• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የሕወሓትን “ሌጋሲ” በጨረፍታ

December 29, 2016 05:11 am by Editor Leave a Comment

የወያኔው መንግሥት ያላወረሰን ነገር የለም፡፡ ሁለመናችንን እከክ በእከክ አድርጎናል – በቀላሉ በማይድን እከክ አውርሶን ወያኔም እኛም ጣር ላይ እንገኛለን – አሸናፊው ባልለየለት እልህ አስጨራሽ የአውራ ዶሮዎች ጦርነት ተጠምደን፡፡

የመለስና የድርጅቱ የሕወሓት ውርስ (ሌጋሲ) በአሥራዎች ቀርቶ በመቶዎች ዓመታትም ተዝቆ የማያልቅ ዕዳ አሸክሞናል፡፡ በኢኮኖሚውና በትምህርቱ ረገድ የደረሰብን ኪሣራ ምናልባት በጊዜ ሂደትና ደጋግ ዜጎች የአስተዳደሩን ልጓም ሲይዙ ሊስተካከል ይችላል፡፡ ይህም ሲባል ሚሊዮኖችን በእሳት አለንጋው እየገረፈ የሚገኘው ድህነት ጥርሱን አግጥጦና ዐይኑን አፍጥጦ ዜጎችን የበይ ተመልካች በማድረግ ከማንኛውም ጨዋታ ውጪ እያደረጋቸው እንደሆነና በትምህርቱም በኩል በዘልማድ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 85 በመቶው እንደሆነ ከሚነገርለት የሀገራችን ገበሬ በዕውቀት የማይሻሉ ምሩቅ ማይማን ሀገርን እየመሩ እንደሚገኙ ልንክድ አይገባም፡፡ ከዚያ በመለስ ያለው ሌላው ሥነ ልቦናዊ፣ ሞራላዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ዝቅጠት ግን በተከድኖ ይብሰል ብቻ የሚታለፍ ሣይሆን በተለይ ጤነኛ ነኝ የሚል በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖር ዜጋ ሁሉ ሊነጋገርበትና የጋራ መፍትሔ ሊሻበት የሚገባው እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የትም ብንኖር በመጨረሻው ቢያንስ ልጆቻችን ሀገራችን ብለው መፈለጋቸውና መመለሳቸውም አይቀርም – የሰው ወርቅ አያደምቅም፡፡ ስለሆነም ለዚህች የወል ጎጆኣችን ማሰብና መጨነቅም አለብን፡፡ አንዳንዶቻችን ዛሬ በሰው ሀገር የደላን መስለን ብንኖርም እንደብሂሉ “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም”ና ነገ ተመልሰን የምንገባበት ሀገር ያስፈልገናል፡፡

እንጂ በኢኮኖሚ ረገድ ጥቂት እናውራ ካልንማ እንዲህም ሆነናል፡፡…

በብዙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በወላጅና በመምህራን በሚቋቋሙ የምገባ ኮሚቴዎች የድሃ ቤተሰብ ተማሪዎች በቀን አንዴ ምግብ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ይህም በጎ ሥራ የተጀመረው ተማሪዎች ባልታወቀ ምክንያት በተለይ እኩለ ቀን አካባቢ እየተዝለፈለፉ ሲወድቁ በመታየቱ ያን ክስተት ተከትሎ በተደረገ ጥናትና ክትትል ተማሪዎች እንዲያ የሚሆኑት ያለ ምግብ ወደ ትምህርት ቤት ስለሚመጡ እንደሆነ በመረጋገጡ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎችን ቢያንስ በቀን አንዴ ለመመገብ በብዙ ትምህርት ቤቶች የምሣ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡

እኔ ራሴ በተሣተፍኩበት የአንድ ትምህርት ቤት ገጠመኝ አማካይነት ይህን አንገብጋቢ ጉዳይ በተጨባጭ ማስረዳት እችላለሁ፡፡

በክፍል ውስጥም ከክፍል ውጪም በ“ሀ” ት/ቤት ውስጥ ተማሪዎች ዘወትር እየተዝለፈለፉ (ፌይንት እያደረጉ) ይወድቃሉ፡፡ ለምን እንደሆነ ተጠና፤ ርሀብ ነው፡፡ የመምህራን ኮሚቴ ተቋቋመና የገንዘብና የምግብ ርዳታ ማሰባሰብ ተጀመረ – እንደዬአቅማችን በየወሩ ገንዘብ ለማዋጣት ብዙዎቻችን ቃል ገባን፡፡ በቅድሚያ ግን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ተማሪዎች መለየትና ከአቅማችንም ጋር የሚመጣጠን የተረጂ ብዛት እንዲኖረን ማድረግ ነበረብን፡፡ ለዚህም የባሰባቸውን ብቻ ለመምረጥ በየክፍሉ ምዝገባ መካሄድ እንዳለበት ተስማማን፡፡ አንዱ መሥፈርት የምሣ ሣህን የማይዝን ተማሪ ማስቀደም ነበር – ከምግብ ጥራትና ዓይነት በፊት፡፡

አንድ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ምዝገባው ተጠናቀቀ፡፡ አንዷ ተማሪ ባለመመዝገቧ መንታ መንታ ታለቅሳለች፡፡ ያልተመዘገበችው የምሣ ሣህን እንደምትይዝ በተማሪ በመጠቆሙ ነበረ፡፡ ይህች ተማሪ በዕንባ እየተነፋረቀችና ሣግ እየተናነቃት የሚያምር የምሣ ሣህኗን ከፍታ ለመዝጋቢዎች አሳየች – አንዲት ትንሽ የተላጠች ድንች ናት የተቋጠረችላት፡፡ ተማሪዋም መዝጋቢዎችም ተያይዘው እዬዬ፡፡ ለምን ተብላ ተጠየቀች፡፡ መልሷም – “እቤታችን የሚበላ ነገር የለም፡፡ ይህም የተቋጠረልኝ ከጓደኛ እንዳላንስ ተብሎ ነው፡፡ ቁራሽ እንጀራ የምንቀምሰው ከስንት አንዴ ነው፤ የሚሰጠንም ሁላችን በአንድ ጊዜ ሣይሆን በየተራ ነው…”፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ በየትምህርት ቤቶች እየዞሩ ወተትና ዳቦ እንዳላደሉ አሁን ልጆቻችን በጠኔ እያለቁ ነው፡፡ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የዶሮውን ቅልጥም “የአሞራ ነው”፣ ቅቤውን “የቀለጠ ሞራ ነው” እያሉ እንዳልተሞላቀቁና በዚያም ሳቢያ ለሥራ ጉብኝት ወደውጪ ሊሄዱ ሲሉ ጃንሆይ እንዲያነጋግሯቸው ከቦሌ አየር ማረፊያ እንዳላስመለሱ ዛሬ ወያኔ በነቀዘ እህልና እህል ቅጠል በማይል የአፈር ሽሮ ልጆቻችንን  ለተለያዩ ህመሞች እየዳረጋቸው ነው፡፡ ለማንኛውም የወያኔ ውርስ ከዚህም በላይ ነው፡፡ ለሚለቀስበት እናልቅስ፡፡ በከንቱ ግን ዕንባችንን አንጨርስ፡፡

አዎ፣ በቁም ሞተናል፡፡ በየቦታው የነገሠውን ርሀብ ብትሰሙ አልቅሳችሁ አታባሩም – የሰው አንጀት ካላችሁ፡፡ ገንዘባችን ወድቋል፤ እጅጉን ተንቋልም፡፡ ሥራ ያለውም ሥራ የሌለውም በእኩል ይራባል፡፡ በዚህ የቀጣና ዘመን ጠግቦ የሚያድር አንድም ሌባና አጭበርባሪ ነው፤ አንድም ወፍራም ደሞዝ የሚከፈለው የግልና የመያድ ሠራተኛ ነው፤ አንድም በጉቦና በሙስና የጠገበ ኅሊናቢስ ዜጋ ነው፤ አንድም ከውጭ ገንዘብ የሚላክለት ዕድለኛ ሰው ነው፤ አንድም የሚከራይ ቤትና ንብረት ያለው ዜጋ ነው … ታሪኩ ብዙ ነው፡፡ ገመናችን ቁልል ነው፡፡

እንጂ እንደእውነቱ ከሆነ በአሁኑ ወቅት ከአሥርና ከአሥራ አምስት ሺህ ብር በታች የተጣራ ወርሃዊ ገቢ ያለው ሰው ኑሮ እየኖረ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ይታያችሁ – ተጣርቶ 300 እና 400 ብር የሚደርሳቸው ብዙ -እጅግ ብዙ “ሠራተኞች” አሉ፡፡ ይህን ደሞዝ የሚከፍል ወገንም እነሱ ራሳቸውም ምን ዓይነት ፍጡራን እንደሆኑ ሳስበው ሁሌም በጣም ይገርመኛል፡፡ “ላያስችል አይሰጥም፡፡” አሉ? “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” ይባላልና ታዲያ መንግሥት ተብዬውና የግል ባለሀብቶች ይህን የሕዝብ ችግር አያውቁም ወይም ሊያውቁ አይፈልጉም፡፡ እነሱን አይነካማ! እነሱን የሚመለከት ችግር ቢከሰትማ በደቂቃና በሰከንድ ውስጥ ዐዋጁን አናት ባናት ያዥጎደጉዱታል፡፡ ስንቶች በርሀብ እያለቁ ለአንድ ሀብታም የቀድሞ “ፕሬዝደንት” – ለግርማ ወ/ጊዮርጊስ – ስንት መቶ ሺህ ብር በየወሩ ይከሰከስ የለም? ምቀኝነት ተጠናውቶኝ እንዳይመስላችሁ – ማሰብ የሚችል የመንግሥት ባለሥልጣን መጥፋቱን ለመጠቆም ብዬ ነው፡፡

ከፍ ሲል የጠቀስኩት አግራሞት የሚገርመኝ ስለሚቀጥለው ምክንያት ነው – በአዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት አንዲት ሁለት ሜትር በሦስት ሜትር የሆነች ክፍል ቤት ለመከራየት ከፈለግህ – መሀል ከተማ በትንሹ ሁለት ሺህ ብር – 10 ኪ.ሜ ያህል ትንሽ ወጣ ካልክ 1200 ብር – ከመሀል ከተማ 15ኪ.ሜ ወጣ ብለህ ደግሞ 800 ብር ገደማ ነው፡፡ 300 ብር ይዘህ ምን ልትሠራበት ነው ታዲያ? የ800 ብሩን ልከራይ ብትልና ከከተማ ብትወጣ ትራንስፖርቱ ብቻ በትንሹ 600 ብር ነው፡፡ ደምረው ከፈለግህ – 600+800 = 1400፡፡ በዚያ ላይ ሰው ቤት ስለተከራዬ ወይ ስላለው ብቻ በሕይወት አይኖርም፤ ምግብ፣ ልብስ፣ ህክምናና ሌላ ሌላ ወጪዎች አሉበት፡፡ በአሁኑ ወቅት ገበያው ሰማየ ሰማያትን አልፎ ድሃ  አይነካሽ ሆኗል፡፡ ጤፍ በኩንታል 2000 (ሠርገኛው)፣ ዘይት በሊትር ባማካይ 60፣ … ሥጋና ቅቤ (ደግነቱ እነዚህኞቹ እንኳን በህልምም መምጣት ካቆሙ ሰንብተዋል) … ልባሽ ጃኬትና ልባሽ ጫማ ከአንድ ሺህ ብር በላይ፣ አንድ ኪሎ ምሥር ክክ 55 … ስንቱን ብዬህ … ገንዘባችን እንደዱሮው የጀርመን ዳች የወንደላጤዎችን ቤት ግድግዳ ማሳመሪያነት ሊውል ጥቂት ጊዜ በቀረው በዚህን የኢኮኖሚ ድቀትና የገንዘብ ግሽበት ወቅት አንድ ሺህ ብር ምንድን ናት? ምንም! መጥፎነቱ “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” እንዲሉ ሆኖ ይሄ እንደአሸን የሚፈላ የነጨቡዴ ሕንፃና ቁራሽ ዳቦ ሆኖ  አንጀት ጠብ የማይለው የአስፋልትና የባቡር መንገድ በተለይ በባዕዳንና በአሽቃባጭ የወያኔ ደጋፊዎች  ሲታይ የኔን ዓይነቱን የብሶት ጽሑፍ “የምቀኛ ወሬ ነው” ማስባሉ አልቀረም፡፡

በዚህ እንደ እሳተ ገሞራ በሚጋረፍ የኑሮ ውድነት የ2000 ብር ደሞዝተኛ ልጁን እንዴት ያስተምር?  ምን እየመገበ፣ ምን እያለበሰ፣ የትምህርት መሣሪያዎችንና ትራንስፖርቱን እንዴት እየቻለ ያስተምረው?  ፍርድ ለራስም ነውና እውነቱን ፍረዱ፡፡ “ትልቁ ተከፋይ” የ5000 ብር ደሞዝተኛ ልጁን እንዴት ያስተምር? የቤት ኪራዩ ብቻ ከዚህ ገንዘብ የሚልቅ ይወስድበታል፡፡ እዬዬም እኮ ሲደላ ነው፡፡ ሌብነትና ኢሞራላዊነት እንደባህል የተወሰዱት እኮ ምናልባትም በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህኛውንና የዚያኛውን ወሮች ጠርዝና ጠርዝ አገናኝቶ ለመስፋት ስንቶች ስንትና ስንት መከራ እንደሚያዩ እናውቃለን – ለዚህ ነው ወያኔዎች ሕዝብን አደህይቶ መግዛት ከጓዳው ባለፈ አንድም ነገር እንዳያስብ የሚያደርግ መሆኑን አምነው ማደህየትን በመመሪያ ደረጃ የሚተገብሩት፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥ ማሰብ የሚሣነው ሕዝብ እንደመፍጠር ያለ ወንጀል ደግሞ ሊኖር አይችልም – አእምሮንና ኅሊናን መግደል ሥጋን እንደመግደል በቀላል ቅጣት የሚገላገሉት ወንጀል አይደለም – ነፍስን ለመግደል የመሞከር ያህል አካላዊም ሆነ መንፈሣዊ አመክሮ የሌለው ትልቅ ኃጢኣት ነውና፡፡

በዚህ የፈተና ዘመን – ዘመነ መንሱት – ሁላችንም የተያያዝነው “ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ” ዓይነት ይመስላል –  ግን ቄስ የለ ደብተራ፣ ጳጳስ የለ ሊቀ ገበዝ … ሁላችንም ተያይዘን በጠፋንባት ሀገር  ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ መቀደስ ቢያምረን “ማን ነው የሚቀድሰን?” የሚለው ጥያቄ ከባድ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ እናንተም አስቡት፡፡ መቀደስ አምሮን አምሮን ይቀራል እንጂ አንድም ሰው የለም፡፡ ማተቡን ጠብቆ በፅድቅ የሚቆይ አንድ ሰው እንኳ ቢኖር እኮ ነው እንዲህ የሚባል፡፡ የሰው መጽሐፍ ርዕስ ኮርጀሃል እንዳልባል እንጂ “አልጠፋንም ብለን አንዋሽም” ብለን እውነቱን ከመመስከር የሚያግደን አንድም ተጨባጭ ማስረጃ የለንም፡፡

የሆነው ሆኖ ሀገራችን በከፍተኛ ችግር እየተደቆሰች መሆኗን ለአፍታም አንርሳ፡፡ ለምሣሌ አሁን እኮ ድርቅ ባልገባበት በአገር ሰላም ሕዝብ በርሀብ እያለቀ ነው፤ በሽታ የርሀብ ታላቅ ወንድም ነው ብንል ርሀብ ያደቀቀለትን ሰው አንድ በሽታ በቀላሉ ለሞት ያበቃዋል፤ በዚህ ሂደት ስንቱ ሕይወቱን እያጣ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ እንደኢትዮጵያ ሕዝብ አቻዮ ይኖር ይሆን ግን? የሆዱን በሆዱ ችሎ ሕዝቡ አሁንም እንደዱሮው ይስቃል፤ ይጫወታል፡፡ ከነፈገግታውና ከነወዙ ነው፡፡ ግን ግን ከተሞች በዕብድና በወፈፌ እየተሞሉ መምጣታቸውን ጥቂት በመዘዋወር ብቻ መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል በሚስተዋሉ አንዳንድ ነባራዊ ክስተቶች የሕዝቡን ድህነት መገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል – ልመና ከቁጥጥር ወጥቷል – በረንዳ አዳሪነት ከቁጥጥር ወጥቷል – ጠጪነትና ሰካራምነት ከቁጥጥር ወጥቷል – ሴተኛ አዳሪነት እግር አውጥቶ እየሄደ ነው፡፡ ይህ “ሥራ” ዱሮ በተወሰኑ ሥራ አጥ እህቶቻችንና ልጆቻችን ይካሄድ ነበር፡፡ አሁን ግን ከሥራ ወጥተው በጊዜ የሚሰለፉበት የሁሉም ሴቶችና የጥቂት ዲያብሎሣውያን ወንዶች ተደራቢ መተዳደሪያ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ በታች ያለውን ከ18 ዓመት ዕድሜ በታች የሆነ ባያነብብኝ ደስ ይለኛል፡፡

ሞራልና ሃይማኖት ከሀገራችን መሰደድ ከጀመሩ ቆየት ቢልም አሁን ግን ለይቶላቸው የጠፉ ይመስላል፡፡ ሕጻናት ወንዶችን በጠራራ ፀሐይ እየጠለፉ በመውሰድ ለሰይጣናዊ ወሲብ ንግድ የሚዳርጉ ብዙ ድርጅቶችና ተባባሪዎቻቸው እንዳሉ እየሰማን ነው፡፡

 ሰሞኑን በአንድ አካባቢ -አዲስ አበባ ውስጥ – እንዲህ ሆነ፡፡ አንድ ታዳጊ ከትምህርት ቤቱ ሲወጣ ይጠለፋል፡፡ ለ15 ቀናትም ይጠፋል፡፡ መጨረሻ እንደምንም ይገኛል፡፡ የጠለፉት ግብረሶዶማውያን ልጁን እንዳይሆን አድርገው ነው የለቀቁት፡፡ ሌላው ቀርቶ ከንፈሩ ቆስሎና አባብጦ ነጋሪት አክሏል፡፡ የዚህም ታሪኩ ብዙ ነውና ሆድ ይፍጀው፡፡ የዚህ ዓይነት ጉድ ግን በየሥርቻውና በየመንደሩ እንደፋሽን ተይዟል፡፡ ትምህርት ቤቶችን በልቅ ወሲብና በተመሳሳይ ፆታዎች ግንኙነት በመበከል የሀገራችንን ባህላዊና መንፈሣዊ ዕሤቶች እያጠፉ ያሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ሰይጣናዊ  ድርጅቶች መኖራቸው ይታወቃል – በሃይማኖቶቻችን ውስጥም በአመራርና በአገልግሎት ደረጃ በመስረግ ጭምር፡፡ በጭፈራ ቤቶችና በዝጉብኞች የሚሠራው ሁሉ ሲሰማና ሲታይ የሎጥ ዘመን ሶዶምና ገሞራ በጣት እስኪነኩ የቀረቡ ይመስላሉ – በፈጣሪ ታጋሽነትም እንዲሁ መደነቃችን አይቀርም፡፡ ሰውን በተስፋ መቁረጥ ማዕበል ማላጋት፣ ከነባሩ ደገኛ አስተሳሰብና አሠራር ማውጣት፣ ዋልጌነትንና ገንዘብ አምላኪነትን ማስፋፋት… የነዚህ የጥፋት አምባሳደሮች ዋና ተልእኮ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ሰደዳዊ ወረርሽኝና የተጋቦት በሽታ ኢትዮጵያን የማዋረድና ከእግዚአብሔር ፀጋ የመነጠል ትልቁ ዓለም አቀፍ ዘመቻ አካል ነው፤ ይሄው ታላቅ ሚሌኒየማዊ “ስኬት”ም አንዱ የወያኔ ሌጋሲ ነው፡፡ ግን ግን በመጨረሻው ውድ ዋጋ ይከፍሉበታል፤ ወዮ ለዚያ ቀን!…

ለማጠቃለል ያህል – አንድ ፃዲቅ ኢትዮጵያዊ አቡን ወይም ቀሲስ ቢኖረን ከችግራችን ሃምሣ በመቶው በተራገፈልን ነበር፤ አንድ ቅን አሳቢ ፖለቲከኛ ቢኖረን ከችግራችን ሃምሣ በመቶው በተቃለለልን ነበር፤ አንድ ህግን ተመርኩዞ የሚነግድ የቢዝነስ ሰው ቢኖረን ከችግራችን ሃምሣ በመቶው በተቀረፈልን ነበር፤ ካለሙስና የሚፈርድ አንድ ዳኛ እንኳን ቢኖረን ከችግራችን ሃምሣ በመቶው በተቀረፈልን ነበር፤ አንድ እውነተኛ ምሁር ቢኖረን ከችግራችን ሃምሣ በመቶው በተቀረፈልን ነበር፣ ያላንዳች ማስመሰል – በትክክለኛው የፈሪሃ እግዚአብሔር  ፈለግ የሚመራ አንድ ትዳር ቢኖረን ከማኅበራዊ ችግሮቻችን ሃምሣ በመቶው በተወገደልን ነበር፣ ካለጉቦና እጅ መንሻ በንጹሕ ኅሊና የሚያገለግል አንድ ፖሊስ፣ አንድ ወታደር፣ አንድ የደኅንነት አባል፣ አንድ የማዘጋጃ ቤት ሹም፣ አንድ የመሬት አስተዳደር ባለሥልጣን፣ አንድ የቀበሌ አመራር፣ አንድ የመንጃ ፈቃድ መስጫ ቢሮ ኃላፊ፣ አንድ የጉምሩክና ቀረጥ ቢሮ ሹም፣ አንድ የሰበካ ጉባኤ ሊ/መንበር፣ አንድ የደብር አለቃ፣  … ቢኖረን ኖሮ ይሄኔ ስደታችንና እንግልታችን ቅጥ ባላጣ ነበር፡፡  ምክንያቱም የአንዱ በረከት ለሌላውም ይተርፋልና እነዚህን መሰል ምናባዊ ዜጎች ወደ እውናዊነት ቢመጡልን እንደናርዶስ ሽቱ መዓዛና ጠረናቸውም ብዙዎችን ወደነሱ ይስብልን እኛንም በፀዳላዊ ትውፊታቸው ከጥፋት ይታደጉን ነበርና፡፡ የምኞት ባሪያ አንሁን እንጂ ምኞት በራሱ መጥፎ አይመስለኝም፤ እናም አይከለከልም፡፡ ስለማይከለከልም ደጋግ ዜጎችን ለማየት ተመኘሁ፡፡ ለዚያ ያብቃን፡፡ ደግሞም ዕድሜና ጤና እንጂ ይህ ቆሻሻ ዘመን አልፎ ታሪክ የማይሆንበትና ወርቃማ ዘመን የማይብትበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የተቸገርነው ካልጠፋ ዘመን ራሳችንን አጉል ዘመን ላይ  አግኝተነው ነው፤ ቸር እንሰንብት፡፡

ተሻለ መንግሥቱ (teshalem1@gmail.com)


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የገዳ ሥርዓት እና የኦሮሞ ገዢ መደብ June 20, 2022 11:34 pm
  • “የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው” ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል June 12, 2022 07:09 pm
  • የሰሜን ምዕራብ ዕዝና የአማራ ልዩ ኃይል ተከዜ ክፍለ ጦር ዕውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው June 12, 2022 06:21 pm
  • ሀገር በቀል ባህላዊ የግጭት አፈታቶችን በተገቢው በመጠቀም ዘላቂ እርቅና ሰላምን ማምጣት ይቻላል June 12, 2022 05:40 pm
  • የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በገረጂና በቀበና ያስገነባቸውን የመኖሪያ አፓርትመንቶች አስመረቀ June 12, 2022 05:35 pm
  • በኦነግ ሸኔ ፈርሶ የነበረውና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀመረ June 10, 2022 09:13 am
  • ጃዋር በዳውድ ኢብሣ ቀይ መስመር ተሰመረለት June 8, 2022 12:59 pm
  • ወልቃይት: ቢመረንም ለመዋጥና ራሳችንን ለመመልከት እንሞክር June 8, 2022 11:53 am
  • እብድ ይሻለዋል እንጂ አይድንም፤ ሐጂ ጃዋር አሁን ለምን ብቅ አለ? June 8, 2022 05:59 am
  • ሕዝብ ድምፅ የነፈጋቸው “ፓርቲዎች” የሽግግር መንግሥት ይቋቋም አሉ June 7, 2022 01:11 am
  • “አድጌ እንደናንተ መሆን እፈልጋለሁ” June 5, 2022 06:58 pm
  • በሳምንት ለ100 ያህል ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ሥራ ጀመረ May 30, 2022 02:20 am
  • የጥቁር አንበሳ ዕጩ መኮንኖች (ካዴቶች) ተመረቁ May 29, 2022 04:01 pm
  • “ኢትዮጵያን መንካት አይቻልም!!” በሚል ቁጭት ነው እየሠራን ያለነው May 29, 2022 01:04 pm
  • “ከሞፈርና ቀንበር ወደ ትራክተር” በሚል መርህ ለአማራ ገበሬዎች የግብርና ሜካናይዜሽን ተሰጠ May 29, 2022 02:02 am
  • ኢትዮ 360 “የወያኔ፣ የጁንታ ሚዲያ ነው” – ባለከዘራው ጄኔራል May 27, 2022 02:51 am
  • “እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ የሚያጣሉን ፖለቲከኞች ናቸው” የአማራ ወዳጃቸውን አደራ ቤት የመለሱ የቅማንት ተወላጅ May 27, 2022 01:40 am
  • ትግራይን አገር እናደርጋለን፤ “በውይይት እና በጦርነት” ሁሉንም ጉዳይ እንቋጫለን – የወንበዴው መሪ ደብረጽዮን May 26, 2022 09:18 am
  • “ሁለቱ የምዕራብ ዕዝ ተዋጊ ዶክተሮች” May 26, 2022 08:19 am
  • ወደ ትህነግ ሊተላለፍ የነበረ አምስት ሚሊዮን ብር ከ20 ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ May 25, 2022 01:57 am
  • የጦርነቱ ስትራቴጂያዊ እውነታዎች May 19, 2022 09:37 am
  • በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም የሚውል የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የዓለም ባንክ May 16, 2022 10:22 am
  • በአዲስ አበባ 1 ሺህ 98 የብሬን እና 2 ሺህ 162 የክላሽ ጥይት ተያዘ May 16, 2022 10:10 am
  • በአዲስ አበባ ከተማ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ከ5 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላርና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች ተያዙ May 16, 2022 09:53 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2022 · Goolgule