ከሁለት ሰአቱ የኢቲቪ ዜና አወጃ ተከትሎ የቀረበውን “ያልተገሩ ብዕሮች” ዶክመንተሪ በደረቁ ሌሊት ድጋሜ ስርጭቱ ተከታትየ ጨረስኩት … ላፍታ እንደተጠናቀቀ ዝም፣ ጭጭ አልኩና በሃሳቤ በህዝብ ገንዘብ ከፍተኛ ወጭ እየተደረገባቸው የሚሰራጩትን የመንግስት የህትመት ጽሁፍና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን አሰብኳቸው … በምናብ ብዙ ርቄ ሔጀ በዶለደመ፣ ባልተገራ እና በተባውና በተገራው ብዕር ውስጥ ራሴን አትኩሮት ሰጥቸ የመገናኛ ብዙሃን ውጤቶች በሃሳብ ተመላለስኩባች! ሰፊ ሽፋን ያለውን ኢቲቪና ራዲዮኑን፣ በየቀኑ እየታተሙ የሚወጡትን እነ አዲስ ዘመንን ጋዜጣንና የመሳሰሉት እሰብኳቸው … አስቤ አሰላስየ ወደ ደረስኩበት ድምዳሜ ከማቅናቴ በፊት ግን በ”ያልተገሩ ብዕሮች” ዘጋቢ ፊልም ዙሪያ የታዘብኩትን ቀዳሚ አድርጌ የተሰማኝን ላካፍልዎ ወድጃለሁ…
“ያልተገሩ ብዕሮች” …
… ስለ ጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ከባለሙያዎች የቀረበው መግለጫ ዘጋቢ ፊልሙ የተነሳበትን አላማ በሚያሳካ መልኩ የተጠናቀረ ስለሚሸት፣ ስለሚመስል አልተመቸኝም። ከሙያው ጋር ግንኙነት የሌላቸው ወገኖች የሰጡት አስተያየት የግል አመለካከታቸው ነውና ብዘለውም ባዕድ በሆኑት ሙያ የሰጡት ግምገማ አልተዋጠልኝም። “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ” ሆኖብኝ ልቀበለው አልተቻለኝም፣ አልወደድኩትም! ምስክርነት ግምገማቸውን ያለወደድኩት “የመገናኛ ብዙሃን ውጤቶች አያጠፉም!” ከሚል እሳቤ ተንደርድሬ ሳይሆን ላጠፉት ጥፋት ቅጣት መቅጫ ወፈር ያለ ህግ ተቀምጦ በህግ መጠየቅ ሲገባ ጅምላ ነቀፋን ማቅረብ ባልተገባቸውን ነበር በሚል ነው። የመንግስት ሃላፊዎች የሰጡት ገለጻና ማብራሪያም የተጻፈውን ህገ ደንብ ከማብራራት አልፎ ጥፋት እየተካሔደ በሆደ ሰፊ መታለፉንና አሁን ግን መንግስት ማምረሩን የሚያስረዳ ከመሆን ያለፈ ፍሬ ነገር የለውም።
ብቻ … ገና ከጅምሩ ዘገቢ ፊልሙ ድምጻቸው በሚስብ ጋዜጠኞችና በምስል ቅንብር ደምቆ፣ መልዕክቱ ግን በህግ በተያዙና በሚፈለጉ ተጠርጣሪ የመገናኛ ባለሙያዎች ላይ ከፍርድ በፊት ጥፋተኝነትን የሚለድፍ ሆኖ ታይቶኛል። ሳጠቃልለው የ “ያልተገሩ ብዕሮች” ዘጋቢ ፊልም ፍርድ ቤት ገና እያየው ባለውና ባልወሰነባቸው በጦማሪ ጸሃፍት፣ በአምደኞች እና በነጻው መገናኛ ብዙሃን የሚቀርበውን ክስ ለማጠናከር የተሰራ መሆኑ ያሳብቃል፣ ወንጀሉን ለማጠናከርም ለውንጀላው ምስክሮች በመንግስት ቴሌቪዥን የሰማሁትን ያህል ተሰማኝ!
ከዘመነ ጃንሆይ ፣ ዘመነ ደርግና ዘመነ ኢህአዴግ የመንግስትን አቋም እያራመዱ በጣም በወረደ ዋጋ ለነዋሪው በየቀኑ እየታተሙ ይቀርባሉ። ዳሩ ግን ትናንትም ሆነ ሃገር ምድሩን በሚሞላ ቁጥር የመታተማቸውን ያህል ቁም ነገር አላቸው የሚባሉት ገጾች የስራ ፈላጊዎችን ቀልብ የሚስቡት ማስታወቂያዎችና የጨረታ ማስታወቂያዎች ብቻ መሆናቸውን ቢያንስ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን አውቃለሁ። ብዙሃኑን ነዋሪ እውነትንና ጠቃሚ መረጃን ቢይዙ አንኳ አጓጉተውት አይገዛቸውም!
ወደ ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ መስኩም ስናመራ የምናየው እውነታ ተመሳሳይ ነው። ዘመኑ የመረጃ ነው፣ ዘመነኛ የመገናኛ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ያንጠለጠለው የታደለው ቀርቶ በስማ በለው ከሚነገሩት መስማት የሚናፍቀው የሃገሬ ሰው ቁጥር የትየለሌ ነው። ጭብጥን መረጃ ከሃላፊት ጋር ይዘው ፈርጀ ብዙ በሆነ መንገድ የሚሰራጩ መረጃዎችን በፍቅር የሚከታተለው ወገን መረጃ እንደ እለታዊ ፍጆታው የቆጠረው ይመስላል። ዛሬ ዛሬ ከስልጡን ለውጥ ፈላጊ እስከ መደዴው የኔ ቢጤ ያለ መረጃ መተንፈስ አይቻለውም።
አትኩሮት ሰጥቶ ከሚከታተለው የራዲዮ፣ ቲቪ መርጦ ጀሮውን ይሰጣል። ለህትመት ውጤት ለሆኑት ጋዜጣና መጽሄቶችን ያለው እየተጋፋ ገዝቶ፣ የሌላው እየተከራየ መረጃን ይመገባል። ያሻውን ይመርጣል፣ ያሻውን አንቅሮ የመትፋት ያህል አይቀርባቸውም!
በ “ባልተገሩ ብዕሮች ” የቀረቡት ባለሙያዎች ያልመረምሩት እውነታ ይህ ነው። በጥናታዊው ዘገባ የቀረቡት ባለሙያዎች በዋናነት የህዝቡን ነጻ መረጃ የማግኘት መብት አክብረው ሙያዊ “የተገራ ያልተገራ ብዕር” ግምገማ አድገው አላሳዩንም።
ይልቁንም ቀርበው የደሰኮሩበት የህዝብን ገንዘብ መሰረት አድርጎ ከሚንቀሳቀው ኢቲቪ ይልቅ እየፈራ እየተባም ቢሆን ከጽፈኛ ተቃዋሚዎች ልሳንነት የሚደበውን ኢሳትን ይከታተላል፣ በመንግስት ደጋፊነት የሚፈረጀውን ኢቢኤስን ደረቱን ገልብጦ ማየት ይፈልጋል። የኢትዮጵያ ራዲዮን ትቶ ጀርመን እና አሜሪካን ብሎም በሃገር ቤት የመንግስት እጅ የለባቸውም የሞላቸውን የተመረጡ የኤፍ ኤም አዳዲስ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ያምናል ፣ ማየትና መስማትን ይመርጣል። የዚህ ሁሉ የነዋሪው ግልጽ ሽሽት ምን ይሆን የሚለው ዳሰሳ መላ ምት ውጤት በዘገባ በቀረቡት ባለሙያዎች ቢነገረን ያምር ነበር። “ነበር ባይሰበር “…
ይህ የሆነው ለምን ይሆን? ብዙሃን ነዋሪ ምርጫ እንዲህ የሆነው ምን ቢሆን ነው? እውን ውስጣቸው ባልተገራ ብዕር የታጨቁ መረጃዎች ስለተሞላ ነው ማለት ይቻል ይሆን? አይመስለኝም በሚል የሚሸፈን ሳይሆን ህዝቡ የፈለገውን ማየት መስማት አይሻምና ነው ባይ ነኝ! … “ያልተገሩ ብዕሮች” ምንጭ እያስተዋለ መርጧልና ያለተገራው ብዕር በሰፊው ያለበትን ቦታ አሳምሮ ተረድቶታል…! እናም የማይፈልገውን አይቀርበውም ኩሩው ህዝብ እንዲህ ነው!
አይ “ያልተገሩ ብዕሮች!” ? ጊዜ ደጉ፣ መስማት፣ ማየት፣ መናገር መልካም!
ሰላም ለሁላችሁ!
___________________________________________________________________
ይድረስ ለ”ጥቁር እንግዳዋ” ፈርጥ ተዋናኝ … ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ብሶታችን ንገሪልን!
- ለባህሬኗ ወዳጀ ለአርቲስት እስከዳር ግርማይ …
ብርቱ ወዳጀ እስከዳር Esky አንች የብርቱም ብርቱ ሰው መሆንሽን አውቃለሁ። ከባህሬኑ የስደት ኑሮ ግብግብ፣ ለወገን ድጋፍ ማድረግና ባህልን ከማስተዋወቅ አልፈሽ ተርፈሽ “የጥቁር እንግዳን” ፊልም ለዛሬ ያበቃሽ ድንቅ እህታችን ነሽ። ፊልሙን በቡድን ከማዘጋጀት እስከመተወን ባደረግሽው ድንቅ ጥረት በባህሬን ምድር የክብር ቀይ የክብር ምንጣፍ አስነጥፈሽ ስማችን በረከሰበት የአረብ ሃገር ፊልምሽን ስታስመርቂ የኮራሁት ኩራት ከውስጤ አይጠፋም። ያንን ስሜት ሌላ ጊዜ አወራዋለሁ … ዛሬ ወደሳበኝ ግስጋሴሽ እና ልታደርሽልኝ ስለምፈልገው መልዕክት ጭብጥ ላምራ … !
ወዳጀ እስከዳር ግርማ ልጆችን ከማሳደግ የአረብ ሃገር ስደት ኑሮን ግብግብ ጋር ታግለሽ ዛሬ “ጥቁር እንግዳ” የሚለው ከ25 ዓመት በኋላ ወላጆችዋን ፈልጋ ስለተመለሰችው ስለማደጎዋ ልጅ ምስኪኗን ሳራ ሆነሽ የተወንሸው አስተማሪ ፊልም በሃገር ቤት ፊልም መናኘት መታየት በመጀመሩ የተሰማኝን እርካታ ከፍ ያለ ነው። ይህንን በአይነቱ ልዩ የሆነውን በማደጎ ችግር ላይ ያተኮረ ፊልም ስታስተዋውቂ ከበርካታ ታዋቂና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን የማግኘት እድሉን በማግኘትሽ ደስታ ተሰምቶኛል። ደስታየ ወሰን ያጣውም ከፊልም ማስተዋወቁ በተጓዳኝ በአረቡ አለም እና በቀረው አለም እኛ ስንጮህ አልሰማ ያለውን የጩኸት መልዕክት በቀጥታ ለሹሞቻችን ትነግሪ ታስረጃቸዋለሁ በሚል ነው። እርግጥ ነው በዋናነት ፊልምሽን ማስተዋወቅ ቢኖርብሽም በአረቡ ስደተኛ ህይወት መልዕክት ሳታስተላልፊ ትቀሪያለሽ አልልም። መብት ጥበቃው ጎድሎብን ኑሯችን ማክበዱን፣ ሰቆቃችን መቀጠሉን ታስተላልፊያለሽ የሚል ጽኑ እምነት ቢያድርብኝም አሁን በአደጋ ተከበናልና የወዳጅነቴና ማስታወስ ግድ ብሎኛል!
ወዳጀ ሆይ … በጥረት ትጋትሽ ፣ የብርቱም ብርቱ እየሆንሽ በማየቴ ደስ ቢለኝ በመንገድሽ የስደተኛውን መከራ ታስታውሽ ዘንድ ደጋግሜ ልማጸንሽ ወደድኩ … በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖምን እንዳገኘሻቸው በገጻቸው ካንች ጋር የተነሱትን ፎቶ ስመለከት የተሰማኝ ደስታ የማደንቀው ትጋት ብርታትሽን ነው። አሁንም ደግመሽ ካገኘሻቸው ግን በፈጣሪ ብለሽ ብየ የምማጸን፣ የማወራሽ መልዕክቴን እና ለስላስ ያደረግኳትን ለእሳቸውና ለሚመሩት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ወቀሳየን አድርሽልኝ! ስለ አረቡ አለም የዜጎች ስቃይ ሰቆቃ አንችን ቢሰሙሽ በአጽንኦት ንገሪልኝ!
አዎ ከ12 ዓመት በኋላ ከእገታ ስላዳንሻት፣ ስለታደግሻት የኮንትራት ሰራተኛ እህትን ዋቢ አድርገሽ በአረቡ አለም ስላለው የዜጎች መከራ ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ለዜጎች መብት መከበር የሚቆም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደናፈቀን ንገሪልኝ፣ ስደተኛው ይህ ናፍቆታልም ብለሽ ምሬቱን ንገሪያቸው! አደራ እህታለም! ንገሪያቸው፣ አንችን ከሰሙሽ ተማጸኛቸው!
ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም ያኔ ሳውዲ ላይ ወገን ሲበደል፣ የበደሉ ብድር መላሽ እንደሆኑ ፎክረው ሳያደርጉት ስለቀሩ “በቀል የእግዚአብሔር ነው!” በሚል ተጽናንተን ትተነው እንጅ ከፍቶናል። የዚያ በደል ቁስል ሳያሽር በኮንትራት ሰራተኞች ላይ በደል ተደጋግሞ ሲፈጸም ተመልክተን በቴዎድሮስ እና ሳውዲ ውስጥ ያስቀመጧቸው የውጭ ጉዳይ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ስለመብታችን መደፈር የፈየዱትን ማየት አልቻልንምባ አዝነን አላበቃንም። ከሁሉም የሚያስከፋው ካንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ራሳቸው ዶር ቴዊድሮስ በአካል ላዩ፣ ለጎበኟቸው በህግ ማዕቀፍ ወደሳውዲ ለመጡ የኮንትራት ሰራተኛ ግፉአን የፈየዱት ነገር ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ማድረግ እንጅ ለበደላቸው ፍትህ ርትዕ እንዲያገኙ ማድረግ አይደለም። ይህን ባለማድረጋቸው በቅርብ የምናውቅ፣ አግብቶን የምንቆረቆር ዜጎች አንገታችን መድፋታችን ንገሪልን … !
አሁን አሁን እኔ በግል በነጻነት እጽፍ እናገርበት የነበረው ሃገር ከፍቶብኛል፣ ለሁለት አስር አመታት እንደ ሃገሬ በነጻነት እንቀሳቀስ የነበረበትን ሃገር ያከፉብኝ ያገሬው ሰዎች ብቻ አይደሉም! … ሳውዲ ያለውን መከራ ስቅየቱን እየሰማሁ “የዝሆን ጀሮ ይስጠኝ” በሚል መረጃ ቅበላው ላይ በአደባባይ መታየቱን አለመሻቴ ቢያምም ከአደጋ ለመጠበቅ የተወሰደ ራስን የመውደድ አሳፋሪ አማራጭ መከተሌ እያሳዘነ እያሳፈረኝ የማጫውትሽ ነገር ቢኖር የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤታቸውና ደጋፊዎቻቸው የወገኖቻችን መከራ ስለተናገርን በአይነ ቁራኛ እያዩን መቸገራችንም ጭምር ነው! ይህንንም ክሽፈት ንገሪያቸው!
ወዳጀ ዛሬም ደፍሬ በደፈናው የምነግርሽ በዚህ ወቅት ከቀናት በፊት በሪያድ የተስተዋለው አሳዛኝ ድርጊት ነው። የዚህ አይነቱ ዘመቻ ወደ ሌሎች ክልሎች እንደሚዛመት ሰምቻለሁ። በዚህ ዘመቻ “ለህገ ወጦች” ተብሎ የሚጀመረው በእኛ ላይ የገነነው የማጥራት፣ ማጥቃት ዘመቻ ህጋዊውን ነዋሪ ጭምር በከፋ ፈተና ውስጥ እንዳይጥለው ስጋቴ ከልምድና ተሞክሮ የመነጨ ነውና ይረዱልኝ ዘንድ አሳውቂያቸው። እናም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃላፊም ሆኑ ሹሞቻችን ስለምንዋረድ፣ ስለምነገፋ ስደተኞች ተቆርቋሪነታቸውን ያሳዩን ዘንድ ድምጽሽን ከፍ አድርገሽ እኔንም አንችንም ሁላችንንም ሆነሽ በተበደለው ወገን ስም አሳውቂያታቸው!
አደራ በሰማይ አደራ በምድር!
አክባሪና አድናቂ ወዳጅሽ
ነቢዩ ሲራክ
Leave a Reply