስለእውነት! እምዬ ምኒልክ ወላዋይ ነበሩ ወይ?
ወለላዬ ከስዊድን
በለው! says
ይድረስ ለፕሮፈሰር ተከስተ ነጋሽ :
የታሪክ አላዋቂነትዎን ያርሙት።
ከዳላስ ቴክሳስ ።
__> ይችን ደብዳቤ የምጽፍልዎ አንደና በኤስቢኤስ በአውስትራልያው የአማርኛ የሬድዮ ስርጭት ላይ በእርሶ እና የኢትዮጵያን ታሪክ አዋቂ ይሁኑ አይሁኑ ሳይገልጹ እርሶ እና ባለቤትዎ ስማቸውን ጠቅሰው ያው ፎቶግራፋቸው እንደሚያሳየው የውጪ ሰው ናቸው ማለትም ነጭ ስለ ኢትዮጵያ ሴቶች ጻፍን ብለው ሲናገሩ መጀመርያ ባለቤትዎን እንክዋን በሚገባ ቦታ አልሰጥዋቸውም መጽሃፉን አብረን ጻፍን ከማለት ሌላ ሴትን ማክበር ከቤት ይጀምራል። ዋናው መልክቴ ለርሶ ስለባለቤትዎ ሳይሆን ፡ መቼም ለሴቶች መብት ታጋይም በመሆኔ ጠቀስኳቸው እንጂ ጉዳዬ ጀግናዋ ንቁዋ እና ብቸኛዋን ንግስት እሌኒን ማለት ከአዳል እና ከአማራ የተወለዱትን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት የተዛነፈ ያልተሙዋላ በደንብም የማያቁትን አስመልክቶ መሴ ማርሾን ዡል ከአጤ ላሊበላ ጀምሮ ስለ አጤ ዘረያቆብ፡ አጤ በእደ ማርያም ፡አጤ እስክንድር ፡ አጤ አምደ ጽዮን ፡ አጤ ናኦድ ፡ አጤ አጤ ልብነ ድንግል ፡ አጤ ገላውዲዮስ ፡ አጤሚናንስ ፡ አጤ ሰርጸ ድንግል ፡አጤ ኢያሱ ቀዳማዊ ፡ ታሪክ ዜና እና መዋዕልን ያጠቃልላል። ከእነዚህ 16መስሃፍት ውስጥ ስለ አጤ ዘረያቆብ ፡ አጤ በእደ ማርያም ፡ አጤ ናኦድ እና ልጃቸው አጤ ልብነድንገል መለስ ብለው ቢያነቡ ወይም ቢያጠኑ ትልቅ የታሪክ ችሎታዎን ያስተካክልሎዎታል ብዬ በሚገባ አምናለሁ። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ስለ እራሱ ታሪክ ወይም ስለ አለም ታሪክ ለማወቅ የታሪክ ፒኤችዲ አያስፈልገውም። ያለውን የታሪክ መጸሃፍ ሁሉ ስራዬ ጉዳዬ ብሎ ማንበብ እና መመራመር እና ፈረንጅ የጻፈውን እራሱን ከፍ እያደረገ ጥቁርን ዝቅ እያደረገ አሜን ብሎ መቀበልም እንዳይሆን ጥናቃቄን የራስን ታሪክ በሚገባ አውቆ ቀድሞ በመጠንቀቅ ጭምር ማለት ነው።
>> ፕሮፌሰር ተከስተ እርሶ ስለ ንግስት እሌኒ ከተናገሩት ይዘገንናል የልጅን ሚስት ለአባት እነሆ።
“ንግስት እሊኔ ከአዲያ እና ከንባታ ይወለዳሉ። የአጼ ዘርያቆብ ባለቤት ነበሩ የሚል ነው። ” ከዚህ በታች ያለው በትክክሉ የንግስት እሌኒ ታሪክ ነው። ለዚህም ከላይ እንዳስቀመጥኩት የመሴ ፕርሾን ዡልን መጽሃፍ ያንብቡ። ከዚህ ውጪ በመሄድ ምንም አዲስ ታሪክ ሊፈጠር አይቻለም ሃቁ የኢትዮጵያን ታሪክ ምንያህል በሚገባ ያውቁታል ነው።
ፕሮፌሰር ተከስተ ፡ ንግስት እሌኔ አይደሉም ሐድያ እና ከምባታዋ ንግስት ጽዮን ሞገሳ ናቸው። ንግስት እሌኒ የአጼ ዘረያቆብ ባለቤት አይደሉም ታሪክ እንደሚያስራዳው በተለያየ መጸሃፍ ተጽፎ ይገኛል። ለርሶ የማዝልዎ የበድጋሚ የፐሴ ፕርሾ ዡልን መጽሃፍ ነው። የአጤ ዘረያቆብ ባለቤት ንግስት ጽዮን ሞገሳ ይባላሉ ብሄራቸውም ከንባታ እና ሕዲያ ነው። ንግስት እሌኒ የአጤ በእደ ማርያም ባለቤት ናቸው። ማለት የአጤ ዘረያቆብ ባለቤት። ንግስት እሌኒ በእርግጥ ልጆች አልወለዱም ። ስላልወለዱ አጤ በእደ ማርያም ንግስት ሮማነ ወርቅንም አግብተው ወልደዋል ። ንግስት ሮማንወርቅ የአጤ እስክንድ በእደ ማርያም እናት መሆናቸው ነው። በተጨማሪ ፓንክረስት ስለንግስት እሌኒ የጻፉትንም የቅርብ ጊዜን መጽሃፍ ያንብቡ እና እራስዎን ያርሙ!!::
__ በተረፈ ስለ አጤ ምንይልክ ትልቅ ውሸት ስላስቀመጡ ይሄም ከመጽሃፍዎ መታተም ጋር የተያያዘ አዲስ ዘመቻ ጣልያን ሊቀለብስ የማይችለውን ታሪክ መቀልበስ እራሱ ጽፎ ከተሰራጨው ጭምር በሚገባ በእየአሃጉር ተቀምጦ ስላለ በተለይ ፈረንሳይ ፡ እንግሊዝ ፡ ጀርመን ፡ ፓርቱጋል ፡ ስፔን ለኢትዮጵያ ብለው ሳይሆን ለራሳቸው ታሪክን በመበወዝ ስለማይቀበሉ የአጤ ምኒልክ የጥቁር ሕዝብ አኩሪ ታዓሪክ ለዘለዓለም ይኖራል።
የራስ መንገሻ ዮሐንስን የሃይለስላሴ ጉግሳን ፡ የመለስ ዜናዊን አሰቃቂ እፍረት ታሪክ ፡ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጬ ቡድንን አሳፋሪ እራስን የሸጡ የመጀመርያዎቹ ጥቁሮች ታሪክ ለመሸፈን ሲባል በአጤ ምኒልክ ላይ እየተደረገ ያለው ዘመቻ በሃሰት ኤርትራን አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ቦታ ስለሌለው እስከመጨረሻው ትምህርት የጎደለብዎትን እንዲያገኙ እናደርጋለን የኢትዮጵያ ልጆች ለከርስ መጸሃፍ ለማሳተሚያ የማንገዛ። ጣሊያን እራሱ የጻፈውን እና ያሳተመውን በጊዜው ማንበብ ይኖርቦዎታል አሁን በውዞ የሰጠዎትን ትተው ይሄውም በማስረጃ እነሆ እናም ከጣሊያኖች ጋር ይጠያየቁበት።
** ባለቤትዎ ነጭ ስለሆኑ አዩ ነጭ ያለዎትን ይዘው መላክ የጻፈው አድርገው የሚያዩ ከሆኑ ከነጮቹ ሳጥን ይውጡ እና የአለም ታሪክ ሜዳ ላይ ይቁሙ። በስሜት ፡ በጥላቻ ፡ በገንዘብ ማንኛንም ታሪክ የጥሩም ይሁን የመጥፎ ሆንዋል እና ተመዝግቦ ይገኛል እና ማንም ሊሰርዘው አይችልም ምክኒያቱም ቴክኒዎሎጂው የረቀቀ በመሆኑ። እንደገባኝ በጣሊያን ስለሚያምኑ ያውም ትግሬዎችን ሊውጣቸው መንጋጋ ውስጥ አግብቶ ምኒልክ አንበሳው በፍጥነት በነቃው አይምሮአቸው ደርሰው ያስተፉትን ወገኖችዎን የረፈረፋቸውን አማራው እና ኦሮሞው ሰራዊት በብዛት ግንባሩን እየሰጠ ያዳናቸውን እየሰደቡ ጣሊያንን ያለው ነው ትክክል ሲሉ በስብሰባ ላይ ስለተሰሙ ይሄው ሃቁን ያግኙት ከዚህ ቀጥሎ ባለው መጽሃፍ እና ገጽ ።
“Memoire d’Afrique Page 393” “Adua. E. Bellavia. P. 227”
“La Prima Guerra d’ Africa, R. Battagalia, PP, 793—800.”
“Douze ans en Abyssinia…PP.528-530; Adua. Belavitta P, 394”
“L’ Italia in Africa, Serie Storico, Vol I, Tome II, A Vitale ,PP. 122-123”
ከዚህ በላይ ለፕሮፌሰር ተከስተ የጻፍኩት ታሪካዊ ስህተታቸውን እንዲያርሙ ስለ አጤ ሚኒልክ በወያኔ እየተደረገ ያለውን የሃሰት ዘመቻ በሚገባ ስለደረስኩበት አጤ ምኒልክን እና ጀግንነታቸውን አስመልክቶ የጻፍኩት በኢትዮፓትሪኦትስ ድህረ ገጽ መውጣቱን ለማረጋገጥ ስገባ ስለ አደዋ ክብረበአል ለመሳተፍ የሄዱ እህት አጤ ሚኒልክ ሲሰድቡ ሰምተው መምጣታቸውን የጻፉትን ስመለከት ምናይነት አጋጣሚ ነው ብዬ ባንድ ፊት ስገረም በሌላ በኩል የፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽም በኤስቢኤስ ሬድዮ ከጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ስለ ጻፉት መጸሃፍ በሚገባ የተቀነባበረ የእፍረት ታሪክ መደለዣ በማድረግ ስለ ሴቶች እያወሩ ነገር ግን ዋና አላማው አጤ ሚኒልክ የመንገሻ ዮሐንስ የልዋጭ ልዋጭን አሳፋሪ ከጣልያን ጋር ያደረጉትን ውል መረብን መሸጥ ማደብዘዣ ዜሮ ዘዳጋር አንድ ሆኖ አገኘሁት። ባይሆን ኖሮ ዩኒፎርም ወይም አንድ የሆነ ምንም ያልተዛነፈ መልክት እንደ አንድ አክተር አጥንቶ እንደሚጫወተው ተከስተም በዚህ መልክ ስለ አጤ ምኒልክ ባልተናገሩ ነበር። ሰውዬ ባጭሩ ከጣሊያን ያገኙት ጉርሻ እንዳለ ግልጽ ነው ብሎም ከወያኔ። በመሆኑም ኤስቢኤስ ላይ የተናገሩትን በአደዋም በአል ስብሰባ ላይ የደገሙት የዘመቻው ዋና አፈ ቀላጤ ስለተደርጉ ብቻ ነው። ሃቁ በሙሉ ተከስተ የተነጋሩት አጤ ምኒልክን አስመልክቶ ውሸት ነው ። በበኩሌ ኢትዮጵያ ብዙ የታሪክ እናት ስለሆነች የአጤ ሚኒልክ ጀግንነት ሃቅ ባይሆን ኖሮ የታሪክም ድሆች ከሆኑ ብሄሮች ስላልተፈጠርኩኝ የታሪክ ባለቤቶች ከሁኑት ከኢትዮጵያ ብሄሮች እንጂ ያውም የጦር እና የስልጣኔ ባለቤቶቹ ምንም ስለ አጤ ምኒልክ ባላስተባበልኩኝ ነበር በዚህ መልክ ። እኔ የምናገረውም ፡ የምጽፈውም ማስረጃ አምጪ ብባል ማስረጃ የማቀርብበት እና ማስረጃም ገና ሳልጠየቅ በማቅረብ እታወቃለሁ ስለምጽፈው ሁሉ። ይሄም የአጤ ምኒልክ ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም።
ከኢትዮጵያወርቅ (የሐረርወርቅ) ጋሻው።
ዘብሄረ አንድ ኢትዮጵያ።
Email: yehar9@aol.com
ኢትዮጵያ ለከርሳችን የአገራችንን ታሪክ እና ክብር ልአላዊነት በማንሸጥ ወላዋይ ባልሆንን ሃሞተ መራር ልጆችዋ ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር።
Please read the following
http://ethiopatriots.com/pdf/Dagmawi-Atse-Minilik-ahgurawi-jegna.pdf
Tsehay Demeke says
እናቱን ጠርቶ አባቱን የማይደግም ይሄ ያባንዳ ልጅ ስለ እምዬ ምኒልክ ለማውራት ብቃት የለውም።
ስነ ልቦናው የተዛባ በመሆኑ እራሱን ዝቅ ያደረገ እና ነጭ አምላኪ ነው። ኑሮውን ተመልከቱ።
የኢትዮጵያዊነት አሞት ስለሌለው በዚህ ወራዳ ሰው እንዳትበሳጩ አደራ እላለሁ።
አዎ “ፕሮፌሶሩ” ን ማለቴ ነው።
ይህ ሹምባሽ ቡሉቅባሽ የሙንጣዙ ልጅ
ሌላ ምን ሞያ አለው
ልቅላቂ አተላ ጋን መሸከም እንጅ።
Mes says
እኔ የማዝነው በጋባዦቹ የሃፍረት ሥራ ነው ፣የሄ ሰውዬ የመጀመሪያው አይደለም ንጉሳችን ሲያዋርድ ፣ ብዙ አድርባዮች በእኛ ኮሚኒቲ ውስጥ አሉ ማህበራትን እነመራለን የሚሉ እነዚህ እራሳቸውን መቀየር ካልቻሉ
ከንዲህ ያሉ የባንድ አስተሳሰብ ከሚያናፍሱ “ዶክተር ፣”ፕሮፌሰር ” መላቀቅ ካልቻሉ ኢትዮጵዊው ዝም ማለቱ ሊበቃ ይገባል ፣እንዲህ አይነት ነገር በስዊድን ብቻ አደለም ፣በሌሎችም አውሮፓ አገሮች ፀረ ሚኒሊክ እንግዶች በአደዋ በአል የተጋበዙ ነበሩ ። ይህ ነገር መብቃት አለበት! !!
ለሹንባሽ ልጆች ቦታ መስጠት ይብቃ! !!