
ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ሀብትንና ብልጽግናን አመጣ ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ወያኔ የሥልጣን ወንበሩ ላይ በመውጣቱ ትግሬዎች ሁሉ አልፎላቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ላይ የጠነከረ እምነት አላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ ውይይትም ይሁን ንትርክ ይደረጋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተፈራ ርእስ ነው፤ ውስጥ-ውስጡን እንጂ አደባባይ አይወጣም፤ ይህንን ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ አደባባይ ለማውጣት ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል፤ አረጋዊ በርሄ፣ ገብረ መድኅን አርአያ፣ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ አብርሃ ደስታ (አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ይለኝ ነበር!) እየደጋገሙ ቢያነሡትም ሌሎች በቁም-ነገር የተቀበሉት አይመስልም፤ ሕዝቡ ግን በራሱ መንገድ እየተናገረና ምስክርነቱን እየሰጠ ነው፤ በመቀሌ የተሠራውን የመኳንንት መንደር ሕዝቡ አፓርቴይድ ብሎ ሲሰይመው፣ በአዲስ አበባ የተሠራውን መንደር መቀሌ ብሎ ሲሰይመው እየመሰከረ ነው፤ “የለሁበትም!” እያለ ነው።
የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ ‹‹ያመኛል›› ማለቱ ይገባኛል።
ወያኔ ትግሬ በመሆኑ ብቻ ትግሬ ሁሉ ዕዳ አለበት ማለት እንደወያኔ ማሰብ ነው፤ ወንጀል በዘር አይተላለፍም፤ እያንዳንዱ ሰው ለሠራው ሥራ ሁሉ ኃላፊነትን ይወስዳል፤ ጊዜው ሲደርስ ውጤቱንም ለመቀበል ይገደዳል፤ ይህ የሚሆነው ሰው ሁሉ በመንፈሳዊ ኃይል በጎ መንፈስ አድሮበት፣ አእምሮው በትምህርት ተገርቶ በትክክል ማሰብ ሲችል ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን በአለበት ሁኔታ በጎ መንፈስ የራቀው ይመስላል፤ አእምሮም ጭራሹኑ በእኩይ መንፈስና በጥላቻ እየዛገ ነው፤ ስለዚህ ያስፈራል፤ በደቡብ ሱዳን ሁለት መቶ ሰዎች በዘር ተለይተው ታረዱ ሲባል ያስፈራል፤ በናይጂርያ፣ በኮንጎ የሚካሄደውን የዘርና የሃይማኖት እልቂት ስንሰማ ያስፈራል፤ በ1997 ዓ.ም. መለስ ዜናዊና አዲሱ ለገሰ እንዳስታወሱን የሩዋንዳ የጎሣ እልቂት በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ አለ፤ የቅርብ ተኳሽ የሆነው የአግዓዚ ጦርም አድፍጦ መጠበቅ ያስፈራል፤ ሌላውም ይህንን አውቆ አድፍጦ መጠበቁ ያስፈራል፤ ሰማይ ጠቀስ የሠሩት፣ የሥልጣን ኃላፊነትን ችላ ብለው በሥልጣን የሚነግዱና የሚከብሩት፣ የማይኖሩበትን ሕንጻ የሚክቡት፣ ከሕዝብ ጋር ያላቸው የአይጥና የድመት ኑሮ ያስፈራል፤ አቶ አስገደ ወያኔ መደንገጡን ይነግረናል፤ መደንገጥ የማይቆጣጠሩት ፍርሃት ነውና አደጋ ያመጣል፤ አደጋው አደጋን ይጠራል፤ ይህም ያስፈራል።
በትግራይ ዙሪያ ያለው ምንድን ነው? የትግራይ ሕዝብ በየትኛው አቅጣጫ ነው አንደልቡ እየተዘዋወረ ለመሥራትና ለመኖር የሚችለው? ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ከሰሜን ከወገኑ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ደም አቃብቶታል፤ በደቡብ-ምሥራቅ ከወሎ መሬት ቆርሶ የወሎን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ በደቡብ-ምዕራብ ከጎንደር መሬት ቆርሶ የጎንደርን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ የራስን ወገኖች አስቀይሞ ሱዳንን በመሬት ለመደለል የሚደረገው ጥረት ሁሉ ፋይዳ የለውም፤ ሱዳን ለራሱም ያልበጀ አገር መሆኑ እየታየ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ይበልጥ ይታያል፤ በትግራይ ውስጥ ደግሞ ወያኔ የፈጠረው አፓርቴይድ የወያኔን የኑሮ ደረጃ ወደሰማይ ሲያስጠጋው፣ የቀረውን ወደአንጦርጦስ የደሀነት ገደል ውስጥ ከቶታል፤ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ከነልጆቻቸው እየተዘዋወሩ የሚለምኑ ሞልተዋል፤ ይህ ልመናም ለወያኔ ለመገበር ነው፤ ብዙዎቹ እንደሚናገሩት የሚለምኑት የማዳበሪያ ዕዳቸውን ለወያኔ ለመክፈል ነው።
ወያኔ ከሀያ ዓመታት በላይ አፍንጫ እየያዘ ያስከፈለውን የሚመልስበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፤ ጥያቄው ወያኔ እንዲመልስ የሚገደደው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ጥላቻ ወደንዴት፣ ንዴት ወደቁጣ ተለውጦ ሲገነፍል ምጽዓት ደረሰ ማለት ነው፤ ሁሉም ሰው ራቁቱን ይሆናል፤ አንደአውሬ ከጥፍሩና ከጥርሱ በቀር ሌላ መሣሪያ አይኖረውም፤ ሰው ሁሉ በክፋት ወደአውሬነት ይለወጣል፤ ጠመንጃና ቦምብ አያገለግሉም፤ ሕንጻው ምሽግ አይሆንም፤ መኪናው፣ ባቡሩ፣ ታንኩ ከቆመበት አይነቃነቅም፤ የትም አያደርስም፤ ጭፍራ ሁሉ በየራሱ ፍዳ ታንቆ እንኳን ለሌላ ሊተርፍ ለራሱም የማይበቃ ይሆናል፤ ለነገሩ ጌታና ሎሌም የለም፤ ሁሉም በአውሬ እኩልነት የተፋጠጠ ነው፤ ርኅራኄ ተሟጦ፣ መግል ያዘለ ልብ ፈርጦ፣ ውይይትና ክርክር አብቅቶ፣ ጥርሱን ያገጠጠና ጥፍሩን የሳለ መንጋ በደም የሚራጭበት ሁኔታ ነው።
ሌላ አገር እንዲህ አልሆነም፤ እዚያ አገር እንዲህ አልሆነም፤ የሚባል ነገር የለም፤ እኛ ዘንድ ሌላ ነው፤ የኢትዮጵያ ደሀዎች እንባ የእግዚአብሔርን ሰማይ አጨቀየው!
“ክፋት እንደእሳት ይቃጠላል፤ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፤ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደዓምድ ይወጣል፤ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቁጣ ምድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም፤ ሰው በቀኙ በኩል ይነቅላል፤ ይራብማል፤ በግራም በኩል ይበላል፤ አይጠግብምም፤ እያንዳንዱም የክንዱን ሥጋ ይበላል፤ ምናሴ ኤፍሬምን፣ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤…” ኢሳይያስ 9/18-21
ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም፤ ሚያዝያ 2006
WARNING! WARNING!! WARNING!!!!
TO ALL ETHIOPIANS!!!!!!!!!!
This is the timely warning to all of us, specially for those who lost their mind – Helina, just only for the sake of their daily bread (forgetting their nature of MORTALITY).
Brothers and Sisters! Time is very short. So, please lets think over and over about this issue and listen to Professor’s advise carefully. He is preacher of Gospel/Truth without Bible through out his age. Praise God for such kinds of Individuals, who usually cry out not for their benefits, but for all members of the society (Ethiopians).
I would, therefore, like to encourage all Ethiopians to stand and do their part so that we can avoid this huge fear from the heart of our people. I strongly agree with Professor that ”SIN CAN NOT BE TRANSFERRED TO OTHERS.” In other words, everyone would be punished as per his wrong doings against the LAW/TRUTH. Or as the word of God says: ”EVERYONE WILL REAP WHAT HE SAW.” Specially those who are making business at the expense of others’ life. Really, shame on them!.
The main responsibility at present is, therefore, to take action together to avoid this fearful ETHNIC CONFLICT, which is coming like a very heavy CLOUD.
Thank you professor!!! and Praise God for all your effort to tell the Truth.
Finally, I would like to say: HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THIS ARTICLE SAYS TO ALL OF US.”
GOD BLESS ETHIOPIA!!!!
HELINA/MIND