በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግፍና የፍትህ መጥፋት ስለበዛ ህዝባዊ አመጽ በሁለት መንገድ ሊነሳ ይችላል ሲሉ ቆይተዋል አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች። አንደኛው ህዝብ ራሱ ድንገት የሚያነሳውና የሚመራው (spontaneous አመጽ) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፖለቲካ ወይም በሲቪክ በተደራጁ ሃይላት ታቅዶ የሚመራ በቅስቀሳና በጥሪ የሚነሳ ሊሆን ነው። ከወር በላይ የሆነውና በኦሮሞ ክልል ውስጥ በሰፊው የተነሳው ተቃውሞ የአዲስ አበባውን ማስተር ፕላን ተከትሎ የተፈጸመውን ማፈናቀል እንደ ማቀጣጠያ አድርጎ የተነሳ በህዝብ የተመራ ህዝባዊ አመጽ ሆኖ ብዙ ሰው በሚገባ እንደተረዳው የህዝቡ ጥያቄ የመንግስት ለውጥ ጥያቄ ነው። ለብዙ ዓመታት ታምቆ የቆየ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ እጦት፣ የመሬት ነጠቃው ጉዳይ ናቸው ዛሬ ይህን ህዝብ አስመርረው- አስመርረው ጎዳና ላይ ያወጡት።
ህዝቡ በየቦታው ሲጨፍርና መፈክር ሲያሰማ በአብዛኛው ይል የነበረው በመረጥነው እንተዳደር፣ ፍትህ ፣ነጻነት፣ የመሬት ነጠቃው ይቁም፣ መሬታችን የኛ፣ የመሳሰሉትን ነው። ይህ የሚያሳየው የህዝቡ ጥያቄ የስር ነቀል ለውጥ ጥያቄን ያዘለ መሆኑን ነው። ይህ ጥያቄ በርግጥ የሁሉ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው። ዛሬ በኦሮምያ ጠንከር ያለ ተቃውሞ እየተሰማ በሌሎች አካባቢዎች ተቃውሞው እምብዛም ያልሆነበት አንዱ ምክንያት የአዲስ አበባውን ማስተር ፕላን ተከትሎ የህዝብ ቁጣ ሲገነፍል የኦሮሞ ወጣቶች በተወሰኑ አካባቢዎች የህዝብ ግንኙነት ስራ መስራታቸውና ወጣቶች ማህበራዊ ድረ ገጾችን እየተጠቀሙ ትግሉን በማቀጣጠላቸው ነው። በሌሎች አካባቢዎች የውስጥ ለውስጥ ስራዎች እምብዛም አልተሰሩምና ተቃውሞውን ማቀጣጠል አልተቻለም እንጂ በደል በሁሉም ክልሎች እስከ ጥግ ድረስ አለ።
በዚህች አጭር ጽሁፍ ስር አስተያየት ለመስጠት ያነሳሳኝ ነገር ግን ይህ አይደለም። ለአስተያየት ያነሳሳኝ ጉዳይ ትግሉ ምን ላይ እንዳለና ፍጻሜው ምን ሊሆን እንደሚችል ትንሽ አሳብ ለማካፈል ነው። አሁን በስፋት በኦሮሚያ የተጀመረው ተቃውሞና በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በአነስተኛ ሁኔታ የተነሳው የተናጠል ተቃውሞ አንደኛ ምን መጨረሻ ሊኖረው ይችላል? ብሎ መወያየት በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ውጤታማ ለውጥ ለማምጣት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ መወያየት ወሳኝ ነገር ነው። የኦሮሞ ኢትዮጵያውያንን ተቃውሞ ስናይ እጅግ አስደናቂና የተናበበ ነው። ምን አልባትም በአገራችን የሰላማዊ አመጽ ትግል ውስጥ ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዝ ነው። ይህ ትግል አሁንም በተጠናከረ መንገድ መቀጠል ያለበት ሲሆን ነገር ግን ይህ ህዝባዊ አመጽ ወደ ፍጻሜ ደርሶ ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት በሌሎች ብሄሮች መደገፍ አለበት።
አሁን ያለውን የኦሮሞ ህዝብ ተቃውሞ ስናይ ወዴት ነው የሚሄደው፣ እስከምን ደረጃ የመድረስ አቅም ይኖረዋል፣ ምን አይነት ለውጦችን ያመጣል፣ ብለን ስናጤን ትግሉ በዚሁ ክልል ታጥሮ ከቆየና ሌሎች አካባቢዎችም ካልፈነዳ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ አይመልስም። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ ቢሰረዝ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ተመለሰ ማለት አይደለም። ከፍ ሲል እንዳልነው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የሆነ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው። ምን አልባትም መንግስት ሲጨንቀው ኦህዴድን አስገድዶ ይሰበስብና ተለውጠናል በሉ፣ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቁና አረጋጉ በማለት ለማስቀየስ ይሞክራል። ትግሉ አሁንም ከገፋና በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ በክልሉ አዲስ ምርጫ ይካሄድ ኦሮሚያ በመረጠችው ትተዳደር ሊል ይችላል። የኦሮሞ ህዝብ በጥያቄው ከገፋ፣ መንገድ እየዘጋ ካስቸገረ፣ ካመጸ፣ የመጨረሻው ርምጃ ይህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በህወሃት ኢህአዴግ ጥላ ስር ባለ እጅግ ጠንካራ ፌደራል ስርዓት ውስጥ ኦሮምያ ውስጥ እንደገና ምርጫ ቢካሄድም ጥያቄው አይፈታም።
የኦሮሞ ህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄም ሆነ ነጻ የሆነ የክልል መንግስት ምስረታ በወያኔ መራሹ ፌደራል መንግስት ስር ፈጽሞ እውን አይሆንም። “የጉልቻ መለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” እንደሚባለው አዲስ የሚመረጡትም ቢሆኑ ከላይ ያለው መንግስት እስካልተለወጠ ድረስ ለኦሮምያ መሰረታዊ ለውጥ አይመጣም። ከፍተኛው ስልጣን ያለውና የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዘውር የያዘው ፌደራል መንግስት ስለሆነ ክልሉ አዲስ ምርጫ ቢያካሂድም ከዚህ አምባገነን ስርዓት አይላቀቅም። በመሆኑም ሰፋ አድርገን ካየነው የአሁኑ የኦሮሚያ ህዝብ ጥያቄ በዋናነት የፌደራል መንግስት ለውጥ ጥያቄ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፌደራል አካባቢ ያለው ዘረኛ መንግስት የሚያሽከረክራቸው የኦህዴድ አመራር አባላትንም ይመለከታል። ታዲያ የኦሮሚያ ጥያቄ ከላይ ከቁንጮው አካባቢ መስተካከል አለበት ብሎ ከተነሳ ይህ ጥያቄ ደግሞ የመላው የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው የሚሆነው። ፌደራል መንግስቱን በሃቀኛ ፌደራል ስርዓት አዋቅሮ የክልል መንግስታትትን በሃቀኛ ስርዓት ለመምራት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል መደባለቅ አለበት።
በመሆኑም ኦሮምያ ብቻውን ታግሎ የራሱንም ሆነ የኢትዮጵያን ጥያቄ እንዲፈታ ሃላፊነት ሊጫንበት አይገባም። ኦሮሞ እየታገለ ያለው ለሃቀኛ ፌደራሊዝም እንደመሆኑ ትግሉን ልንደግፈውና የትግሉን መሪ ቃል ከፍ አድርገን የጋራ አድርገን ልንነሳ ይገባል።
ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት የኦሮምያን አካባቢ ህዝብ እያነቃቁ ያሉ ጀግና የኢትዮጵያ ልጆች ትግሉ ወደ ፍጻሜ ይሄድ ዘንድና የመንግስት ለውጥ አምጥቶ የተሻለ ስርዓት ለመገንባት እንዲቻል ትግሉ ሁሉን አቀፍ እንደሆነ ማሳየት አለባቸው። በአንጻሩ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የኦሮሞ ወገኖቻችን ያነሱት ጥያቄ የኛም ነው። እኔም ኦሮሞ ነኝ በማለት ህብረትን በማሳየት ነው ትግሉ ጫፍ ደርሶ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣው። ትግሉን በተለያየ ማህበራዊ ድረ ገጽ የሚያቀጣጥሉ የኦሮሞ ወጣቶችም የለውጥ ጥያቄን ከፍ አድርገው ማንሳት ሲጀምሩ ይህ መሪ ቃል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ወደ ጎን መተሳሰር (link) ይፈጥራል። ትግሉ የአካባቢን የመልካም አስተዳደር ችግር መሰረት አድርጎ ከፍ ያለው ጥያቄ ደግሞ የለውጥ ጥያቄ መሆኑን ማሳየት ተገቢ ነው። ይህ ሲሆን በስፋት የኦሮሞ ወገኖች የጀመሩትን ትግል ሁሉም ይቀላቀልና የጋራውን የችግር ቤት አፍርሰው እንደገና ጥሩ አድርገው ይሰሩታል። በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የፖለቲካ ድባብ የተነሳ የተናጠል ትግል ውጤት አያመጣም ብቻ ሳይሆን ሆኖለት አሸንፎ የፌደራል መንግስትን ስልጣን ቢይዝም ለኢትዮጵያ ጥሩ አይደለም። ከገባንበት የቡድነኝነት ክብ አንወጣም። አሁን ያለውን በከፍተኛ ሁኔታ በኦሮምያ አካባቢ ታጥሮ ያለውን ተቃውሞ ስናይ ሄዶ ሄዶ ምን ይሆናል? ስንል። ሄዶ ሄዶ ህብረትን ነው የሚጠራው። ለዚህ ነው ሌሎቻችንም የኦሮሞው ጥያቄ የኔም ነው ብለን የጋራ ጥያቄ አድርገን ልንነሳ ይገባል የሚያስብለን።
አሁን ያለው የኦሮሞ ህዝብ ትግል ሲጠናከርና ሌላው ህዝብም ሲቀላቀለው ጥያቄው አድጎ የለውጥ ጥያቄ ሲሆን ትግሉ ወዴት ነው የሚሄደው ልንል እንችላለን። በአዳንድ አገሮች እንዲህ አይነት ቀውስ ሲነሳ በገዢው ፓርቲ አካባቢ መፍረክረክ ይነሳና ለለውጥ ይዘጋጃሉ። አንዳንድ አገር ደግሞ መፈንቅለ መንግስት ይነሳና የሽግግር መንግስት ሊነሳ ይችላል። አንዳንድ አገር ደግሞ መሪዎች እየፈረጠጡ ጥለው ይጠፉና ማእከላዊ መንግስት ሲዳከም ወደ ውይይት ሊመጡና መላ ሊፈጥሩ ይችላሉ። የሃገራችንን ጉዳይ ስናይ ለምሳሌ መፈንቅለ መንግስት የመነሳቱ እድል በጣም ጠባብ ነው። በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ከአንድ ብሄር በወጡ መኮንኖች የሚመራ ሰራዊት ወደዚህ ያመራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ማን ላይስ ነው መፈንቅለ መንግስት የሚያደርገው? ሃይለማርያም ላይ እንዳይባል ሰውየው የነዚሁ መኮንንኖች አሻንጉሊት በመሆናቸው የመፈንቅለ መንግስት እድሉን ተስፋ ያሳጣዋል። በሌላ በኩል በፓርቲው ውስጥ የመሰንጠቅና ለለውጥ ክፍት የመሆን አዝማሚያ ይኖር ይሆን ወይ? ብለን ስናስብ ከመፈንቅለ መንግስቱ የተሻለ እድል ሊኖረው ቢችልም ይህ ሁኔታ የሚወሰነው በቤተሰቦቻቸው የግፊት መጠንና በራሱ ህወሃት አካባቢ ባሉ ሰዎች የመለወጥ ልብ ላይ የተመረኮዘ ነው። ቢያንስ ስለ ህዝቡ ብለው ባይሆንም ስለራሳቸው ፍጻሜ ብለው ተቃውሞ በረታና እንለወጥ የሚል ነገር ያነሱ እንደሆን ብለን ስናስብ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይህ ተስፋ የለም። ህወሃት ይራራል፣ ይለወጣል ብለው የሚያስቡባቸው ጊዚያት አልፈዋል። ተቃውሞው ሲበረታና መንግስት መውጫ መግቢያ ሲያጣ፣ መንገዶች ሲዘጉ ምን አልባትም አንዳንዶች የኦሮሞውን ጥያቄ ወደ ብሄርተኛና የመገንጠል ጥያቄ አውርደው፣ የራሳቸውን ካድሬዎች እያነሳሱ ኦሮሞ የመገንጠል ጥያቄ አስነሳ በማለት አገር አፍርሰው ትግራይን በመገንጠል እንገላገል የሚል ነገርም ያነሱ ይሆናል። ወያኔ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ ላይ ሙጭጭ ያለው ለክፉ ቀን ትሆነኛለች እስከዚያው ልዝረፍ ብሎ የሚኖር ነው የሚመስለውና እንዲህም ልንጠረጥር እንችላለን።
እንግዲህ ኦሮምያ አካባቢ ያለው ተቃውሞ ሲከር ውሎ ቢያድር ተጽእኖው እስከ ምን ነው፣ የሚለውን ስናይ ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ ቤተመንግስት ሄዶ ወታደሩን ተጋፍቶ መንግስት ይለውጣል ወይ? ብለን ስናስብ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከባድ ነው ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ይሁን እንጂ በአራቱም ማእዘናት ያሉ ህዝቦች ሲያምጹ ግን መንግስትን ቤተ መንግስት ብቻ ያስቀራሉና ተፈላጊ ለውጥ መምጣቱ አይቀርም።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲነሱ በተቃውሞው ጊዜ ብዙ የሰራዊቱን አባላት በየመንገዱ ይማርካሉ፣ የሚማረከው የሰራዊት አባል ደግሞ ለስርዓቱ መውደቅ በጣም ጉልህ አስተዋጾ አለው። ስለዚህ የኦሮሞ ወገኖቻችን የራሳቸውንም ሆነ የሌላውን አካባቢያዊ ጥያቄዎችና አገራዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ዛሬ የእንተባበር ጥያቄ እያሰሙ ነውና ሁሉም ብሄሮች ድጋፍ ሊያሳዩ ይገባል። የኦሮሞ አክቲቪስቶች ለውጥ ለኢትዮጵያ አገራችን ሲሉ፣ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ እኔም ኦሮሞ ነኝ፣ የኦሮሞ ትግል የኔ ነው ስንል የመንፈስ አንድነትን እናዳብራለን። ይህ አገራዊ አንድነት የባህል ማንነታችንን የሚጻረር አይደለም። ጥያቄው ከላይ ቁንጮው አካባቢ የተበላሸውን አስተዳደር ለውጠን ለሁሉም ብሄሮች የምትሆን የተባበረች ኢትዮጵያ እንገንባ በመሆኑ ባህላዊ ማንነታችንን አክብረንና ጠብቀን ለተሻለ ፌደራል ስርዓት እንታገላለን።
በሌላ በኩል መዘንጋት የሌለብን ነገር ይህ መንግስት የሚወድቀው ከትግሉ እጅግ ሰፊውን ሽፋን በሚይዝ ሰላማዊ አመጽ ሲሆን ነገር ግን የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ወገኖች ደግሞ ሽፋን ሊሰጡት ይገባል። ህዝቡ አምጾ ሲያበቃ ወታደሩ ምን ይሆናል? ብዙ ጊዜ በህዝባዊ አመጽ ጊዜ በጣም ተደራጅቶና ሃይለኛ ሆኖ የሚወጣው ወታደሩ ነውና በኢትዮጵያ ሁኔታ ህዝባዊ አመጹ እጅግ ሲከርር ወታደሩ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ያሰፈልጋል። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያውያን ምሁራን መወያየት አለባቸው። ዝም ብሎ ዛሬ እዚህ ከተማ ተቃውሞ ነበር ብቻ ሳይሆን ትግሉን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ ያሉትን ተለዋዋጮች (Variables) በማጤን ትግሉን መምራት ያስፈልጋል። በህዝብ የተነሳው ይህ አመጽ አሁን አመራር የሚፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷልና።
በሌላ በኩል ትግሉ እየገፋ ሳለ አንዱ መደረግ ያለበት ነገርና አንድ የትግል ስልት ተደርጎ መያዝ ያለበት የታጠቀውን ማለትም ፖሊስንና ወታደሩን የማግባባት ስራ ዜጎች ሁሉ እንዲካፈሉት ማድረግ ነው። በዚህ በኩል ሚዲያዎችና ትግሉን በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚያስተባብሩ ወጣቶች ትልቅ ስራ ይጠበቅባቸዋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወይ ልጁ፣ ወይ ወንድሙ፣ ወይ ጓደኛው፣ ወይ ዘመዱ ወታደር ወይ ፖሊስ ሊሆን ይችላል። ወታደር ወይም ፖሊስ ባል ያላቸው ሴቶች አሉ። እነዚህ ወገኖች በግለሰብ ደረጃ ይህን የታጠቀ ሃይል በወገኑ ላይ እንዳይተኩስ ብቻ ሳይሆን ከለውጥ ጎን እንዲቆምላቸው ሊያግባቡና ሊማጸኑ ይገባል። እንዲህ ሲሆን ወታደሩን መማረክ ይቻላል።
በአረብ ስፕሪንግ ጊዜ ግብጽ ውስጥ የታየው ነገር ይገርም ነበር። የግብጽ ወታደር ጸጥታ አስከብር ተብሎ ሲመደብ ለህዝብ ወገንተኛነቱን አሳይቷል። ገለልተኛ ተቋም ስለነበር ያልታጠቀው ህዝብ መንግስትን መለወጥ ችሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ግን የተለየ ነው። የወታደሩ አመራሮች ድሮ ጫካ የነበሩ የህወሃት አመራሮች ናቸው። ሃያ አምስት አመት ሙሉ ሰው አላፈሩምና ሙሉ በሙሉ ከፍተኛውን ስልጣን የአንድ ብሄር ሰዎች ይዘውታል። ስለዚህ ህዝባዊ አመጽ ጫፍ ሲደርስ ወታደሩ ወደ ህዝብ ወግኖ ወይም ገለልተኛ ሆኖ ይመለከታል ማለት አይቻልም። ለዚህ ነው ከስር ከስሩ ኢትዮጵያውያን የወታደሩን አባል እየማረኩ ይህ ተቋም ለለውጥ እንቅፋት እንዳይሆን ማድረግ የሚቻለው።
ይህ ህዝብ የቀሰቀሰው አመጽ መንግስትን ለመጣል ከሚኖረው ጉልህ ሚና ባሻገር የሽግግር መንግስት ለመመስረት የወታደሩ ሚና ወሳኝ ነው። በሌላ በኩል አንድ በጣም ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው ነገር የተጠቁ ተቃዋሚዎች ጉዳይ ነው። እነዚህ ተቃዋሚዎች (ሃቀኛ ተቃዋሚዎችን ማለቴ ነው) ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠናከረ መንገድና በህብረት ሊቆሙ ይገባል። እንደ ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት አርበኞች፣ ትህዴን ወዘተ የመሳሰሉት ወደ ውህደት ማምራት አለባቸው።
ስር ነቀል ለውጥ ይመጣ ዘንድ የግድ የታጠቁ ሃይሎችም የህዝቡን ሰላማዊ አመጽ ደግፈው ለውጡን ካላመጡ የትግሉ ፍጻሜ ተፈላጊውን ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ነገር ግን መንግስትን ለመለወጥና አዲስ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ትግል ውስጥ ትልቁ ትግል ህዝባዊ አመጹ ነው። ያም ሆኖ ግን ህዝቡ መንግስትን ገዝግዞ ሲያዳክም እነዚህ የታጠቁ ሃይሎችም በታክቲክ አግዘው ለውጡን ካላመጡ በህዝባዊ አመጽ መንግስት ቢፈርስ የሆነ የሃይል ክፍተት አገሪቱን እንዳይመታትና በዚህ መሃል ደግሞ አንዳንድ አክራሪ የብሄር ኢንተርፕሩነርስ ገብተው አገሪቱን እንዳይበጠብጡና አንድነታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እነዚህ የታጠቁ ሃይላት የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት የማረጋጋት ስራ ሊሰሩ ይችላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎች አንድ ጉዳይ ላይ መስማማት አለባቸው። ይህ ማለት አንድ ርእዮት ይኑራቸው ማለት አይደለም። የተለያየ ርእዮት ይዘው ይሆናል። ይሄን ተራራ ለጊዜው አልፈው በኢትዮጵያ ውስጥ የተውጣጣ የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማማት የግድ አለባቸው። ልዮነቶች ሁሉ በሽግ ግሩ ወቅት ሊነሱና ወደ ህዝብ ቀርበው ህዝብ የመረጠው ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ሰዓት የሚኖረው ትግል የአይዲዮሎጂ ሳይሆን አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ መስመር እንድትገባና የፖለቲካው ምህዳር ሰፍቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት በመድረክ የሚከራከሩበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። በዚህ ጥላ ስር ሁሉም የፖለቲካ ተቋማት ሊሰባሰቡ ይችላሉ። ይህ ሲሆን ትግሉ አመራር ያገኛል። ለውጡ ወደ ቤተ መንግስት ሲደርስና መንግስት ተፈረካክሶ ሲወድቅ እነዚህ የተደራጁ ሃይላት በቀጥታ የሃይል ክፍተት ሞልተው የሽግግር መንግስቱን በማቋቋም ሊቀጥሉ ይችላሉ።
እዚህ ላይ አንድ ኢትዮጵያውያንን ያሰለቸ ጉዳይ ማንሳት ተገቢ ነው። ህዝቡ ተባበሩ፣ ተባበሩ፣ ተባበሩ … እያለ ሲጮህ ይታያል። ይሁን እንጂ ስለምን መተባበር አቃተን እንላለን። አንዳንዱ አገር ወዳድ የሆነና በተቃዋሚዎች አለመተባበር ውስጡ የበገነ ሰው በቃ እኛ ኢትዮጵያውያን የመተባበር ችግር አለብን ይላል። አይደለም። እንደ ህዝብ እኛ ኢትዮጵያውያን የመተባበር ችግር የለብንም። እንዴውም ከሌላው ህዝብ በተሻለ አብሮ የመብላት፣ ችግርን የመካፈል ባህል አለን። ይሁን እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይተባበሩ ካደረጋቸው ጉዳይ መካከል አንዱ የመንግስት ሰርጎ ገብነት ባህርይ ነው። የሚገርማችሁ ነገር ተቃዋሚ ፓርቲ የተባሉ ድርጅቶች ሁሉ ተቃዋሚ አይደሉም። አንዳንዶቹ በራሱ በህወሃት የተቋቋሙ ናቸው። የውስጥ አርበኞች ሆነው የሚያገለግሉ የተቃዋሚውን ጎራ በተከላካይነትና በአጥቂነት የሚያዳክሙ መሳሪያዎች ናቸው። በሌላ በኩል በእውነተኛ ተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል ደግሞ እንዲሁ እስከ አመራር ሾልከው የሚገቡ አባላትን ስለሚመለምል በሃገራችን ተቃዋሚዎች እንዳያብሩ ትልቅ መሰናክል ፈጥሯል። ሌሎች የምንጠረጥራቸው ምክንያቶች ሁሉ ያላቸው አስተዋጾ በጣም አናሳ ነው። ትልቁ ያለመተባበር ምክንያት የወያኔ ሰርጎ ገብነት ባህርይ ነው።
ታዲያ ችግሩ ይህ ከሆነ ዘንዳ ሃቀኛ ተቃዋሚዎች አሳቾችን ከስራቸው የመለየት ስራ መስራት አለባቸው። ከፍ ሲል እንዳልኩት በሽግግር መንግስት ምስረታው ዙሪያ ለመስማማት አሳብ አቅርቦ በዚያ ላይ አልሳተፍ ያሉትን የመንግስት ደጋፊ ናችሁ ብሎ አፋጦና ጨክኖ የሚይዝ የሚያጋልጥ አመራር እስካላገኘን ድረስ መቼም ህብረት አይኖርም። የግድ ሚና የመለየት ስራ መሰራት አለበት። ሚዲያዎችና የቆረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደጋግፈው እነዚህን ህብረት የማይፈልጉና ህብረትን የሚያደናቅፉ ሃይሎችን የማጋለጥ ስራ መሰራት አለበት። በዚህ ደረጃ ጨካኝ ሆነን ነው ህብረትን የምንመሰርተው። በአንድ ቀን ወርክሾፕና ሰሚናር ወይም በራሪ የጥሪ ወረቀት ህብረትን መመስረት አይቻለም። ስንዴውን ከእንክርዳዱ ካለየንና ጨክነን የማውገዝ ስራ ካልሰራን ወያኔ በዚህ ታክቲኩ ሊቆይ ይፈልጋል። የወያኔ ትልቁ ጉልበት ወታደሩ ሳይሆን የተቃዋሚው ወገን መፈረካከስ ነውና ይህንን ጎራ መምታት አንድ የትግል ስትራተጂ ተደርጎ በሃቀኛ ታጋዮች ዘንድ መታወቅ አለበት።
ሌላው በታጠቁ ሃሎች ዘንድ ያለው ጉዳይ ደግሞ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ነው። በብሄር ላይ ቆሞ የታጠቀ ሃይል ኢትዮጵያን ነጻ ያወጣል እያሉ መጃጃል መቆም አለበት። ውህደት ያስፈልጋል። ካልሆነ ደግሞ ራስን ችሎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል እንጂ በማይሆን አጠማመድ መግባት አስፈላጊ አይደለም። ጥበብም አይደለም። ይህን በግልጽ መወያየት ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት በትህዴንና በግንቦት ሰባት አርበኞች በኩል የተጀመረው ጥምረትና ውህደት ቶሎ መግፋት አለበት። አንዳንዶች በትህዴን ላይ ያላቸው ጥያቄ የሚመለሰው ትህዴን ለውህደት በሚያሳየው ቁርጠኝነት ነው። በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ እንደ ትህዴን ግራ የሚያጋባ ሽምቅ ተዋጊ ያለ አይመስለኝም። ይህን የምልበት ምክንያት። አንደኛ ይህ ድርጅት ከተቋቋመ ረጅም ዓመታትን አስቆጥሯል። የሚገርመው ቁጥሩ ደግሞ ከሃያ ሽህ በላይ (> 20,000) ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ አለው ይባላል። የሚገርመው ግን ይህን ያህል ግዙፍ ሰራዊት ይዞ ይሄ ነው የሚባል ውጊያ እንኳን አርጎ አያውቅም። አንድ ወረዳ ቀርቶ ቀበሌ አልያዘም።ትግሉን ኣገር ቤት ኣላስገባም። ህወሃት ወደ ጫካ ሲገባ ሰባት ሆነው ሲሆን በስድስተኛ ወራቸው ትግራይ መሬት ውስጥ ጦርነት ጀምረዋል። ትህዴን በትግራይ ህዝብ ከተደገፈ መደበቂያ አለው ማለት ነው። ሰርጎ እየገባ ወታደራዊ ጥቃት በማድረግ መንግስትን አስጨንቆ ብዙ ሊሰራ ብዙ ሊማርክ የሚችል ሃይል ይዞ ነገር ግን ኪነትና ስፓርት እየሰራ ቁጭ ካለ ያስጠረጥራል። አገር ወዳዶች ይሄ ቡድን ድንገት አገር ሲበጠበጥ (ልክ አሁን የኦሮሞ ህዝብ ያነሳውን ትግል አይነት ሲፈጠርና መንግስት ሲፈረካከስ) እንደተጠባባቂ ሆኖ በጦርነት ስም አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ሌላ ህወሃት ሊሆን ይችላል ብለው ሰዎች ቢሰጉ አይፈረድም። ወይም ይህ ቡድን በዚያ በኤርትራ አካባቢ ያሉ የታጠቁ ታጋዮችን ትግል እያሳነፈ የህወሃትን እድሜ ያራዝማል ተብሎ ሊጠረጠር ቢችል ትህዴን እባክህ አትቆጣ። ለሽምቅ ውጊያ መቶዎች በቂ ናቸው። ሃያ ሺህ ስንት ክፍለ ጦር ስንት ብርጌድ ነው? በደርግ ጊዜ ህወሃት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ህዝቡ ማን ነህ ምንድነህ አላለም። እያገዘ ነው አዲስ አበባ ያስገባቸው። አሁን ግን በተፈጠረው ዘረኛ ስርዓት ምክንያት ህዝቡ የሚመጡ ታጋዮችን ማን ነህ ምንድን ነህ ማለት ጀምሯል። ስለዚህ ወንድሜ ትህዴን ሆይ በጋራ አርማ ለጋራዋ አገራችን ተዋሃድ። እንዴውም ለመዋሃድ ሌሎቹን ቀስቅስ።
ግንቦት ሰባት አርበኞችና ሌሎች ብሄራዊ አጀንዳ ያላቸው ይህን ድርጅት መምከርና ህብረት መሻሉን አሳይቶ ወደ ጋራ ግንባር መምጣት አስፈላጊ ነው። ዖነግ የኦሮሞን ህዝብ ልብ ማሳየት አለበት። ኢትዮጵያ ብዙው አካሏ ኦሮሞ ነው። ኦሮሞ ነች ኢትዮጵያ። የፈለገውን ያህል ጥሩና መጥፎ ታሪክ እናሳልፍ የኦሮሞ ህዝብ ግን አገሩን የሚወድና የአገሩ ተቆርቋሪ በመሆኑ ቶሎ ብሎ ህብረ ብሄራዊ ትግል ውስጥ መግባት አለበት። ወያኔ በብሄር ተኮር ትግሎች አይደነግጥም። እንዴውም ያበረታታል። የሚገርመው በአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ ውስጥ ባለው ተቃውሞ ውስጥ አንዳንድ የኦነግን ባንዲራ የሚይዙ ሰዎች የራሱ የወያኔ ደጋፊና ካድሬዎች ናቸው። ይሄ የሚያሳየው መንግስት ኦነግን ስለወደደ ሳይሆን ብሄርተኛ ትግሉ ከብሄራዊ ትግሉ ይሻለኛል ብሎ ስለሚያምን፣ የኦርሞን ህዝብ ከሌላው ነጥሎ ለማሳየትና ድጋፍ ከሌላው ወገኑ እንዳያገኝ ለማድረግ ነበር። እንዲህ ዓይነት መሰሪዎችን ተቃዋሚው ሊነቃባቸው ይገባል።
በሌላ በኩል የትጥቅ ትግሉ አንድ ቦታ ብቻ በጣም ጥገኛ መሆን የለበትም። ለምን ኤርትራ ውስጥ ስልጠና ይካሄዳል፣ ለምን ከኤርታራ ድጋፍ ታገናላችሁ ማለት ተገቢ አይደለም። የማግኘት የመሰልጠን መብት አላቸው። ከዚህ አልፎ ግን እጅግ ሲበዛ በዚያ አካባቢ ብቻ ጥገኛ መሆኑ ከትግሉ ባህርይና ከሚያስከፍለው መስዋእትነት አንጻር ተገቢ አይደለም። ሁል ጊዜ አዳቫንቴጅ እንዳለ ሁሉ ዲስ አድቫንቴጆች ስላሉ ሌሎች አማራጮችንም መጠቀምና በምስጢር መያዝ ተገቢ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ትግሉ የግድ አገር ቤት መግባት አለበት። እንዲህ ህዝቡ ሲያምጽ የታጠቁ አካላት ብዙ ክፍተት ስለሚያገኙ በሽምቅ ውጊያዎች መንግስትን ወጥረው ሊይዙና ለውጡን ሊያፋጥኑ ይችላሉ። በመሰረቱ ነጻ አውጪ ታጋይ በህይወት የሚቆየውና ትግሉ እየበረታ ሰራዊቱ እየጠነከረ የሚሄደው ትግል ሲያደርግ ነው። ስልጠና ብቻ አይደለም። ስንት ሰራዊት ሲሰለጥን ነው ትግል የሚጀመረው? አይደለም። የነጻነት የትጥቅ ትግል የሚጀመረው በጥቂት ተዋጊዎች ነው። እነዚህ አካላት እንደ መንግስት የማይነጥፍ ባጀት የላቸውም። ህይወታቸው የሚመሰረተው ህዝቡ በሚያቀብላቸው ስንቅ፣ እየማረኩ በሚያገኙት መሳሪያ ነው። የሚማርኳቸው ወታደሮች እየሰለጠኑ ቁጥሩን እያበዙ ይሄዳሉ። ዋናው የገቢ ምንጩና ወታደራዊ አቅሙ የሚደገፈው ራሱን ትግሉን ነው። የሽምቅ ተዋጊና የነጻ ኣውጪ ዋና የገቢ ምንጭ ምርኮና የህዝ ድጋፍ ነው። ለረጅም ጊዜ ስልጠና እያደረገ ከቆየ ብዙ ሺህ እስኪሆን ከጠበቀ ወጪው ከባድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አይቀጥልም። የዚህ ሰራዊት ህይወት ሁል ጊዜም በትግል ውስጥ ነው። ትግል ካቆመ ኣይኖርም። ስለዚህ የታጠቁ ሃይሎች ሜጀር የሆኑ ኦፕሬሽኖች ማካሄድ ባይችሉ የሽምቅ ውጊያዎችን በማድረግ የመማረክና በሁለንተናዊ መልኩ ራስን የማብቃት ስራ መስራት ያለባቸው ይመስለኛል። የበለጠውን እነሱ ያውቃሉ።
በአሁኑ ሰአት ታጋይ ኤርትራ ገባ፣ ወጣቶች ኤርታራ ገቡ መባሉ ግማሽ ትርጉም ቢኖረውም ትልቁ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ በረሃ የገባ ሰው ነው ትግል ገባ የሚባለው። የቴፒ ወጣቶች በጣም ጥቂት ሆነው ከግንቦት ሰባትና አርበኛች ከትህዴን የበለጠ ሲሰሩ ታይተዋል። ብዙ ስልጠና የወሰዱ፣ ትንሽ አቅም ያላቸው የታጠቁ ሃይላት ደግሞ ከዚህ የተሻለ ሊያደርጉ ህዝቡ ይጠብቃል። ስለዚህ ህዝባዊ አመጽ የመጨረሻ ውጤት እንዲያመጣ የግድ የህብረት ትግል ውስጥ መግባት አለብን። ህብረቱ በህዝቦች ደረጃና በፓርቲዎች ደረጃ መሆን አለበት። በህዝቦች መካከል የሚኖረው ትብብር በመረዳዳት (understanding each other) ላይ ያተኮረ፣ በፍቅርና በአንድነት ላይ ያተኮረ ቢሆን ጥሩ ሲሆን ፓርቲዎች ደግሞ አገሪቱን በሽግግር ጊዜ ውስጥ አሳልፎ ወደ ዴሞክራሲ ለማቅናት በሚያስችል ጠቅላላ አሳብ ላይ መስማማት ጥሩ ነው።
ጀግናው የኦሮሞ ህዝብም አሁን የጀመረውን ትግል ከፍጻሜ አድርሶ፣ የመንግስት ለውጥ መጥቶ አገራችን የተሻለ ስርዓት ውስጥ የምትገባው ህብረት በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ህብረት በታጠቁ አካላት ዘንድ፣ ህብረት በሰፊው ህዝብ ዘንድ ሲያይል ነው። ህብረት ሲባል ሁላችን አንድ እንሁን አይደለም። አንዳንድ ከህብረት የተጣሉ ሁል ጊዜም ይኖራሉ። የኛ መከፋፈል ግን በዛ። ስለዚህ ይህን የበዛ ክፍፍል እናጥብና በተወሰነ ደረጃ ሰፋ ያለውን ማህበረሰብ ልብ የሚያሳርፍ ህብረት እንፍጠር ነው።ህብረት ህብረት ህብረት አስሬ…… የሚያሰኘን አገራችን ራሷ የህብረት አገር በመሆኗ ነው። ተፈጥሮአችን ይህ በመሆኑ ትግላችንም ሆነ ድላችን በህብረት ላይ መመስረት አለበት።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
geletawZeleke@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply