ለብዙ ኢትዮጵያዊያን፤ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠልና የአገነጣጠሏ ሁኔታ፤ የውስጥ አካላችንን ያኔም፣ አሁንም እያንጠረጠረው ነው። በርግጥ በየኪሳችን ያለ የየግል ንብረት ስለተነጠቀብን አይደለም። በኤርትራ መገንጠል የቀረብን የግል ጥቅም ስለነበረም አይደለም። የሀገር ጉዳይ፤ ከንብረት፣ ከአባትና እናት፣ ከኑሮ የበለጠ ክብር የምንሠጠው ነው። በወቅቱ የቅርብ ጓደኛዬ የነበረ ኤርትራዊ፤ በኤርትራ መገንጠል ፍንደቃው ጊዜ አልሠጥህ ብሎት፤ መኖሬንም ረስቶ፤ ለሳምንታት ከወገኖቹ ጋር ሲጨፍር ከረመ። በመጨረሻም ቀን ቀንን እየወለደ፤ ሳንገናኝ ብዙ ጊዜ አለፈ። መራራቅ መራራቅን ነውና የሚያስከትለው፤ በየጎጣችን ተሸጉጠን፤ በመካከላችን የነበረው ጓደኝነት፤ ጊዜን መቀራረብ አላድሰው አለና ጠፋ። በርግጥ እኔም መላዕክ አልነበርኩም። ልክ ያለሁበት ቤት እንደተቃጠለ፤ በግል ሰው እንደበደለኝ፤ ብሽቀት ሰውነቴን ወሮት፤ እልህ ዓይኖቼን አውሯቸው፤ ንዴቴን የማሳርፍበት አጥቼ፤ መለስ ዜናዊንና ኢሳያስ አፈወርቂን አግኝቼ አንቄ ልገድላቸው ተመኝቼ ነበር። በዚያ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ብቻ መላ ሰውነቴን ወራው፤ የግል ጓደኝነት ሆነ የግል የሚባል ነገር ቦታ አልነበረውም። እናም የኤርትራ መገንጠል ልቤን ስለቦረቦረው፤ ከያዝኩት ሰውነት የቀረበ ስላልነበረኝ፤ ለምንም ጉዳይ ቦታ አልሠጠሁም ነበር። ምግቤንም እንዴት እንደበላሁት፣ በውቅቱ ሥራዬንም እንዴት እንደሠራሁ፤ የቤት ኪራዬን እንዴት እንደከፈልኩ ማሰቡ ይቸግረኛል። እናም ለኤርትራዊው ጓደኛዬ አሳቢ ነበርኩ ብዬ አልዋሽም።
በቅርብ ጊዜ አንድ ኢሜል ደረስኝ። የላኪውን የኢሜል አድራሻ ስላልለየሁት፤ ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያው ልልከው ምንም አልቀረኝም ነበር። ፈታሻ እንከን አጽጂ መርማሪዬ ንጹህ ነው ሲለኝ፤ ከፈትኩት። የቀድሞ ትዝታውን ጠቃቅሶና እኔ በየድረገፆች የማወጣቸውን ጽሑፎች እንደሚመለከታቸው ገልጾ፤ መገናኘት እንደሚፈልግ የጻፈልኝ፤ የድሮው ኤርትራዊ ጓደኛዬ ነበር። ተገናኝንና ብዙ ተጫወትን። እንዳስቀየመኝ እያወቅሁ፤ ለምን እሺ ብዬ እንዳገኘሁት ጠየቀኝ። እኔም እንኳን እሱን፤ በዓለም ዙሪያ እዚህ አሜሪካ መጥቶ ከሚኖር ሰው ጋር ሁሉ ወዳጅነት እንደማደርግና፤ ለኔ በስደት ሀገር፤ የፖለቲካ ጉዳይ እንጂ የሰው ጠላት እንደሌለኝ ገልጨለት፤ ጭውውታችን ቀጠልን። ብዙ የምንስማማበት ጉዳይ ነበረን። የሁለታችንም ፍላጎት አልተሟሉም። ሁለታችንም የኢሳያስ አፈወርቂና የመለስ ዜናዊ ጠላቶች ነን። ኤርትራ ከሕልም ቅዠት ወጥታ አንዲት እርምጃ ወደፊት ካለመሄዷ አልፋ፤ ወደኋላ ተጉዛለች። ኢትዮጵያም በሰመመን አለች የለችም የምትባልበት እንጥልጥል ላይ ሆናለች። ሁለታችንም ልባችን ተሰቅሏል። እናም በመካከላችን የነበረው አራራቂ ፖለቲካ፤ ገደል ገብቷል። እኒህ ሁለት መሪዎች፣ እኒህ ሁለት አጥፊ ድርጅቶች፣ እኒህ ሁለት አፍራሽ የፖለቲካ አመለካከቶች ያደረሱትን ጉዳት በአንድ መነፅር ማየት ቻልን። ሁለታችን፤ እኒህ መናጢ እርጉሞች አልን።
በጭፍን ወደፊት መሄድ፤ መደናበር ነው። አዎ! ኤርትራ ሀገር ተብላ የራሷ ስንደቅ ዓላማና የራሷ አምባሳደሮች አሏት። ደንበሯም ከሱዳንና ከጅቡቲ ጋር የተከለለ ነው። በርግጥ ከ”ጎረቤቷ” ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግልጽ አይደለም። እንግዲህ፤ ይሄ ጉዳይ ለያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምን ማለት ነው? ኤርትራ በአሰብ ወደብ ዙሪያና በባህር በርነቷ ብቻ የምትታይ ናት ወይ? የዓለም ፖለቲካስ በዚህ ረገድ ያለው እምነት ምንድን ነው? የዓለም ፖለቲካስ በዚህ ረገድ በተግባር ምን ፈጽሟል? ዓለም ዛሬ የደነገገውን ነገ የሚያፈርስበት ሀቅ አለ ወይ? በዚህ ላይ ነበር እኔና ኤርትራዊው የቀድሞ ጓደኛዬ፤ የዛሬው አዲሱ ትውውቄ የተነጋገርነው። የደረስንበትም ስምምነት እንዲህ ነበር።
መጀመሪያ በጊዜው የተደረገው የፍጥነት መገንጠል ትክክል እንዳልሆነ ተስማማን። ታዲያ እንግዲህ፤ ከዚህ የመነጨው ሁሉ ስህተት ነው፤ ማለት ነው። አፈጻጸሙም ሆነ ፍጻሜው ትክክል ያልሆነ ጉዳይ፤ ሄዶ ሄዶ ሊፈጥር የሚችለው፤ ያው ድንብርብር ነው። እናም ላሁኑ ላለንበት ሁኔታ ተጠያቂው፤ ወገንተኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባና ሕዝባዊ ኃይልታት ሓርነት ኤርትራ – ሸዓቢያ ናቸው። በነዚህ ድርጅቶች የሚመሩ መንግሥቶች፤ መፍትሔ ፍጹም ሊያመጡ አይችሉም። እንዲያውም እኒህ ሁለት ድርጅቶች የሕዝቡ ጠላቶች ናቸው። እናም መደምሰስ አለባቸው ነው። ቀጥሎ ደግሞ፤ ለማንኛውም ወደፊት ለሚቀርብ መፍትሔ፤ መጀመሪያ የተደረገውን በመመርመር፤ ስህተቱንና ጉድለቱን አጣርቶ ማውጣት አስፈላጊ ነው። አሁን በተግባር ላይ የዋለው የኤርትራ መገንጠል፤ ማንን ጠቀመ? ብለን ስናጤን፤ ሁለት እንዳሻቸው የሚያደርጉ አምባገነኖችን ከመፍጠር በቀር፤ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮም ሆነ የልማትና ሰላም መንገስ፤ ጉዳይ ቦታ አላገኘም። ስለዚህ፤ የምክክርና የመፍትሔ አፈላላጊ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከዚህ በተረፈ አሁን በጎን ሁሉም እንዳለ፤ እንዴት ሁለቱ ሀገሮች በሰላም ይኑሩ? እንዴት ልማትን ያስተባብሩ? እንዴት የአሰብን ጉዳይ ይወስኑ? እንዴት የየግል መሪዎቻቸውን ያጥፉ? እና የመሳሰሉት ውይይቶች፤ የአፍ ማልፊያና ጊዜ ማጥፊያ ከመሆን አያልፉም። ኤርትራዊያን ከመሪያቸውና ከመሪያቸው ፖለቲካ ነፃ ሆነው፤ ኢትዮጵያዊያንም ከመሪያችንና ከመሪያችን ፖለቲካ ነፃ ሆነን፤ ከሕዝቡ አንጻር ጉዳዩን መመልከት አለብን።
ምንልባት ስምምነት ላይ መድረስ ካስፈለገ፤ የስምምነቱ ማጥንጠኛ የሚሆነው፤ እኒህን ሁለት መሪዎችና እኩይ መሪ ድርጅቶች እንዴት እናጥፋ የሚለውን ለማስተናገድ መሆን አለበት። በርግጥም የኒህ የሕዝብ ጠላቶች መወገድ መሠረታዊ ስለሆነ፤ እነሱን ለማጥፋት መተባበሩ ግድ ነው። ከዚህ ውጪ ግን ሕዝብ ለሕዝብ የሚል ግንኙነት የወግ ነው። ሕዝብ ግንኙነት ሊመሠርት የሚችለው ነፃ ሲሆን ነው። ነፃ ባልሆነ ሕዝብ መካከል ግንኙነት ለፈጥእር አይችልም። ካለም በታጋዮቹ በኩል ነው። ከርህራሄ ቢሱ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በማበር ወገንተኛ አምባገነኑን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለመደምሰስ፤ ከወገነኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር በማበር ርህራሄ ቢሱን ኢሳያስ አፈወርቂን ለመደምሰስ መነሳት፤ የእሬያ ታጥቦ ጭቃነት ነው። ምክንያቱም፤ ወገነተኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለኤርትራዊያን፤ ርህራሄ ቢሱ ኢሳያስ እፈወርቂ ለኢትዮጵያዊያን፤ አያስቡማና! በርግጥ አኩርፈው ሌላ ቢቀባጥሩም፤ አንዳቸው ለሌላቸው ዘብ ሊቆሙ ይቻላሉ። መመሥረት ያለበት፤ በኤርትራዊያን ታጋዮችና በኢትዮጵያዊያን ታጋዮች መካከል ብቻ ነው።
በተጨማሪ ባሁኑ ሰዓት፤ በምንም መንገድ ቢሆን ሊከተል የሚችለው መፍትሔ፤ በሁለቱ መሪዎችም ሆነ በዓለም አቀፍ ተጽዕኖ፤ መሪዎችን የሚጠቅም እንጂ፤ ሕዝቡን የሚጠቅም ሊሆን አይችልም። ሕዝቡ የሚጠቀመው፤ አፋኝ መሪዎቹ ሲወገዱለትና በነፃ የራሱን ፍላጎት ለማሟላት መወሰን ሲችል ብቻ ነው።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
መስከረም ፩ ቀን፤ ፳፻፰ ዓመተ ምህረት
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply