ስብሃት ነጋ የኢህአዴግ አባትና ፈጣሪ የሆነው ህወሃት የመጨረሻው ታሪኩ ጠቦ እንደሚቋጭ ይፋ አደረጉ። ችግር የህወሃት ልዩ በረከትና ስጦታ እንደሆነ በማመልከት ህወሃት ውስጥ ልዩነትና መፈርከስ አደጋ ተከስቶ እንደማያውቅ ሸመጠጡ።
አቶ ስብሃት ጠቦ የሚጠናቀቀውን የህወሃት ስውር አጀንዳ የገለጹት ከጋዜጠኛ ደረጃ ደስታ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ነበር። በኢህአዴግ የመከላከያ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈልና የኩዴታ አደጋ ሊያስከትል የሚችል አደጋ እንደተረጋገጠ ተጠቅሶ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ስብሃት “አዲስ አበባ መንግስት ገልብጠው የክልሎችን ድጋፍ ቢጠይቁ ማን እሺ ይላል” በማለት ነበር የመለሱት። አንዴ በመከላከያ ውስጥ የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ ሊያጋጥም የሚችልበት አግባብ እንደሌለ፣ ጠያቂው እንዳለው የመፈንቅለ መንግስት አደጋ ቢያጋጥም እንኳ የህወሃት ስጋት እንዳልሆነ አስመስለው አቶ ስብሃት የመለሱት የክልሎችን ስም በመጥራት ተቀባይት እንደማይኖረው ነው። ይህም አባባላቸው እኛን ገልብጦ አገር አንድ አድርጎ መምራት አይቻልም የሚል እንደምታ ያለው ቢመስልም፤ “ሪፑብሊክ” ለመመሥረት የተነሳውና እስካሁን በነጻአውጪ ስም አገር እየገዛ ያለውን ህወሃት የመጨረሻ የመጥበብ ዓላማ በማስረጃ የገለጹበት ነው፡፡
ህወሃት “ኢህአዴግ” የሚባለውን ድርጅት ሲያበጀው የአገልግሎት ዘመን መድቦለት እንደሆነ ስለ ድርጅቱ የወደፊት መድረሻ ድንበሩ ከሚያወሱ የድርጅቱ የተለያዩ ማረጃዎችና ነባር አባሎቹ መጠቆሙ ይታወሳል። ህወሃት 40ና 50 ዓመት ኢትዮጵያን በብሔር ፖለቲካና በዘር እያጋጨ ለመግዛት የሳለው ስዕል እንዳሰበው ካላዘለቀው እንዴት ጠቦ እንደሚጠናቀቅ የጠቆሙት ስብሃት፣ አስተያየታቸው አካሄዱ የገባቸውን በሙሉ አበሳጭቷል።
በ1997 የምርጫ ወቅት ተፈጥሮ በነበረውና በራሱ በቅንጅት ሰዎች ሽኩቻ በተኮላሸው ህዝባዊ ድል ግለት ወቅት ኢንዲያን ኦሽን የተሰኘው ጋዜጣ “ህወሃት ወደ ትግራይ የማፈግፈግ እቅድ ይዟል” በማለት የዘገበውን ዘገባ በማስታወስ በአቶ ስብሃት መልስ ላይ አስተያየት የሰጡ፤ በቅድሚያ አቶ ስብሃትን “አቦይ ብላችሁ አትጥሩት። አባታዊ አንደበትና ምግባር የለውም” በሚል ማሳሰቢያ ከሰጡ በኋላ “የስብሃት ንግግር ህወሃት ታሪኩ ሲጠናቀቅ ጠቦ እንደሚቋጭ ነው። ለዚህ ሲል ነው ህዋሃት ከአንቀጽ 39 ጋር ቅበሩኝ የሚለውና የአማራ ክልል መሬትን እየዘረፈ የመውጫ ቀዳዳ ፍለጋ ሌት ከቀን መሬት እየቆረሰ አዲስ ካርታ የሚያመርተው፤ ዓለምአቀፋዊ ድንበርም ለትግራይ እንዲኖራት ያደረገው” ብለዋል።
“ህወሃት ካለውና ከተፈጠረበት ክፉ ዓላማ አንጻር በቀጣይዋ ኢትዮጵያ ‘ቦታ አይኖረኝም’ የሚል ድምዳሜ ላይ ስለደረሰ ሁልጊዜ ሲጨንቀው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ስዕል ያሳያል። የስብሃትም ንግግር ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው” በማለት ምልከታቸውን የተናገሩት የጎልጉል የዘወትር አስተያየት ሰጪ “ውሳኔውና ህልሙ ስኬት የናፈቀው የቅጥረኞቹ የህወሃት ሰዎች ጭንግፍ ምኞት ቢሆንም መላው የትግራይ ህዝብ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥርት ያለ አቋም በመያዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚቆም መሆኑን ማሳየት እንደሚገባው” አመልክተዋል።
ከህወሃት ሊቀመንበርነታቸውና ከስራ አስፈጻሚነታቸው አራት ጊዜ ማመልከቻ በመጻፍ በፈቃዳቸው እንደለቀቁ ያመለከቱት ስብሃት ነጋ በኤፈርት ጉዳይ ከወ/ሮ አዜብ ጋር ስምምነት እንዳልነበረቸው ፍንጭ ሰጥተዋል። አያይዘውም ህወሃት የመከፋፈል አደጋ አጋጥሞት እንደማያወቅ፣ እንዲያውም በየጊዜው የሚነሱ የሃሳብ ልዩነቶች የድርጅቱ ልዩ ስጦታውና በረከቱ አንደሆነ ተናግረዋል። ልዩነትና በልዩነት ጥግ ድረስ ደርሶ መፋጨት የህወሃት የጥንካሬው መሰረት እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ስብሃት በድህረ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ህወሃት ለሁለት ተከፍሎ አደጋ ላይ የወደቀበትን ጊዜ አስተባብለዋል። እነ አቶ ስዬንም “የተባረሩ” ሲሉ አቅመ ቢስ አድርገው ስለዋቸዋል።
ኤርትራ ራሷን በወጉ መከላከል እንኳ የማትችል አገር እንደሆነች የጠቆሙት ስብሃት ኤርትራን ተማምኖ የሚከናወን የተቃውሞ ትግል የጤና ነው ብለው እንደማያምኑ “እብደት ነው” በማለት ኢህአዴግም ሆነ እሳቸው በእንቅስቃሴው ላይ ስጋት እንደሌለባቸው ለመግለጽ ሞክረዋል። ስብሃት በአሜሪካ ከተለያዩ ወዳጅ ሚዲያዎች ጋር እየተወደሱ ጥያቄና መልስ ያካሄዱ ሲሆን በተለይም ስለ መለስ ቅንድብ ከዘፈነው ሰለሞን ተካልኝ ሲቀርቡላቸው የነበሩት ጥያቄዎች የሚያዝናኑ ነበሩ። ጥያቄና መልሱን የተከታተሉ “ጠያቂው መልሱን አስቀድሞ ጥያቄ ማስከተሉ ጥሩ ተማሪ መሆኑንን በማረጋገጥ የምስክር ወረቀት የፈለገ አስመስሎታል” ሲሉ የለበጣ አስተያየት በማህበራዊ ገጾች ላይ አስፍረውበታል። አቶ ስብሃት በአሜሪካ ከጠባቂዎቻቸው ጋር በመሆን መደባደባቸውና በፖሊስ ይፈለጉ እንደነበርም መዘገቡ ይታወሳል። አቶ ስብሃት ከፖለቲካው ፈላጭ ቆራጭነት ወጥቻለሁ ቢሉም የሚሰጡዋቸው አስተያየቶችና ትንቢቶች አሁንም “የህወሃት የኋላ ዘዋሪ” እንደሆኑ አመላከች እንደሆነ ተጠቁሟል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply