በምኒልክ ዘመን በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ተፈፅሟል የተባለውን የጡትና እጅ መቁረጥ ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና ጭፍጨፋ ለማስታወስ በሚል በአርሲ አኖሌ አካባቢ በ20 ሚሊዮን ብር የተሰራው ሃውልት፣ በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድርን ጨምሮ በርካታ የኦህዴድ ባለስልጣናት በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ሃውልቱን ያሰራው አካል ያለፈን ታሪክ መዞ ቂም በቀልን ለማውረስ ሳይሆን ቀጣዩ ትውልድ ከአስከፊው ድርጊት እንዲማርና ወደፊት ድርጊቱ እንዳይደገም ነው ሃውልቱ የተገነባው ብሏል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን በበኩላቸው ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ አንደኛው ወገን ሃውልቱ በህዝቦች መካከል ቅራኔና ቂም በቀል የሚፈጥር ነው በማለት ሲቃወም ሌላው ወገን በበኩሉ ድርጊቱ ዳግመኛ እንዳይከሰት መማርያ እንጂ የበቀል አይደለም ሲሉ የሃውልቱን መቆም ይደግፋሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አወዛጋቢ በሆነው የአኖሌ ሃውልት ዙሪያ የታሪክ ምሁራንንና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡
“ጡት ስለመቆረጡ በፅሁፍ የተቀመጠ መረጃ አላገኘሁም”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ፖለቲከኛና የታሪክ ምሁር)
ሃውልቱ ለምን እንደተሰራ የተጨበጠና ጠለቅ ያለ መረጃ የለኝም፡፡ የታሪክ መረጃዎች እንደሚታወቀው አንድም በፅሁፍ ይተላለፋሉ፡፡ ሌላው ደግሞ በአፋዊ ንግርት (አፈታሪክ) የሚተላለፍ ነው፡፡ እኔም የዶክትሬት ማሟያ ፅሁፌን የሰራሁት አፈ-ታሪክን ተጠቅሜ ነው፡፡
በ1879 አፅመ ጊዮርጊስ የተባሉ የአፄ ምኒልክ ታሪክ ፀሃፊ (አንዳንዶች የኦሮሞ ታሪክ ፀሃፊ ናቸው ይሏቸዋል) በዚያን ጊዜ እንደሰላይ ነበረ የሚሰሩት፡፡ እኚህ ሰው የምኒልክ ጦር ከመንቀሳቀሱ በፊት የሚዘመትበትን ህዝብ ባህል፣ አኗኗሩን ካጠኑ በኋላ እንዴት መወገድ እንደሚችል ሃሳብ ያቀርቡ ነበር፡፡ እኔ ጋ ባለ አንድ መፅሃፋቸው ላይ ስለዚህ ስለ አኖሌ ጉዳይ ሲፅፉ፣ በአንድ በኩል አፄ ምኒልክ ከ1879 ዓ.ም በፊት ለአራት አመት አርሲን ለማስገበር ጦርነት ሲያካሂዱ እንደነበር ተርከዋል፡፡ መስከረም 1879 ላይ የምኒልክ የአባታቸው ወንድም የሆኑት ራስ ዳምጠው ናቸው የመጨረሻውን የአርሲ ጦርነት ያካሄዱት፤ ምኒልክ እንጦጦ ነበሩ፤ በዚያ ጦርነት ላይ የምኒልክ ሰራዊት ለሶስት ቀናት መዝረፍ፣ ማቃጠልን ጨምሮ ሽማግሌና ህፃናት ላይ ብዙ ጉዳት አድርሷል፡፡ የአፅመ ጊዮርጊስ ፅሁፍ እንደሚለው፣ በወቅቱ ራስ ዳምጠው “እኔ ተኩስ ሳልል እንዴት ሰራዊቱ ትዕዛዜን ሳያከብር ተኩስ ጀመረ” በሚል እንጂ በሰዎች እልቂት ሃዘን አልተሰማቸውም ነበር፡፡
ለአፄ ምኒልክ በላኩት መልእክትም ሰራዊቱ ከትዕዛዛቸው ውጪ በመሆኑ በእጅጉ ማዘናቸውን እንጂ ስለጠፋው የሰው ህይወት ሃዘን እንደተሰማቸው አልገለፁም ነበር፡፡ በዚህ የሦስት ቀን ጦርነት በወቅቱ “አዞሌ” አሁን “አኖሌ” በሚባለው ቦታ ላይ 12ሺህ ሰው ተገድሏል፡፡ ከዚህ መረጃና ጦርነቱ አሰቃቂ ነበር ከሚለው እውነታ ውጪ እኔ እስካሁን እጅ ቆርጠዋል፣ ጡት ቆርጠዋል የሚል የፅሁፍ መረጃ አላገኘሁም፡፡ በ1984 ወደ አኖሌ በሄድኩበት ወቅት፣ የአርሲ ሰዎች እጅና ጡት የተቆረጠበት አካባቢ ነው ብለው ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው አሁንም ድረስ እጅና ጡት ተቆርጧል የሚለው ታሪክ በሰፊው የሚነገር ነው፡፡ ሆኗል አልሆነም የሚለውን ለማረጋገጥ በደንብ ምርምር መደረግ አለበት እንጂ ለምን ታሪኩ እንዲህ ተነገረ ወይም ተባለ ብሎ ማውገዝ ከባድ ነው፡፡
ሌላው ማስታወስ ያለብን ለምሳሌ እነ ወለጋ የተወረሩት እስከ 1877 ዓ.ም ነበር፡፡ ነገስታቱ በሰላም ነው እጃቸውን የሰጡት ጅማም እንደዚሁ ነው፡፡ አርሲ ግን ለረጅም ጊዜ አልቀበልም ብሎ ስለነበር በጣም ብዙ አሰቃቂ ጦርነቶች ተካሂደው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ሁኔታው ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄንን ሃውልት ያቆሙ ሰዎች፣በአንድ በኩል በታሪክ የሰሙትን ለማስታወስ ብቻ ብለው ይሆናል፡፡ በኔ እምነት ሃውልቱ የነበረውን ሁኔታ ለማስታወስና ለወደፊት እንዳይደገም የተሰራ ይመስለኛል፡፡ እኔ መገንባቱ ምንም ችግር የለውም ነው የምለው፡፡ ታሪክን በሚገባ ካነበብን፣ አፄ ቴዎድሮስ የግዛት አንድነትን ለማምጣት የተጉ ተደርገው ነው የተቀረፁት፡፡ በአዲስ አበባም ያሰሩት መድፍ በስማቸው ከተሰየመው አደባባይ ላይ ተቀምጧል እንዲሁም ጎንደር ሃውልታቸው ቆሟል፡፡ ነገር ግን ሸዋ እና ወሎ ያሉ ሰዎችን ከንፈር መላጥ፣ እጅ መቁረጥ፣ ከነህይወት ገደል መክተት፣ ማቃጠል የመሳሰሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ፈፅመዋል፡፡ አፄ ዮሐንስ ደግሞ እነዚህን “ጋሎች እና እስላሞች” ክርስቲያን አድርጉ ብለው ወሎ ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈፅመዋል፡፡
በአጠቃላይ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ሃውልት ሲሰራ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፤ ነገር ግን ያለፈ ታሪክ ያስከተለው ጉዳት በቀጣይ እንዳይደገም በሚል እሳቤ ሃውልት ሲቆም ለበቀል ነው በሚል መደምደሙ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ ሃረር ጨለንቆ ላይ ለተፈፀመው ጭፍጨፋ ሃውልት ተሰርቷል፡፡ የራስ መኮንን ሃውልት ደግሞ ሃረር ከተማ ላይ አለ፡፡ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ላይም የምኒልክ ሃውልት ተቀምጧል፡፡ በአንፃሩ በምኒልክ ጉዳት ደርሶብናል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ታሪክን በሃውልት ለማስታወስ የሚደረጉ ነገሮች በጥንቃቄ መቃኘት አለባቸው፡፡
“ሀውልቱ የኦሮሞን ህዝብ 100 ዓመት ወደ ኋላ የጎተተ ነው”
አቶ አበባው መሃሪ (የመኢአድ ሊቀመንበር)
የሃውልቱን መገንባት አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ጀግንነት የሰሩ የኦሮሞ ልጆች አሉ፡፡ የሚኒልክ አማካሪ ከነበሩት መካከል ወደ 80 በመቶ የሚሆኑ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ጣሊያን በተሸነፈበት ጦርነትም የኦሮሞ ልጆች ገድል ቀላል አይደለም። እነዚህን ታሪኮች ወደ ጎን ገፍቶ አኖሌ ላይ ብሄሮችን ሊያቃቅር የሚችል ሃውልት ከመገንባት ይልቅ የእነዚህን ጀግኖች ሃውልት አቁመው ቢሆን ኖሮ፣ ኢትዮጵያዊነት ይበልጥ ይፀና ነበር፡፡ የታሪክም መገለጫ ይሆን ነበር፡፡ እንደኔ እይታ የአኖሌ ሃውልት የኦሮሞን ህዝብ ወደ ኋላ 100 ዓመት የጎተተ እንጂ ወደፊት ያራመደ አይመስለኝም።
በሌላ በኩል እኔ ይሄ ሃውልት የኦሮሞዎች ፍላጎት ያለበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ያሰሩት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአጠቃላይ ግን ሃውልቱ ሁለቱ ትላልቅ ብሄር ብሄረሰቦች- አማራና ኦሮሞው እርስ በእርሳቸው ተጋጭተው ትልቅ የነበሩት ትንሽ እንዲሆኑ ታልሞ የተደረገ ሴራ እንጂ የኦሮሞን ህዝብ ለመጥቀም የተደረገ ስራ አይደለም፡፡ ሃውልቱ ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ሳይሆን ጉዳት ነው የሚያመጣው፡፡ ከሌላው ብሄር ጋር ቅራኔ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ከፍተኛ ጉዳትም ያስከትላል፡፡
በዚህች ሃገር ታሪክ ውስጥ ብዙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ተፈፅመዋል፡፡ እከሌ ይሄን አድርጓል እያልኩ መወንጀሉን አሁን ባልሻም በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉት አያሌ ግጭቶች የብሄር ተቃርኖ መሰረት ያላቸው አይደሉም፡፡ እኔ አገዛለሁ በሚሉ ከብሄረሰቡ የወጡ ነገስታት (ከሸዋ አፄ ምኒልክ፣ ከትግራይ አፄ ዮሐንስ፣ ከጎጃም ንጉስ ተክለሃይማኖት፣ ከጎንደር አፄ ቴዎድሮስ) ሃገሪቱን አንድ አድርገው ለመግዛት ባደረጉት ጥረት ብዙ ግፍ ተፈፅሟል፡፡ በወቅቱ ለግዛት አንድነት እምቢ ያለውን፣ ያመፀውን ቀጥተው ነው የሚያስተዳድሩት፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን ህዝቡን እየመገበ አይደለም ስልጣን የያዘው- እየገደለ፣ እያሰረ፣ እያባረረ ነው ስልጣን ላይ የተቀመጠው እና እንዲህ ያሉ ታሪኮች ባይነሱ መልካም ይመስለኛል፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ታሪኮች እንደታሪክ ተፅፈው ሊቀመጡ ይችላሉ፣ ነገር ግን እንዲህ ተደርገሃል በሚል ቂም በቀልን መቆስቆሱ ለዚህች ሃገር አይጠቅምም፡፡ የአኖሌ ሃውልትም የኦሮሞዎች ሃውልት ሳይሆን የካድሬዎች ሃውልት ነው፣ ስለዚህ የብሄሩን ታሪክ የማይወክል ሃውልት መቆሙን እቃወማለሁ፡፡ መቆም ያለበት ሃውልት የኦሮሞን ታሪክና ጀግንነት አጉልቶ የሚያሳይ ሃውልት ነው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ገዳ ስርአት በሃገራችን የመልካም አስተዳደር ስርአት ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ታሪኮች ተፅፈው ቢቀመጡ ጠቃሚ ነው፡፡ ሌላው አፄ ምኒልክ ጡትና እጅ ቆረጡ የሚለው ታሪክ ይወራል፡፡ በአንድ ወገን ደግሞ የኦሮሞ አባገዳዎች በግንባራቸው ላይ የሚያደርጉት የአማራን ብልት በመስለብ የተገኘ ነው የሚሉ የአማራ ካድሬዎችም አሉ፡፡ ስለዚህ ባህር ዳር ላይ ደግሞ ለዚያ ሃውልት ይቁም ከተባለ ምንድን ነው የሚሆነው? በአጠቃላይ እኔ የምመክረው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በካድሬዎች ሴራ አንድነቱን አሳልፎ እንዳይሰጥ ነው፡፡
“የሃውልቱ ፋይዳ ታሪክን ማስተላለፍ ነው”
አቶ ቡልቻ ደመቅሣ (ፖለቲከኛ)
በአለም ታሪክ ውስጥ መጥፎም ጥሩም የሰሩ ሰዎች ሃውልት አላቸው፡፡ የጣሊያን ህዝብ ግማሹ ሙሶሎኒን አይወደውም ግን ሃውልቱ አለ፤ የሞስኮ ህዝብ ግማሹ ስታሊንን አይወደውም ግን ሃውልቱ አለ፡፡ የሚወደው ክፍል ሃውልቱን ያቆማል፣ የማይወደው ግን ሃውልት ሊቆም አይገባውም፣ ከቦታው አስወግድ ማለት አይችልም፡፡ እኛም የኦሮሞ ምሁራን የተሰራን ሃውልት፣ የተፈፀመን ታሪክ ተመልሰን እንለውጥ ማለት የለብንም፡፡ በሃውልቱ መገንባት ላይም ቅራኔ የለኝም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በአፄ ምኒልክ እጅግ በጣም ተበድሏል፡፡ ባሪያ ሆኗል፣ ተጎሳቁሏል ግን እሱ ታሪክ ነው፡፡ የአኖሌ እንደተባለው ተፈፅሟል፣ በሰነድ ላይ የሰፈሩ ፅሁፎችን ባላነብም ታላላቅ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን አረጋግጠውልኛል፡፡
የሃውልቱ ፋይዳ ታሪክን ማስተላለፍ ነው፡፡ እኛ ከዚህ ታሪክ ነው የወጣነው፣ ከዚህ ታሪክ ነው የበቀልነው፣ ከታሪካችን እንማር— በሚል ሃውልቱ መገንባቱ ነውር የለውም፡፡ ታሪክ በመፅሃፍ መልክም ለትውልድ ይተላለፍ የለም እንዴ? ሃውልቱ ይፍረስ የሚለውን ቅስቀሳ አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡ ሃውልቱ የበቀል ሳይሆን የመማሪያ ነው፡፡ መኖር አለበት፡፡
“እውነተኛ አርቲስት የጥላቻ መንፈስ አያንፀባርቅም”
ዶ/ር ሃይሉ አርአያ (ፖለቲከኛ)
ስለ አኖሌ ሃውልት የጠለቀ ግንዛቤው ባይኖረኝም በአጠቃላይ በሀገራችን የተገነቡ ሃውልቶችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ተናግሬያለሁ፡፡ በሃገራችን የታየው የሃውልት ግንባታ የሚያሳዝንና አደገኛም ነው፡፡ ምክንያቱም የእውነተኛ ሃውልት አላማ ህዝብን ማሰባሰብ፣ የብዙሃኑን ተጋድሎና መንፈስ የሚያንፀባርቅና ለመጪው ትውልድም ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ አሁን በሃገራችን የማያቸው ሃውልቶች ግን ህዝብን የሚያሰባስቡ ሳይሆኑ የሚያራርቁ ናቸው፡፡ ቂም በቀል አስታዋሽ፣ ቁስል ቆስቋሽ ናቸው፡፡ ስለዚህ ፋይዳቸው ዝቅተኛና አደገኛ ነው፡፡
በአጠቃላይ የሚገነቡትና የተገነቡት ሃውልቶች ገፅታ ከፋፋይ ነው፡፡ ወደ ኋላ የሚመልሰን ነው ስል፣ ከሃገሪቱ መፃኢ እድል አንፃር ተመልክቼው ነው። አሁን የሚያስፈልገን ያለፈውን ቁስል እያስታወስን በመካከላችን ቅራኔና ጥላቻ፣ ቂም በቀል ማናፈስ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ አዲስ ህይወትና ራዕይ ማምጣት ነው መሆን የነበረበት፡፡ ግጭትና አንዱ በሌላው ላይ በደል ማድረስ በኛ ሀገር አይደለም የተጀመረው፡፡ አሁን ታላላቅ መንግስታት ሆነው የምናያቸው አገራት ህዝቦች፣ በየዘመኑ ከፍተኛ እልቂትና በደሎች አሳልፈዋል፡፡ እነዚያ እልቂቶችና በደሎችን በማስታወሻ ፅፈው ያስቀምጧቸዋል እንጂ 24 ሰዓት ሙሉ ቂም በቀል የሚቀሰቅስ ሃውልት የሰሩ አይመስለኝም፡፡
ለምሳሌ 6 ኪሎ ያለው የሰማዕታት ሃውልት ያሳዝነኛል፡፡ ምክንያቱም ሃውልቱ የሚያስታውሰው መራራ ነገርን ነው፣ እልቂትን ነው፡፡ እርግጥ በውጭ ወራሪ የተፈፀመን ታሪክ ነው የሚያስታውሰው፣ ከዚያ አኳያ ምናልባት የወረራውን ግፍ የሚያሳይ ስለሆነ፣ ሃውልቱ ተገቢ ነው ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ያም ቢሆን ዛሬ አለማችን ትንሽ እየሆነች በመጣችበት ጊዜ፣ተበዳይና በዳይ ህዝቦች መቀራረባቸው አልቀረም፡፡ ዛሬ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ በከፍተኛ ሁኔታ ህዝብና መንግስትን እየደገፈች ነው፡፡ ከዚያ አኳያ ሲታይ፣ ያ ሃውልት ጠቃሚ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ እኔ በግሌ እንዲህ ያለ ሃውልት ጠቀሜታው አይታየኝም፡፡ በሰዎች መካከል መተባበርን መቀራረብንና መፈቃቀርን የሚሰብክ ሃውልት ነው መገንባት ያለበት እንጂ ቂም በቀልን የሚያስታውስ መሆን የለበትም፡፡
አኖሌ ላይ እንደተባለው ጡት መቁረጥ የመሳሰሉት ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በሌሎች ሃገሮች እንደሚፈፀመው ተፈፅሟል ቢባል እንኳ የዛሬ 100 ዓመት ገደማ የተፈፀመ በደል፣ ዛሬ ላለነው ትውልዶች አብሮ መኖርና መስራት እንቅፋት መሆን የለበትም፡፡ ይሄ ሃውልት ግን የሚሰብከው መፈቃቀር ጠፍቶ፣ ጥላቻ ስር እየሰደደ እንዲሄድ ነው፡፡ የጥላቻና የቂም በቀልን ችግኝ የሚኮተኩት ነው፡፡
እኔ በግሌ በአፈታሪክ ጉዳዩን ሰምቻለሁ፣ በፅሁፍ ግን አላጋጠመኝም፡፡ ከተፈፀመም በእውነት ታሪኩ አሳዛኝ ነው፡፡ በየትኛውም ጦርነት ሴቶች የተለየ ክብር እና ጥበቃ ነው የሚደረግላቸው፡፡ ጡት መቁረጥ የሚለውን እኔ ማመንም ይቸግረኛል፡፡ ይሄን ድርጊት የፈፀመው ምን አይነት ህዝብ ነው?
ከዚህ ሃውልት ማንም አይጠቀምም፡፡ ቂም በቀልን ማስታወስ እሳቱ የሚበላው አስታዋሹንም ጭምር ነው፡፡ እኛ ደግሞ የሚያስፈልገን እንዲህ ያለው ነገር አይደለም። ታሪኩ አይረሳ ነገር ግን በመዝገብ ተመዝግቦ ይቀመጥ፣ ታሪኩ ተጠንቶ በትምህርት መልክ ይሰጥ፡፡ የኛን አብሮ መኖር ህልውና የሚፈታተንና መርዝ የሚረጭ ሃውልት ማቆም ግን ተገቢ አይደለም፡፡ መጥፎ መጥፎውን እናስብ ከተባለማ፣ መንቀሳቀስ የማንችል ሰዎች ነው የምንሆነው።
እኔ ይሄን ሃውልት የሰራው አርቲስትም ይገርመኛል። በእኔ እምነት አርቲስት አይደለም፡፡ እውነተኛ አርቲስት ይሄን የቂም በቀልና የጥላቻ መንፈስ ማንፀባረቅ የለበትም፣ ምክንያቱም አርቲስት የፍቅር ስሜት ያለው፣ ሩህሩህ፣ ህዝብን የሚያፈቅር ነው፡፡ ሰላምን፣ የህዝብ መተባበርን የሚፈቅድ ነው፣ እውነተኛ አርቲስት፡፡ እናም የሃውልቱን መገንባት አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡
“ፖለቲካዊ ግብ ያለው ሃውልት ነው”
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የፍልስፍና ምሁር)
በዚህ 24 አመት ውስጥ የታሪክ ነጋሪ ነኝ በሚል ፈሊጥ፣ ብዙ መርዶ ነጋሪዎች በዚህች ሃገር ላይ ተበራክተዋል፡፡ ይሄም ሃውልት የመርዶ ነጋሪዎቹ ሃውልት ነው፡፡ ታሪክ በጣም ውስብስብ ነገር ነው፡፡ ብዙ ዓመት መጠናት አለበት፡፡ መርዶ ነጋሪዎች ግን ከየት እንደሚያመጡት ባይታወቅም፣ በእንደዚህ ያለ ጊዜ እንዲህ ተደርጓል የሚሉ ማስረጃ አልባ ታሪኮችን እያወሩ፣ሁልጊዜ በህዝቦች መሃል ግጭትና ፀብ ተንጠልጥሎ እንዲቀር የሚያደርጉ ሰዎች ሥራ ነው ብዬ ነው ሃውልቱን የምወስደው፡፡ የመርዶ ነጋሪዎች ሃውልት ነው፡፡ የታሪክ ውጤት አይደለም፡፡
ለምሳሌ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሃውልት መኖር ያለበት፣ ያ ታሪክ እንዳይደገም የሚያሳስብ አዎንታዊ ሚና ስላለው ነው፡፡ አውሮፓ፣ አሜሪካ — ወዘተ እንዲህ መሰል ድርጊቶች የተፈፀሙበት ሃገር ሁሌ ተመሳሳይ ሃውልት አለ፡፡ ይሄኛው ጠብ ለመጫርና ህዝብን ለማለያየት የተሰራ ስራ ነው፡፡ ሃውልቱ የተሰራላቸው ወገኖችና የቋንቋው ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ዜጎችን ድጋፍ እንኳ ያላገኘ ሃውልት ነው፡፡ እንደው በደፈናው ሃውልቱ ፖለቲካዊ ግብ ያለው ሃውልት ነው፡፡ ለወደፊት ከዲሞክራሲውና ከሃገሪቱ እድገት ጋር ሁኔታዎች ይሻሻላሉ ከሚል እሳቤ በመነሳት፣ ምናልባት ይህ ሃውልት በሰፊው ህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ስለማይኖረው ቂም በቀልን የማስተላለፍ ሃይሉ ሊቀንስ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አርቆ አሳቢ ነው፡፡ ህዝቡ እንደ ካድሬዎቹ አይደለም የሚያስበው። ህዝቡ እንደዚያ ቢያስብ ኖሮማ፣ ከተለያየን ቆየን እኮ! በየክልሉ ያለው አብዛኛው ህዝብ አርቆ አሳቢ እና ለሀገሩ ቀናኢ ነው፡፡ አንዳንድ ወጣቶች የካድሬዎቹን መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ፡፡ ግን ግዴለም የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንካራ ማህበረሰባዊ ትስስሮሽ ያለው ህዝብ ስለሆነ፣ይህን መሰል ሃውልት በድንጋይም ሆነ በብረት ተሰራ ዋጋ አይኖረውም፡፡ በጊዜው በብዛት በአርበኝነት የእዚችን ሃገር ባንዲራ በክብር ያቆሙት እኮ የብሄሩ ተወላጅ አርበኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሃውልቱ የጥላቻ ግንብ ቢሆንም መጪው ትውልድ ሊቀበለው አይችልም፡፡
“ሃውልቱ ቢገነባ ሌላው ምን ያንጫጫዋል?”
አቶ ገብሩ ገ/ማርያም (የመድረክ አመራር)
የኢትዮጵያ ችግር ዘርፈ ብዙ ሆኖ እያለ፣ ሰሞኑን ለምን አኖሌ ላይ ሃውልት ተሰራ ብለው የሚንጫጩ ሰዎች ይደንቁኛል፡፡ የሰው ልጅ ጡት እኮ ነው የተቆረጠው! የሰው እጅ እኮ ነው የተቆረጠው! በጥይት ሲሆን እኮ ወዲያው ነው የሚሞተው፡፡ ባህላቸውን ለማክበር ወተት ተሸክመው የሄዱ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ጡታቸው የተቆረጠው፤ ይሄ ነው ታሪኩን ልዩ የሚያደርገው፡፡ እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ድርጊት በዓለም ላይ ተፈፅሟል የሚሉ የታሪክ አዋቂዎች አላጋጠሙኝም፡፡ ታዲያ ዛሬ ለነዚህ ሰማእታት ሃውልት ቢገነባ የታሪክ ፀሃፊ ነን፣ አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች ምን ያነጫንጫቸዋል? እነዚህ የታሪክ አዋቂ ነን ባዮች እኮ በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት፣ ኦሮሞ ሸዋ ውስጥ ያልነበረ ብሄር ነው ብለው ሲፅፉ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱ እንደሚያወሩት፣ የሃውልቱ ፋይዳ ቂም ለማስተላለፍ አይደለም፡፡ በፊት እንደዚህ ነበረ ለማለት ነው፡፡ አሁን የድንበር ክለላዎችን እናስወግድ በሚባልበት በ21ኛው ክ/ዘመን ዘመን ቂም አይኖርም፡፡
ለምን የህውኃት ሰዎች ሃውልት ሲሰራ እነዚህ ሰዎች አልተንጫጩም? እኔ ይገርመኛል! ይሄኛውስ ከሰማዕትነት በምን ይለያል? ታሪኩን በሚገባ አውቃለሁ፡፡
ሰዎቹ አንድ በአል ለማክበር ወተት፣ ገንፎ፣ ቅቤ እና አባገዳዎች የሚይዙትን ተሸክመው በአላቸውን ለማክበር ሲሉ ነው ከበዋቸው፣ ዋና አዛዣቸውን መጀመሪያ ገድለው፣ ከዚያ በኋላ ሴቶቹን ጡታቸውን፣ ወንዶቹን እጃቸውን እየቆረጡ የለቀቁዋቸው፡፡ ይሄ በሌላ አለም የተፈፀመ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በወደቁበት ቦታ ላይ ሃውልት መስራት ምንድን ነው ነውሩ? መንጫጫቱስ ከምን አይነት ንቀት የመነጨ ነው? የብሄር ልዩነት አስፍቶ ግጭት ያመጣል የሚባለው የማይሆን ቅዠት ነው። ይልቅስ የምሁራኑ አስተሳሰብ ነው የሚያሰፋው፡፡ እኔ በአጠቃላይ የምለው ሃውልቱ መገንባቱ ጥሩ ነው፣ እነዚያን ሰማዕታት እናስታውስበታለን ነገር ግን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንደመሆናችን፣ ዘመኑ የሚፈቅደውን ስራ እንስራ ነው መባል ያለበት፡፡ መንጫጫቱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ እንደህ አይነት ታሪክ ደርሶብናል የሚሉ ካሉም፣የራሳቸውን ይገንቡ ሌላውን ግን አይንኩ፡፡ የቀይ ሽብር ሃውልት ሲሰራ፣ በነጭ ሽብር ኢህአፓ የፈጃቸው ሰዎች ሃውልትስ? ዛሬም ድረስ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ታሪክ አዋቂዎች፣ ፕሮፌሰሮች የማስተላልፈው መልእክት፣ ወሬ በማናፈስ ይህቺን ሃገር አትበትኗት የሚል ነው፡፡
“ዛሬ የኦሮሞን ህዝብ እየበደሉ ያሉት እነሱ ናቸው”
ዶ/ር ሞጋ ፍሪሣ (የኦፌኮ አመራር፤ ፖለቲከኛ)
ወደ ኋላ ሄዶ ታሪክ ጎልጉሎ ማውጣት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምኒልክ ግዛት ለማሰባሰብ ጦርነት አካሂደዋል፣ ይሄ የሚታወቅ ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ይሄ ተደረገ ብለው ታሪክ ለመንገር የሚሞክሩት እነሱ እነማን ናቸው? ዛሬ የኦሮሞን ህዝብ አንድነት በማናጋት ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው እኮ እነሡ! ታሪክን ለመንገር ብቁ አይደሉም፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የአኖሌ ታሪክን ማውጣቱ ትርጉሙ ምንድን ነው? ይሄን ለማድረግስ ምን የሞራል ብቃት አላቸው? ለወደፊት በሚገባ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚፃፍበት ጊዜ ለሃገራቸው ጥሩ የሰሩ ሰዎች ታሪክ ይወጣል፡፡ እነሱም ዛሬ ወንድሞቻቸውን እየገደሉ እኮ ነው? ታሪክ ለመፃፍ ብቁ አይደሉም፡፡ አሁን ታሪክ ብለው የሚያወሩ ሽማግሌዎችም እውነተኛ ኦሮሞ አይደሉም፡፡ በገንዘብና በጥቅም ተደልለው ነው፣ ታሪኩን ይሄ ነው ብለው የሚያወሩት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ በጣም ደግ ህዝብ ነው፡፡ በነሱ አካሄድ ቢሄድ ኖሮ፣ ኦሮሞና አማራው ተፋጅቶ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ህዝቡን እያፋጀ፣ በሌላ በኩል ደርሰው ታሪክ ነጋሪ ነን ማለት አይገባቸውም፡፡
መጀመሪያ ራሳቸውን ከኢህአዴግ ምርኮ ነፃ ማውጣት አለባቸው፡፡ እኔ የልዩ ቀዶ ህክምና ባለሙያ (Special Surgeon) ነኝ፡፡ ታሪኩን አልተመራመርኩም ነገር ግን በጦርነት ጊዜ ብዙ ነገር ይፈፀማል፡፡ ለምሳሌ ድሬደዋ ላይ ብቻ የተፈፀሙ የድሮ ታሪኮችን ጎልጉለን ብናወጣ ብዙ ነገር እናገኛለን፡፡ ያሸነፈው አካል እንዲህ ያለ ነገር መፈፀሙ የተለመደ ነው፣ እነሱ አሁን የሚሰሩትን ጥፋትና ተንኮል ለመሸፈን ሲሉ ነው ይሄን ያመጡት፡፡ ሰዎች እርስ በእርሳቸው በሚናከሱበት ጊዜ ላይ፣ ይሄን ሃውልት መገንባቱ በእሳት ላይ ቤንዚን መጨመር ነው፡፡
ዛሬ መነገር ያለበት አንድነታችንን ስለምንጠብቅበት ሁኔታ ነው፡፡ ዛሬ ከወገኖቻችን ጋር ተስማምተን የሃገራችን የአንድ ኢትዮጵያን ጥቅም የምናስከብርበት ጊዜ መሆን አለበት እንጂ ወደ ኋላ ሄዶ ታሪክ እየመዘዙ እንዲህ ያለውን ነገር መፈፀሙ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ዛሬ እኮ የኦሮሞን ህዝብ እየበደሉ ያሉት እነሱ ናቸው፡፡ (ምንጭ: አለማየሁ አንበሴ አዲስ አድማስ 24 May, 2014)
Taye Chefo says
This is up to the Oromo people. I wonder why the so called historians in this discussion say they haven’t found any written document in this regard. Let me ask them few questions. What percentage of Ethiopian history was recorded in the old times? And how many Oromo historians/writers were there in those days? The fact is the Oromo used to pass its history through oral narratives, just like the Gada System. Did the Oromo People record how the Gada System works in those days? Never. The case of Anole cannot be different. And the Oromo will not blame anybody but the system for what happened during that time. But it should be kept in statue and narrate the story! God bless Ethiopia!
yy says
I have no objection to the built of historic memory. But my worry is it is not a time to do so. we may get time after detail investigation of history in dispassionate way. then we can do in stable way. still the history of death and killing continued in Ethiopia, as well as in oromia so how the killer built history as a memory or as a excuse?
Natoolee says
*******************************************************************
…እውነት ነው ተበዳዩ ኦሮሞ ነው:: የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ የአኖሌ የግፍ ታርክ ሀሰት ነው ያለበት ግዜ ፈፅሞ ዬለም:: ለኦሮሞ ሕዝብ ዛሬ የተሻለ ግዜ ቢሆንም ሕዝቡ የሚፈልገውን ነፃነት ተጎናፅፏል ማለት ግን አይደለም::…
*******************************************************************
በዘመነ ሚኒሊክ የኦሮሞ ሕዝብ መበደልን በተለይም አርሲ አከባቢና ሐረርጌ ጨለንቆ አከባቢ ሲኖሩ በነብሩ ኦሮሞዎች ላይ አሰቃቂ በደል መደረሱን ለማመን የግድ የተፃፈ ታሪክ ሊኖረን አይገባም:: እንኳን ስለ ኦሮሞ በደል መፃፍ ይቅርና እንደ ሕዝብ መኖሩ እንኳን ለዓለም ሕዝብ እንዲታወቅ በማይፈለግበት ዘመን ይህ የግፍ ታሪክ ይፃፋል ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው:: የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ፖለትከኛ ወይም ታሪክ አዋቂ ኦሮሞ በዚህ የአኖሌም ሆነ የጨለንቆ ታሪክ ላይ አማራ ጡቴን እጄን ቆረጠ ያለበት አጋጣሚ መቼም አልነበረም ነጌም አይኖርም ይልቅ የሚኒሊክ ሥረዓት ለሆዱ ያደረውን ወይም ማስተዋል የጎደለውን አማራውንም ኦሮሞውንም ትግሬውንም እና ሌላውንም የሥረአቱ አግልጋይ በዚህ ሕዝብ ላይ አዝምቷል ነው እያለ ያለው::
የመንግስቱ ኃይለማሪያም የደርግ ሥረዓት የፈፀመውን ግፍ ከዬትኛው ብሔር ጋር ነው ያገናኘነው? የዘመን ፊውዳል ሥረዓት ከስግብግብነቱና ራስ ወዳድነቱ የተንሳ የሕዝቦችን ሀብት በተለይም የኦሮሞን ሕዝብ ከብትና መሬት ለመዝረፍና ሠፊውን ሕዝብ ለማስገበር ከተላያዩ አካባቢዎች በተሰባሰቡ ፍውዳሎች የተፈፀምን ግፍ ወደ አማራ ሕዝብ መጎተቱ ተቀባይነት ዬሌለው ነው:: በዘመኑ የተፈፀመው ግፍ በሥረዓቱ ፈፃሚነት እንጂ በሸዋ የአማራ ብሔር ፈፃሚነት መተግበሩን የመሰከረ ወይም ያሰተማረ ሰው ወይም ድርጅት ዬለም አኖሌ ያወገዘው የሚኒሊክን ሥረዓት ነው:: በዘመነ ሚኒሊክ አማራውም ሆነ ኦሮሞው የባላባት/ የፊውዳሎች አሽከር እንጂ የመሬት ባለቤት አልነበርም እናም ሥረዓቱ የሁለቱም ሕዝቦች ጠላት መሆኑ ሊሰመርበትና ሊታወቅ ይገባል::
በሌላ በኩል የኦሮሞ ሕዝብ እንድሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ የዚህችን ሀገር የድንበር ነፃነት እንዲጠበቅ መታገሉ እውነት ነው:: ግን ምን አተረፈለት ብለን ስንጠይቅ ሌላ ባርነት ይሆናል መልሱ:: ምክንያቱም በወቅቱ ሀገሪቷን ሲመሩ የነበሩት ፊውዳሎች የሕዝቦችን የመሬት ባለቤትነት ነፃነት; ንብረተ የማፍራት ነፃነትን; የኃይምኖትን ነፃነትን; በቋንቋ የመጠቀም ነፃነትን በአጠቃላይ ሰው እነድዜጋ ሊኖረው የሚገባውን ነፃነት በመግፈፍ ሕዝቦች ያስጠበቁትን የድንበር ነፃነት ወደ ከፋ ባርነት አሸጋግረውታልና:: ለዚህም ነው ይህንን ይሄን ሃውልት መቃወም ማለት ከመቶ አመት በፊት የነበረን ሥረዓት መናፈቅ ማለት ነው የምለው:: ይሄ የአኖሌ ሃውልት ለኦሮም ሕዝብ ታላቅ የታሪክ ምእራፍ እና በኢትዮጵያው ውስጥ በኢትዮጵያዊነት የመኖር እምነቱን አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ሃውልት ከመሆኑም በላይ ለኢትዮጵያ ጌጦቿ የሆኑትን ብሔር ብሔረሰቦችን ክብር ያጎናፀፈና አብሮነታችንን እጅግ የሚያደምቅ ሃውልት ነው:: ምክንያቱም ሚኒሊክ ማስተዋልና ዕውቀት በጎደለው ዐእምሮው ብዙህነታችንን ከስጋት በመቁጠር አንድ ኃይማኖትና አንድ ቋንቋ የሚለውን መርህ ለማስፈን ብዙ ግፍ በመፈፀሙ:: እናም አኖሌ ለዚህ ሰው ክብር አትሰጥም:: ለዚህ ጨካኝና በሕዝቦች ደም ለጨቀየ አምባ ገነን ክብር ስጡ ይምትሉ ከሆን በይፋ ይነገርንና […]:: ዛሬ ላይ የአኖሌን ታሪክ የመርዶ ነጋሪ ታሪክ አድርጎ ማቅረቡ ከተፈፀመው ግፍ በላይ ሊያም ይችላል:: መርዶ ነጋሪ ታሪክም ቢሆን ያልሞተን ሞት ቦሎ የነገረበት ታሪክ ባለመሆኑ ዛሬ ላለው መርዶውን ማርዳት ታርክን የማስተላለፍ አካል በመሆኑ ሊበርታታ እንጂ ሊወገዝ አይገባም:: መርዶው ታፍኖ እንዲቀር የፈለጉ አፋኞች ግዜው የከዳቸው መሆኑን ሊያውቁትና እውነቱን ሊቀበሉት ይገባል::
በሚኒሊክ ዘመን በሥረዓቱ የተፈፀምን ግፍ ዛሬ ከአማራ ጋር እያገናኙ ያሉት የአማራ ፀሀፊና ታሪክ አዋቂ ነን ባዮች ናቸው:: በተለይም የአንድነቱ ሊቀመንበር ሰሞኑን ከሪፖትር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ብብሔር መደራጀትንና(በፖለቲካ ፓርቲ ደርጃ) ክልሎችን በብሔር ማካለልን እንድሚያስቆም የድርጅታቸው እምነት መሆኑን ነገረውናል:: ሶማሊኛ እየተናገሩ ሳይሆን በአማርኛ እያናገሩን ስለኢትዮጵያ አንድነት ማወራቱ ጥርጣሬን ይጭራል እናም ዛሬም የአኖሌን ታሪክ የፖለቲከኞች ፍላጎት እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት አይደለም ቢሉን አይደንቀንም ደግሞስ ይህ መሆኑን በዬትኛው ጥናት አርገግጠውልን ነው? ይልቅ ዶ/ር ኃይሉ አረዓያ ያሉት ‘’የመጠፋፋት ታሪክን በሃውልት ከማቆም የስኬቱን ማቆሙ ይመርጣል’’ አግባብነት ቢኖረውም ኃውልቱ ግን አሁንም ስለሥረዓት እንጂ ስለ ብሔረሰብ አለማውሳቱን አውቀን ወታደራዊ ደርግን በአንባገነንነቱ እንድምናወግዘው ሁሉ የሚኒሊክን አምባገነንነትና የግፍ ታሪክም በጋራ ማውገዝ አለብን::
አንዳንዶች ኦህዴድ ይህንን ሀውልት የማቆም ሞራል ዬለውም የሚል አሰተያየት ሰጥተዋል እውነቱን ለመናገር ከሆነ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ ተማሪ ገበሬ ነጋዴ ወይም ምሁር በኦሮሞነት ማንነት ሲገፋ ሲሰደብ ወይም ሲታሰርና ሲገደል አላጋጠመኝም በፖለቲካ አቋሙ ግን በስመ ኦነግነት ወይም በሌላ ሥም መሸማቀቁና መዋከቡ መታሰሩ መስደዱና መገደሉ ሀቅ ነው:: ዛሬ ላይ ኦሮሞ ኦሮሚይ የሚባል መንግስትና (state) በመንግስቱም አፋን ኦሮሞ የትምህርት; የሥራ; የንግድ; የዳኝነት; የፖለቲካና የአስተዳደር ቋንቋ ሆነ እንዲያገለግል ያስጠበቀበት ሁኔታ እያለ ኦህዴድ ይህንን ሃውልት የመገንባት ሞራል ዬለውም መላቱ ሚዛናዊነት የገደለውና ተገቢነት ዬሌለው መሆኑ ልንገነዘብ ይገባል:: ይልቅ የዚህ ኃውልት መቆም በኦሮሞ ትግል ታሪክ ውስጥ ኦህዴድን ትልቅ ቦታ ያሰጠዋል::
በአጠቃላይ የአኖሌን ጉዳይ ለፖለቲካ ፍጆታ በማዋል ላይ ያሉት በስመ አንድነት ሽፋን “የአባ ገዳን “ከላቻ” ከአማራ ብልት ጋር ለማያያዝ የሚሞክሩ ጠባብና ራስ ወዳድ የሀሰት አንድነት ሰባኪዎች” ናቸው:: የአኖሌ ጉዳይ ከሚኒሊክ ሥረዓት ጋር እንጂ ፈፅሞ ከአማራ ብሔር ጋር አለመገናኘቱን እያወቁ ከአማራው የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት የሚጥሩ ኃይሎች ጉዳያቸውን ቆም ብለው ቢያስቡ መልካም ነው:: ትልቁ የኢህአዴግ አርቆ አሳቢነትና ቅንነት መገለጫ እንደዚህ አይነቶቹን ለዘመናት የታፈኑ እውነቶችን በመቀበል የግፈኞችን መቃብር አርቆ በመቆፈር እውነትን ከተቀበረችበት ወጥታ በክብር ትቆም ዘንድ መስራት መቻሉ ነው:: ድንጋይን ድንጋይ ማለት መቻል አለብን:: የአኖሌን የግፍ ታሪክ በሃውልት ማየትን አንሻም ማለት የሚኒሊክን ግፍ በክብር መዘከር ስለሚሆን የአኖሌንም ሆነ የጨለንቆን የግፍ ታሪክ ከአማራው ጋር ማቆራኘቱን አቁመን የሚኒሊክን የግፍ ታሪክ በጋራ በማውገዝ የዜጎችዋ ሁለንታናዊ ነፃነት የሚጠበቅባትን የተሻለች ኢትዮጵያን በጋራ ለመግንባት አብረን እንቁም:: Galatooma!!!
hadhaawa says
Abo tebarek ato anole
Andu atse bekerb me alenye mesleh naziw minlik ye blackoch j uses belony fegeg aderegen
yehen kumata nugusachewun chikanewun ena aramanenatun titow
emiye etiye abiye eyalu besew kusilina dem endehum resa lay mechefer menein yamelakital?
dr.dereje y. says
pls stop distorting the history of oromo,especially you habeshians.u(habesha) are nothing for oromos!
chu says
የኦሮሞ ህዝብ አንድም ቀን ባለፉት ስርኣቶች የደረሱበትን በደሎች የአማራን ህዝብ እንደ ህዝብ ተጠያቂ አድርጎት አያዉቅም:: በደሉን የፈጸሙት ስርኣቶች እንደሆኑ ሁላችንም የምናዉቀዉ ጉዳይ ሆኖ ሳለ የደረሰዉን በደል ለማስታወስ የተሰራዉ ሀዉልት በምን ስሌት በህዝቦች መካከል ቂም ልፈጥር እንደምችል አይገባኝም:: እነዚህ ሀዉልቱ ለምን ተሰራ ብሎ የሚከራከሩ ወገኖች ሌላ ጊዜ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ ጨቆዋኝ ሆኖ አያዉቕም ብሎ ስነግሩን አልነበረም እንዴ?ታዲያ የትኛዉን እኒያዝ አሁን? እንደዚያስ ከሆነ ታዲያ ደርግ ያደረሰዉን ጭፍጨፋ ለማስታወስ በትግራይ ብዙ ሀዉልቶች ተሰርቶዋል እነዚያንስ ምን እንበላቸዉ ታዲያ? እሱንስ ለምን አልተቃወሙም? ነዉ መንግስቱ ሀይለማሪያም አማራ ስላልሆነ? በጣም የሚገርም ነገር እኮ ነዉ:: ሕዝብን ያጋጫል ከተባለ የጨፍጫፊዉ የሚኒልክ ሀዉልት መሃል አዲስ አበበ ላይ ሆኖ ጥቻን ሳይፍጥር እዚያ ሩቅ አኖሌ የተሰራዉ እንዴት ልቀሰቅስ ይችላል? Ato Abebaw yemibalu sewuye degmo Tarik malet silalefe neger mehonun erasu ayakum ende? Tarikin ende Tarik erasu atansu eyalun new ende? “Ye Oromon hizb 100 amet wede huala yegotete” silu tinish ayafirum. And ye Oromo ababal astawesegn nigigirachewu “Kan humna qabu si reebeet booyicha si dhoorka” tirgumu gulbetegna ketkitoh endataleks yikelekilehal aynet neger new.
Sanyii says
Natoolee,
God bless you. Pls Keep on challenging those who tells us to be one speaking in their language(Amharic). If they want us to be Ethiopian let them make Afaan Oromo Federal Language and teach their children this great language as they ask us to learn their useless language.
Henok says
If Amharic language is useless as you said. what about yours?
please think twice before u write
Nbyu says
It is not based on tangible evidence and therefore it is fabricated by stupids!
Lemessa says
All Oromos at each corridor knows this fact very well.
minilik says
gobenan alfo yetederege neger yelem,yih wenjel tefetsimo kehone yaw gobena dache mehonu new teteyaqiw