ፈታኙን ወቅት ለማለፍ …
የሳውዲ የምህረት አዋጅ አልቆ በሪያድ መንፉሃ ላይ አለምን ያሳዘነ ሰቆቃ ተፈጸመ …ስጋት ነግሶ ፣ ኑሮ ከብዶን ጨንቆን ጠቦን ከርመናል! በዚህ ክፉ ቀን ወገን ወገኑን ለመርዳት ደፋ ቀና በማለቱ ረገድ የሃገሬ ልጅ ከጫፍ እስከ ጫፍ በቁጭት ስሜት ሲንቀሳቀስ የፖለቲካው ትኩሳት ወላፈን እያጓተተን አልሰነበትንም አይባልም። ግልጥልጥ አድርግን እናውራ ካልን የኑሮ ውድነት እና ድህነቱ እየደቆሰን ቢያስቸግረን ከወገን ቤተሰቦቻችን ተለይተን ፣ የእማማ ኢትዮጵያውያን ምድር ለቀን በስደት ስንባዝን በደረሰብን የከፋ አደጋ ለመቋቋም ከምናደርገው ትግል ባልተናነሰ ልዩነትን የሚያገዝፉ መሰናክሎችን ማለፉ የከበደ አበሳ ሆኖብን ሰነባብቷል!
በዚህ ፈታኝ ወቅት መፈተን ግድ ሆነና የዜጎች እንግልት ከሪያድ አልፎ ወደ ጅዳና አካባቢው ሲሸጋገር በርካታ ወገኖች በግልና በቡድን በመሰባሰብ በጎ እርዳታ ለማድረግ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ቀጠሉና ወገኖችን ለመርዳት ብቸኛው አደራጅ ለሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ኢንባሲና ቆንስ ነመ/ቤቶች ” ለወገኖቻችን እንድረስ !” በሚል ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አገኘ። የጅዳ ቆንስል በማህበራትና በኢህአዴግ ድርጅቶችን “በነጻ የበጎ እርዳታ ድጋፍ እናቅርብ ” ባይ ዜጎች ጋር ጥምር አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት በአይነቱ ነጻ የተባለውን “ወገን ለወገን ደራሽ ” የተባለውን ኮሚቴ አቋቋመ። ኮሚቴው የእርዳታ እና ድጋፍ ሰጭ፣ የመረጋጋትና የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴን አቋቋመ።
የጅዳ ሸረፍያው ሁከት…
በኮሚቴው መዋቀር መባቻ በጅዳ ሸረፍያ በተባለው አንድ ሰፈር “ወደ ሃገር እንግባ !” ብለው ድልድይ ስር ከተቀመጡ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዲት አራስ እህት “ልጇን ሜዳ ላይ ጥላ ሔደች !” ተባለና ህጻን ወድቆ ተገኘች፣ ያንኑ ቀን ከቀትር በኋላ ሌላ አሳዛኝ ክስተት በድልድይ ተከሰተ። ከድልድዩ የቅርብ ርቀት አንድ ወንድም በድንገት በመኪና አደጋ ሞተ! የቀን ጸሃይ ፣ የማታው ወበቅ ያደከመውን ወገን አስቆጣው። ሸረፍያ ታመሰች! ጸጥታ አስከባሪዎች ጸጥታ ለማስከበር አካባቢውን ከበቡት ፣ ፍጥጫ ነገሰ! በሁኔታውን ግራ የተጋቡት ፖሊሶች ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ ሁከቱን ለማረጋጋት ሞክረው ባይሳካላቸውም ከጅዳ ቆንስል የተላኩ የድርጅት አባላት ሁከቱን ለማረጋጋት ቻሉ !
በተፈጠረው ግርግር የተደናገጡት በድልድዩ ሁለት ሳምንታትን በመከራ የገፉ ወገኖች “ለደህንነታችን ሰጋን! ” ሲሉ በዚያው ምሽት ወደ ጅዳ ቆንስል ተመው በመምጣት በቆንስሉ አካባቢ ባለው ሜዳ በአሳዛኝ ሁኔታ ከተሙ። የወዳደቀ እንጨት ፣ፕላስቲክና እንጨት እየለቃቀሙ ጎጆ ሰሩ ! በከፋ ቀን ያልታሰበው ያልተገመተው ሁሉ ይሆናልና ፣ ያላሰብነው ሆነ ! ውሎ ሲያድር የሰው ቁጥር እየበዛ የጅዳ ቆንስል በከፋቸው ዜጎች ተጥለቀለቀ …
አስደሳቹ የወገን ርብርብ …
ይህን ጊዜ ነበር ሰው ለሰው ልብሱ መሆኑን የታዘብኩት። የከፋቸውን ለማጽናናት ፣ የጠማ የደረቀውን ጉሮሮ ለማርጠብ፣ በርሃብ የታጠፈውን አንጀት ምግብ በማቅረብ በመታደግ ፣ በተለይም ህጻናትን ለመደገፍ የተደረገው ርብርብ ፍጹም ልዩነታችን ያስረሳ ልዩ የታሪክ አጋጣሚ ነበር ። … ፍጹም ከህሊናየ የማይጠፋ ህብረት !
የወገኖች የሜዳ ቆይታ ከሳምንት እንዳያልፍ የተደረገው ጥረት የሚያስደስት ሲሆን ይህንን ለማደረግ “የዜጎቸ ስቃይ አኔንም ያገባኛል! ” በሚል ቀድሞ እስከ አስር ሽህ የሳውዲ ሪያል በማዋጣት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ መጨረሻዎቹ ቀናት የሰሜንና ደቡብ ” ዋይት ” ማህበር አባላት ምግብ እና ውሃ በማቅረብ ያሳዩት ትጋት ከእድሜ ጠገብ ወንድሞች ያልጠበቅኩት ነበር ። ይህ ማህበር በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ በእርዳታ አልፎ በማረጋጋቱ ኮሚቴ በመታቀፍ ያሳየው ፋና ወጊ እንቅስቃሴ ወደር አልነበረውም! የጅዳ ኮሚኒቲ ፣ የኢህአዴግ የድርጅት ፣ ለአደጋው የተቋቋመው ኮሚኒቴ ፣ የኦሮሞ ልማት ፣ የጂዳ ቆንስል ሰራተኞች ፣የሳውዲው ትውልድ ኢትዮጵያዊው የመርባይ ቤተሰቦች ፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰቦች እና በግል ከጎናችን የተሰለፉ ነዋሪዎች ውሃ ምግብ በተወሰነ ደረጃ ከማቅረብ ጀምሮ ሻንጣ በማጓጓዝ እና ዜጎችን በማመላለስ ማስተናገዱ ረገድ በህብረት የሰሩትን በጎ ምግባር ሳስበው ኩራት ይሰማኝል! ይህ ለበጎ ምግባር የተደረገ ትብብር የባጀንበትን የከረረ ልዩነት ከአዕምሯችን ሲያጠፋው በህብረት ለአንድ አፍታም ቢሆን የከፋውን ህይዎት ጠግኖት ማየት መቻል ስለ እውነት ያኮራል!
የሽሜሲው መጠለያ ቆይታና የግፉአኑ ምሬት …
በዚህ መንገድ በቆንስላው ለቀናት የቆዩት ወገኖች መካ መግቢያ የቅርብ ርቀት ወደ ሚገኘው የሽሜሲ መጠለያ እስር ቤት ተላኩ ። “ወገኖቻችን ወደ ማጠለያ ገብተው ወደ ሃገራቸው በሰላም ሊመለሱ ነው !” ብለን ደስታችን ወሰን ባጣበት አጋጣሚ ግን ወደ መጠለያው የተወሰዱ ወገኖች ከመጠለያው ሳይገቡ ከግቢው ውጭ ፈሰው ለሶስትና አራት ቀናት እንግልት እንደ ደረሰባቸው ተሰማ ! ተከፋን ! እኔም እንደለመድኩት በሰላም የሸኘናቸውን ወገኖች ሮሮ መስማት ጀመርኩ ! በቀጣይ ቀናት በግልና ከኮሚቴው ጋር በመቀናጀት የውሃ ፣ የምግብና የመጸዳጃ ጥያቄውን ለሚመለከታቸው ለማቅረብ ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ። በእርዳታና ድጋፍ ሰጭው ኮሚቴ በኩል የውሃ አቅርቦቱን ለማድረግ በተደረገው ሙከራ በአርባ አውቶቡስ የሞላውን ወደ ሶስት ሽህ የሚሆነውን ሁሉንም ማስተናገድ አቅም አጣን ! የሚቻለውን ግነወ አደረፍን። እለተ ሃሙስ ከሽሜሲ መጠለያ በር ሜዳ ይ የተጣሉት ወገኖች ሮሮ በማየሉ ማታውኑ የእርዳታ አስተባባሪዎች ባደረጉት ጥረት የሰሜንና ደቡብ “ዋይት” ማህበር አባላት ለአርብ ጠዋት የምግብ እና ውሃ እንዲ ያቀርቡ ተጠይቆ በማህበሩ ይሁንታን አግኝቶ አርብ ጠዋት አቅርቦቱን ለመከወን ቀጠሮ ተያዘ !
የሽሜሲው ሁከት …
እንዲህ እንደሆነ ሃሙስ በአርብ ተተካ ! አርብ ጎህ እንደ ቀደደ በተንቀሳቃሽ ስልኬ በውሃ ጥማት እና በርሃብ የታመሱት ወገኖች በተለይም ህጻናትን የያዙ እናቶች እንባ የተቀላቀለበትን የምሬት ጩኸት እያመመኝ መስማት ጀመርኩ … በደረሰባቸው ሰቃይ አምርረው “ወደ ጅዳ እንመለስ ፣ ሱቅ እንኳ ከሌለበት ቦታ ከምንሰቃይ ሰው ሊያየን ወደሚችል ቦታ እንሄዳለን! ” ያሉኝን መልዕክት ለማሰማትና መፍትሔ ለማፈላለግ ብሞክርም ሙከራየ የተሳካ አልነበረም ። እናም እኩለ ቀን ላይ ምሬት ፈንቅሏቸው ወደ መካና ጅዳ አውራ ጎዳና መውጣት ሲሞክሩ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር መጋጨታቸውን ተረዳሁ! የሁከት ብጥብጡን ጅማሬ ሂደት በቀጥታ በስልክ መረጃውን ከሚያቀብሉን ግፉአን ወገኖች ድመጽ አልፎ የሚሰማው የተኩስና የሁከት ጫጫታ ድምጽ እየሆነ ያለውን ያሳይ ነበር … ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰሜንና ደቡብ “ዋይት” ማህበር አባላት ለአርብ ጠዋት የምግብ እና ውሃ አዘጋጅተው ወደ ሽሜሲ ሊንቀሳቀሱ ሲሉ የሁከቱን መረጃ ደረሳቸው! የተዘጋጀው ምግብ ማቅረብ ሳይቻል ቀረ!
ከሰአታት በኋላ የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች እና የሳውዲ መንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ችግሩ እስኪከሰት ዘግይተውም ቢሆን ባደረጉት ድርድር ሁከቱ በርዶ ለሶስት ሰአታት ተዘግቶ የነበረው የጅዳ መካ አውራ መንገድ ተከፈተ … የተዘጋጀው ምግብ ማቅረብ ያልቻሉት ወንድሞች ምግብ ውሃውን በሽሜሲ ላሉት ወገኖች መድረስ ባይችሉም በመካ ኩደይ በተባለ አካባቢ በተመሳሳይ መንገድ “ወደ ሃገር እንግባ! ” በሚል አደባባይ ለወጡት ወገኖች ምግብና ውሃውን በአፋጣኝ መንገድ አቀረቡ ፣ አሁንም ካለው የህዝብ ብዛት አንጻር ምግቡና ውሃው ለሁሉም ባይዳረስ እንደሚሆን እንደሚሆን አድረገው እርዳታውን አከፋፈሉ ! ወገን ለወገን ደራሽ መሆኑን ለማየት ፣ ለመስማት ብሎም የመከራው ቀን በጎ ስራ እማኞች ለመሆንን ታደልን !
ይቅርታው …
አርብ ምሽት – የወገን ለወገን ደራሽ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ አድርገን አንዱን አንስተን አንዱን ስንጥል አመሸን። እኩለ ሌሊት ስብሰባው ሲከወን የኮሚቴውን አካሔድ ለማስተካከል የተወሰደው ውሳኔ ተላለፈ፣ ከጎናችን ሆነው ደፋ ቀና የሚሉትን ወገኖች አስከፋ : ( ውሳኔው መተግበር ቢኖርበትም ከውሳኔው በፊት መስራት ያለብንን ስራ ባለመስራታችን ወንደሞቻችን አስቀይመናል! የሚሰራ ይሳሳታል ፣ ስንሰራ ተሳስተናል! ይቅርታችን የከበደ ነው ! የአካሔድ ጠፋቱ አካል ነበርኩና ያች ምሽት ለእኔ ከባድ ነበረች … የከበደኝ መሆን ያለበት ወገንን ለመታደግ የሚደረገውን ሂደት ለማስተካከል የተደረሰበት ውሳኔው ሳይሆን ቡና እየጨለጡ የሚፈላሰፉ በበዙበት ከባቢ ደጋግ በጎ አድራጊ ወንድሞቻችን በማስከፋታችን ነበር! በዚሁ ስብሰባ “ገጽታችን እንገንባ! ” የምትለው የአንዳንድ ወገኖች አካሔድ አንድምታ ግራ ሲያጋባኝ አለም አቀፉን ህብረት እየነቀነቀ ያለውን የወገን ለወገን የመድረስ አላማ ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚጎትት ምሽት ላይ በስልክ ካደረግኩት የራዲዮ ውይይት ጋር በአንድና በሌላ አቅጣጫ ሲሳሳብ ከፊቴ ተደቀነ! ስብሰባው እኩለ ሌሊት ተጠናቀቀ! … ወደ ቤት ገብቸ እንዲህ ስል የተጎዳ ስሜቴን እንዳሻኝ ስሜት ህመም ፣ ተስፋ ህልም ስጋቴነወ እንዳሻኝ በምገልጽባት የፊስ ቡክ ገጼ ተነፈስኩት …ተቃዋሚው ባንድ ወገን መንግስትና ደጋፊው በሌላ ወገን ይሳሳባሉ ፣ ሁለት ዝሆኖች ይታገላሉ ፣ ድሃ መውጫው ቀዳዳ ጠቦታል ፣ ወገኔ ከዝሆኖች ጥል ስር የበቀለ ያልታደለ ሳር ሆኖ ይደቆሳል ፣ የባሰውኑ ታምሜ አመሸሁ ! አይመሽ የለም መሽቶ ከተማሩ ከተመራመሩ ፣ ከወለዱ ከከበዱት ወንድሞቸ ጋር ወገኔን መረጃ ከማቀበል በተግባር ወደ መርዳት ልሸጋገር ስብሰባ ተቀመጥኩ ! ትልልቆቹ አንሰን ቢታየኝ ህምም ታምሜ እኩለ ሌሊት ወደ ቤት ገባሁ ! ያየሁ የሰማሁ የሆነውን ለመርሳት እየሞከርኩ አይተኛ የለም ተመስገን ብየ ተኛሁ ! ዛሬ እንጃ ! የማውቀው የትናንቱን ክፉ ቀን ነው !
በተስፋ የተጀመረው ቀንና የምስራቹ …
እለተ ሰንበት ቅዳሜ – በልጀ የማለዳ ሳቅ ታጅቤ በተስፋ ተነሳሁ … እንዲህም አልኩ …ዛሬ እንጃ ! የማውቀው የትናንቱን ክፉ ቀን ነው! ልጀ ሆይ! መውለድ ደጉ ዛሬን ባንች ፈገግታ በተስፋ ሊጀመር ነው! ተመስገን! ተመስገን! ተመስገን! መልካም ቀን ለሁላችሁ !
የእኔን የሃጥዑን ጸሎት ሳይሆን ልጆቻቸውን ታቅፈው ጨንቋቸው ፣ ጮኸው ሰሚ ያጡትን ወገኖች ሃያሉ አምላክ አልተዋቸውም! እግዚአብሔር አምላክ በስደት የተሰበረውን የወገኖቻችን ጉዳት ሰማ ! የጨነቃቸው የጠበባቸው በደስታ ፊስታ ተናኙ ! በጭንቀት ሁከት የሰነበቱት ወገኖች ወደ ሃገር ቤት ለመሄድ ዝግጅት መጠናቀቅ መረጃ የደረሰኝ በተስፋ የጀመርኩትን ቀን የሚያበላሽ ቧልት ሰምሁና አዘንኩ ። ሞራል ያጡ ፣ በወገን ችግር ጀርባ በቪዛ ሽያጭ ፣ በድለላ እና በመሳሰሉት ጥቅምን በማጋበስ የለመዱ ክፉዎች በዚህ ክፉ ቀን እንኳ ስለሚንገላታው ወገን አይጨነቁም! ለጆቻቸውን ስለሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት እያደር መበለሻሸት ግዳቸው አይደለም! እናም ተበሳጭቸ ከጅዳ ኮሚኒቲ ካፍቴርያ እንደወጣሁ ስልክ ተደውሎ የምስራች መልዕክት ደረሰኝ!
“ነቢዩ ደስ ብሎናል ! እንኳን ደስ ያለህ ! ትናንት እየደወልን ስጨናንቅህ የነበርነው ሁላችንም ወረቀታችን አልቆልን ወደ ጅዳ አየር መንገድ እየተጓዝን ነው! ” ተመሳሳይ የስልክ ጥሪ ደረሶኝ ተመሳሳይ የምስራች ሰማሁ! ዛሬ ለቅሶ የለም! እኒያ ሲንገላቱ የሰነበቱ ወገኖች ሳቅ በሳቅ ሆነው ፣ በደስታ ተውጠው የምስራቹን ሲያበስሩኝ የተሰማኝ ደስታ ወሰን የለውም ! አዎ ወደ አራት ሽህ የሚገመቱት ወገኖች የሃገራቸውን መሬት ለመርገጥ መታደላቸው በእርግጥም ታላቅ የምስራች ነው ! ተመስገን !
ከሽሜሲው ግጭት የምንማረው …
ከሽሜሲው ግጭት ብዙ ልንማር ይገባል ። በጅዳ ቆንስል የቅርብ ርቀት ከትመው ለሳምንት ከቆዩ በኋላ ወደ ሺሜሲ መጠለያ በወገን ትብብር የተወሰዱት ወገኖች በመጠለያው ግቢ እንዳይገቡ ተደርገው ነበር። በጠራራው ጸሃይ በአውቶቡስ እና በሜዳ ላይ ያለ ምግብና ወሃ መሰንበታቸውን የጅዳ ቆንስል ሰራተኞችና ሃላፊዎች ወደ መጠለያው ሲገቡና ሲዎጡ ይመለከቷቸው ነበር ። ያም ሆኖ ከሶስትና ከአራት ቀናት በላይ ህጻናትን የያዙተን ጨምሮ አቅመ ደካማ እህቶች በወሃ ጥማት ሲጠበሱና በርሃብ አንጀታቸው ሲታጠፍ ከቅርብ ርቀት ያሉት የቆንስል መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችና ሃላፊዎች መፍትሄ አላፈላለጉላቸውም። በዚህ መሰል አስከፊ ሁኔታ ህጻናት ደክመው ፣ ነፍሰ ጡር እህቶች ደክመው ፣ የተወሰኑት አዕምሯቸው ተነክቶ ታዝበናል። የሁከቱ መንስኤ ለቀናት በርሃብና በውሃ ጥማት የተቸገሩት ግፉአኑ ወገኖች ትዕግስት ማጣት እንጀ ሁከትን ለማስነሳት ታቅዶ የተፈጸመ እንዳለሆነ ግልጽ መሆን አለበት!
“ወደ መጠለያ አስገባሁ !” ብሎ በመጠለያው በር ሜዳ ላይ ያፈሰሳቸውን የሳውዲ መንግስት አካል ከመሞገት ባለፈ ይህን መሰል አስነዋሪ ስራ እንዳይሰራ የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች መስራት የነበረባቸውን ስራ በበቂ ሁኔታ ሰርተዋል አልልም። የጅዳ ቆንሰል ሃላፊዎች ወደ መጠለያው የተላኩ ዜጎቹን ጉዳይ በእግር በእግር ተከታትለው ማስፈጸም ነበረባቸው። ይህ አልተደረገም ወይም ተደርጎ አልተሳካም ይሆናል። በአንድ አቅጣጫ ያልተሳካውን በሌላ አቅጣጫ ለማስፈጸም የቆንስሉ ሃላፊዎች ያደረጉት ሙከራ አንድ ሁለት ቀን ቢከሽፍ ከአራት ቀን በላይ መጓተቱ ዲፕሎማቶቻችን ከፍተኛ ጫናን ፈጥረው ጉዳዩን በማስፈጸሙ ረገድ እንዳልተሳካላቸው በግልጽ ያሳያል። የሳውዲ መንግስት እና የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች በፈጻሚና አስፈጻሚ አለካት መካከል መግባባት ቢኖር ኖሮ ዜጎችን ወደ መጠለያው እንኳ ማስገባት ቢገድ ካሉበት ቦታ ምግብና ውሃ በማቀበል አጠቃላይ ሂደቱን መቆጣጠር ይቻል ነበር። በሂደቱን የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች በቅርብ ተከታትለውት ቢሆን ኖሮ አነወዱ አንኳ ቢያስቸግር የጉዳዩን አሳሳቢነት ለማስረዳት ከከፍተኛ የሳውዲ መንግስት ሃላፊዎች መድረስ ይችሉ ነበር። ከዚህ በተጓዳኝ ለመገናኛ ብዙሃን በአሰራር የሚገጥማቸውን መሰናክል በማቅረብ ድምጻቸውን ሊያሰሙ ይገባ ነበር ። ይህ አልሆነምና ትኩረት ባለመሰጠቱ ሰው ተራበ ተጠማ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ሆኑ ! ወደ ዝርዝር ሳንገባ ካለፈው ጥፋት ልንማር ግድ ይለናል! ካለፈው ስህተት ከተማርን ከተመሳሳይ ሁከት ልንድን እንችላለን !
የማይበጀን ሁከት ፣ የማይፈይድልን መረጃ ….
ይህን መሰል ችግር መቅረፍ የሚቻለው ሁላችንም ያገባናል ብለን በህብረት ስንደጋገፍ ብቻ ነው! ሰላማዊ ሰልፍ አና የአደባባይ ላይ ተቃውሞ በማይፈቀድ በማይታሰብባት ሳውዲ አረቢያ ችግር እንኳ ቢሆር የሚፈታባቸውን መንገዶች ከማፈላለግ ባለፈ ሁከት አመጽን መከተል አይጠቅመንም። ወደ ሁከት የሚወስደውን ሁሉ እንቅስቃሴ በማስዎገድ እና መረጃን በመለዋወጥ ችግሮች እንዲሰሙ ማድረግና ማስተካከል ይቻል ይመስለኛል! በነጻነት መረጃን ከተለዋወጥን የማይቻል የለም ይቻላል! ነዋሪውን ለማረጋጋረት ብሎ ያልሆነውን ሆነ ብለን “የዋሽቶ ማስታረቅ! ” ዘይቤ ፍጹም አይበጀንም! ገጽታን እናሳምር ምናምን ብለን “ቅባቱን ” ተጠቅመን መረጃውን እና እውነቱን ካዛባነው መረጃው ዘባተሎ ይሆናል ፣ ከዚሁ ጋር ችግሩን ለመታደግ የምንወጣ የምንወርደው ሁሉ የተዛባው ባለቅባት መረጃ ተአማኒነትን ያሳጣናልና ድካሙን ሁሉ የእንቧይ ካብ ያደርገዋልና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል : )
የስኬቱ ባለድርሻዎች …
በመላ ሳውዲ ችግሩ በእኛ ላይ ከጠና ወዲህ ወገኖቻችን ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ የሚደረገው ስኬት በተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የተከወነ አይደለም ። በሃገር ቤት በውጭ ሃገር ያሉ ወገኖች በሳውዲ መንግስት ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ ፣ በሳውዲ አረቢያ የተለያዩ ከተሞች የምንገኝ ሁላችንም በህብረት የሰራነው ስራ ውጤት ነውና ደስ ሊለን ይገባል! ምስጋናውም ለሁሉም ነው ! ወገንን መደገፍ ምስጋና ካስፈለገው ማለቴ ነው … ደስ ሲል …!
ለወገን ደራሹ ወገን ነው ፣ በህብረቱ ፣ እንበርታ! (ፎቶዎቹ የተላኩት: በነቢዩ ሲራክ)
Leave a Reply