በመጀመርያ ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ደጋፊና ተደጋፊ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን በሙሉ ጠሯቸው። ሰበሰቧቸው። እንዲህም አሏቸው። “ወደ ደደቢት አብራችሁን ትሄዳላችሁ፤ እዛ እንደደረሳችሁም አመጣጣችንንና አካሄዳችንን በደንብ አድርጋችሁ ታጤናላችሁ። ከዚያ ስትመለሱ ሁሉንም ነገር ለህዝቡ ትናገራላችሁ።…”
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የሃገር መሪ ሆነው የሚሰሩት እኝህ ሰው መልዕክታቸውን በዚህ አላበቁም። አይናቸውን ፈጠጥ፤ ጉሮሯቸውንም ጠረግ-ጠረግ አደረጉና ንግግራቸውን ቀጠሉ “ስለረጅሙና መራራው ትግላችን፤ ከጅምራችን እስከ አያያዛችን የታዘባችሁትን ሁሉ ንገሩን። ጥሩውንም ይሁን መጥፎውን ነገር ሳትደብቁ ተናገሩ።…”
ድምጻዊው በዝማሬ፣ ጸሃፊው በድርሰት፣ ተዋንያኑ በተውኔት ስለ ህወሃት የአርባ አመት ጉዞ እንዲመሰክሩ የተሰጠች ትእዛዝ መሆንዋ ነው። አጭር፣ ግልጽ እና ቀጭን መልዕክት ነበረች።
የስርዓቱ ደጋፊ ሳይሆን ይልቁንም ተደጋፊ የሆኑት ሁሉ የዘመቻውን ጥሪ በደስታ ተቀበሉ። ወደ ደደቢትም አመሩ። የታዘቡትንም ነገር ሲናገሩ ሰማን።
ልብ እንበል! እነዚህ የጥበብ ሰዎች ናቸው። ጥበብ ደግሞ የሕዝብ አገልጋይ ናት። ጥበብ ለእውነት የምትቆም ዘብ ናት። ጥበብ አንድን ህብረተሰብ የመቅረጽ እና የመለወጥ ሃይል አላት።
በአለማችን የጥበብ ሰዎች ሚና ጎልቶ የሚታየው ተፈጥሮ ባደላቸው የጥበብ ስራ ብቻ ሳይሆን፤ እነዚህ ሰዎች በጥበብ ስራቸው ውስጥ ለህዝብ በሚያስተላልፉት እውነተኛ መልእክትም ጭምር ነው።
አርቲስቶች አክቲቪስቶች መሆን አለባቸው ብሎ መከራከር አይቻልም። ይህ የራሳቸው ምርጫ ነው። መሆን ካለባቸው ግን የህዝብን እንባ ማበስ ነው የሚገባቸው። ወቅቱን ጠብቆ እንደሚቀየር ድሪቶ መንግስት ሳይሆን ከህዝብ ጎን መቆም ያስከብራቸዋል።
ጥበብ ቆራጥነትን ትጠይቃለች። መስዋዕትነትን ልታስከፍልም ትችላለች። ፍሬዋ ግን ሁል ጊዜ ጣፋጭ ነው። እውቁ ቻይናዊ አርቲስት አይ ዌዊ እዚህ ላይ ይጠቀሳል። አሜሪካዊቷ ጁዲ ችካጎም እንዲሁ። ጃማይካዊው ቦብ ማርሌይ እና የናይጄርው ፌላ ኩቲ በአለማችን ላይ ለውጥ ያመጡ የጥበብ ጀግኖች ናቸው። የኛዋ አርቲስት አስቴር በዳኔም ለዚህ ዋቢ ነች። ማህበራዊ ድረ-ገጾች ይህንን አስረግጠውልናል።
“ህዝቡ አጎብዳጆች ይለናል።” አለች አርቲስት አስቴር በዳኔ ከዚያ ሁሉ መንጋ ተነጥላ። ‘እውነት ነጻ ያወጣችኋል!’ የሚለው ክርስቶሳዊ አባባል የተዋሃዳት ወጣት። እውነትን ተናግራ ራስዋን ነጻ አወጣች። እርግጥም የህሊና ነጻነትዋን ለማወጅ መድፈር ነበረባት። ማማጥም ነበረባት። አርቲስትዋ እንደጦር የፈራችው ከፊትዋ ተደርድረው የነበሩ ጉምቱ ባለግዜዎች አልነበሩም። ምክንያቱም ጉዳዩን ለነሱ አስቀድማ ተናግራ ነበርና። ይልቁንም ከአጠገብዋ የነበሩ የስራ ባልደረቦችዋ እና የሙያ አጋሮችዋ እንደጦር ያስፈራሉ። እንደ ይሁዳ አሳልፈው ሊሰጧትም ይችላሉ። ደደቢት ላይ ሲደርሱ ሁሉም በአንድ ማሰብ ጀመሩ። ደደቡ… አንድ ግዜ ተኑሮ ለሚሞትበት አለም ሁሉም ከራሱ ተጣላ። ሁሉም ከህሊናው ሸሸ። ሁሉም ለማደር አጎብዳጅ ሆነ። በመጨረሻም ሁሉም አስቴርን በአርባ ክንድ ራቁዋት። ግና እርሷ ጣርያ ስትነካ እነሱ ደግሞ ሲዘቅጡ አየን።
የኪነ-ጥበብ ሰዎቻችንን መፈተኛ ግዜ ብቅ አለ። ግን ይህ ሁሉ ወጪ እና ሽርጉድ ለምን አስፈለገ?
ጉዞውን ከመጪው ምርጫ ጋር የሚያያይዙ ወገኖች አሉ። ጉዞውን እንደምርጫ ዘመቻነት ለመጠቀም…። ይህ የዋህነት ይመስላል። ምክንያቱም ህወሃት አንድም ግዜ በምርጫ ዘመቻና ግልጽ በሆነ ውድድር ምርጫ አሸንፎ አያውቅም። ነብሳቸውን ይማርና አቶ መለስ ከነ ስዬ ቡድን ጋር በተለያዩ ግዜ ተናግረውታል። “ህወሃት በስብሷል!” ነበር ያሉት። ላለፉት ፪፫ አመታት ይህ የበሰበሰ ስርዓት ነው ሃገሪቱን እየገዛ ያለው። ይህ የበሰበሰ ስርዓት በምርጫ ሳይሆን የህዝብን ድምጽ በመስረቅ ነው እስካሁን ያለው።
ከምናከብራቸውና ከየምናደንቃቸው የኪነጥበብ ስዎች ውዳሴዎች ሰማን። ንዋይ ደበበም እጅግ አድርጎ ሲረግመው በነበረው ደደቢት ላይ ዘፈነ። እንዲያውም በስሜት ዘፈነ። “የሃገር ነቀርሳዎች” ሲላቸው የነበሩትን እነ ሳሞራን፣ እነ አባዱላን፣ … እያቀፈ … አልረሳም እያለ አቀነቀነ።
በዚያ የቀውጢ ወቅት ከሰለሞን ተካልኝ ከተቃዋሚ ወገን ወጥቶ ህወሃትን ሲቀላቀል ድምጻዊው ነዋይ ደበበ እንደ እብድ ነበር ያደረገው። ያዙኝ፤ ልቀቁኝ አለ። የንዴት ቃላትን ሁሉ በዘፋኙ ላይ አዥጎደጎደው። “ማሰብ የማይችል ደደብ ሰው!” አለ ነዋይ። ቀጠለናም “ሰለሞን ተካልኝ ስጋ የሚበላ በሬ ነው።” ሲል ድምጻዊውን ከሰብአዊ ፍጡርነት ወደ እንስሣነት ጎራ መድቦት ነበር።
ዛሬ በዚያው መድረክ ላይ አዲስ ትእይንት እያየን ነው። የግዜ ሃዲድ ላይ ሆኖ የሚመለከተው ሁሉ በትዝብት የሚያስቆዝም አሳዛኝ ድራማ፤ አርቲስት ብለን የምንጠራቸው ወገኖቻችን የሚፈጽሙት የፖለቲካ ዝሙት። ነዋይ ደበበ በግዙፉ የሰለሞን ተካልኝን ትከሻው ላይ ለመጠምጠም እጆቹ በጣም ሲረዝሙ በመገናኛ ብዙሃን ተመለከትን። … አጃኢብ አለ ያገሬ ሰው!
አዕምሮ ማሰብ ሲያቆም፣ አንገታቸው አዙሮ ማየት ሲሳነው፣ ልቦናችን የቅርቡን ክስተት ሲዘነጋ፣ የስነ-ልቦና ችግር ነው ከማለት ውጭ ምን ይባላል?
የሰራዊት ፍቅሬ ማጎብደድ ደግሞ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። ይህ ሰው በ፩፱፹ዎቹ በነበረው የርስ በርስ ውግያ ወታደር ሆኖ ከደርግ ወገን ነበር የተሰለፈው። ዛሬ በሽሬ ሽንፈቱ ላይ ጥሎት የሸሸው የጦር ታንክ ላይ ቆሞ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እጆቹን እያወጣ ደግም ቀለደ። ለካስ ደርግ እንደዚህም አይነት ወታደር ይዞ ነበር ህወሃትን ይፋለም የነበረ? ሰራዊት ፍቅሬ ዛሬ ዝናው ሳይሆን ሃብቱ ጣርያ ነክቷል። አሰልቺ ድምጹና ምስሉ እጅ-እጅ እስኪል በቴሌቪዥን እንዲቀርብ በገዢው ፓርቲ ተፈቅዶለታል። ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውሉ የስርዓቱ በዓላት ቁጥር እጅግ በዝተዋል። የብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ የከተሞች ቀን፣ የአርሶ አደሮች ቀን፣ የአርብቶ አደሮች ቀን፣ … ባዛር ለልማት ወዘተ። የማስታወቂያ ወጪው ከዝግጅቱ ወጪ አይተናነስም። ሁሉንም የማስታወቂያ ስራ ለሰራዊት ፍቅሬ ሰጥተውታል። ታዲያ እሱም ገሚሱን ለባለስልጣናቱ ማካፈሉ የግድ ነው። የዚህ ሰው መንቀልቀል ምስጢር ይህ ብቻ ነው። ሰራዊት ፍቅሬ በዚህ ሁኔታ የማስታወቂያ ስራውን በሙስና መስመር ውስጥ አዝልቆታል።
አንደኛው ተደጋፊም ተነስቶ “ይህ ነገር በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፊት ለፊት ሃውልት ሊሰራለት ይገባል።” ሲል ተደመጠ። ሰውዬው ይህንን አምኖበት እንዳልተናገረ ሰዎቹም ይገምታሉ። መቼም ለእለት ጉርስ ሲባል እንደዚህ አይነት ለህሊና የሚጎረብጥ ነገር እያደረጉ ከመኖር፤ በልመና መተዳደር ክብር ነው።
ከጅምሩ የስርዓቱን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሂደት ለመገምገም ወደ ደደቢት በረሃ መሄድም አያስፈልግም። ኢትዮጵያ ዛሬ ከገባችበት መከራ ለማውጣት የህወሃት አነሳስን ማጥናት ምንም ፋይዳ የለውም። መነሻው ጥሩም ይሁን መጥፎ፣ መድረሻው ግን አላማረም። ይህ ስርዓት ሃገሪቱን ባህር አልባ አገር አድርጓታል። የባህር በር የአንድ ሃገር ምስጢርም ነው። ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም ሉአላዊ ሃገር ምስጢር እንኳን የላትም።
ህዝቧም ከአፈናው ሰንሰለት ገና አልወጣም።
በአመለካከት ልዩነታቸው ብቻ ወገኖቻችን እንደ ጥጃ ሲታሰሩ የደደቢት ተጓዦቹ ይመለከታሉ። ሃሳባቸውን በነጻ የገለጹ ዜጎች የሽብርተኛነት ታርጋ ተለጥፎላቸው በግፍ ሲፈረድባቸው ይሰማሉ። ኢትዮጵያውያን እንደ ምጽዓት ሲሰደዱ በአይናቸው ይመለከታሉ። ለነጻነትና ለእኩልነት ታግለን መጣን የሚሉን ደግሞ በአንዲት ጀንበር ሚሊየነር ሲሆኑ ይታዘባሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ እንደሙያቸው አንዲት ቃል እንኳን ተንፍሰው አያውቁም። ወደ በረሃው መጓዙ እንደ ሲሲሊው የማፍያ ቡድን ከደደቢት ምሽግ ውስጥ ቃል-ኪዳን ለመግባባት ካልሆነ በቀር ፋይዳው አይታይም።
“ህዝቡ አጎብዳጆች ይለናል።” አለች አስቴር በዳኔ። ህዝብ ምን እንደሚላቸው የምትሰማው እርሷ ብቻ አይደለችም። ጆሮ ያለው ሁሉ ይሰማዋል። ይህን እያወቁ ግን አጎብዳጅ ምሆናቸውን ጭራሽ በብሄራዊ ቴሌቭዥን ወጥተው አሳዩን።
ህዝቡ ብቻ አይደለም። በእርግጠኝነት ለመናገር እነዚያ ባለ-ስልጣናትም አድርባዮቹን ይንቋቸዋል። በባህር ዳሩ የኢህአዴግ ጉባኤ “የኢህአዴግ አባል ለመሆን አንዱና ዋናው መስፈርት አድርባይነት ነው” በማለት አድርባይነትን የፈጠረውና ያስፋፋው ራሱ ህወሃት እንደሆነ ተናግረው ነበር። “አድርባይነት” ስርዓቱን በሚፈታተን ደረጃ መስፋፋቱን ከመግለጻቸውም በላይ አድርባዮቹን እንዴት እንደሚበቀሏቸውም ባህርዳር ላይ መክረዋል።
ደብረጽዮን ትእዛዙን ሲሰጡ ትንሽም ቢሆን ዲፕሎማት ነበሩ። ከትእዛዞቻቸው መሃል እንዲት እንዲህ የምትል መልእክት ነበረች። “…ችግሮቻችንንም ንገሩን።”
ይህች ሃረግ የኪነ-ጥበብ ሰዎቹ የህዝብን ብሶት በአደባባይ እንዲናገሩ በር ከፋች ነበረች። እነ አበበ ባልቻ ይህችን እድል ተጠቅመው ስለ-ኪነጥበብ መውደቅ እንኳን ትንሽ መልእክት ከማስተላለፍ ይልቅ ልወደድ ባይነትን መረጡ። ይህን ጥሬ ሃቅ የመናገር ድፍረት ያለው አንድ ሰው ጠፋ። ሁሉም ምስጋናና ውዳሴውን አበዛ። ለማደር የሚደረግ ካንገት በላይ ውዳሴ … መቼም ያሳዝናል።
በጭምጭምታም እንደሰማነው፤ በደደቢት አንዳች የተለወጠ ነገር የለም። ደደቢት ድሮም በረሃ – አሁንም በረሃ ነው። የአካባቢው ህዝብ ላይም ምንም የሚታይ ለውጥ የለም። ይህ ህዝብ ከሃያ አመታት በፊት የመናገር መብት አልነበረውም። ይህ መብት አሁን ብሶበት ሕዝቡ የመናገር ብቻ ሳይሆን የውጭ ራዲዮ እንኳን የመስማት መብቱን ተነፍጓል።
ይህችን ሃቅ የጎበኘ አንድ የኪነ-ጥበብ ባለሞያ እንዴት አስችሎት ዝም ይላል? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነበር። “ስለ እውነት የቆመ አንድ ሰው ይጥፋ?” የሚለው ጥያቄ በህዝብ ዘንድ እየተብላላ እያለ ነበር አስቴር በዳኔ ብቅ ያለችው። ይህች አርቲስት የህዝቡን ጥያቄ ይዛ በድፍረት ወረወረችው። መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ገጾችም በዚሁ ጉዳይ ተጨናንቀው ከረሙ።
ለድቅድቅ ጨለማ ትንሽ የብርሃን ፍንጣቂ ትበቃለች እንዲሉ የዚያን ሁሉ የውሸት ክምር አንድ እውነት አፈራረሰው። ህዝብ ያከብራቸው የነበሩ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ሁሉ ወረዱ። የማያልፈውን የህዝብ ፍቅር በሚያልፍ ነገር ቀየሩት።
ጥሪ የተደረገላቸው አርቲስቶች ሁለት አማራጮች ነበራቸው። ጥሪውን ተቀብሎ ሄዶ እውነትን መመስከር አሊያም እንደ ገጣሚ ታገል ሰይፉ ጥሪውን አለመቀበል። ገጣሚ ታገል ሰይፉ በኤፍ ኤም ፱፯ ራዲዮ ሲናገር እንዲህ ነበር ያለው።
“ባለፈው የመቀሌ ጉዞ ላይ እኔ አልሄድኩም። አርቲስቶች ሲሄዱ ጥሪ ተደርጎልኛል። ነገር ግን የደደቢቱን ጉዞ ስላላመንኩበት ቀርቻለሁ። ስለማልፈልገው ማለት ነው። … ለነሱም የምለው ነው። በተለይ ባለፉት 15 አመታት ብዙ ነገር አልተሰራም። ለስነ ጽሁፍ የሚመች ግዜ አይደለም። ስነጽሁፍን ትኩረት አልሰጡትም። እያየን ነው።“
ታገል ሰይፉ ቀደም ሲልም በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሃሳቡን ተቆርጦ እንዳስቀረበት ተናግሯል። ደደቢት ድረስ ሄዶ ሃሳቡን የማያስተላልፉለት ከሆነ መቅረቱ አይነተኛ አማራጭ ነው። አበበ ባልቻን፤ ሙሉ አለምን፣ ነዋይ ደበበን፣ … አርቲስቶች እና የኪነጥበብ ሰዎች ብለን ጠርተን፤ አስቴርንና ታገል ሰይፉን ምን ልንላቸው ይሆን? … ማህበራዊ ፍርዱን ከህዝቡ ያገኙታል።
ህወሃት ግን አንድ መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር አርቲስቶቹን ወደ ደደቢት የወሰዳቸው። እዚህ ተነስተን፣ አፈር ለብሰን፣ አፈር በልተን፣ የፈረስ ሽንት ጠጥተን የያዝናት ስልጣን ናት። ይህችን ስልጣን በምርጫ እንደማናስረክብ እናንተም አረጋግጡልን … እንዲሁ ተቃጥላችሁ ታልቃላችሁ እንጂ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ አታስቡ … የሚል መልዕክት።
እኔም በዚህች ቀልድ ጽሁፌን ልቋጭ። አንድ የህንድ ኢንቨስተር አዲስ አበባ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያንን የቀብር ስፍራ አይቶ በሊዝ ሊገዛ ፈለገ። የአዲስ አበባ ባለስልጣናትን ጠርቶ እንዲሸጡለት ጠየቀ። ባለስልጣናቱም መልሰው ሌሎች ቦታዎች ሳያልቁ የቀብር ስፍራ ለግዜው እንደማይሸጡለት ነገሩት። ህንዱ መለሰና መከራቸው። “እኛ አገር ሰው ሲሞት እናቃጥላለን እንጂ አንቀብርም። ለምን ይህን ለም ቦታ ታባክናላችሁ?” ባለስልጣናቱ መለሱ፣ “እኛ አገር ደግሞ ሰውን በቁሙ ነው እንጂ ሲሞት አናቃጥልም!”
aduye markeshaw says
እውነት ነው ክንፈ፦ እነ ሠራዊት ፍቅሬ በ11ኛው ሰዓት የጀመሩት ፍቅር ከረረ።
liyu afer says
እነዚህ የታሪክ አተላዎች ናቸው
የኛዋ የሴት ቁንጮ
Gugsa says
Kinfe, you are always nive in Your writings. You don’t have the moral capacity to boost Tgel Seifu who is a pupet of the Woyanes. He is one of the “Aytnew gize serawit..”