ስለ ብሔራዊ እርቅና መግባባት ጉዳይ አጠር ምጥን ተደርጎ የተዘጋጀውን ባለ አምስት ነጥብ የዳሰሳ ጥናት (survey) ለዚሁ ጉዳይ ሲባል ብቻ ወደ ተዘጋጀው ድህረገፅ እዚህ ላይ በመጫን በመሄድ ድምፅዎን ያሰሙ። የዝምተኛው ብዙሃን ድምፅ ጭምር ሳይቀር እስቲ ይሰማ!
ፖለቲካውንና ፍልስፍናውን አርባ አመት አውጠንጥነን አረጀንበት። እንዲሁ ስንባዝን እድሜያችን አልቆ አንድ ባንድ ወደ ሞት ልንሄድ ነው። እርቅና መግባባትን ማን ጠላ? መላው ጠፍቶብን እንጂ። አይ መላውም አልጠፋን እንደ እውነቱ ከሆነ። ኢትዮጵያ መፍትሔ ሊያመጡ የማይሳናቸውን ልጆች ወልዳ ሳለ እንደ መካን ቁጭ ብላ መቆዘም አይገባትም። እስቲ የልበ ሰፊው፦ የአስተዋዩና የጨዋው ሕዝብ ድምፅ እንስማው።
ባለስልጣኑ በራሱ ጡንቻ ተማምኖ ተቃዋሚውን ከመንጫጫት በላይ ምን ያመጣል ብሎ ሲንቅ፦ ተቃዋሚው ምንም ይሁን ምን ባለስልጣኑ ከመንገድ ይጥፋ ብሎ በጥላቻ ሲሞላ፦ ኢትዮጵያ በመሃከል እፎይታን ሳታይ አንዱ ትውልድ እያለቀ ሌላው ትውልድ ያንኑ የመከራ ቅርስ ሊወርስ ዛሬ ደረስን።
ንቀት ውላ ስታድር ውድቀትን ትከናነባለች። ጥላቻ ጊዜዋ ደርሶ በተራዋ ስልጣን ላይ ስትወጣ ንቀትን ትላበስና ታሪክ ራሱን ይደግማል። ታዲያ ከዚህ የመኝታ ቅዥት ወደ ፈውስ የሚያመጣን እርቅና መግባባት ብቻ ሳይሆን አይቀርም።
ሁላችንም እንንቃ። የአርባ አመታት የመከራ ጉዞ እጅ እጅ ይበለን። ባለስልጣኑም ሆነ ተቃዋሚው አንዱ ያለ ሌላኛው ለኢትዮጵያ ዜሮ መሆኑ ይግባው። ሁለት ዜሮ ምን ፋይዳ ይፈጥራል? ወደ እግዚአብሔር እንጩህ፦ ትንቢተ ኤርምያስ 33፡3 እንዲህ ይለናል፦ “ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ።” በብሔራዊ ደረጃ የአምላክን እርዳታና በረከት መጠየቅ አይታፈርበት። ሳናሰልስ ሁላችንም “የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን አስባት” ብሎ መማፀን የኢትዮጵያዊነት ምልክት ይሁንልን።
እባክዎን አምስት ደቂቃ ይውሰዱና የተዘጋጀውን ባለ አምስት ነጥብ የዳሰሳ ጥናት ላይ ይሳተፉ። ኢትዮጵያዊ መቼ ተባብሮ ቁም ነገር ይሰራና ለሚሉት መልስ እንስጥ። ኢትዮጵያ ትጎበኝ ዘንድ በደጅ ነው። ገና ምኑ ገና፦ ኢትዮጵያ ሁሉም እፎይ ብሎ የፍቅር መንደር እስክትሆን ድረስ ነፍሳችን አታርፍም። ስለ ተሳትፍዎ እግዚአብሔር ያክብርልኝ። እግዚአብሔር ለሁላችንም እጅግ አስቸጋሪ የሆነብንን የኢትዮጵያ እንቆቅልሽ ይፍታ። አሜን።
Leave a Reply