‶…ልዑሉ በሰዎች መንግስት ሁሉ ላይ ሙሉ ስልጣን እንዳለውና እነዚህንም መንግስታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ…″ ዳን.4፡32
ሉዓላዊ መንግስት (sovereign nation) በሌሎች ቅኝ ግዛት ወይም ባርነት ስር ያልወደቀ ራስ-ገዝና ነጻ መንግስት ሲሆን የሃገሪቱ የአመራር አካላት እንደመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካላት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ የህዝቡም ሰላምና የሁለንተና እድገት በሃገሪቱ አመራር አካላት ብቃትና ቅንነት ይወሰናል፡፡ ሉዓላዊነት ሌሎች አካላት በአንድ ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ (meddle) ዋስትና እንደሚሰጥ በማሰብ አንዳንድ መንግስታት በማንአለብኝነት ከእግዚአብሔርም ከሰውም የሚያነካካ እርምጃ ሲወስዱ ይስተዋላሉ፡፡
ከነዚህም አንዱ ለትምህርታችን በቅዱሱ መጽሀፍ በስፋት የተተረከልን የባቢሎን ንጉስ ናቡከደነጾር ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ባርያዬ/አገልጋዬ እያለ ደጋግሞ የሚጠራውና ስኬትን ያበዛለት ንጉስ የዙፋኑንና የስኬቱን ምንጭ ዘንግቶ በብዙ ትዕቢትና ነውር ሲመላለስ የምድር ነገስታት ገዢ ከሆነው ከልዑል (the most high) እግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ወጣ—‶መንግስት ከአንተ ዘንድ አለፈች″ (ዳን.4፡31)፡፡ እንደጥፋቱም ጥልቀት አስተማሪ የሆነ ተጨማሪ ቅጣት ተበየነበት—‶ለሰባት ዘመን እንደአውሬ በዱር ተሰድደህ ትኖራለህ″ (ዳን.4፡32)፡፡ ንጉሱን ለዚህ ሁሉ ቅሌት ያበቃው ከላይ በርዕሱ እንደተጠቀሰው ልዑል እግዚአብሔር በሰዎች መንግስት ሁሉ ላይ ሙሉ ስልጣን እንዳለውና ሹም ሽርም በእጁ እንደሆነ አለማወቁ ነበር፡፡
ልዑል በሉዓላዊ መንግስት እንዲሰለጥን የሃገሬ መሪዎች ያውቁ ይሆን?
መሰልጠን ማለት ያገባኛል በሚልና በባለቤትነት መንፈስ በሃይልና ስልጣን በሰዎችና አሰራራቸው ላይ ጣልቃ መግባት ማለት ነው፡፡ እውነት ነው የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት በሉዐላዊ መንግስት አመራርና አሰራር በቀጥታ መሰልጠን አይችሉም፡፡ ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔር የኢህአዲግን መንግስት ጨምሮ በሁሉ ይሰለጥናል፡፡ ‶ከፍ ካለው በላይ ከፍ ያለ ይመለከታልና″ (መክ.5፡8) ልዑል በሰው ልብ የታሰበውን፣ በጓዳና በአደባባይ የሚደረገውን ያውቃል፡፡ እርሱን ፈርተን ህዝቡንም አክብረን በመልካም ብናስተዳድር ስልጣናችን ይጸናል/ይረዝማል፤ መተካታችንም በክብር ይሆናል፡፡
እንደባቢሎኑ ንጉስ እግዚአብሔርን ባለመፍራትና ሰውንም ባለማፈር በምንወስዳቸው እርምጃዎች ልዑሉ ሊንቀን፣ መንግስትን ሊነጥቀን፣ በግል ሊቆነጥጠን፣ ለወደድነው ሳይሆን ለወደደውም ስልጣኑን ሊሰጥ ይችላል፡፡ በተለይም እንደኢትዮጵያ ባሉ በጸሎት የሚበረቱ የእምነት ሰዎች ባሉበት ሃገር የልዑል ጣልቃ ገብነት ይፈጥናል፡፡
በገዛ ስልጣኑ መንግስትን ከደርግ ነጥቆ በሃገራችን የሾማችሁ የኢህአዲግ አመራር አካላት እያደገ ከመጣው የማንአለብኝነት አካሄድ ተመልሳችሁ በህዝቡና በእግዚአብሔር ፊት ቅንነት ያለበትን እርምጃ እንድትወስዱ አበረታታለሁ/እጸልይማለሁ፡፡ ናቡከደነጾር ተጸጽቶ ከክፉ ስራው በተመለሰ ጊዜ መንግስቱን እንደመለሰለት/እንዳጸናለት ምናልባትም ሽንገላ የሌለበትን የተሃድሶ እርምጃችሁን አይቶ ልዑል ህዝቡን ዳግም ሊያስገዛላችሁና የስልጣን ዘመናችሁንም ሊያረዝም ይችላል፡፡ በልበ-ደንዳናነት በአመጽ ብንጸና ግን ያሰማራነው ጦር እንኳን እግዚአብሔርን የህዝቡንም እንቅስቃሴ ሊያስቆም አይችልምና ለዘር ማንዘር የሚተርፍ ጠባሳ ትታችሁ እንዳታልፉ በጌታ ፍቅር አሳስባለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የአብያተክርስቲያናት መሪዎች እንደባለአደራ ነብያቶችንና ሊቃውንቱን አማክራችሁ የእግዚአብሔርን ሃሳብና የህዝቡ/መንግስት ምላሽ ምን ሊሆን እንዲገባ ምክር እንድትሰጡ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
‶እግዚአብሔር ሆይ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ″ ዘፍ.49፡18
ዶ/ር ሳምሶን—ከሃገር ቤት
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply