የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር በሽግግር ፍትህ ዙርያ ያሉ የፖሊሲ አማራጮችን ለውይይት መነሻ እንዲሆኑ የቀረቡበትን የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮች ሰነድ ይፋ አድርጓል።
በዚህም ተጠያቂ የሚሆኑ አጥፊዎች በሚለዩበት መንገድ ላይ ኹለት አማራጮች የቀረቡ ሲሆን፣ የመጀመሪያው አማራጭ በወንጀል ክስ ሂደቱ ዋና ጥፋት ፈፃሚዎችን፣ ትዕዛዝ የሰጡ፣ ያቀዱ፣ የመሩ እና ከፍተኛ ሀላፊነት ኖሮባቸው ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ግለሰቦች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ክስ እንዲመሰረት ማድረግ የሚል ነው፡፡
ኹለተኛው አማራጭ ደግሞ፤ የወንጀል ክስ ሂደቱን በማንኛውም ደረጃ በጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ ሰዎችን በማካተት እንዲከናወን ማድረግ የሚል ነው፡፡
በፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች መሰረትም የትኞቹ ጉዳዮች እንደሚያስከስሱ፣ በተቋማዊ ጉዳዮች፣ እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማውጣት፣ እርቅ፣ ምህረት፣ ማካካሻ እንዲሁም ተቋማዊ ማሻሻያዎች ላይ አማራጮች የቀረቡ ሲሆን፣ ውሳኔ የሚያስፈልጓቸው ጉዳዮችም ይፋ ተደርገዋል፡፡
ሰነዱን መነሻ በማድረግ በሽግግር ፍትህ ዙርያ በአገር-አቀፍ ደረጃ ውይይት እና ክርክሮችን በስፋት በማካሄድ፣ በአገራችን ነባራዊ ኹኔታ የተሻሉ አማራጮችን በመለየት እና የፖሊሲ መነሻ ሃሳቦቹን በማዳበር በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ መታሰቡንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ከዚህ አንፃር፤ በቀጣይ በአገር-አቀፍ ደረጃ ተከታታይ የፖሊሲ ውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ የገለጸው ፍትህ ሚኒስቴር፤ በቅድሚያ ለዚህ መነሻ ይሆን ዘንድ ሰነዱን ለህዝብ ይፋ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ብሏል።
ከውይይቶች ባሻገርም በሰነዱ ዙሪያ ያሉ አስተያየቶችን ለሚኒስቴሩ ማቅረብ እንደሚቻል ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ለውይይት የቀረበው የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮች ሰነድ ከዚህ በታች ይገኛል።
Leave a Reply