የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ከዚህች ከአዲስ አበባዋ የመሬት ነጠቃ ጥያቄ በጅጉ ገዝፎ የሄደ ነው። ከፍተኛው ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ ህወሃት ይህን ዘረኛ ፖለቲካውን ተሸክሞ አዲስ አበባ ከገባ በሁዋላ በተለይ ኦሮሞንና አማራን ጸጥ አድርጎ ለመግዛት የተጠቀመው ዘዴ በነዚህ ክልሎች ውስጥ ከታች እስከ ላይ ያሉትን ባለስልጣናት በአልተማሩና የማስተዳደር ችሎታ በሌላቸው ነገር ግን ታዛዥ ብቻ በሆኑ ሰዎች መሙላት ነበር። ወያኔዎች ይህን ያደረጉበት ምክንያት ህወሃት ይዞት የተነሳው ጥያቄ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ ባለመሆኑና ዋናው ዓላማው የሆነ የራሱን ክብ ለመጥቀም በመሆኑ እነዚህን ክልሎች አፍኖ የሚይዝለት አስተዳደራዊ መዋቅር ስላስፈለገው ነው። ህወሃት ያሻውን ያደርግ ዘንድ “የራሴ” የሚለውን ክብ ለመጥቀም ይችል ዘንድ በየክልሉ የራሱን መጠቀሚያዎች መፈለግ ስለነበረበት ነው። በነዚህ ክልሎች ሰው በባትሪ ተፈልጎ የሚሾመው ህወሃት የአሳቡ እስኪሞላ ድረስ ፈረስ የሚሆኑትን ሰዎች በማግኘት ላይ የተመሰረተ ነበር። የማይጠይቅ፣ የሚፈራ፣ ለጥቅም የሚንበረከክ፣ እውቀት የሌለው፣ በባትሪ እየተፈለገ የሚሾመው ህወሃት ቀድሞ ላሰበው የግል ጥቅም ስራው አንድ ራሱን የቻለ ስትራተጂ አድርጎ ስለወሰደው ነው። ውሎ ሲያድር ይህ ስትራተጂ ምን አመጣ? ከባድ የመልካም አስተዳደር ችግር በተለይ በኦሮምያና አማራ ክልሎች አመጣ። የበቁ የነቁ የኦሮሞ ተማሪዎች ወይ በኦነግ ወይ በተቃዋሚ እየተፈረጁ ተወገዱ። የኦሮሞ ህዝብ ልቡ አዘነ። የተማሩ ልጆች እያሉኝ፣ ጥሩ ጥሩ ማስተዳደር የሚችሉ ልጆች እያሉኝ ለምን እንዲህ አደራጋችሁኝ? እያለ አነባ። አማራው አካባቢም እንደዚሁ ታዛዡን እየፈለጉ ሲሾሙ በክልሉ ቀልጣፋ አገልግሎት ጠፋ፣ ህዝቡ ወደ ወረዳ ወደ ክልል ወደ ዞን ሲሄድ የሚያገኛቸው ባለስልጣናት ችግሩን የማይረዱ አንዳንዴም በሚያሳፍር መልኩ ህዝቡ የሚለው እንኳን የማይገባቸው ሆነው ተገኙ።
ተራው ሰው የበለጣቸው መሪዎች በየቦታው በመኖራቸው ህዝቡ ከአመራር አካላቱ የሚጠብቀው ነገር ጠፋ። በተለይ የነዚህ የሁለቱ ክልሎች ትልቅ ችግር ይሄ ነው። ህወሃት እነዚህን ክልሎች ከቀጣበት መንገድ ሁሉ በጣም አስከፊው ቅጣት ይሄ ነው። በራሳቸው ልጆች በጃዙር ቀጣቸው። በርግጥም ልጆች እያሏቸው የተማሩትን የተሻሉትን እያባረረ በማይሆኑ ሰዎች እንዲተዳደሩ መደረጉ ትልቅ ቀውስን አምጥቷል። ህወሃት እነዚህ ሰዎች መሳሪያው ስለሆኑና እላይ ቆልለውት እየሰገዱለት ስለሚኖር ደስ ብሎታል። የመጣው ማህበራዊ ቀውስ ግን ልክ የለውም። ይህ ችግር በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ቢታይም በኦሮምያና በአማራ ግን የከፋ የከፋ ሆኖ ይታያል። በአንዳንድ ቦታዎች ህወሃት ስልጣን ሲይዝ የወረዳ ሊቀመንበር የሆኑት ህወሃት ከመምጣቱ በፊት ችሎታ የሌላቸው ጥሩ ምግባር ያልነበራቸው ወዘተ ነበሩ። እነዚህን ሰዎች እየሰበሰበ የቀበሌ ምክር ቤት፣ የወረዳ ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤት እያለ ነው ይሾም የነበረው። ህዝቡ ለጊዜው ይስቅ ነበር። ይሁን እንጂ መራራው እውነት ግን እነዚህ ሰዎች የዚህን ህዝብ እጣ ፈንታ የሚወስኑ ስለነበር ሳቁ ወደ አዘን በፍጥነት ተቀየረ። አንዳንድ ለምልክት ከየብሄሩ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ደግሞ ህወሃት በአጃቢ ስም የቁም እስር አስሯቸው የህወሃትን ፍላጎት እያስፈጸሙ እንዲኖሩ ተደርገዋል።ይህ ችግር ለብዙ አመታት ሲቆይ የመልካም አስተዳደር ብሶቱን አበዛና እነሆ ዛሬ ህዝቡን በእንባ አራጨ።
አንዱ የዛሬው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የሚያስተዳድሩትን ህዝብ ጥለው ህወሃትን ቆመው የሚያበሉ የክልሉን አስተዳዳሪዎች ማውገዝ፣ ህወሃት የፈጠረው ይህ ራስ ወዳድና ስግብግብ ፖለቲካ እንዳስቆጣቸው ለመግለጽ፣ ለውጥን ለመሻት ነው። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከመልካም አስተዳደሩ ችግር በተጨማሪ አጠቃላይ የፖለቲካው አወቃቀር ህዝቡን ግራ ግብት አደረገው። በተፈጥሮ ሃብት፣ በባህል፣ በፖለቲካ ተሳትፎዎች ግልጽ የሆነ ስምምነት የለም። ይሄ ጉዳይ ከፍተኛ ማህበራዊ ምስቅልቅል አመጣ። ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን ስትኖር አንዳንድ ክፉ ትውስታዎች (memories) ነበሯት፣ ብዙ መልካም ትዝታዎችም (good memories) ነበሯት። የህወሃት ፖለቲካ የቆመው ግን መጥፎዎቹን ትዝታዎች (bad memories) እየመረጠ በነዚያ ላይ ነው ቤቱን የሰራው።
ነገር ግን ፖለቲካ ዓላማው በጎ ለውጥን ማምጣት በመሆኑ ለማህበረሰብ ለውጥ እንደ ኤነርጂ አድርጎ ሊጠቀምባቸው የሚገባው ጥሩ ጥሩ ትዝታዎችን በማጉላት ነበር። የኛ ፖለቲካ ግን በተቃራኒው መጥፎ ትዝታዎችን በማጉላት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠረው ኤነርጂ ኔጌቲቭ እንዲሆን እየታገለ ነው። ታዲያ ፖለቲካ በመጥፎ ትዝታዎች ላይ ሲቆም አንዱ ውጤት ይህ ነው። ቡድኖችን ማጋጨት፣ ብሄራዊ ማንነትን ማኮሰስ፣ አገርን ማስጠላት ስደትን ማብዛት ነው። ይህ ጉዳይ ህዝቡን ውስጡን ጎድቶታል። ፖለቲካ በመልካም ትዝታዎች ላይ ቆሞ እነሱን እያራገበ መጥፎዎቹን ሊያርምና ሊክስ ነበር የሚገባው። አለመታደል ሆነብንና የህወሃት ፖለቲካ መጥፎዎቹን እያራገበ፣ ማራገብ ብቻ ሳይሆን ማጣፈጫ ጨው ጨመር እያደረገ የውሸት ታሪክ እየጻፈ አበላሸው። ይህ ጉዳይ በጣም ጎድቶናል። ትልቅ ብሄራዊ ስብራትም አመጣ።
አሁን የህዝቡ ጥያቄ የለውጥ ጥያቄ ነው። ድሃው ህዝብ በቃል የሚገልጻቸውና የማይገልጻቸውን ውስብስብ ችግሮቹን በማስተር ፕላኑ ለመግለጽ ይሞክር እንጂ ብሶቱ የትየለሌ ነው። ትልቁ ብሶት የተበላሸውን የሶሺዮ ፖለቲካ ስርዓት እንዲለወጥ ከመፈለግ ነው። ህዝቡ ለውጥ ያለ ልክ ተርቧል። ጥያቄው ይሄ ነው። ወለጋ ውስጥ ያለውን ኦሮሞ፣ ምእራብ ሃረርጌ ያለውን ኦሮሞ ወዘተ … ገንፍሎ እንዲነሳ ያደረገው ጉዳይ የመልካም አስተዳደር እጦትና ይህን ተከትሎ የመጣው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግፎች ናቸው።
ታዲያ የህዝቡ ጥያቄ የለውጥ ይሁን እንጂ በዚህ የለውጥ ወራት ጊዜ የትግላችንን ፍሬ ሊለቅሙ ከሚጣደፉ ወያኔዎች መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው። በሃገራችን የሚመጣው ለውጥ ግዙፍ ለውጥ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን እንደገና አፍርሶ የሚሰራ መሆን የለበትም። ኢትዮጵያን እንደገና የሚያንጽ ስራ ነው የሚያስፈልገው። ስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት ኪዳን ውስጥ ልንገባ ይገባል። ይህ ማለት ኢትዮጵያን በመገንጠል ሪፈረንደም ወይም በሌላ መንገድ አፍርሰን እንደገና እንስራ ወይም እንገነጣጠል ማለት አይደለም። ኢትዮጵያን እንደዚህ ለማሳብ አይቻልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽ የሆነ የቡድኖች የድንበር ክልልም የለም። እነዚህ አሁን ያሉት ዘጠኝ ክልሎች ትናንት ወያኔ የፈጠራቸው፣ እንዳሻው የሰራቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ስትፈጠር ዘጠኝ ክልል ነበረች የሚል ታሪክ የለም። ወያኔ በፈጠረው ኮራብትድ ክልል የመገንጠል ሪፈረንደም አይሰራም። አገራችን አንድ ናት። የተቀየጠው ህዝብ ብዛት ከብሄሮች ቁጥር በልጧል። ወያኔ እንደሚለው ሳይሆን የጋራ ግዙፍ ታሪኮች አሉን። የጋራ ሃብት አለን። ወንዞቻችን የተፈጥሮ ሃብቶቻችን የጋራ ናቸው። አንዳንድ የወያኔ አባላት ከዚህ በፊት ጥለውት የነበረውን የመገንጠል ጥያቄ ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ ሲነሳባቸው ሊያነሱ ይችላሉ። አምነውበት ባይሆንም ለጊዜው መሸሸጊያ ይሆነናል ከሚል ትግራይን ለመገንጠል ያስቡ ይሆናል።
ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በቀጥታ አይደለም። እንዲህ አይነት የህዝብ ተቃውሞ ሲነሳ ይህንን ትግል ሃይጃክ በማድረግ ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያ አገሪቱን አፍርሰው፣ በተለይ አማራውንና ኦሮሞውን አባልተው ነው የሚሄዱት። የመገንጠል ጥያቄው ከሌላ ብሄር እንደመጣ አድርገው ሌላውን ብሄር በየቤትህ እደር አይነት ከበተኑ በሁዋላ የሚያስቡትን ለማድረግ ይሞክሩ ይሆናል። ከዚህ በፊት አንስተውት ጥለውት የነበረ ጥያቄ ቢሆንም ወያኔ አይታመንምና ይህን ብንገምት አይፈረድም። ሃያ አምስት ዓመት ሲዘርፉ ቆይተው አሁን የመገንጠል ነገር ቢያመጡ ፍጻሜው ምን ይሆናል? የሚለውን ጥያቄ እናዘግየውና እንደዚህ ሊያስቡ ስለሚችሉ ለዚህ ፍላጎታቸው የኦሮሞም ህዝብ ሆነ የአማራ ወይም የደቡብ እንዲሁም ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመች አይሆንም። የኦሮሞ ጥያቄም ሆነ የሌላው ህዝብ ጥያቄ የለውጥ፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ናቸው።
የለውጡ ጥያቄ ኢትዮጵያን እንደገና የማነጽ ስራ ነው። ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ ማለት እኛ በቋንቋ የተለያየን ቡድኖች አብረን ስንኖር የአንድ ቡድን የበላይነት ሳይኖር እንዴት አብረን በእኩልነት እንኑር? እንዴት አድርገን ያለንን ባህል በአንድ በኩል ወደ ላይ እያሳደግን በሌላ በኩል ወደ ጎን እየተማማርን እንኑር? የቋንቋ ሃብቶቻችንን እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም? እንዴት አድርገን የተሻለ ብሄራዊ ማንነት እንገንባ? በአካባቢያችን ያለውን የተፈጥሮ ሃብት እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀም? ፖለቲካዊ አሰላለፋችን እንዴት እናድርገው? በሚሉ ጉዳይች ዙሪያ የመግባቢያ አሳብ ማምጣትና በዚህ ስምምነት ላይ መተዳደር ማለት ነው መስማማት ማለት::
ኢትዮጵያን እንደገና ማነጽ ማለት ወደፊት ለቡድኖች ሁሉ እኩልነትን የሚያመጣ አሳብ ማመንጨትና በዚያ ላይ አቋም ይዞ አዲሲቷን ኢትዮጵያን መገንባት ነው። በመሆኑም የለውጡ ጥያቄ ሰፊ ነው። ኢትዮጵያውያን ለውጥ ሲያነሱ አገራቸውን ለማፍረስ አይደለም። ኢትዮጵያ ማለት ኦሮሞ ነው። ኦሮሞ ማለት ኢትዮጵያ ናት። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ነው። ስለሆነም የኦሮሞን ጥያቄ እንደግፋለን። ለውጥ ይምጣና የተሻለ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ማእቀፍ ውስጥ እንግባ። ሁላችን የኦሮሞ ወንድሞቻችንን ጥያቄ ደግፈን ለመልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲ እንታገል። በትግላችን ላይም ሆነ በውጤቱ ላይ በአንድም በሌላም መንገድ ለወያኔ መሰሪ ዓላማ እድል ፈንታ አንሰጥም።
ኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ያነሳውን የትግል ችቦ ሌላው ኢትዮጵያዊም ተቀብሎ ያበራል!
እግዚአብሄር ኢትዮጵያችንን ይባርክ
ገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply