• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የምርጫ 2007 10ቱ ቃላት

January 8, 2015 03:34 am by Editor Leave a Comment

የዚህ ጽሑፍ ግብ በምርጫ 2007 ቁም ነገር መስራት የሚፈልግ የምርጫ ፓርቲ ማድረግ ከሚገቡት ሌሎች እጅግ በርካታ ዝግጅቶች በተጨማሪ ከግንዛቤ ሊያስገባቸው የሚገቡ 10 ነጥቦች መዘርዘር ነው። ምርጫው ነፃ እና ፍትሃዊ ካልሆነ ከምርጫ መወጣት (ቦይኮት ማድረግ) ጠቃሚ ነው ለሚሉ ወገኖችም መልስ ይሰጣል ይኽ ጽሑፍ። መልካም ንባብ።

(1) መንግስት በስልጣን መኖር የሚችለው፥

(ሀ) ህጋዊነት የሚለግሰው ህዝብ ሲኖር፣

(ለ) ህዝብ የሙያ ትብብር ሲለግስ፣

(ሐ) ህዝብ የግብር ክፍያ ትብብር ሲያደርግ፣

(መ) የመንግስትን የአገር ተፈጥሮ ሃብት እና አገራዊ ኢኮኖሚ ባለቤትነት ህዝብ እሺ ሲል ብቻ ነው።

እነዚህን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ህዝብ አሳልፎ ለገዢው ቡድን አሳልፎ የሰጠው በፍራቻ ወይንም በፈቃደኛነት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ የእነዚህ የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ባለቤት ህዝብ ነው።፡ ስለዚህ ነው የመንግስት ስልጣን ምንጭ ህዝብ ነው የሚባለው። ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ነው የሚባለውም ስለዚህ ነው። ስለዚህ የመንግስት ስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ የመንግስት ስልጣን ለመለገስ የተሳተፈባቸው ምርጫዎች ህገወጥ ሊሆኑ አይችሉም። ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች የመንግስት ስልጣን ባለቤት ባለመሆናቸው እራሳቸውን ከምርጫው በማግለል ምርጫውን ህገወጥ አደረግን ማለት አይችሉም። ህዝብ እስከተሳተፈ ምርጫው ህጋዊ ነው። አብላጫ ድምጽ ያገኘውም ፓርቲ ህጋዊ አሸናፊ ፓርቲ ነው። የተባበሩት መንግስታትም ሆነ የምዕራቡ ዓለም መስፈርት የሚለው ይኽንኑ ነው። (ስድስቱ የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ሰላማዊ ትግል 101 በሚል ስያሜ በቅርብ ገበያ ላይ በዋለችው መጽሐፍ ውስጥ በሰፊው ቀርቧል።)

(2) በምርጫ በስልጣን ላይ ያለን መንግስት ህጋዊነት ማሳጣት የሚቻለው የመንግስት ስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ እራሱን ከምርጫ ሲያገል ብቻ ነው። አንድ ህዝብ በምርጫ አልሳተፍም ካለ ምርጫ የለም። አሸናፊ ፓርቲ የሚባልም ነገር የለም። ስለዚህ ህዝብ ከሚሳተፍበት ምርጫ እራሳቸውን ብቻ በማግለል (ቦይኮት በማድረግ) ምርጫውን ወይንም  አሸነፈ የሚባለውን ፓርቲ ህጋዊነት እናሳጣዋለን ብለው የሚያስቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካሉ የአስተሳሰብ ዝንፈት ወይንም ጨቅላነት አለባቸው። ህዝብን ሊተኩ ወይንም እራሳቸውን ከህዝብ በላይ አድርገዋል ማለት ነው። አምባገነንነትም በልጅነቱ ይኽንኑ ነው የሚመስለው።

(3) ዴሞክራሲ በሰረጸባቸው እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ አይነት አገሮች ውስጥ ምርጫ ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት መሆኑ ማረጋገጫ መንገድ ነው። በእነዚህ አገሮች ምርጫ ቦርዱም ሆነ የህዝብ ታዛቢዎች (የምርጫ አስፈጻሚዎች) ገለለተኛ በመሆናቸው የመራጩ ህዝብ ድምጽ ይሰረቃል የሚል ስጋት የለም። የምርጫ ፓርቲዎች ድምጽ ለማስከበር በሚል የሚያደርጉት ስትራተጂያዊ ዝግጅት አይኖርም።

(4) ዴሞክራሲ በሰረጸባቸው እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ አይነት አገሮች ውስጥ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝባቸው እንዲመርጣቸው ስለሚጠይቁ ፓርቲዎቹ የመንግስት ስልጣን ባለቤት አለመሆናቸውንም ማረጋገጫ ነው ምርጫ። ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት በመሆኑ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ የፈለገውን ይቀጥራል (ይመርጣል)። ያልፈለገውን አይመርጥም (አይቀጥርም)። በእነዚህ አገሮች ከሞላ ጎደል ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ይደረጋል። ስለዚህ በእነዚህ አገሮች ምርጫ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው።

(5) ዴሞክራስ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ ምርጫ የህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤትነት ማምጫ መንገድ ነው። በእነዚህ አገሮች ፥

(ሀ) ሶስቱ የመንግስት ዘርፎች የተነጣጠሉ ባለመሆናቸው፣

(ለ) የኢትዮጵያ ህገ መንግስት እንባ ጠባቂ ብሎ ያሚጠራው ተቋም ነፃ ባለመሆኑ፣

(ሐ) በዘልማድ አራተኛው የመንግስት ዘርፍ ተብሎ የሚጠራው ነፃ ፕሬስ እንደልቡ በነጻነት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ፣

(መ) በመንግስት እና በፓርቲ መካከል ሊኖር የሚገባው ቀጭን ቀይ መስመር ባለመኖሩ፣

(ረ) ምርጫ ቦርዱም ሆነ የህዝብ ታዛቢዎች (የምርጫ አስፈጻሚዎች) ገለለተኛ ባለመሆናቸው ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ የደረጋል ብሎ ማሰብ ላም ባልዋለበት ኩበት መልቀም ይቻላል ብሎ እንደማመን ነው።

በእነዚህ አገሮች ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ይደረግ የሚለው ጥያቄ የሚቀርበው እንደ መታገያ አሳብ መሆኑ ታውቆ የምርጫ ፓርቲዎች ከምርጫ ሳይወጡ ህዝባቸውን የመንግስት ስልጣን ባለቤት ለማድረግ ማለትም ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር የጀመሩትን ጉዙ መቀጠል አለባቸው። ስለዚህ ነው በእነዚህ አገሮች በሚደረግ ምርጫ የምርጫ ስትራተጂ ሲቀየት የህዝብ ድምጽ እንዳይሰረቅ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት በስትራተጂ ውስጥ የሚካተተው።

(6) ዴሞክራሲ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ በሚደረግ ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ካልተደረገ በሚል ምክንያት ከምርጫ መውጣት ለኢህአዴግ (ገዢው ፓርቲ) ጭንቀት መቀነስ ብቻ ሳይሆን ደስታን መለገስ ነው። ባቄላ አለቀ ቢባል ፈስ ቀለለ እንደሚባለው ነው የሚሆንለት ለኢህአዴግ (ገዢው ፓርቲ)። ምክንያቱም የመንግስት ስልጣን ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ እስከተሳተፈ ድረስ ምርጫው ህጋዊ ነው። ያሸነፈውም ፓርቲ ወዲያው አለም አቀፍ እውቅናን ያገኛል። የገንዘብ እና የቁሳቁስ እርዳታም ይቀጥላል። ይኼን ሃቅ ቀደም ብለው በኢትዮጵያ የተደረጉት አራት አገር አቀፍ ምርጫዎች አስተምረውናል።

(7) ዴሞክራሲ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ በሚደረግ ምርጫ በመሳተፍ የህዝብን ድምጽ ማግኘት ግን ለኢህአዴግ (ገዢው ፓርቲ) መከራ እና ጭንቀትን ይፈጥራል። ይኽን ሃቅ በምርጫ 97 ያስተዋልነው ነው። ሽንፈትን አልቀበልም ካለ ድምጽ ይከበር የሚል እንቅስቃሴ ሊፈጠር ይችላል። ይኽንንም ሃቅ በምርጫ 97 አይተናል። አንዴ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከጀመረ ከዚያ ወዴት እንደሚሄድ መገመት አዳጋች ነው። ስለዚህ የምርጫ ፓርቲዎች ለዚህ አይነት አጋጣሚም ቀደም ብለው መዘጋጀት ይበጃቸዋል። አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ጠብቂ በሚለው መመራት ጠቃሚ ነው።

(8) ዴሞክራሲ ባልሰረጸባቸው አገሮች ህዝብ ድምጽ የመሰረቅ እድሉ ከፍተኛ ነው። በሰላማዊ ትግል የህዝብ ነፃ አውጭ እራሱ ህዝቡ መሆኑ ታውቆ የምርጫ ፓርቲዎች እምነታቸው በውጭ አገር ድጋፍ ወይንም በምርጫ ቦርድ ሳይሆን በህዝብ ላይ መሆን አለበት። ስለዚህ የምርጫ ፓርቲዎች ህዝብ ድምጹን እንዳይሰረቅ ማድረግ እንዲችል ማሰልጠን እና ማደራጀት አለባቸው። የምርጫ ፓርቲዎች ማድረግ ከሚገቧቸው ስራዎች ውስጥ ጥቂቱ የሚከተሉትን ያካትታል፥

(ሀ) በህዝብ ታዛቢዎች ላይ ገለልተኛ እንዲሆኑ ጫና በማሳደረ፣

(ለ) ለምርጫ እድሜው የደረሰ በሙሉ ለምርጫ እንዲመዘገብ እና የምርጫ ካርድ እንዲወስድ በማድረግ፣

(ሐ) ህዝቡ የምርጫ ካርዱን የሚቀጥሉት አምስት አመቶች በአገሩ አቅጣጫ ላይ ውስኔ መስጫው መብቱ መተግበሪያ አድርጎ እንዲያምን በማድረግ፣

(መ) በምርጫ እለት የምርጫ ካርድ የወሰደ መራጭ በሙሉ በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ በማሳመን፣

(ሠ) በምርጫው ዕለት በድስፕሊን የታነጹ እና በምርጫ ህግ የሰለጠኑ የእምነት ጽናት ያላቸው የእጩ ታዛቢዎች በየምርጫ ጣቢያው በማሰማራት ታህሳስ 12/2007 ተመረጡ የተባሉት የህዝብ ታዛቢዎች በእድሜ የገፋውን መራጭ ህዝብ ሳያደናግሩ የምርጫ ካርዶችን እና የምርጫ ኮሮጆዎችን በገለልተኛነት እንዲያስተናግዱ በመከታተል፣

(ረ) እጩዎች ህዝቡ እንዲመርጣቸው የሚያደርጉ መልዕክቶች፣ የትምህርት ደረጃ፣ ማራኪ ባህሪ፣ ተወዳጅነትም እንዲኖራቸው በማድረ (ማሰልጠን ይቻላል)፣

(ሰ) ገዢው ፓርቲ ከሽንፈት ማምለጫ መከራከሪያ እንዳይኖረው እና ሽንፈትን  ሳያንገራግር እንዲቀበል ለማድረግ ይቻል ዘንድ በሚሸነፍባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እና የምርጫ ክልል ወረዳዎች ሽንፈቱ በከፍተኛ ድምጽ (landslide) እንዲሆን ማድረግ

(ሸ) የምርጫ ጣቢያዎች ሲዘጉ ድምጽ ተቆጥሮ አሸናፊ እስኪታወቅ መራጩ ህዝብ ከየምርጫ ጣቢያዎች ርቆ እንዳይሄድ ማድረግ።

የህዝብ ድምጽ ከተሰረቀ መራጩ ህዝብ ድምጼን ካላከበርክ እኔም የአንተን ገዢነት አላከብርም የሚል እንቅስቃሴ ሊጀምር ይችላል። ስለዚህ በእነዚህ አገሮች የሚደረግ ምርጫ በአግባቡ ከተያዘ እና ከተመራ የህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤትነት ማምጫ መንገድ ነው። ዴሞክራሲን ማምጫ ነው።

(9) ዴሞክራሲ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ የሚደረግ ጠብመንጃ-መር ትግል (ለምሳሌ፥ ትጥቅ ትግል፣ የከተማ ግድያ፣ ሽብር፣ በፕላን ያልተመራ ሰላማዊ አመጽ፣ ወ.ዘ.ተ. ) አምባገነን ማምጫ ነው።

ግርማ ሞገስ
ግርማ ሞገስ

(10) ዴሞክራሲ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ በሚደረግ ምርጫ የምርጫ ፓርቲዎች በተካሄደው ምርጫ የተገኙ ፖለቲካዊ እና ድርጅታዊ ድሎችን መልቀም የሚያስችሉ ዝግጅቶች ቀደም ብለው ማድረግ አለባቸው። ይኽን ለማድረግ በቅድመ-ምርጫ ዝግጅት፣ በምርጫ እለት እና ከምርጫ ማግስት ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን (Scenarios) ቀደም ብለው መተንተን እና ቀዳዳዎችን መድፈን የሚያስችሉዋቸው ዝግጅቶች ማድረግ አለባቸው። በምርጫ 2007 የተገኙ ድሎች እንደ ምርጫ 1997 መባከን  የለባቸውም። ገዢውን ፓርቲ ሊያስበረግጉ እና ሊያስቆጡ ከሚችሉ ድንፋታዎች፣ ዛቻዎች፣ ፉከራዎች፣ ትንኮሳዎች፣ መፈጸም የለባቸውም ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች። ገዢው ፓርቲ ሽንፈት በደረሱበት አካባቢዎች ሽንፈትን የጀግኖች ሽንፈት አድርጎ መቀበል የተሻለ አማራጭ አድርጎ እንዲዎስድ ማበረታታት ያስፈልጋል።

girmamoges1@gmail.com

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

Recent Posts

  • በፋኖ ስም ከአማራ ገበሬና ከዳያስፖራ የሚሰበሰበው በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የጥቂት አመራሮች መበልጸጊያ ሆኗል November 20, 2026 08:54 am
  • የቴሌኮም ጌትዌይ፣ የዳታ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደህንነት – የዌብስፕሪክስ ጉዳይ ከባለቤትነት ክርክር በላይ ነው! November 17, 2026 11:54 pm
  • “የጫካ ቱጃሮች!”— የፋኖ አመራሮች ስለተሰማሩበት የገንዘብ ዝርፊያ አስደንጋጭ መረጃ November 17, 2026 05:43 pm
  • በየወሩ 4 ሚሊዮን ብር እየተከፈለው ሀገር ሲያፈርስ የነበረው ሪፖርተር November 16, 2026 01:17 am
  • ሻርኮቹ ከውጭ እስከ ሀገር ውስጥ ያደሩት ድር፣ ዌብስፕሪክስን (WebSprix) የመጠቅለሉ ድራማና ብሔራዊ ስጋት November 14, 2026 12:42 am
  • የመለስ ዜናዊን ጭንብል የገፈፈው የትህነግ ሚዲያ (EMF) ምስክርነት November 13, 2026 03:32 pm
  • ትህነግ በወታደራዊና በፖለቲካዊ መስክ እንደሞተ ሁሉ በሪፖርተር በኩል የሚዲያ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል November 13, 2026 01:13 am
  • በከባድ ታክስ ማጭበርበር የሚፈለጉት አቶ አበባው ደስታ፣ አማራጭ የቴሌኮም ጌትዌይ ፕሮጀክትን ሊጠቀልሉ ነው November 12, 2026 03:50 am
  • “ፋኖ ወደ ኦሮሚያ ገብቶ ሕዝብ እየገደለ ነው” የኦነግ ሸኔ (OLF/OLA) ተወካይ ጃል ጅረኛ November 10, 2026 05:12 pm
  • ከትህነግ የተማረኩና ከውጭ ሀገራት የገቡ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች በቃሊቲ ለእይታ ቀረቡ November 6, 2026 03:36 pm
  • የመንግሥት ኃላፊዎች ወደ ሁርሶ የተወሰዱበት ምሥጢር November 5, 2026 12:43 pm
  • መንግሥት ሰማ፤ ሪፖርተር ተዘጋ፤ ግን ለምን? ምሥጢሩ ምንድነው? November 3, 2026 12:09 am
  • ኢትዮጵያ በሰማይ ላይ ነዳጅ የሚሞሉ የኢሉሺን (Il-78) አውሮፕላኖችን ከሩሲያ ልትገዛ ነው October 30, 2026 08:57 am
  • ካይሮ ያጣችውን የሩሲያ ጄቶች አዲስ አበባ የታጠቀችበት ምሥጢር October 29, 2026 10:26 am
  • ኢትዮጵያ ሱ-35 ተዋጊ ጄቶች እና የኤስ-400 ዘመናዊ የአየር መከላከያ ስርአት በመታጠቅ ከሰሃራ በታች ብቸኛዋ ሀገር ሆናለች October 28, 2026 11:00 am
  • ሻዕቢያ ኢትዮጵያን በ“ካሚካዜ” ድሮኖች ለመምታትና በዘር ግጭት ለማፍረስ ሰፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተሰማ October 27, 2026 11:14 pm
  • ጆን መዲድ “ቀዝኖ እና ልብሱ ተበላሽቶ” ነው መከላከያ የማረከው October 27, 2026 08:41 pm
  • በጆን መዲድ መማረክ አደረጃጀቱ እየተፈረካከሰ በመሆኑ እነ ወዲ እምበይተይ፣ ምግበይ፣ ቀጣዮች ሊሆኑ ይችላሉ October 27, 2026 09:17 am
  • ከታክስ ስወራ እስከ ሐሰተኛ ጋብቻ፦ በኢትዮጵያ የታጠቁ ቡድኖች ደጋፊ ዳያስፖራዎችን ለማደን የተዘረጋው አዲሱ የአሜሪካ መረብ October 21, 2026 09:26 am
  • ኔታንያሁ የሶማሊላንድን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ አዲስ ቀጣናዊ ካርታ ይፋ አደረጉ October 20, 2026 03:20 pm
  • ትውልደ ሶማሊያዊቷ ናፊሳ በተዘቀዘቀ የአሜሪካ ሠንደቅ ፊት በሶማሊኛ ምርጫ ቅስቀሳ ማድረጓ ቁጣ ቀሰቀሰ October 20, 2026 09:21 am
  • በአሜሪካ የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች ደጋፊዎች ላይ የተደቀነው አዲስ ስጋት October 19, 2026 08:58 pm
  • ዜግነት ሊያሰርዝ በሚችለው የኢልሃን ዑመር ምርመራ ላይ አዳዲስ መረጃ ተገኝቷል October 19, 2026 04:45 pm
  • በትግራይ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ስም በአስቸኳይ ሊቀየር ይገባል! October 19, 2026 02:55 am
Copyright © 2026 · Goolgule