መግቢያ፤
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ከተመሠረተ ጀምሮ የተለያዩ ስሞችን፣ መርኆዎችን፣ ተግባራትን፣ ባጠቃላይም ማንነትን ተከናንቧል። ይህ ማለት፤ በሂደቱ እየተቀያየረ የሄደ ድርጅት ነው። ሲነሳ፤ አሁን የያዘው እምነት፣ ግብና አሠራር አልነበረውም። እግረ መንገዱን ለዕለቱ የሚረዳውን የፖለቲካ አቋም እየውለበለበ ተጓዘ እንጂ፤ ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ አቋም አልነበረውም። ይህ የሚነግረን፤ ይህ ድርጅት፤ አጋጣሚዎችን ተጠቃሚነትን፣ ሥልጣንን፣ ቂምና በቀልን፣ የሕልውናው መሠረቶች አድርጎ የተጓዘ እንጂ፤ መርኆ ወይንም ሕዝባዊ ግንዛቤ ያላነገበ ድርጅት መሆኑን ነው። ይህን ቡድን የሚያሽከረክረው የማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ኦፍ ትግራይ ፍጹም ማርክሲስት አይደለም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ትግሬዎችን ነፃ ሊያወጣ የተነሳ ድርጅት አልነበረም። በርግጥ ስሙ፤ ከትግራይ ብሔራዊ ድርጅት፤ በብዙ መንገዶችና ስሞች አልፎ ( ንቅናቄ፣ ግንባር ) አሁን ወደ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ተሸጋግሯል። መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ ነውና፤ የዚህ ድርጅት የተለያዩ ስሞች፤ ጊዜያዊ ፍላጎቱን ለማሟላት መጠቀሚያ መገልገያዎች እንጂ፤ የእውነተኛ ተግባሩና ግቡ ገለጮች ስላልነበሩ፤ መለዋወጣቸው፤ ለመሪዎቹም ሆነ ለአባላቱ፤ ግድ አልሠጣቸውም።
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ባለቤቶች፤ ሕልውናቸው በጦርነት የታናጸና አሁንም “በጦርነት ላይ ያለን ነን!” ብለው የሚያምኑ ግለሰቦች ናቸው። ለዚህ መሠረቱ፤ ራሳቸውን የውጭ አድርገው መመልከታቸው ነው። ጠላት ብለው አማራውን፣ ኦሮሞውን፣ ኦጋዴኑን፣ አኙዋኩን፣ ደቡቡን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሒዶ ቤተክርስቲያንን፣ ደርግን፣ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ግለሰብና ድርጅትን ፈረጁ። በዚህ ስሌት፤ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ “ጠላት!” ተብሎ ተፈረጀበት ማለት ነው። የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ያዘዛቸውን ስላላደረጉ ጠላት ተባሉ። እናም ከ “ሌሎች” ተመደቡ። ምን ጊዜም ቢሆን “ሕዝቡ የኛ አይደለም፤ እኛም የሕዝቡ አይደልንም።” የሚል እምነት ስላላቸው፤ ዛሬ ወይንም ነገ ሕዝቡ ይነሳብናል የሚል ፍራቻ አላቸው። እናም እነሱ “የኛ” ብለው ከሰበሰቡት ውጪ ያለ ግለሰብ፣ ጋዜጠኛ ሆነ ሰላማዊ ሰልፈኛ፤ መምህር ሆነች እርጉዝ ሴት፣ ድርጅትም ሆነ ሌላ ስብስብ፤ “አጥፊያችን ስለሆኑ እናጥፋቸው!” የሚል ነው አመለካከታቸው። እናም ለማንኛውም የፖለቲካ ክስተት፤ መልሳቸው ያኔ በበረሃ በነበሩበት ወቅት ይሠጡት የነበረው መልስ ነው፤ “በለው!”፣ “አባረው!”፣ “እሰረው!”፣ “ግደለው!”። ይህ አጠቃላይ መገለጫው የሆነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የማንነቱ መግለጫ ነው። እስኪ የዚህን ድርጅት የሕይወት ጉዞና የሂደት ደረጃዎቹን እንመልከት። በዕድገቱ ያሳያቸው አራት የዕድገት ሂደት ደረጃዎች አሉ። አሁን አራተኛውን የሂደት ደረጃ በማጠናቀቅ ላይ ነው።
፩ኛ. ፍርሃት
ይህ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የመጀመሪያ የዕድገት ደረጃው፤ ከተነሳበት፤ ትግራይን ገንጥሎ የራሱ የሆነ መንግሥት ማቋቋም ከሚለው መርኁ ወጥቶ፤ ኢትዮጵያን ለማጠቃለል ያደረገው ጉዞና፤ ሥልጣኑን በጁ የያዘበት ወቅት ነበር። በዚህ ሂደቱ፤ ለተለመው ሁሉ ዕቅድ፤ መነሻው ፍርሃት ነበር። በትግራይ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀበለን ወይ? በትግራይ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኔ የበለጠ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓን) ይደግፍ ይሆን ወይ? በትግራይ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባርን (ጠርናፊትን) ከኔ ይልቅ ይቀበል ይሆን ወይ? በትግራይ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረትን (ኢዲዩን) ይደግፍ ይሆን ወይ? የሚሉት የመጀመሪያዎቹ እንቅልፍ ነሺ ፍርሃቱ ነበሩ። በነዚህ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ፍርሃት እንዲኖረው አስተዋፅዖ ያደረገው፤ በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች በአመራርና በአባልነት በዝተው መገኘታቸው ነበር።
ታዲያ ለነዚህ ድርጅቶች ሕልውና የነበረው መልስ፤ በግልጽ እንደታየው፤ በድርጅቶቹ ላይ ጦርነት መክፈት ነበር። በዚህ ሂደቱ፤ ስሞቹን ቀያይሯል። ግቦቹንም ለዋውጧል። ከውጪ ብቻ ሳይሆን፤ በድርጅቱ ውስጥ፤ ድርጅቱ የነበረውን ዓላማና ግብ አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረቡትን ፈጅቷል። ፈጅቶም አልቀረ፤ ጊዜያዊ ሂደቱን ይረዱት ዘንድ፤ ግቦቹን ለዋውጧል። በዚህ ደረጃው ያደረጋቸው ጦርነቶች፤ በትግራይ ከሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት አንጻር ጠላት ከሆነው ከደርግ ጋር ሳይሆን፤ በትግራይ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከደርግ ለማዳን ከተነሱ ድርጅቶች ጋር ነበር። በተጨማሪም፤ በዚህ ድርጅት ውስጥ አሽከርካሪ የሆኑት ግለሰቦች፤ የማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ኦፍ ትግራይን መሠረቱ። ይህ ፍጹም የማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅት አይደለም።
በመጀመሪያ የብሔር ጥያቄ፤ ለማርክሲስት ሌኒኒስቶች፤ ለዋናው የዓለም አቀፍ የላብ አደሩ አምባገነንነት መሸጋገሪያ፤ የፖለቲካ መሣሪያ ነው። የብሔር ጥያቄ የአርሶ አደሩ ጥያቄ አይደለም። የብሔር ጥያቄ የላበደሩ ጥያቄ አይደለም። ይህ በትግራይ ለሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ የተለየ ሳይሆን፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የሚናገር ሀቅ ነው። የብሔር ጥያቄ፤ “የኔን ወገን ለብቻዬ ልግዛው!” ባዩ የብሔርተኛ ከበርቴው መደብ ጥያቄ ነው። በዚህ የከበርቴ መደብ ዙርያ፤ ሥልጣን ናፋቂ ምሁራን ይኮለኮሉበታል። የብሔር ጉዳይን አስመልክቶ በማዘጋጀት ላይ ያለሁት መጽሐፍ ስላለ ሲወጣ ትንታኔውን ማየት ይቻላል፤ ለአሁኑ ግን በዚሁ ልለፈው። ይህ የማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ኦፍ ትግራይ፤ የብሔራዊ ከበርቴውን የብቻ ሩጫ ለመግታት ያደረገው ጊዜያው የትግል ስልቱ ሳይሆን፤ ከሌሎች ታጋይ ኤትዮጵያዊ ድርጅቶች ለይቶ፤ በትግራይ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብቻው ለመገንጠልና ለመግዛት ያራመደው ግቡ ነበር። እዚህ ላይ ላሰምር የምፈልገው፤ የብሔርን ጥያቄ የማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ኦፍ ትግራይ ሲያራምድ፤ ስልት አድርጎ ሳይሆን ግብ አድርጎ የያዘው እንደሆነ ማሳየቴን ነው። ይህ ደግሞ ከመሠረታዊ የማርክሲስት ሌኒኒስት እምነት ጋር የሰማይና መሬት ያህል ርቀት አለው። በዚህ ስሌት፤ የማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ኦፍ ትግራይን፤ በመርኅ የሚመራ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን፤ የአድማ ጠንሳሾች ወሮበላ ቡድን ነው ማለት ይቻላል።
ከላይ የተጠቀሱትን ድርጅቶች ካወጋ በኋላ፤ በትግራይ በሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያለውን ፍራቻውን በአእምሮው ጀርባ ሸጉጦ፤ አጋጣሚው በር ስለተከፈተለት፤ ወደፊት ሄጄ ሥልጣን ብነጥቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያደርገኛል? የሚለው ፍራቻው ዋናውን ቦታ ያዘ። እናም ለዚህ መፍትሔ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማጭበርበር፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን)፤ የሚል ተቀጥላ ድርጅት አቋቋመ። አከታትሎም የኦሮሞ ድርጅት መሠረተ። እንግዲህ እኒህ ድርጅቶች ምን ዓይነት አባላት ነበሯቸው? ምንስ ዓይነት አመራር ነበሯቸው? ነፃነትና የውስጥ አሠራርስ ነበሯቸው ወይ? ብሎ የሚጠይቅ ያለ አይመስለኝም፤ ግልጽ ነው። ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናላ! እንግዲህ በዚህ ወቅት የነበረው ፍራቻ፤ ለሂደቱ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን እንዲያተገብር አስገደዱት። ድርቅን ተጠቅሞ የትግራይ ወገናችንን ለሞት በሚዳርግ ሂደት አስገብቶ፤ ድርጅቱንና መሪ ግለሰቦችን በሚጠቅም መንገድ መሣሪያና ገንዘብ ሰበሰበበት። ለፖለቲካ ግቡ ያመቸው ዘንድ፤ የትግራይ ወገናችንን በገበያ አስደበደበው።
ቀጥሎም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሚል ጋቢ በላዩ ላይ ደርቦ አሸሸ ገዳሜ ማለቱን ያዘ። ደርጋማ የሆነው የአረመኔው የመንግሥቱ ኃይለማርያም አምባገነን ቡድን በሩን ብው አድርጎ ስለከፈተለት፤ ይኼን አጋጣሚ ተጠቅሞ፤ ሕዝቡ በያለበት ባለ አቅሙ ቢታገልም፤ ሰተት ብሎ አዲስ አበባ ገባ። በዚህ ወቅት የነበረው ፍራቻ፤ ደርግ ያንሰራራብኝ ይሆን ወይ? ኢሕአፓ ተመልሶ ያድግ ይሆን ወይ? ሕዝቡ ባይቀበለኝስ? አማራው ምን ያደርገኝ ይሆን? የዓለም መንግሥታት ባያውቁኝስ? የሚሉት ነበሩ። ለዚህ መልስ ያደረገው፤ ካድሬዎቹን በየመንግሥታቱ መናገሻ ከተማ እየሄዱ እግር እንዲነሱ፤ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን አቅፎና ሸዓቢያን ተደግፎ፤ መንግሥት እመሠርታለሁ እያለ ማባበል ነበር። ኢሕአፓ ከገባበት ገብቶ እንዳያንሰራራ ድምጥማጡን ማጥፋት ነበር። አማራውን ደግሞ በሁለት መንገድ ማጥቃት ያዘ። ባንድ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) በሚል ሻማ የጎለተውን የስም ድርጅት፤ ወደ የብሔራዊ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሚል የለውጥ ቀለም በማሽቆጥቆጥ፤ ከአማራ አለመወለድ ብቻ ሳይሆን፤ ፍጹም ዝምድና የሌላቸውንና አማራን በጠላትነት የፈረጁ የራሱ ሰዎችን ሰባስቦ በአመራር ላይ በማስቀመጥ፤ የይስሙላ ድርጅት ፈጥሮ መምታት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ በመላ ኢትዮጵያ በሚኖረው አማራ ላይ በቀጥታ፤ በኑሮውና በመኖሪያው ላይ በተዘዋዋሪ በመዝመት፤ ሕልውናውን ማሣጣት ነበር። በሁሉም በኩል መተንፈሻ በሚያገኝበት ደረጃ ተሳካለት። ይህ የመጀመሪያው የዕድገት ሂደቱ ደረጃ ነበር።
፪ኛ. መደላደል
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ከላይ በቁጥር አንድ የተዘረዘረውን በተግባር ካዋለ በኋላ፤ ፍርሃቱን እንደተሸከመ ወደ መደላደሉ ተሸጋገረ። ምን ጊዜም ቢሆን ከላይ የተዘረዘረው እስከ ዘለቄታው የማይለቀው ፍርሃት መሆኑን ልብ ማለት አለብን። በዚህ በሁለተኛው የዕድገት ደረጃ ላይ፤ የመጀመርያ ተግባሩ፤ የሚፈልገውን የመደላደያ ሕገ መንግሥት ማጽደቅ ነበር። በዚህም ላይ የሀገሪቱን አስተዳደር በሚፈልገው መንገድ አዋቀረ። በየቦታው የራሱን ሰዎች መደበ። የይስሙላ ምርጫዎችን አዘጋጀ። የመጀመሪያውን ፍራቻውን ለመቋቋም የተጠቀመበትን የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን አረመኔያዊ በሆነ መንገድ አሰናበተ።
ከደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል አማራ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን፤ በቀጥታ ራሱ ድርጅቱ በማዘዝም ሆነ በመሳተፍ አፈናቀለ፣ ሀብታቸውን ዘረፈ፣ ገደል። አሽከር የሚሆኑትን የሹመት ካባ በማከናነብ፤ የድርጊቱ ወራሽ አደረጋቸው። በአኝዋኮች ላይ፣ በኦጋዴኖች ላይ፣ በኦሮሞዎች ላይ ዘመተ። እኒህ ተግባራቱ፤ ለመደላደል ያመቹኛል ብሎ የወሰዳቸው ነበሩ። ተደጋጋሚ የይስሙላ ምርጫዎችን አካሄደ። ጠንካራ ተቃዋሚዎች ይሆናሉ ያላቸውን፤ እንደ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ያሉትን ገደለ። መጀመሪያ ያዋቀራቸውን አስተዳደራዊ ግዛቶች በወዘ። አላደረግኩም እያለ የማለ የተገዘተበትን በግልጽ አደረገው። ወልቃይትን፣ ጠለምትን፣ የጠገዴን ግማሽ አካልና በወሎ ደግሞ ሁለት ወረዳዎችን ወደ ትግራይ ጠቀለለ። እዚህ ላይ ሁለት ወፍ በአንድ ደንጋይ እንዲሉ፤ አማራውን አሳነሰ፤ የራሱ የሚለውን የትግራይ ክልል በለሙ የአማራው ክልል መሬት አሰፋ። ለይስሙላ ያሳየውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል እንዳልነበር አደረገ። በዚህ የመደላደል ወቅቱን አጠናቀቀ።
፫ኛ. እብሪት
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ አንደኛና ሁለተኛውን የዕድገት ደረጃዎቹን ካጠናቀቀ በኋላ፤ ቀንደኛውን ተቃዋሚ አጠፋሁ ብሎ ደረቱን ነፋ። አሁን በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ክንፉን ዘረጋ። ልቡን አሳበጠ። ለወደፊቱ ሊነሱ ይችላሉ የሚላቸውን በእብሪት አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት፤ ሌላ ተቃዋሚ እንዳይነሳበት፤ ከግር ከግሩ መንቀል ያዘ። በአኳያው ደግሞ፤ በትግራይ ክፍለ ሀገር ሙሉ ለሙሉ ቁጥጥር በማድረግ፤ ሕዝቡ ያለሱ ሌላ አማራጭ እንዳያስብና እንዳይኖረው፤ የሚችለውን አደረገ። ሕዝቡን ወርቅ ነህ አለው። ታሪክህ ከሁሉ ይበልጣል አለው። አንተ የተለየህ ነህ አለው። ከጎንደርና ከወሎ ለም መሬት ነጥቆ የወሰደውን ከትግራይ ሰው ወስዶ አሰፈረበት። ይህ ሁሉ ጥረት፤ በትግራይ ያለው ኢትዮጵያዊ፤ የሱ ዋና ደጋፊ በመሆን እንዲያገለግለው ነበር።
ከመደላደሉ ወጥቶ፤ ከውጭ ሀገር ሊመጣ የሚችልበትን ጫና፤ ከኔ የተሻለ አታገኙም በሚል እብሪት፤ ተቋቋሚ ለመሆን ዛተ። ይህ ግን እነሱ የሚፈልጉትን በሙሉ በተግባር እያዋለ፤ የሀገራችንን ክብር ለነሱ በመገበር ነበር። ለሙን የሀገራችንን የእርሻ መሬት በኪሱ ለሚያስገባው ልቃሚና፤ ለወደፊቱ ሀገራችን እንድትስቃይ በሚዳርግ ርካሽ የብዝበዝ የእርሻ ዘዴ ቸበቸበው። ለዚህ ማስተማመኛ እንዲሆነው፤ የተጠናከረ ተቃዋሚ እንዳያድግ ከሥር ከሥሩ መምታቱን የዕለት ተዕለት ሥራው አደረገው።
በሀገር ውስጥ ምንም ዓይነት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ያልፈቀደው እንቅስቃሴ እንዳይኖር በሩን ሁሉ ጥርቅም አደርጎ ዘጋ። ሕዝቡ ምንም ዓይነት ዜና እንዳያገኝ፤ የውጭ ሀገር የስልክና የድረገጽ አገልግሎት በሀገር ውስጥ በመገደብ፤ ሀገራችን በነዚህ አገልግሎት ከዓለም የመጨረሻውን ወለል እንድትይዝ አደረገ። ባሁኑ የዓለም የሥልጣኔ ደረጃ፤ ከዓለም በስልክና በኢንተርኔት አገልግሎት የመጨረሻውን ወለል መታቀፍ፤ በሀገር ያለውን መንግሥት ምንነት ገላጭ ነው። በእብሪት የማይደረግ የለም። በተጨማሪም የሀገራችንን ጥሬ ቁጥብ ሀብት በማናለብኝነት በመዝረፍ፤ ሕንጻዎችን ጀኔራሎች፤ የንግድ ባለቤትነቱን ሚኒስትሮች፤ ፈላጭ ቆራጭ አዛዥነቱን የድርጅቱ ካድሬዎች፤ የኪሳቸው ንብረት አደረጉት። ድርጅቱ የሀገሪቱን ታሪክ ማጥፋትና ማንኛውንም ግለሰብ በራሱ ምስል መቅረጽ ያዘ። መጽሐፍት በሙሉ እሱ የሚለውን ብቻ ማስፈር ያዙ። የራሱ ምሁራን የትምህርት መስኩን አጠቃለው ያዙ። በማንኛውም መንገድ ሀብታሞችና አዛዦች የድርጅቱ ቅምጥሎች ብቻ እንዲሆኑ ተደረገ። ሕዝቡ በረሃብ፣ በጥማት፣ በመብት እጦት ዳሸቀ። የእብሪተኛ መጥፎ ገጹ ግን፤ ቀጥሎ የሚመጣውን ማገናዘብ አለመቻሉ ነው። ይህ እብሪቱ ከ “ጠላት!” ብሎ ከመደባቸው፤ እስከ “የኔ!” ያላቸው ክፍሎች ድረስ በመጎንተሉ፤ ጠላቶቹ እየበዙ ብቻውን የቀረበት ሀቅ ከተፍ እንዲል አደረገበት።
፬ኛ. ቁልቁል
አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት ብሎ ወደ መጨረሻው የዕድገቱ ደረጃ በመጓዝ ላይ ያለው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሕይወት፤ አራተኛውን ደረጃ የያዘው፤ ድርጅቱ ሳያውቀው፣ ሳይዘጋጅለትና ሳያቅደው ነው። ጉዱ ደግሞ፤ ይህ ዕድገት ሊከተል የቻለው፤ ራሱ ባስቀመጠው የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ ተመሥርቶ ነው። በርግጥ በዕለት ተዕለት ኑሮው ላይ ብቻ ያተኮረ አካል፤ የረጅም ዘመን ጥርቅም ሂደት የሚያስከትለውን ውጤት ከሩቅ መገንዘብ አይችልም። የሆነውም ይኼው ነው። ሥልጣን ይዞ፣ ተደላድሎ፣ እብሪት ጎጥሮት ከሰነበተ በኋላ፤ ሌላ ሰውነት ያዘ። የነበረበት፣ የታገለለት፣ መሠረታዊ የሆነው ዓላማው ግቡን መታ ብሎ፤ የአመራሩ አባላትና በጉያቸው የሸጎጧቸው የቤተሰብ ጥርቃሚዎቻቸው፤ ከስብስብ አንድነት ይልቅ፤ ባሁን ሰዓት የየግል ሕልውናቸው የበላይነቱን ወስደ። እስከዛሬ ሙጫ ሆኖ አንዳቸውን ከሌላቸው አጣብቆ የያዛቸው የ “ሌሎች” ፍርሃት፤ እየደበዘዘ ሄደና፤ መደላደሉ እብሪትን አስከትሎ፤ እስካሁን ያቆየንን እስከዘለዓለሙ እየተገበርን እንቀጥላልን የሚለው፤ ወደ ግል ሕይወታቸው አስተሳሰባቸውን እንዲያቀኑ አደረጋቸው። ፍርሃቱ ሲጠፋ፤ የመተባበሩ ፍላጎት ደበዘዘ። እናም ሀብት ተሯሩጦ ለግል መሰብሰቡ ደራ። ካሁን በኋላ ቁልቁል መሄድ እንጂ ጣራውን አልፎ ሌላ ጣራ ማበጀት አይቻልም። ጣራውን ደረሱበት። ከንግዲህ ወደ ታች ብቻ ነው ቀሪው ሕይወታቸው።
መደምደሚያ፤
ከመጀመሪያው ተቆራኝቶት የነበረው ፍርሃቱ መታገስ በያዘበት ደረጃ፤ እንደጋሪ ፈረስ ዓይኖቹ በመደላደሉ ደልበው፤ በእብሪቱ ተጋርዶ፤ ባሁኑ ሰዓት ሳያውቀው በዙሪያው ያለው ሂደት ከቁጥጥሩ ውጪ ሆነ። ዙሪያው ሲገለባበጥ፤ መደናበር ያዘ። እናም የታገሰለት ፍርሃት ዓይሎ አጎደረበት። ቀንድ ሆኖ ከራሱ ላይ ተጫነው። መደላደሉና እብሪቱ ከፍርሃቱ ጋር ተደማምረው የበለጠ አደናበሩት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተብትቦ ከያዘው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ስንሰለት ራሱን እያላቀቀ መጣ። እስከዛሬ የሰማው፣ የተቀበለው፣ የቆመለት ሁሉ ለራሱ ለሕዝቡ ሕይወት ሳይሆን፤ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መተንፈሻ ሳምባ መሆኑን ተረዳ። ፖለቲካው ትርጉም፤ ኑሮው ጣዕም አጣ። እናም፤ “የለም አንድ ነን!” “ባንድነት እንነሳ!” አለ። “ኢትዮጵያ አንድ ናት! አትከፋፍሉን! ጠላታችን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብቻ ነው!” አለና ተነሳ። ካሁን በኋላ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አውሬነቱ ብቻ ነው የቀረው። ይገድላል። ሰው ይበላል። አይመርጥም። ለኛ ለውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ያለን መንገድ፤ በአንድነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መሰለፍ ነው። መሰባሰቢያችን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት መቀበል፣ የኢትዮጵያ ሀገራችንን ዳር ደንበርና ለም መሬት ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ማለት፣ የሕግን የበላይነት መቀበል፣ እና የያንዳንዱ/ዷን ኢትዮጵያዊ(ት) የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብት ተቀብለን፤ እያንዳንዳችን በኢትዮጵያዊነታችን የምንሳተፍበት የፖለቲካ ምኅዳር እንዲኖር መጣር ነው። እንበርታና ተግባራዊ እንሁን። ኢትዮጵያዊያን እናቸንፋለን።
ቅዳሜ፤ የካቲት ፳ ፩ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት (02/28/2015)
ተጨማሪ ጽሁፎችን በአቶ አንዱ ዓለም ተፈራ ብሎግ ላይ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
yagersew says
አንተ እና መሰሎችህ የት ናችሁ? looosersssss!
yagersew says
So why do you think they are successful..? is it not because your kind are loosers! why do they succeed these long? why do they win all? why not all others? ትክክለኛ መስመር ሁሌም ያሸንፋል!!! check back all who tried to catch up power and loose..pls start from ኢህአፓ and to semayawi..they all loose except Tplf/Eprdf.