በርካታ ከሳውዲ ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ ዜጎችን በሚመለከት የጀርመንና የአሜሪካ ራዲዮን ጨምሮ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን አንድ አይነት የሚመስል መረጃ ግፉአን ተመላሾችን እማኝ እያደረጉ መረጃ አቀብለውናል ። “ራፕለር ” በታዝነው ሳምንት ባቀበለን መረጃ ሻንጣቸው ጠፍቷቸው በአንድ የሻንጣ ማጠራቀሚያ ግቢ ሻንጣቸውን ሲፈትሹ የሚያሳየውን ፎቶ አስደግፎ የተመላሾችን አስተያየት አካቶበታል። ዜጎች ወደ ሳውዲ ሲሰደዱ ከቤተሰብ ፣ ከዘመድ አዘመድ አዝማድና ከተለያዩ ቦታወች የወሰዱትን የብድር ገንዘብ ስላልመለሱ ኑሯቸው የሰመረ እንዳልሆነ እየተናገሩ ነው ። ሃገር ቤት ገብተው የስራ ማጣት እና እሳት የሆነው የኑሮ ውድነት ግራ ያጋባቸው በርካቶችም አሁንም መልሰው ለስደት እንደቋመጡ እኛ የምንቀርበው መረጃ ባይስማማ የፈረንጆቹ መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡት የገሃዱን እውነት አንድምታ ያሳያል።
በግል ሃገር ግብተው የማገኛቸውን በርካቶች ሃገር ቤት ተመልሰው የጋጠማቸው የኑሮ ውድነት አማሯቸዋል። መልሶ ማቋቋሙ ደግሞ ከወሬ ባለፈ አለመጀመሩን እየሰማን ነው ። ባሳለፍነው እሁድ በጀርመን ራዲዮ እንዎያይ ፕሮግራም የቀረበው ተመላሽ ወንድምም ተመላሾችን በማደራጀቱና መልሶ በማቋቋሙ ረገድ የተጀመረ ነገር እንደ ሌለ መረጃውን አካፍሎናል። በአንጻሩ በመንግስት ኢቲቪና የቀሩት በስሩ የሚተዳደሩት መገናኛ ብዙሃን የሚናገሩት የሚታመን ከሆነ “ተመላሾቹ በየክልሉ ተደራጅተው እራሳቸውን የሚያቋቁሙበት ስራ ተጀመሯል!” የሚል መልካም መረጃ እያስተላለፉ ይገኛሉ …ከዚህ ጋር ያያዝኩት አዲስ ዘመን ጋዜጣ “ከስደት ተመላሾች ሥልጠና ጀምረዋል !” በሚል ሁላችንም ሳውዲን ለቀን ወደ ሃገር እንገባ ዘንድ የሚያበረታታ መልካም የብስራት ዜና አሰራጭቷል። … እውነት ከሆነ ማለቴ ነው ! ይህንን አሻግሮ ተቀምጦ “እውንት እውሸት “ማለት አይቻልምና ሊናገሩ የሚገባቸው ባለቤቶቹ ብቻ ናቸው ። ተመላሾች ሆይ ምን ትላላችሁ?
አለም አቀፉ የስደተኞች ተጠሪ IOM መስሪያ ቤት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም $13.1 ሚሊዮን ዶላር ወይም 9.5 ዩሮ እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርጓል ። የስደተኞች ንብረት በተለይ የሻንጣ ጌጣጌጡን መጥፋት ጉዳይ አሳሳቢነት ግን ከፍተኛ ሃላፊዎችን ሳይቀር ያስደመመ እንደሆነ በሚሰራጩት መረጃዎች ለመረዳት አልገደደንም ።
“ወደ ሃገር ግቡ አንገባም ፣ እንግባ አትገቡም …”
ከአሰሪያቸው ጋር የማይሰሩና በህገ ወጥነት የተፈረጁ ዜጎች ወደ ሃገር እንዲመለሱ የሚጠይቀው የሳውዲ መንግስትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኢንባሲና የቆንስል መስሪያ ቤቶች ጥሪ ነው ። ጥሪው በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰነዳቸውን ያላሟሉ የሚባሉት በባህር በኡምራና ሃጅ ብቻ ሳይሆን በስራ ኮንትራት መጥተው ከአሰሪዎቻቸው ጋር የማይሰሩ “ህገ ወጥ ” የተባሉ ዜጎች ግን “ሳውዲን ለቃችሁ ውጡ! ” የሚለውን ጥሪ ችላ በማለት ዘና ብለው የተለመደ ኑሯቸውን መኖር ጀምረዋል። ፍርሃትና ጭንቀቱ የት እንደገባ ባይታወቅም የሳውዲ መንግስት ባሳለፍነው ሳምንት ጉዳያቸውን ጀምረው ላልጨረሱ የሰጠው የሁለት ወር ማስተካከያ ጊዜ ገደብ ነዋሪውን ያዘናጋው ይመስላል። ያን ሰሞን በስጋት እቃቸውን ሲጠራርፉ የነበሩት ዛሬ እቃቸውን ወደ ነበረበት መልሰው የለመዱትን የመዘናጋት ኑሮ መግፋት ይዘዋል። አንዳንዶቹን ጠይቄያቸው “ዛሬም የሳውዲ መንግስት አይጨክንም ህጉን ያሻሽለዋል !” በማለት ሲመልሱልኝ አንዳንዶቹ ደግሞ “ሃገር ቤት የሄዱት የኑሮ ውድነት እያማረራቸው እየሰማን መሄዱ ማበድ ነው “ሲሉ መልሰውልኛል ። እስርና ቅጣቱስ አልኳቸው እንዴት ትቋቋሙት አላችሁ? አልኳቸው ” የፈለገው ቢሆን እዚሁ ሁኔ መቋቋም እና መቀበሉ ይቀላል !” ሲሉ ክችም ያለ መልስ ሰጥተውኛል ! እኒህ ለእኔ ቀቢጸ ተስፈኞች ናቸው ..
የሳውዲን መንግስት ወደፊት ጠንከር ብሎ ይወስደዋል ተብሎ የሚጠበቀውን እርምጃ የፈሩ ጥቂቶች አሁንም ወደ መጠለያ በመግባት እና ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው። ያም ሆኖ በጅዳ የሽሜሲ መጠለያ ሰነዳቸው ይሰራላቸው ዘንድ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ በስልክ እየደወሉ “ተቸገርን! ።የምግቡ ችግር ቢቻልም ፣ በመጓጓዙ ላይ ዘገየን፣ መላ ወደሚገኝበት ቦታ ጩኸልን !” እያሉ ተማጽነውኛል ። ትናንት ሰኞ ከቀትር በኋላ ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት መረጃ ያቀበሉኝ “ከመዲናና ከጅዳና ከተለያዩ ቦታወች ከቀናትና ከሳምንታት እና ከወር በፊት ወደ ሽሜሲ ገባን!” ያሉኝ ወገኖች ” ጉዟችን ለማፋጠን በቆንስላችን ክትትልና ትብብር ስለማይደረግልን እየተጉላላን ነው !” ሲሉ ጭንቀታቸውን ገልጸውልኛል። በኮንትራት ስራ የመጡትን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ችግሩ መቋጫ አግኝቷል ቢባልም አሁን ድረስ ችግሩ አለመፈቱን ነዋሪዎች ከሽሜሲ መጠለያ በምሬት ገልጸውልኛል ። “ካለፉት ሶስት ቀናት ወዲህ ወደ መጠለያ ለመግባት ፈልገን ወደ መጠለያ የሚወስደን የሚቀበልን አጣን! ውጡ ብለውን እንውጣ ስንል የሚያስወጣን አጣን !” ያሉኝ በርካቶችም በጅዳ ሸረፍያ እንደሚገኙ አጫውተውኛል ። ህግን ተጋፍተው በሳውዲ ለመኖር ተስፋቸው የተሟጠጠ እንህኞች የሚደግፋቸው ይሻሉ … !
የጀዛን … እውነት
በጅዛን በተደጋጋሚ የሚደርሰኝ መረጃ በማቅረቤ ያን ሰሞን የወገን ለወገን ደራሽ ኮሚቴን የጠለፉት የመንግስት ፖለቲካ ድርጅት አንዳንድ ካድሬዎች እዚህ ጅዳ ከጎኔ ተቀምጠው አዲስ የማጥላላት ዘመቻ ጀምረዋል። የወገንን ሳይሆን ለመንግስት ሃላፊዎች በማደገግደግ እንደፈለጉ በሚፈነጩበት የህዘብ ግንኙነት የፊስ ቡክ ገጽ ” እውነቱ ይሄ ነው ” በሚል ባስነበቡን መረጃ የእኔን ሳይሆን የተበዳዮችን እውንት ጥላሸት ሊቀቡት ከጅለው ሳይ አዝኛለሁ። “በሉ !” ትዕዛዙን ይፈጽሙ ዘንድ አንደተባሉት በማስተጋባት እውነቱን ” ውሸት!” ብለውታል። ሳያፍሩ፣ ሳይፈሩ!
የተሳሳተ መረጃ ደረወሶኝ ይሆን ስል አጠራጠሩኝ ። ግን እንዲያ አልነበረም ። መረጃውን ለማጣራት ጅዛኖችን ደጋግሜ “ሃሎ” ብያቸው ነበር … ያገኘኋቸው አስገራሚና አሳዛኝ መረጃዎች ” አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል !” አስብሎኛል ። ከህግ ታሳሪዎቹ ጋር በነበረኝ ቆይታ “የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች የእናንተን ጉዳይ እየሰሩ እንደሆነ ተነግሮኛል ፣ እውነት ነውን? !”ያልኳቸው ወንድሞች የተባለው መረጃ ትክክል አለመሆን ተበሳጭተው የሚጠይቅላቸው ስላጡትነና በሚሰራው ስራ ዙሪያ ብዙ አጫውተውኛል ። በአሳዛኝ እና በአስገራሚው የስደት ህይወት እጁ የተቆረጠውን ወንድም ፣ ታናሽ ወንድሙን እና እሱ በርሃ ላይ ሲጓዙ ተይዘው ዛፍ ላይ ታስረው ተንጠልጥለው ሲውሉ አቅም አንሶት ከፊቱ ላይ ደክሞ ተዝለፍልፎ የሞተ ታናሽ ወንድሙን ታሪክ ወንድሙ ራሱ ይነግረናል … ይህ ወንድሙን በበርሃ ላይ ያጣ ወንድም ስድስት ወር እንዲታሰር ቢፈረድበትም ከአመት በላይ ጠያቂ አጥቶ መንገላታቱን መስማት ያማል ! ይህንንም በድምጽ ይዠዋለሁ ! ትሰሙታላችሁ … እናም በጀዛን ፍርዳቸውን የጨረሱ የህግ ታራሚዎች ድምጽ “ወደ ሃገር እንድንገባ ድጋፍ የሚያደርግልን የመንግስታችን ሃላፊዎችን አጣን ! ” የሚል ነው ! የጅዛን እውነቱ ይህ ነው!
መንግስት ሆይ ስማን … ወገን ሆይ ስማን!
ሰነድ የሌላቸው ዜጎች “ህግን ተላልፋችኋል!” ተብለው “ከሃገር ይውጡ!” ተብሏል! ዜጎች ከሃገር ውጡ ሲባሉ መንገዱን በማመቻቸቱ ረገድ ከኢትዮጵያ መንግስት የኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች ከመረጃ ጀምሮ ብዙ ይጠበቃል! ቢያንስ ሁሌ እንደምለው “መውጣት አልፈልግም !” የሚለውን ዜጋ ምክንያት ሊሰማበሊደመጥ ይገባልና ፣ ስሙት ! ” እንውጣ!”ሲል እንግልት የሚገጥመውን ዜጋ ታደጉት! በአረብ አሰሪዎች ቤት ሆነው “ወደ ሃገራችን እንግባ ድረሱልን!” የሚሉ የኮንትራት ሰራተኞችን ያላባራ ጩኸት ይሰማል ። የሰማነውን ለሃላፊዎች ብናሰማም መፍትሔ የሚሰጥ ጠፍቷል! ይሀወ አሁንመወ ያሳስባል! “ድረሱልን! ” ሲሉ ደራሽ ያጡትን የኮንትራት ሰራተኞች ፈጥናችሁ ድረሱላቸው! መውጣት ያለበት “ህገ ወጥ ” የተባለ ሁሉ ዜጋ ይውጣ ! አስከፊውን የስደት እንግልትና መከራን ማየቱ ይብቃን!
ሰው ተጨንቆ ተጠቦ ፣ የመረጃዎችን እውነት እውሸት የሙግት ጅማሮ ቀልቤን ባይስበውና መነታረኩን ባልፈልገውም ለሚወረወረው አሳሳች መረጃ እውነቱ ለማስጨበጥ ስድቡን ባልገባበትም ትክክለኛውን መረጃ ከምንጩ ለማቅረብ ወደ ኋላ የምል አይደለሁም! ይህም በመሆኑ ይህንና ያንን በሰፊው እስክመለስበት ሰላም !
አስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
Leave a Reply