
መግቢያ
ያለፉትን 40 ዓመታት ፖለቲካችንን ለመረመረ አገርን በሚመለከት የሚሰነዘሩት አስተያየቶች ወይም የሚሰጡት ትንተናዎች ሁሉ ሳንይሳዊ ይዘት ይኑራቸው አይኑራቸው የሚጠይቅ የለም። በተለይም ፖለቲካ ፍልስፍናዊ መሰረት ያለው ታላቅ ፅንሰ-ሃሳብ መሆኑ ግንዛቤ በሌለበት አገርና፣ ማንኛውም ህብረተሰብንና የአገርን አጠቃላይ ሁኔታ በሚመለከት ረገድ የግዴታ ሳይንሳዊ ትንተና መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ቀርቶ ስሜት ዋናው መመሪያ በሆነበት አገር የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ትክክል መሆናቸውንና አለመሆናቸውን ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ ለመመርመር የሚቃጣ ሰው በፍጹም የለም።
እንደሚታወቀው በተለይም በአብዮቱ ወቅት ሳይንስና ፍልስፍና መመሪያ መሆናቸው ቀርቶ ስሜት የፖለቲካውን መድረክ በመያዙ እንደተከታተልነው ለብዙ መቶ ሺህ ህዝብ መሞትና ለአገር ውድመት የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቶ አልፏል። ዛሬ አገራችን ለምትገኝበት እጅግ አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታ በአብዮቱ ወቅት የተከሰተውና የተካሄደው ስሜት አዘል ፖለቲካ በተለይም የፖለቲካ ተዋናይ ነን የሚሉትን ጭንቅላት በመያዙ ከሳይንሳዊ ትንተናና ውይይት እንዲሁም ክርክር ይልቅ ስሜት በመቅደሙ ሁሉም የሚፈራራና የሚገዳደል ወደ መሆን አበቃ። ይህ ቁስል ዛሬም ያለና ከአብዮቱ የተረፈው የተወሰነ ኃይል ዛሬም ከቂም-በቀል ፖለቲካውና ሰውን ከማስፈራራት ለመላቀቅ ያልቻለ ሆኖ እናገኘዋለን። አብዮቱ ከሸፈና ወደመ ከተባለ ከአርባ ዓመት በኋላም የጭንቅላት ተሃድሶ ባለመካሄዱ የድሮው ዐይነት በተለይም በተንኮልና በቂም በቀል ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ የሚሉት ፈሊጥ አሁንም እንዳሰፈሰፈ እንመለከታለን።
ባለፉት 25 ዓመታት በአገራችን ምድር የተንሰራፋውን እጅግ አሳዛኝና አገር አፍራሽ ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ ዋናው ምክንያት በተለይም በፖለቲካ መድረክ ውስጥ የሚሳተፉት ሰዎች ወይም ድርጅቶች አዕምሮ የቱን ያህል ያልበሰለና መንፈሰ-አልባ መሆኑን ነው የምንገነዘበው። በክርክርና በውይይት ያልታነፀ ጭንቅላት፣ በተለይም ደግሞ ፍልስፍናና ሳይንስን መመሪያው ያላደረገና፣ በየጊዜው አስተሳሰቡንና ድርጊቱን ለመመርመር የማይችል ኃይል የመጨረሻ መጨረሻ የታሪክ ወንጀል ሰርቶ እንደሚሄድ መገንዘብ እንችላለን። ከዚህ ስንነሳ የምንገነዘበው ዋና ሀቅ ለአገራችን መዘበራረቅና ውድመት ተጠያቂው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን የፖለቲካ ኤሊት የሚባለው እንደሆነ መረዳቱ ከባድ አይሆንም።
ስለሆነም በእልክና በአወቅሁኝ ባይነት፣ እንዲሁም ለከፋፍለህ ግዛ እንዲያመች፣ ይሁንና ደግሞ የመጨረሻ መጨረሻ ራሳቸው የተንኮሉ ጠንሳሽ የሆኑ ሰዎችንም ብዙም የማያራምዳቸው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የብሔረ-ሰብ ክልላዊ አስተዳደር የሚሉት ፈሊጥ አዳዲስና ጭንቅላታቸው ያልበሰለ ወጣቶችን በመፈልፈሉ የፖለቲካውን መድረክ አጣበውታል። አገዛዙና የውጭ ኃይሎች አገራችንን ለማዳከምና ለመበታተን በፈጠሩት የታሪክንና የህብረተሰብን ህግ ያላካተተ “ፌዴራላዊ የክልል ፖለቲካ” ተግባራዊ በመሆኑ፣ በተለይም በዛሬው ወቅት የወያኔ አገዛዝ በህዝባችን ላይ በሁሉም አቅጣጫ የከፈተውን ጦርነትና በህዝባችን ላይ የሚፈጽመውን ፋሺሽታዊ ድርጊት ለመዋጋት ኃይላችንን መሰብሰብና በጋራ መታገል ሲገባን የብሔረሰብ-አጀንዳ ሜዳውን በማጣባብ የብዙዎቻችንን አመለካከትና የትግል ስትራቴጂ እየቀየረው መጥቷል ማለት ይቻላል። አገዛዙ የሚያካሂደውን አገር አውዳሚ ድርጊትና በህዝባችን ላይ የሚፈጽመውን ፋሺሽታዊ ጭፍጨፋ ለማቆምና በአገራችን ምድር ሰላም እንዲመጣ ከመታገል ይልቅ የሁላችንም ፍርሃት “ይህች አገር ልትበታተን ነው፤ እንዴት አድርገን ነው ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት መታገል ያለብን” በሚለው ላይ እንድናተኩርተገደናል።
የዛሬውን የተተረማመሰ ፖለቲካ ለራሳቸው ስልጣን መወጣጫና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር አገራችንን ወደ ልዩ አቅጣጫ ለመውሰድ የሚፈልጉ ኃይሎችና፣ በዚያውም መጠን የድህነቱን፣ የተበዝባዥነቱንና የኋላ-ቀርነቱን ዘመን ለማራዘም የሚፈልጉ ኃይሎች የፖለቲካ ሜዳውን ወጥረው በመያዝ የአብዛኛዎቻችን አመለካከት ሊቀይሩት በቅተዋል። በተለይም ለንደን የተካሄደውና ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ አትላንታ የተካሄደው “የኦሮሞ መሪዎች ስብሰባ” (Oromo Leadership Convention) የሚባለው ስብስብ ላይ የተሰጠውን ፓለቲካዊና ሳይንሳዊ ትንተና ሳይሆን ከምሁራን የማይጠበቅ ሀተታ-መሳፍንት አብዛኞቻችንን እንድንጯጯህ ሲያደርግ፣ አንዳንዶቻችንን ደግሞ አስደንግጦናል። ይህንን ዐይነቱን ህብረተሰብን አፍራሽና ኋላ-ቀርትነትን እዚያው ፈርጥሞ እንዲቀር ከሚያደርገው ስብሰባ ላይ የሚሰነዘረውን አስተያየትና በየቴሌቪዥኑም የሚስተጋባውንና፣ የወጣቱን መንፈስ የሚበርዘውን በታሪክና በሳይንስ ያልተደገፈና ሊረጋገጥ የማይችል አመለካከት ካለምንም ርህራሄ መዋጋት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እንደምከታተለው ከሆነ መሪ ነን የሚሉት ሰዎች ጭንቅላት የደነደነ ስለሆነና፣ ለጊዜውም ቢሆን የልብ ልብ ስለተሰማቸው ከእነዚህ ሰዎች ጋር በቲዎሪና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ውይይትና ክርክር ማድረግ በፍጹም የሚቻል አይመስለኝም። ስይንሳዊና የቲዎሪ ክርክርና ውይይት የሚገባቸው አይመስለኝም። ስለዚህም ያለው አማራጭ መንገድ እየመላለሱ ሌላው እንዲረዳው እነሱን በሳይንሱ መንገድ መዋጋቱ ፍቱንና ሊታለፍ የማይችል መሳሪያ ነው ብዬ አምናለሁ።
ችግሩ የዘመናዊነትና የተሃድሶ እጦትወይስ የብሔረ-ሰብ ጥያቄ !
የብዙ አገሮችን ታሪክና የህብረተሰብ አገነባብን ታሪክ ለተመለከተ ብዙ ውጣ ውረድ እንደሚያስፈልገው መረዳት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውም ነገር ከአንድ ሁኔታ በመነሳት እንደየሁኔታው ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው ሂደት ውስጥ እየተሰበጣጠረና ከሌሎች ጋር እየተቀላቀለ፣ በዚያው መጠንም የመጀመሪያው አስተሳሰቡ እየከሰመና አድማሱ እየሰፋ ይመጣል። የማደግ፣ የመበሰጣጠርና፣ እንዲሁም ከሌላው ጋር በመቀላቀልና በመጋባት፣ የአስተሳሰብ አድማስን ማስፋትየሚቻለውና እያንዳንዱ ግለሰብም ከተተበተበበት ዕድገትን ከሚያደናቅፍ ወይም ትራዲሺናል ቫልዩ (Traditional Values) በመላቀቅ ራሱን በራሱ ማግኘት የሚችለው በዚያ ህብረተሰብ ውስጥ በአንዳች ተዓምር ብቅ የሚሉ ግለሰቦች ጥያቄ መጠየቅ ሲችሉና ስርዓቱን መጋፈጥ የቻሉ ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብን ማዳባር በተለያዩ ህብረተሰቦች ልዩ ልዩ ዐይነት መልክ የያዘ ቢሆንም፣ የበለጠ መዳበር የቻለው በጥንታዊቱ ግሪክና፣ በአውሮፓ ምድር ደግሞ ከአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል።
ይህ ዐይነቱ ተሃድሶና መሻሻል የበለጠ እየተስፋፋ ሲመጣ በአንድ አካባቢ የሚኖር ህዝብ በዚያው ባለበት ረግቶ እንዳይኖር ተገደደ። በቴክኖሎጂና በሳይንስ እንዲሁም በከተማዎች ማደግ ምክንያት የተነሳ ከተለያየ ቦታ ፈልሰው የሚመጡ ሰዎች በመኖርናየመፍጠር ችሎታቸውንም በማሳደግ መቋቋም ሲችሉ ከዚያ በፊት የነበራቸውን ውስን አስተሳሰብ አሽቀንጥረው በመጣል ከአዲሱ ሁኔታ ጋር የበለጠ እየተላመዱና ከሌላ ክልል ከመጣው ጋር በመጋባት ራሳቸውን የዚህ ወይም የዚያ ብሔረ-ሰብ አካል ነኝ ብለው ሳይጠሩ የሚኖሩበት አካባቢ አካል መሆናቸውን እየተገነዘቡ መምጣት ቻሉ። የማደግና በህብረተሰብ ውስጥም ተቀባይነትን የማግኘት ኃይል ሊወሰን የሚችለው እያንዳንዱ ግለሰብና ማኅበረሰብ በታታሪነትና በሰለጠነበት ሙያ ለህብረተሰቡ በሚያደርገው አስተዋፅዖ ብቻ እንጂ ከዚህ ወይም ከዚያ ብሔረ-ሰብ በመምጣቱ እንዳይደለ ግንዛቤ ውስጥ ተገባ። ከዚህም በመነሳት እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ዕድል ራሱ ወሳኝ መሆኑን ሲገነዘብ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንዱ ከሌላው የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ሲል የፈጠራ ችሎታውን በማሻሻል ራሱን ማሳደግ የኑሮው ፍልስፍና ድርጎ ለመውሰድ በቃ። በዚህ መልክ ሁሉም በየችሎታው በመሰመራት ሰፋ ላለ የአመራረት ዘዴ ሁኔታዎችን አመቻቸ። የበለጠ ሊያመርት የሚችልበትን የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመፍጠር ራሱን ማሳደጉ ብቻ ሳይሆን፣ ለህበረተሰብአዊ ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት ቻለ።
በዚህ መልክ የዳበረው የስራ-ክፍፍልና እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን በራሱ አግኝቶ ማደግና ራሱን መግለጽ መቻል ቀሰ በቀስ ከዳበረው የፖለቲካ ፍልስፍና አስተሳሰብና ተግባራዊ እየሆነ ከመጣው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በመጣመር የኋላ ኋላ ህብረ-ብሔር ወይም ኔሽን (Nation)ለሚለው አስተሳሰብ መሰረት በመጣል ለካፒታሊዝም ዕድገት በር መክፈት ቻለ። በሌላ አነጋገር፣ የብሔርና የብሔራዊ ስሜት አስተሳሰብ (Nation and Nation-hood) ቀስ በቀስ ሊዳብሩና መሰረታቸውን ማረጋገጥ እየቻሉ መምጣት ከአስተሳሰብ መዳበር፣ በስራ-ክፍፍል (Division of Labour) ማደግና መስፋፋት ጋር የተያያዙ እንደሆን ብቻ ነው። ለምሳሌ በዘመነ ፊዩዳሊዝም ወይም በከብት እርባታ ላይ ብቻ ተሰማርቶ የሚገኝ ህዝብም ሆነ ብሔረ-ሰብ እንደ አንድ ብሔር ሊታይ በፍጹም አይችልም። አንድ ህዝብ ብሔር ሆኖ እንዲጠራ ከተባለ ለስራ-ክፍፍል መዳበርና ለቴክኖሎጂ ግኝትና ምጥቀት አስፈላጊውን መሰረት በመጣል በዚያው መጠንም የአስተሳሰብ መጎልመስን መቀዳጀት መቻል አለበት።
የእኛንና ዛሬ በጎሳና በሃማኖት የሚተራመሱ አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት ያለው ችግር በየጊዜው የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ያለመቻልና ጥያቄ ለመጠየቅ ዝግጁ ያለመሆን ነው። እንደሚታወቀው አንድ ሰውም ሆነ አንድ ህዝብ ጥያቄ ሲጠይቅ ብቻ ነው መልስ ለማግኘት የሚችለው። እንደሚታወቀው ራስን እየመላለሱ መጠየቅ የሎጂካዊ አስተሳሰብና የሳይንሳዊ ግኝት ዋናው መክፈቻ መንገድ ነው። በተለይም ከሬናሳንስ ጀምሮ ያለውን የአውሮፓውን የህብረተተሰብ ዕድገት ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ ጥያቄ መጠየቅና ለአንድ ለተዘጋ ነገር መልስ ማግኘት መጣጣር ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ዋናው ቁልፍ ነገር መሆኑን መገንዘብ እንችላለን። ጥያቄዎችን መጠይቅና ራስን ማስጨነቅ፣ እንዲሁም ደግሞ የመከራከር ልምድ በሌለበት አገር ዕውቀትን ከማዳበር ይልቅ ጭቅጭቅና መነዛነዝን ማስቀደም ይቀድማል። ሰለሆነም እያንዳንዱ ግለሰብ ሎጂካዊ በሆነ መልክ በማሰብና ከመከራከር ይልቅ ወደ ንትርክና እንዲያም ሲል ወደ ድብድብ ያመራል። ቡድናዊና ክልላዊ ስሜት ባየለበት እንደኛ ባለበት አገር ደግሞ የባሰውኑ ወደ ጦርነት በማምራት ታሪክን ማፈራረስና ህዝብን ማፈናቀል እንደሙያ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የብሔረ-ሰብ ፖለቲካንም ሆነ ወይም “ብሔራዊ ፖለቲካን እናራምዳለን” የሚሉትን ሁሉ በምንም ዐይነት በክርክርና በጥሞና ውይይት ማስተማር፣ መማር፣ ማሳመንና ማመን በፍጹም አይቻልም። ጭንቅላታቸው በተወሰነ አስተሳሰብ ስለተቀረጸና ህይወታቸውም ከመጠርጠር ጋር የተያያዘ በመሆኑ የነገሮችን ሂደት በሎጂካዊ መንገድ ለማሳመን በፍጹም አይቻልም። በደነደነው አስተሳሰባቸው በመግፋት የአገር አፍራሽ ተግባራቸውን በተለያየ መንገድ ያፋጥኑታል። ስለሆነም እየተጯጯሁና እየተደናበሩ መኖር ትግል የሚሉት ፈሊጥ ዋናው ስልት ከመሆን አዳዲስ አስተሳሰቦችን በማዳበር ወደ ፊት መጓዝ በፍጹም አይቻልም። በዚህ ዐይነቱ ትግል በሚሉት ፈሊጥ የኋሊት ጉዞ የሚሄዱ ነው የሚመስለው እንጂ እንደሰለጠነ ሰው በሳይንሱ መንገድ ለመወያየትና ለመከራከር በፍጹም አይችሉም።
ወደ መነሻዬ ልምጣና፣ በአገራችን ምድር ውስጥ የጭንቅላት ተሃድሶና ከዚህ ጋር የተያያዘ ቴክኖሎጂያዊ ለውጥ (Technological Revolution) ባለመካሄዱ አሁንም ስለብሔረ-ሰብ ጭቆናና በቁጥር ስለመብለጥና አለመብለጥ፣ እንዲሁም ከቁጥር መብለጥ ጋር የሚመጣጠን ፖለቲካዊ ድርሻ ስለማግኘት ጉዳይ እያነሳን ችግርን ወደ ማይፈታ ጭቅጭቅና ንትርክ ውስጥ በመግባት ተፈጥሮ የሰጠንን የማሰብ ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ እንዲሁም የማቴርያል ሀብትም እናወድማለን። ዋናው ችግራችንም የብሔረ-ሰብን ጥያቄ አድርገን በመወሰድና በማመን መሰረታዊና ለሰው ልጅ ከሚያስፈልገውና የሰውን ልጅ ችግር ከሚፈታው ሳይንሳዊ ምርምር እንሸሻለን።
በቁጥር ብልጫ ላይ የተመሰረተ አስተዳደር የአንድን ህዝብ ችግር ሊፈታ አይችልም !!
የታሪክንና የህብረተሰብን ሂደት ማህደር በደንብ ሳያገላብጡና ሳይመረምሩ የኦሮሞ ኤሊት ነን ባዮች ቀድሞሞ ሆነ ዛሬ እየመላለሱ የሚነግሩን “የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ ከቆዳው ስፋትና ከቁመቱ ጋር የሚመጣጠን የፖለቲካ ስልጣንአልተሰጠውም” እያሉን ነው። ይህንን ዐይነቱን አስተሳሰብ ሲያስተጋቡና ሲያስፋፉ ምን ለማለት እንደፈለጉ ለማብራራት ባይችሉም፣ ውስጣዊ ይዘቱን ስንመረምረውግን ሊሉን የሚፈልጉት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ አንድ ብሔር ብቻ ለብዙ መቶ ዓመታት የፖለቲካ ስልጣንን በመጨበጥ ሀብታችንን (Resources) በመበዝበዝና ዕድላችንን በመወሰን ወደ ኋላ እንድንቀር አድርጓል ይሉናል። ብዙም ሳይራመዱ ደግሞ እዚያው በዚያው ከብዙ መቶ ዐመታት በፊት ተግባራዊ እናደርግ የነበረውን ለዲሞክራሲ ማበብ፣ ለነፃነት መስፋፋትና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ የማያመቸውን የጋዳ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንፈልጋለን ይላሉ። ይሁንና ግን በዚህ ዐይነቱ ስርዓት እንዴት አድርገው ቴክኖሎጂን በማሳደግ ብሔራዊ ሀብት አዳብረው ህዝባቸውን ከድህነት እንደሚያላቅቁት በፍጹም አይነግሩንም። በአጠቃላይ ሲታይም ምን ዐይነት ህብረተሰብ ለመመስረት እንደሚፈልጉም አያስረዱም ወይም አያብራሩም። በአስተሳሰቡ አንድ ወጥ የሆነ፣ አንድ ሃይማኖት ያለው፣ በስራ-ክፍፍል ያልዳበረ፣ ወይንስ ደግሞ የተሰበጣጠረና በስራ-ክፍፍል ላይ በመሰማራት የራሱን ዕድል ራሱ በመወሰን ራሱን በራሱ አግኝቶ ህብረተሰቡንም የሚጠቅም ስርዓት ለመገንባት ፟? ከዚያም በመነሳት የገበያ ኢኮኖሚና ካፒታሊስታዊ ስርዓት ለመገንባት ወይስ ዝም ብሎ ብቻ በከብት እርባታና በሳይንስ ላይ ባልተመሰረተ የእርሻ ክንዋኔ ላይ ብቻ በመሰማራት የሚኖር ብሔረ-ሰብ ነው ? ለመመስረት የሚፈልጉት። ይህንን ጉዳይ ግልጽ ካላደረጉ ደግሞ ዝም ብለው ነው የሚደናበሩት ማለት ነው። አዲሶቹ የኦሮሞ ኤሊት ነን ባዮች እየደጋገሙ “ስለብሔረ-ሰባቸው መጨቆን” ሲነግሩን ጠቅላላው ኦሮሞ እያሉ የሚጠሩት የህብረተሰብ ክፍል ምንም ዐይነት የዲያሌክት ቋንቋ ልዩነት እንደሌለውና፣ የሚያልመው ህልምና ፍላጎቱ አንድ ዐይነት እንደሆነ፣ ሲነሳም ሲተኛም በአንድ ጊዜ እንደሆነና፣ ሃይማኖቱም አንድ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፣ በስራ-ክፍፍልና በመደብም ሆነ በገቢ እንዲሁም ደግሞ በህሊና አወቃቀር (Psychological makeup) ያልተከፋፈለ ወይም ያልተለያየ (undifferentiated) እንደሆነ ነው ለማሳመን የሚሞክሩት። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ኢ-ሳይንሳዊ አቀራረብ ነው። ለዕቅድና ለዕድገት የሚያመች አቀራረብ አይደለም።
ያም ሆነ ይህ አንድን ወጣት ትውልድ ለማደናበርና ጭንቅላቱን አጨልሞ በጥላቻ መንፈስ እንዲወጠር ከማድረግ በስተቀር በብዙ መንገድ እንደተረጋገጠው በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ዕድገትና የአገዛዝ ታሪክ ውስጥ፣ በተለይም ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ አንድ ብሔረ-ሰብ ብቻ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን በመቀዳጀት የሌሎችን ብሔረ-ሰቦች ዕድል ያጨለመበትና ለኋላ-ቀርነታቸውም ምክንያት የሆነበት ሁኔታ የለም። የኢትዮጵያን የፖለቲካ አወቃቀር ስንመለከት በስልጣን ላይ የተቆናጠጡት ኃይሎች ሁሉ በተለያየ ሁኔታ ከዚህኛውም ሆነ ከዚያኛው ብሔረ-ሰብ ጋር በደም የተሳሰሩ እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። በተለይም ኦሮሞዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች መስፋፋት ከጀመሩ ከ16ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የፖለቲካ ማትሪክሱን በመጋባትና በመዋለድ የህብረተሰቡን አወቃቀር እንደለወጡት መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ስምንት መቶ ዓመት ያህል አንድ ብሔረ-ሰብ ብቻ ነው ሲገዛን የነበረው፣ ከህዝባችን ስፋት ጋር የሚመጣጠን የፖለቲካ ስልጣንና ሀብታችንን ወይም ሬሶርሳችንን የመቆጣጠር ዕድል አላገኘንም የሚለው የተረት ተረት ወሬ ብቻ እንጂ በታሪክም ሆነ በሳይንስም የሚረጋገጥ ጉዳይ አይደለም። ስለ አገሪቱ ኋላ-ቀርነት ሲወራ ደግሞ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ከውጭው ዓለም ከነበረን እጅግ ከላላ ግኑኝነት ጋር የሚያያዝ እንጂ የአንድ ብሔረ-ሰብ የበላይነቱን በመቀዳጀቱ የተከሰተ ችግር እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል፟።
ስለሆነም በኢኮኖሚና በማህበረሰብ ያለማደግን ጉዳይ ስንመለከት አንድን ብሔረ-ሰብ የሚመለከት ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለስልጣኔና ለዕድገት የሚያመች ዕድል በታሪኩ ውስጥ እንዳላጋጠሙት እንመለከታለን። በተለይም በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በውስን መልክ በዘመናዊነት (Modernization) ስም የገባው የኢንዱስትሪ ፖለቲካው የነበረውን ስርዓት የባሰውኑ ድህነትን ከመፈልፈል በስተቀር አጠቃላይ የሆነ ብሔራዊ ሀብት (National Wealth) እንዳላዳበረና፣ ጠቅላላውን ህዝብ እንዳልጠቀመ በምድር ላይ የሚታየው ሀቅ ራሱ በቂ ማስረጃ ነው። ስለዚህም ስለ ዕድገትና ስለ ኋላ-ቀርነት በሚነሳበት ጊዜ ነገሩን፣ 1ኛ) ከምሁራዊ ብስለትና ሰፋ ያለ ክርክር ካለመኖር ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል። 2ኛ) በዚህም ምክንያት የተነሳ በራሱ የማሰብ ኃይል ሊዳብርና ሊንቀሳቀስ የሚችል የተገለጸለት የህብረተሰብ ኃይል (Middle Class) መፈጠር ባለመቻሉ ስርዓቱን መጋፈጥ አልተቻለም። በመሆኑም የፊዩዳሉ ስርዓት ዘመናዊ ከሚባለው ጋር በመቆላለፍ የአስተሳሰብ ግድፈት እንዲስፋፋና ድህነት መለዮአችን እንዲሆን ተደረገ። 3ኛ) አገዛዙ ራሱ የተከተለው ለፈጠራ የማያመች የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ሰፋ ያለ በስራ-ክፍፍል ላይ የዳበረ የውስጥ ገበያ እንዳይዳብር አገደ። ይህም ማለት ስለአንድ ብሔረ-ሰብ መበደል ወይም መጨቆን በምናውራበት ጊዜ ከጠቅላላው የአገሪቱ ፖሊሲና፣ ከአገዛዙ ውስን አስተሳሰብ ነጥሎ ማየት ከባድ ስህተት ነው። በተጨማሪም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው አዲሱ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ሁኔታ ለእኛ ዕድገት አመቺ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የዚህን ውስብስበ አዲስ ሁኔታ የመረዳትና ስትራቴጂ የመቀየስ ምሁራዊ ኃይል አልነበረነም።ስለሆነም በተለየያ የዕውቀት ዘርፎች ላይ በመሰማራትና አድማሳችንን ለማስፋት ዕድል ባለማግኘታችን ከውስጥ ያለውን ኋላ-ቀርነትን ከሚያራምደው ፖለቲካና ከውጭ የሚመጣውን ግፊት ደግሞ መጋፈጥ አልተቻለም። ዛሬም ያለን ዋናው ችግርእንደዚህ ያለውን ምህራዊ ዝግጅት ያለማድረጉ ነው። ማንኛውንም ነገር ለመቆጣጠር የሚቻለው ሰፋ ያለ የበሰለ የሳይንስና የምሁራዊ ኩሞኒቲ ሲኖር ብቻ ነው። አገር ወዳድነትና ዕድገትም መዳበር የሚችሉት በዚህ አማካይነት ብቻ ነው።
በቁጥር መብለጥና ይህንን ተመርኩዞ ተወካይነትን ከዚያው ብሔረ-ሰብ ለወጣ የፖለቲካ ኤሊት ኃላፊነትን ስለመስጠቱ ጉዳይ ስንመለከትና በኢምፔሪካልም ለማረጋገጥ እንደሚቻለው ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ ስሌት አካሄድ በፍጹም ሊስራ የሚችልና ለዕድገትም የሚያመች አይደለም። እንደሚታወቀው ከአንድ ብሔረ-ሰብ የተውጣጣ ብቻ ሳይሆን፣ ከተለያዩ ብሔረ-ሰቦች የተውጣጣ የፖለቲካ ኤሊትም ሆነ የገዢ መደብ ራሳቸው ባዳበሩት ቲዎሪና ሳይንስ ስለማይመሩ የባሰውኑ ከዕድገት ይልቅ ፀረ-ዕድገትን ነው የሚያስፋፉት። ሀብትን ከመቆጣጠር ይልቅ ሀብት በውጭ ኩባንያዎች እንዲመዘበርና አካባቢ ወድሞ ህብረተሰብ እንዲመሰቃቀል ከማድረግ በስተቀር ሀብትን በስርዓት የመቆጣጠርና ቴክኖሎጂዎችን የማዳበር ዕድል በፍጹም አይኖርም። የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲውን የሚወክሉት ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች (IMF & World Bank) የማይሆን ምክር በመምከርና ተፅዕኖም በማድረግ የባሰውኑ ድህነት እንዲስፋፋና ነፃነትም እንዲገፈፍ ያደርጋሉ። ይህንን ጉዳይ በብዙ አገሮች የምንመለከተው ሃቅ ስለሆነ የኦሮሞ ኤሊት ነኝ ባዩ ከዚህ ዐይነቱ አጋር አፍራሽ ዕድል ሊያመልጥ አይችልም።
ይህ ዐይነቱ አካሄድ በተለይም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተሞክሮ በፍጹም አልሰራም። የደቡብ አፍሪካ ጥቁሩ ህዝብ ወይም የህብረተሰብ አካል ከአፓርታይድ ለመላቀቅ ያደረገው ትግልና ለጊዜውም የተጎናጸፈው ዕድል የሚደገፍ ቢሆንም፣ ከ25 ዓመት በኋላ ጥቁርን እንወክላለን ከሚል አገዛዝ ስፊው ጥቁር የህብረተሰብ ክፍል የዕድገት ተጠቃሚ ሊሆን በፍጹም አልቻለም። የኤኒሴ (ANC) አገዛዝ ተግባራዊ እንዲያደርግ በተገደደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ (Neo-Liberal Economic Policy) አማካይነት፣ ጥቂት የፓርቲው ካድሬዎች ተጠቃሚ ከመሆንና ሀብት ከማካበት በስተቀር የሰፊው ጥቁር አፍሪካዊ ህይወት ሊሻሻል በፍጹም አልቻለም። የዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ሀብትን ማካበት ውጤት ማህበራዊ ቀውስና(Social Crisis) ከዚህ ጋር የተያያዘ ወንጀለኝነት መስፋፋታና በኤድስ በሽታ መለከፍ ነው። እንደምንሰማው የአገዛዙ አባሎች ከውስጥም ሆነ ከውጭ የንግድ ሰዎች ጋር በመመሰጣጠር ሀብት የሚያሸሹና የተቀረውንም በማከማቸት ራሳቸው ተንደላቀው እንዲኖሩ ሆነዋል። ስለሆነም በጥቁር ይበልጣል የሚባለው የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ በራሱ ኤሊት ቢወከል ከመቆርቆዝና ሀብቱ ከመበዝበዙ በስተቀር የስልጣኔን ዕድል በፍጹም ሊጎናጸፍ አይችልም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ጥያቄው በቁጥር በልጦ የመገኘቱ ጉዳይ ሳይሆን በሳይንስ ጭንቅላቱ የዳበረ ሰፋ ያለ ምሁራዊ ኃይልና ህብረተሰቡንም ለመለወጥ ዝግጁ የሆነ፣ እንዲሁም ህዝቡንና አገሩን ወዳጅ ኃይል ለዕድገት እጅግ ወሳኝ መሆኑን የህብረተሰብን ዕድገት ታሪክ ላገላበጠ መገንዘብ ይቻላል። አገር ወዳድነትና ህዝብን መውደድ ደግሞ ከብሔራዊ ባህርይ ጋር የሚጣመሩ ሲሆን የብሔረ-ሰብን አርማ ለሚያራግብ አገር ወዳድነትና ህዝብ ማለት ምን እንደሆኑ አይገባውም።
በሳይንስና በሎጂክ ሊደገፍ የማይችል የቁጥር ብዛት !!
የኦሮሞ ኤሊቶች እየደጋገሙ የሚሉን ጠቅላላው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ ውስጥ በቁጥር በልጠን የምንገኘው እኛ ስለሆን ስልጣኑም ለኛ የሚገባ ነው፣ ካለበለዚያ ተገንጥለን የራሳችንን ግዛት እንመሰርታለን እያሉ ነው የሚያስፈራሩት። ለብዙ ዓመታት ይህንን ያህልም ሳይረጋገጥ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው የኦሮሞ ብሔረሰብ ቁጥር 31 ሚሊዮን ያክላል እየተባለ ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት አውስታራሊያ ለሚገኘው የአማርኛ ራዲዮ አዘጋጅ ለሆነው ለአቶ ካሳሁን ዶ/ር ሃይሌ ላሪቦ በሰጡት ሰፊና ትምህርታዊ ትንተና የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ ቁጥር ከ7 ሚሊዮን እንደማይበልጥ እቅጩን ነግረውናል። አሁን ደግም የኦሮሞ የአመራር ኮንቬንሽን ላይ ከተሳተፈ ግለሰብ በቃለ-መጠይቅ ምልልስ የሰጠው መልስ የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ ከ50 ሚሊዮን በላይ እንደሚቆጠር ነው። እነዚህን የተምታቱ ቁጥሮች ስሰማ፣ ብዙ ካሰላሰልኩ በኋላ የደረስኩበት መደምደሚያ የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ ከማንኛውም ደም ጋር ሳይቀላቀል በንጹህ መልክይህንን ያህል ቁጥር ሊኖረውአይችልም የሚለው ሳይንሳዊ መረጋገጫ ላይ ነው ለመድረስ የቻልኩት። በሌላ አነጋገር የኦሮሞን ብሔረስ-ሰብ ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ከተፈለገ በታሪክና በህብረተሰብ ውህደት ውስጥ ያደረገውን መቀላቀሎች በልዩ መሳሪያ በማውጣት የነሱ ደምና ጂን ልዩ መሆኑን ከተረዳን የተቀረውን መጠን ካወጣን በኋላ በእርግጥም የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ ቁጥር ይህንን ያህል ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል። ይህንን ዘዴ ከተጠቀምን ደግሞ የግዴታ የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ ቁጥር በጣም አነስተኛ ይሆናል ማለት ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ የአንድ አገር ህዝብ በቤተሰብ (Households) አማካይነት በተደራጀ መልክ ሲቆጠር ዝም ብሎ ለመቁጠር ያህል ሳይሆን ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ዕቅድ ወይም ፕላን እንዲያመችና፣ ከዚያ በመነሳት እንደየደረጃው ከቤት አንስቶ እስከ ትምህርትቤት፣ ህክምና መስጫ፣ ክሊኒኮችና ሌሎች ለአንድ ህብረተሰብ ያስፈልጋሉ የሚባሉ የንጹህ ውሃንና የኃይልን አቅርቦት ለማደራጀትና ለማምረት ነው። በዚህ መልክ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በቤተሰብ ደረጃ (Households)ቆጠራ ሲካሄድ የተለያየ ክፍል ያላቸው ቤቶችና ልዩ ልዩ ነገሮች በመታቀድ ይሰራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የወሊድ ቁጥር አስቸጋሪ እየሆነ በመጣበት በኢንዱስትሪ አገሮች ውስጥ የህዝብ ቆጠራ አዲስ በሚወለዱና በታዳጊው እንዲሁም እድሜው በጠና መሀከል የሚደረግ የህዝብ ቆጠራ (Demography) ይካሄዳል። በዚህ መልክ የሚወለደው የህዝብ ቁጥር እያነሰ የሚሄድ ከሆነ አዲስ የሰራተኛ ኃይል እጥረት ስለሚኖርና ቀረጥና የጡረታ አበል የሚከፍል ኃይል ስለሚያጥር አይ ህዝቡ እንዲወልድ ልዩ ድጎማ ይሰጣል ወይም ደግሞ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ ይካሄዳል። በዚህ መልክ የዲሞግራፊን ችግር መቅረፍ ይቻላል። በተጨማሪም በህዝብ ቆጠራ ውስጥ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን የሴቶችና የወንዶች መጠን ለማወቅ ተያይዘቆጠራ ይካሄዳል። ሌላው የህዝብ አቆጣጠር ዘዴ ደግሞ በገቢና በሀብት ክፍፍል ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ አካሄድ የሀብትንና የገቢን አከፋፈል ዘዴ ለማወቅና የተዛባ ሁኔታ ካለ ማስተካከያ ዘዴ ለመፈለግ ነው። ከዚህም በላይ በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ሰዎችን ለማወቅ ሲባል የሚካሄድ አቆጣጠር ሲሆን፣ ይህም የሚያገለግለው በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠነ ሰው እጥረት በሚኖርበት ጊዜ የተማረ ኃይል እጥረት እንዳይኖር ሲባል ዝግጅት ለማድረግና አስፈላጊውንም እርምጃዎች ለመውሰድ ሲባል ነው። በዚህ መልክ የሚካሄድ የህዝብ አቆጣጠር ዘዴ ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ዕቅድ ያመቻል። ይሁንና ግን በጀርመንም ሆነ በሌሎች የኢንዱስትሪ አገሮች የተለያዩ የውጭ አገር ስዎች ቢኖሩም በተናጠል እየወሰዱ አንተ ከዚህ በሔረ-ሰብ ወይም ከዚህ አገር የመጣህ ነው እየተባለ ለየት ያለ ቆጠራ አይካሄድም። በሂደት ውስጥም አብዛኛው ከጀርመን ጋር በመጋባቱ የተነሳ፣ ከአንድ አገር የመጣው ከሌላ አገር ጋር ከመጣችው ጋር ስለሚጋቡ የህዝብን ቁጥር በጎሳ ደረጃ እየለያዩ መቁጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድም እጅግ አደገኛና ወደ ዘረኝነትም የሚያመራ ስለሆነ በጎሳ ላይ ያተኮረ ቆጠራ ሳይንሳዊ ባህርይ ሊኖረው በፍጹም አይችልም። ስለሆነም የህዝብ መቀላቅል ስላለ ጀርመኑን ከሌላው ለመለየት የሚያስቸግርበት ጊዜ ይኖራል። በተለይም ከላቲንና ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መጥተው እዚህ እየሰሩ የሚኖሩትንና የተጋቡትንና ልጅ የወለዱትን ከጀርመኑ ለመለየት እጅግ ያስቸግራል።
ወደ አገራችን ስንመጣ በተለይም ዶ/ር ሃይሌ ላሪቦ በሚገባ እንደተነተኑት ኦሮሞዎች ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ሲስፋፉ ከተቀረው ብሔረ-ሰብ ጋር በመጋባት ተቀላቅለዋል። በሳቸው አባባል በወለጋ ሆነ በአርሲ ኦሮሞዎች በቁጥር ብዛት ይበልጣሉ ተብሎ ቢገመትም፣ ሀቁ ግን በወለጋ ውስጥ አብዛኛው ከጎጃሙ ጋር የተጋባና የተዋለደ ሲሆን፣ በአርሲ ደግሞ ከጉራጌ ጋር በመጋባት ኦሮሞዎች ጥንታዊ በሆነ መልክ እንደማይገኙና ከማንኛውም ብሔረሰብ ጋር ሳይቀላቀሉ በንጹህ መልክ ሊኖሩ እንደማይችሉ ነው የሚነግሩን። ስለሆነም ይላሉ ምሁሩ፣ ቋንቋ ብቻውን ስለቁጥር መብለጥ መለኪያ ሊሆን አይችልም ብለው እቅጩን ይነግሩናል።ወደ ከፋም ስንመጣ ከኩሎኮንታዎችና ከከፋዎች ጋር በመጋባትና በመቀላቀል ተዋልደዋል። ለምሳሌ የድሮው በኢህአዴግ ተመርጠው የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በአያታቸው ከፍቾ እንደሆነ ይታወቃል። እሳቸው ግን ንጽሁ በንጹህ መልክ እሮሞ እንደሆኑና በአፄ ምኒልክ ዘመን ተገደሉ የተባሉ ኦሮሞዎችን መቃበር ሲያስቆፍሩ ነበር። እንደዚሁ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅት (OLF) እያለ ራሱን የሚጠራው ድርጅት መሪዎች አብዛኛዎቹ በአባቶቻቸው የጎንደርና የመንዝ ቄሶች እንደሆኑ ይታወቃል። እነሱ ግን ንጹህ በንጹህ ኦሮሞዎች ነንና ተጨቁነናል በማለት ነው ስንትና ስንት የዋህ ሰዎችን ሲያሳስቱና ሲያስገድሉየከረሙት። አሁንም በየሜዳው የሚቧርቀው የዘመኑ ተዋናይ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ጃዋር መሀመድ በአባቱ የመናዊና በእናቱ ደግሞ ወሎ እንደሆነ ይነገራል። ሌላው የሚናፈሰው ደግሞ ጃዋር በአባቱ ኦሮሞ ሲሆን በእናቱ መንዜ ነው እየተባለ ነው። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ የኦሮሞ መጨቆንን የሚያነሱት ኤሊት ነን ባዮች ከደሃው የህብረተሰብ ክፍል የወጡ ሳይሆን በሶሻል ስታተሳቸው ሻል ካለ ቤተሰብ ከመጡና የመማር ዕድልም ለማግኘት ከቻሉት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ቀደም ብለው ከውጭው ዓለም አገር ግኑኝነት ስለሚፈጥሩና የጥላቻ ሰለባ ስለሚሆኑ ፖለቲካ የሚባለውን ትልቅ ፅንሰ-ሃሳብ የራሳቸው ጥቅም ማስጠበቂያ አድርገው በመውሰድ ሰፊውን ህዝብ ወደማሳሳት ያመራሉ።
ያም ሆነ ይህ የኦሮሞ ኤሊት ለማሳመን እንደሚሞክረው የኦሮሞ ብሔረ-ሰብ ቁጥር በምንም ዐይነት 31ና50 ሚሊዮን ሊሆን አይችልም። አንድንም ብሔረ-ሰብ በጎሳ እየለያዩ ቁጥሮ ይህን ያክላል ማለት ለሳይንሳዊ ትንተናና ለኢኮኖሚ ፕላኒንግ በፍጹም የሚያመች አይደለም። በታሪክ አጋጣሚ የኦሮሞ ብሔረሰብ በመስፋፋቱና በሄደበት ቦታ ሁሉ ከሌላው ጋር በመጋባቱና በመዋለዱ፣ በዚህም የተነሳ የቋንቋ ተፅዕኖ ስላደረገ በቁጥር ይበልጣል የሚያሰኘው አንዳችም ሳይንሳዊ መረጋገጫ ሊኖር አይችልም። ለአንድ ምሁር ወይም የፖለቲካ ታጋይ ነኝ ለሚል ዋናው መለኪያ የአንድ ብሔረ-ሰብ በቁጥር በልጦ መገኘቱ ሳይሆን፣ የምርምር መነሻውና የአተናተን ዘዴው፣ በዚያ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኘው የፖለቲካና የመንግስት አወቃቀር፣ በዚህም የተነሳ የኢኮኖሚና የማህበረሰብ አደረጃጀት፣ ስለሆነም ብሔራዊ ሀብት የመፍጠርና ያለመፍጠር ጉዳይ ናቸው መነሻና ሳይንሳዊ መንገድ መሆን ያለባቸው። ከዚህም በመነሳት ስልጣንን የጨበጠየገዢ መደብ ከውጭው ዓለም ጋር ያለው ፓለቲካዊ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ ግኑኘነትና፣ ይህ ዐይነቱ ግኑኝነት የዕድገት አጋዥ ነው ወይስ ሀብትን የሚያዘርፍና ወደ ጦርነት እንድናመራ አድርጎ የተደላደለ ህብረተሰብ እንዳንገነባ የሚያግደን ነው? የሚለው የምርምርና የአተናተን ዘዴ ትክክለኛው ሳይንሳዊ መንገድ ነው። በዚህ አማካይነት ይህንን መሰረት በማድረግ ነው፣ ስለ ፖለቲካ፣ ስለማህበራዊና ስለኢኮኖሚ እኩለነት ወይም ፍትሕ መታገልና የተደላደለና ጤናማ ህብረተሰብ እንዲፈጠር የሚቻለው። አንድን ህብረተሰብ በብሔረ-ሰብ ደረጃ እየከፋፈሉ መቁጠር የሚያመቸው ዕድገትና ስላምን ለሚቀናቀኑ ኃይሎች ብቻ ነው። ስለሆነም ማትኮር ያለብን ስለጠቅላላው ህዝባችን አኗኗርና፣ አሁን ካለበት አስከፊ ሁኔታ እንዴት አድርገንና በምን ዐይነት ስትራቴጂያዊ ዘዴልናወጣው እንችላለን በሚለው መርህ ላይ ብቻ ነው ። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ትግል ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ያራዝማል። በጦርነት ዓለም ውስጥ እንድንኖር ያስገድደናል።
fekadubekele@gmx.de
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ህዳር22 ፣ 2016 ዓ.ም
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Such individuals represent and serve themselves. They deliberately put and locked inside a trashed box nobody want.
What can honest Ethiopians do about such individuals? Cursing, alienating, condemning is not the right way. They need to be allowed time to reflect on their chooses.
We learned that the London guy was a Derg cadre. Even some said he has a kind of criminal background. If his background is true, what do we expect of him, if there is anything to expect.
Mr. Gewhar is a naive ambitious young man who wants to be famous and rich. His aim is to exploit the political nature to his advantage, so that he can build a media empire.
There are lots and lots of brilliant, well educated, versed with national and international politics Oromo origin Ethiopians who are currently on the frontline inflicting huge damage to the base of tyrany.
We need to compare the achievements between fourty something years of OLF travel and the two years peaceful protest of fearless, courageous Ethiopian youth.
However insignificant the influence of such groups and individuals, they have kept their relatives, close friends, acquaintances, and few confused individuals away from the popular protest. In aggregate that could be several hundreds, but the protest is in millions. Honest and true citizens of Ethiopians who are currently struggling and paying dear price do not bother at all about what these individuals are talking.
They make good news. That is all.