የሕይዎት ዋስትና ፤ የፍጥረቱ ሲሳይ
ሃሌታዊ ጀምበር ፤ ለዚህች ማሕሌታይ
የተስፋ ብርሃን ፤ የማለዳ ፀሐይ
የድል በረከቱ ፤ መከራን ገላጋይ
እፎይታን አስኮምኳኝ ፤ ሁሉንም አማላይ
ኧረ ምን ነው ቀረሽ ፤ እባክሽ ቶሎ ነይ፡፡
አዝርቱን ውርጭ መታው ፤ ቀረ እንደ ጫጨ
አውድማው ነጠፈ ፤ ዘር መክለፍት ተፈጨ
ሁሉም በቁር ጠፋ ፤ ውሽንፍሩ አፋጨ
ሕይዎት ያለው ፍጥረት ፤ በአጭሩ ተቀጨ
የማለዳ ፀሐይ ፤ ሕይዎት መታደያ
ምን ነው በአፍሪካ ፤ ምን ነው በኢትዮጵያ
ሌሊቱ ረዘመ ፤ ምንድነው ምክንያቱ
አትወጭም እንዴ! ፤ ገደለን ምኞቱ
የድል ፍሬ ፀሐይ ፤ የፍጥረት ሕይዎቱ
በነፍስ ድረሽልን ፤ ይንጋልን ሌሊቱ፡፡
ቁር የቀፈደደው ፤ ያስቀመጠው አስሮ
ልሳኑ የተያዘ ፤ የደረቀው ከሮ
በሙቀትሽ ይንቃ ፤ ይፈታ ሞት ሽሮ
እንደባከነ አይሙት ፤ ቀን ከሌት ተባሮ
ፍጥረት ሕይዎት ያግኝ ፤ በረከት ከአዶናይ
የትግል ፍሬ ፀሐይ ፤ እባክሽ ቶሎ ነይ፡፡
ነፍስሽ ያለው ሁሉ ፤ አንቺ የሆንሽ ሕይዎቱ
ከክቡሩ የሰው ልጅ ፤ እስከ ሕዋሳቱ
ከእጽዋት አዝርእቱ ፤ እስከ አእዋፋቱ
ከእንስሳት ዓሣቱ ፤ እስከ አራዊቱ
አንችን ያግኝና ፤ ይስመር የምኞቱ
ቀየው ጥጋብ ይሁን ፤ እፎይታን ያሽቱ፡፡
ሌሊቱ እረዘመ ፤ ሰው ተስፋ ቆረጠ
አንቺን መበጠበቅ ፤ ቀረ እንዳንጋጠጠ
ይህ ድቅድቅ ጨለማ ፤ የአጋንንቱ አሽከላ
ስንት ከዋክብት ዋጠ ፤ ስንት ሻማ በላ
እንችን እንዳያነጉ ፤ ወዲያ እንዳይከላ፡፡
ተስፋ ነጥፎ ጠፋ ፤ ትውልዱ ታበጠ
መተሽ ነፍስ ዝሪበት ፤ ያንችን ቀን ቋመጠ
ስትዘገይበት ፤ ተስፋ እየቆረጠ
ጨለማን ለመሸሽ ፤ ሁሉም ፈረጠጠ
እግሩ ወዳመራው ፤ ሔደ ሸመጠጠ
ሀገር እየጣለ ፤ ራሱን እየሸጠ
የደም መለያውን ፤ ከድቶ እየለወጠ
ሀገር ወና ቀረች ፤ ውድማው አረጠ
ሁሉም ባዶ ሆነ ፤ ባዶነት ፈጠጠ
አድባር ውቃቤ (ዐቃቤ) አጣ ፤ ቀልብ ደነገጠ
የድል ፍሬ ፀሐይ ፤ የፍጥረት ሕይዎቱ
የማለዳ ፀሐይ ፤ አንቺ አማላይቱ
በነፍስ ድረሽልን ፤ ይንጋልን ሌሊቱ፡፡
ጅቡ ይብላኝ እንጅ ፤ ጥርሱን እያፋጨ
ዐይኔን ወደ ምሥራቅ ፤ ሌሊቱን አፍጥጨ
አንችን እጠብቃለሁ ፤ ጨክኘ ቆርጨ
በአጋንንት ጥቃት ፤ ነፍሴን አስደንግጨ
ወደ ቤት አልገባም ፤ በፍርሐት ፈርጥጨ
ጉልበቴን አጽንቸ ፤ ፍርሐቴን ውጨ
እጠብቅሻለሁ ፤ ሞትን ተጋፍጨ
ተስፋ ላልቆረጠ ፤ በእምነት ለጸና
ምኞቱ ይሠምራል ፤ ቃሉም ይላልና
የጽናቴን ዳር ጫፍ ፤ ከጎሕ ሳላገናኝ
በፍጹም አልገባም ፤ መኝታም አልመኝ
ከቅጽበት የኋላ ፤ ሲደርስ መጨረሻው
ሊነጋ ሲል ሲከብድ ፤ ያ ድቅድቅ ጨለማው
አዎ ሊነጋ ሲል ፤ ጨለማው ግን ሳይገፍ
እሳት የመሰለ ፤ የሰሌዳሽን ጫፍ
ሳላይ ሳላረጋግጥ ፤ የመውጣትሽን ዜና
በጭራሽ አልገባም ፤ ምን ጻዕር ቢጠና
ገብተህ የተኛኸው ፤ ተስፋ ቆርጠህ በኛ
ጨለማን ሳትፈራ ፤ የጋኔን መጋኛ
የአራዊቱን ፉጨት ፤ ያበጠውን ሻኛ
ውጣ ተቀበላት ፤ ጥራት እንድትወጣ
ትንቢቱ እንዲፈጸም ፤ ያ ቀን እንዲመጣ፡፡
ጨለማ የሚያስፈራው ፤ ሰይጤ የሚጥል ገሎ
ብቻ ሲያገኝ ነው ፤ ያለን ተነጣጥሎ
ቆርጠህ ብትወጣ ፤ በመስክ በጎዳና
ሆ ብለህ በአንድነት ፤ ሸንጦህ ፍነና
ጨለማም ጋኔንም ፤ ኃይላቸው ይወድቅና
ጀምበር ትወጣለች ፤ ይዛ የተስፋ ፋና፡፡
እናም ውጣ ውጣ ፤ ስማ አንተም አሰማ
የአውሬ ሲሳይ ሳትሆን ፤ ሳይውጥህ ጨለማ
ሀገርህ ነግቶላት ፤ ወግ ደርሷት እማማ
በቀናው መንገድ ላይ ፤ ተደላድላ ቆማ
ሳታያት እንዳትቀር ፤ ዳኛ ተሠይማ
ውጣ ውጣ ውጣ ፤ ይህ ነው ያደራ ዓላማ፡፡
ኅዳር 21 2007ዓ.ም.
Leave a Reply