
Brotherly advice to Ethiopian Friends በሚል ርእስ በፌስቡክ ገጽህ ለኢትዮጵያውያን ወንድሞችህ የሰጠህውን ምክር አነበብኩት። ጽሁፍህን ሳነብ የመጀመሪያ ባለመሆኑና በፌስቡክ አስተያየቶችህ ላይ ስለምከታተልህም ሃሳብህን ለመረዳት ብዙም አልቸገረኝም። በተለይ ወጣት ኢትዮጵያውያን ወደ ከፍተኛ የፖለቲካ አስተሳሰብ መድረክ መምጣት ለሃገራችን የሚኖረውን ዘላቂ ጠቀሜታ የምገነዘብ በመሆኑ ጀዋር የፖለቲካ ተንታኙ ወጣት እየተባለ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቀርበህ ሃሳብ ስትሰጥ ከአምስትና ስድስት አመት በላይ አውቅሃለሁ። ወጣቱ ጀዋር በዚሁ ከቀጠለ በሃገራችን ኢትዮጵያ ጥሩ ፖለቲከኞችን ልናፈራ እንችላለን የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ። በተለይም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ችግር የሚፈታው በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ፍትህ እና እኩልነት የሚያመጣ ስርአት በመገንባት ነው። የኦሮሞም ጥያቄ ሊፈታ የሚችለው በዚሁ ምህዳር ውስጥ ነው እያልክ በምትሰጣቸው ገለጻዎችና እንዲሁም የመገንጠልን ጥያቄ ያነሱ ክፍሎች ለኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብም አይጠቅሙም እያልክ ስታስተምር የነበርክ መሆኑን እንደማትዘነጋው እርግጠኛ ነኝ።
ውድ ጀዋር
በእድሜ አባትህ ልሆን የምችል ሰው ነኝ። ብዝበዛና ጭቆና እንዲጠፋ በንቃት ላይ በተመሰረተም ይሁን ሌሎች የእድሜ እኩያዎቼ ስሜት እየኮረጅኩ ከ16 አመቴ ጀምሮ ለፍትህና ለነጻነት መምጣት ጠጠር እየወረወርኩ የቆየሁ ነኝ። በተለይም 1966 ህዝባዊ አብዮት ከተቀጣጠለበት ጊዜ አንስቶ በነበረው የተደራጀ ትግል ውስጥ እንደዛሬው በሰኮንዶች መላውን አለም ሊያዳርስ የሚችል የቲክኒዎሎጂ ግኝቶች በሌሉበት ሁኔታ አንድን ሃሳብ በወረቀት አስፍሮ በመዳመጫ አደፍርሶ (አባዝቶ) በአውቶቡስ ወይም በእግር 3 ወይም አራት ቀን ተጉዞ የማደራጀትና ወጣቱን በትግል ዙሪያ ማሰለፍ የነበረበትን አድካሚ ችግር ማወቅ ብቻ ሳይሆን በወጣቱ አእምሮ ውስጥ ሃላፊነት የተመላበት መልእክት ለማስተላለፍ ይደረግ የነበረው ጥረት ቀላል እንዳልነበር በዘመኑ የነበሩ የሃገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ የሚያውቁት ነው። ምናልባትም በወቅቱ በነበረው ትውልድ ያ ሁሉ ድካም ፍሬ አለማፍራቱና ዛሬ በአንዳንዶች የተከፈለውን መስዋእትነት ጭምር ሊያንቁዋሽሹ ሲሞክሩ መታየቱና በዛሬ መነጽር ያንን ዘመን የመገምገም የታሪክ ውዥንብር መኖሩ እውነታውን ለመገንዘብ አላስቻለንም። ለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ በኔ እድሜ የተፈጠሩትንና በአይኔ ያየሁትን በተግባር የተሳተፍኩበትን የህብረተሰብ ሂደት እንኩዋን በሃቅና በ እውነት ላይ የተመረኮዘ ታሪክ ሳይሆን ከፖለቲካው ጋር እየተጣመመ የአሁኑ ትውልድ እንዲጋት ሲደረግ ስላየሁ ያለፉትና የዘመናት የህዝቦቻችና የሃገራችን ታሪኮች ሊያግባቡን ባይችሉ የሚያስደንቅ አለመሆኑን እገነዘባለሁ።
ከላይ ለመንደርደሪያ ይህን ካልኩ ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝን ኢትዮጵያውያን ብለን ራሳችንን ለምንገምት ሰዎች የሰጠህን ምክር ላይ ያለኘን የማጠናከሪያና የልዩነት ሃሳብ እንዲሁም ወጣቱ ጀዋርም ሊያያቸው ይገባል በምላቸው ሃስቦች ላይ እኔም ምክሬን ጀባ ልበልህ። ለዚህም በ 4 ዋና ዋና ሃሳቦችህ ዙሪያ ለማየት እሞክራለሁ።
በተራ ቁጥር 1/ የተጠቀሰው የምክርህ መሰረተ ሃሳብ በፍቅር የምታብዱላትን ኢትዮጵያዊነት ሃሳብ ህዝብን በመውደድና ተግባራዊ በሆኑ ተሳትፎዎች ምላሽ በመስጠት። ለተጎዳው ለታሰረው ለቆሰለው ጩሁ፡ ኢትዮጵያዊነት እራሱ አብስትራክት በግልጽ የማይታይ ነገር ነው የሚል ነው።
ወንድሜ ጀዋር በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊነትን ከኦሮሞ ከአማራ ከትግሬ ከደቡቡ በአጠቃላይም በዚያች ዛሬ ኢትዮጵያ በምትባል ሃገር ክልል ውስጥ ከሚገኙ ህዝቦች ነጥሎ ለማየት የሚፈልጉ ሃገር ማለት ህዝብ መሆኑን የሚዘነጉና በመሬት ክልል ዳር ድንበር ላይ ብቻ የተመሰረተ መገለጫ አድርገው የሚቆጥሩ የሉም ማለት አይደለም። በሌላ በኩል ሃገርና ህዝብን ለማስተዳደር ለመንግስታዊ አሰራር ቅልጥፍናና ለህዝብም ቀጠኛ ተሳትፎ አመችነት ክልል ወይም በድንበር ህዝብን በካርታ ወይም በጂዎግራፊያዊ ድንበር መከለልን ብቻ የተሟላ ነጻነትን የሚያጎናጽፍ አድርገው የሚመለከቱ ወገኖችም አሉ። ወይም በዘመናት የህዝቦች አሰፋፈር አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ያሉበትን ድንበርና ክልል የማንነት መገለጫ አድርገው የሚቆጥሩ ይኖራሉ። በተወሰነ ወቅት የብሄረስብ ጥያቀና አፈታቱ ላይ ዘመኑ ያፈራቸው የፖለቲካ ፈላስፋዎች ግምትም ለዚሁ ጥያቄ የተለያዩ መፍትሄዎች በማቅረባቸው ቀጣዩ ትውልድ ይህን በተግባር ለመተርጎም ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለበት ለመሆኑ አያጠያይቅም።
በሃገራችንም በ1966 የነበረው ወጣት ትውልድ የአጼውን ስርአት ለመታገል በስርአቱ ላይ የነበሩ በመሬት ላይ ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በአለም አቀፍ ደረጃ እንደፋሽን ይታይ የነበረው የሶሻሊዝም አግዋጊ አስተሳሰቦችን ለማወቅ የተነሳሳበት ዘመን ነበር። በዘመኑም የመደብ ትግል የብሄረሰብ ጥያቄ ወዘተ መፈታት ያለበት በማርክሳዊ የፖለቲካ መፍትሄዎች ነው ብለው ስላመኑ ዛሬ የምናያቸው አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ሰዎች ወይም ለብሄረሰብም ሆነ ለኢትዮጵያዊነት እንታገላለን የሚሉ በዚሁ የመፍትሔ ሃሳብ የሚሽከረከሩ ናቸው። ወጣቱ ጀዋርም ኢትዮጵያዊነትን ብሄራዊ ንቅናቄን ያነገቡ ሰዎችን የሚመለከተው ታላላቆቹ ፖለቲከኞች በቀደዱት ጎዳና እንጂ ዛሬ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለበት ነባራዊ ሁኔታ አንዱ ተጨቁዋኝ ሌላውን ጨቁዋኝ በሚያደርግ የብሄረሰብ ጥያቄና በወቅቱ መፍትሄ ይሆናሉ ተብለው የቀረቡትን ሁሉ በሃገራችን በመፍትሄነት በማቅረብ እንደ ቤተሙከራ አይጥ በህዝብ ህይወት ላይ እንሞክርበት የሚባልበት ዘመን ላይ አለመሆናችን ግልጽ ነው። ወደድንም ጠላንም ዛሬ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ሌሎቹ ብሄር ብሄረሰቦች በራሳቸው የዘመናት ትግልም ሆነ በህብረተሰብ እድገት ሂደት በእትዮጵያ ምድር ውስጥ ባይተዋር ከሚሆኑበት አስተሳሰብ ወጥተዋል። ወደድንም ጠላንም ዛሬ የአማራ ህዝብ በሌላው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ እንደ ጨቁዋኝ የሚታይበት ስእል አብቅቶአል።
ዛሬ የትግራይ ህዝብን ለስልጣናቸው ሲሉ አንተ ወርቅ ነህ እያሉ በሌሎች ወንድሞቹ ዘንድ የበላይነት እንዲሰማው ይደረግ የነበረው ሴራ ከሽፎአል። ለአማራውም ለኦሮሞውም ለትግሬውም ለጉራጌውም ህዝብ ህልውናና የመኖር ተስፋ እንቅፋት የሆነውና የሁሉም የጋራ ጠላት የሆነ በስልጣን ላይ ያለ ህወሃት ኢህዴግ የሚባል የፖለቲካ ድርጅትን የሚመሩ ጥቂት አልጠግብ ባዮችና መሰሎቻቸው የዘረጉት ስርአት መሆኑን ህዝብ ከመቼውም በላይ ተገንዝቦአል። ዛሬ እስር እንግልት ግድያ የሚፈጸመው ኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ባነገቡት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን ወንጀል ባደረጉ ጥቂት ከፋፋዮች ነው። በህገመንግስታቸው ጭምር ኢትዮጵያን ለመበታተን ሁን ብለው አስበውም ባይሆን በነበራቸው ጨቅላ አስተሳሰብና የጫካ ወኔ ስሜታዊ ጉዞ ጭምር መገንጥልን የሚደግፍ አንቀጽ ያስቀመጡበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህም ከዛሬው አለማቀፍና አገር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም በግሎባላዜሽን ዘመን አለም በተሳሰረበት ዘመን የመገንጠል ሂደት የሚያስከትለውን እልቂትና አጥፊነት ሃላፊነት ባለው መልኩ የተፈጸመ ደባ መሆኑን ለወጣቱ አክቲቪስት ግልጽ ይመስለኛል።
ወንድሜ ጀዋር
አይ አም ኦሮሞ ፊርስት (I am Oromo First) ባልክበትና ብዙ ውዝግቦች በነበሩበት ወቅት የማለት መብትህ ሊከበር እንደሚገባ ተሟግቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞ ነህ። ስትወለድ ሳታውቀው ሳትፈቅድም ጭምር በተፈጥሮ ያገኘሀው ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተቀዳጀሀው ማንነት አይደለም። ያ ብሄረሰባዊ ማንነትህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን አንተ ብትፈልገውም ባትፈልገውም ሰጥቶሃል፡፡ ሁላችንም በፈቃደኝነት አይደለም የሆነው በዚያች ምድር በመፈጠራችን ብቻ እንጂ። አሁን ባለህበት ሃገር ኦሮሞ መሆን አልፈልግም ማለት ይቻላል? አዎ ይቻላል ምክኒያቱም ፖለቲካዊ ምርጫ ሊሆን ይችላል። የህብረተሰብ እድገት የቤተሰብ አፈጣጠር ህግ ግን አይፈቅድልህም (Naturally) ኢትዮጵያዊነትም እንደዚሁ ነው በፖለቲካ ስርአት መገለጫ በዜግነት ጥያቄ ላይ ኢትዮጵያው የሆነ ሰው አሚሪካዊ ማንነት ሊያገኝ ይችላል። በተፈጥሮ ህግ ግን አይደለም። ለዚህም ነው I am oromo first ማለትህ ሃጢያት አለመሆኑን የተገነዘብኩት። በተከታታይም በወጣትነት ስሜት ለተናገርካቸውም ልክ አለመሆንህን በወቅቱ ላሳይ ሞክሬአለሁ። የወጣትነት እድሜ የማታልፈው የ እልህ የቁጣ የግልፍተኛነት በሌሎች ተሰሚነት እንዲኖርህ የምትፈልግበት እኔነት የሚታይበት ዘመን በመሆኑ እራሴን በዚያ ዘመን አስቀምጬ አየሁህ እንጂ ልፈርድብህ አልቃጣኝም። ኢትዮጵያዊነት የሚለው አስተሳሰብ ኦሮሞነትን አማራነትን ትግሬነትን ወይም የተወለድክበትን ህብረተሰብ የሚያስክድ የሚያጠፋ ከሆነ ከጎንህ ብዙዎች አለን። ኢትዮጵያዊነት የጨቋኝ አስተሳሰብ መገለጫ አድርገው የሚመለከቱትን ደግሞ አለመሆኑን በጽናት እየታገልን እንተማመናለን። ኢትዮጵያዊነትን በጎሪጥ መነጽር እይታ እየታየ ሃገራዊ መተሳሰርን የማይታይ የማይጨበጥ አድርጎ ማስቀመጥ እውነት ኦሮሞን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ይገልጻልን? ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ለማድረግ ህይወታቸውን የገበሩትን እልፍ አእላፍ የኦሮሞ ልጆች የከፈሉት መስዋእትነትና ዛሬም እየከፈሉ ያሉት መስዋእትነት አብስትራክት ነውን? በየመቃብር ቤቱና በየጥሻው ለሃገር ሲሉ የተዋደቁት አጥንታቸው አብስትራክት ነውን? መልሱን ላንተው ትቸዋለሁ።
በተራ ቁጥር 2 የገለጽከው የምክር መሰረታዊ ሃሳብ በታሪክ እንደሚታወቀው የብሄራዊ ንቅናቄዎችን መተናኮል የትም አያደርስም፡፡ ይህ ለኤርትራም አልሰራም አጼ ሃይልስላሴና መንግስቱም የብሄራዊ ንቅናቄዎችን ለመጨፍለቅ በመሞከራቸው ነው የወደቁት እንዲያውም ብሄራዊ ንቅናቄዎች በንዲህ አይነቱ አካሄድ በአሸናፊነት ነው የሚወጡት የሚል ነው።
በርግጥም በታሪክ ሂደት በተወሰኑ ወቅቶች አለም በሁለት ካምፕ ተከፍሎ በነበረበትና በሶሺያሊስቱ ካምፕ ብሄራዊ ንቅናቄዎች ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙ በነበረበት ወቅትና ጭቆና ባለበት ስርአት ውስጥ መቆየትን ያልመረጡ ህዝቦች መራራ ትግል አካሂደው የራሳቸውን ሃገርና ግዛት መመስረታቸው እውነት ነው። በአጼ ሃይለስላሴና በደርግ ጊዘ ብሄራዊ ንቅናቄዎች ለመነሳታቸው በቂ ምክንያቶች ነበራቸው። እርግማን ሆኖብን ህዝቡ በትግሉ ያገኘውን ድል ጭምር ስለምናንኳስስ እንጂ በደርግ ዘመን በመሬት ላራሹ በኢኮኖሚው የነበረን ቀጥተኛ የተዛባ ግንኙነት የብሄር ጭቆናን በመላው ሃገሪቱ መልሶታል። በተለይ በሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ከመሬት ጋር የተያያዘውን መንግስታዊና ሃይማኖታዊ ተጠቃሚነት በመሬት ላራሹ አንኳክቶታል። የሃብት ክፍፍሉ ኢፍትሃዊና አንዱን ብሄረሰብ ተጠቃሚ መስሎ የሚታይበትን የኢኮኖሚ ግንኙነት በጣጥሶታል። በሶሻሊዝም የኢኮኖሚ ፍልስፍና ሁሉም ነበር የደሀየው። ደርግ ወድቆ ህወሃት ኢሃዴግ ስልጣን ሲይዝ የብሄር ንቅናቄዎች በሙሉ በተሳተፉበት የሽግግር መንግስት ሲመሰረት በአንድ በኩል የፖለቲካ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ሊያረጋግጥለት የሚችለውን የከፋፍለህ ግዛ እምብርት ህገመንግስት የመገንጠል መብት ጭምር አካትቷል።
ነገር ግን በውስጡ የብሄራዊ ጭቆና ጥያቄዎች አካልና መገለጫ የሚባሉትን የባህል የቋንቋና የማንነት ጥያቄ ጭምር መፍትሄ መስጠቱ የብሄር ጥያቄን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መመለሱ አሁንም ህወሃት ኢሃዴግን ብንጠላውም የታየ እውነታ ነው። ለዚህም ማረጋገጫው ጀዋር ወንድሜም ሆኑ ሌሎች ስርአቱን የሚቃወሙ ሃይሎች ከኦነግና ከኦጋዴን ነጻ አውጭ በስተቀር ክህወሃት ኢሃዴግ ጋር የነበረው ልዩነት ወይም የፖለቲካው አቅጣጭ በጥቂት አምባገነኖችና በኋላም እየተጠናከረ በመጣው የአንድን ብሄረሰብ ወኪል ነኝ ባዩ ህወሃት ኢሃዴግ መንግስት ጸረ ዲሞክራሲያዊና የጥቂቶች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው ተጠቃሚነት ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ግልጽ ነው።
በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ የሚደረግ ትግል በተለይ በሃይል የተገኘ አሸናፊነቱ ብቻ ህዝባዊ ነው ማለት አይቻልም። ወንድሜ ያነሳሀው የኤርትራ ጥያቄም ኤርትራ በመገንጠሏ ተጠቃሚው ኢሳይያስ አፈወርቂና መሰሎቹ ናቸው፡፡ ወያኔ ኢሃዴግ የብሄር ጥያቄ ሲያቀነቅን ከርሞ በኢትዮጵያ ስልጣን አየር ላይ መሆኗን ሲያውቅ ኢትዮጵያዊ ካባውን አጥልቆ ስልጣን ላይ ቁጭ ብሎ ሌሎችን በመከፋፈል የብሄር ፖለቲካን ወደ ዘረኝነት ፖለቲካ ቀየረው። ልክ እንደ ኢትዮጵያ ኤርትራ ውስጥም በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች እንደሚኖሩ የሚታወቅ ነው። ጭቆናና ነጻነት ምን እንደሆነ ለሚረዳ ሰው ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ በመገንጠላቸው ነጻነትን አግኝተዋል ብለው የሚያሰቡ ካሉ አያስደንቅም። ኤርትራ የምትባል ሃገር መፈጠርዋ በኤርትራ የሚገኙ ብሀረሰቦች እኛ ዛሬ ስለብሄረሰብ ነጻነት በምንፈልገው መስፈርት ከሆነ ገና ብዙ ይቀራቸውል። እና ከዚያም በላይ ሃገሮች ለመሆን ገና መታገል ሊኖርባቸው ነው። ስለዚህ ወንድሜ በቅርቡ በመገንጠል ነጻነታቸውን ያወጁት ጎረቤቶቻችን ኤርትራም ሆነች ደቡብ ሱዳን የመገንጠልና ሃገር የመመስረት ጥሩ ምሳሌዎች አይደሉም።
ዛሬ በርካታ ኤርትራውያን ወንድሞቻችን የታለፈውን የእብደት ዘመን እየተመለከቱ ያንን ያህል በአለም ትልቅ ጦርነቶችና ደም መፋሰስ ከተካሄደ በሁዋላ የተፈጠረውን የነጻነት ውጤት በሃዘን እያስታወሱት ነው። በጣም የሚያሳዝነው ግን እነ ኢሳያስና መለስ ስልጣናቸውን ለማቆየት ሲሉ ዳግም በሁለቱ ህዝቦች መካከል እልቂትን ፈጥረው ዛሬም ድረስ ችግሩ እልባት አለማግኘቱ ነው። ስለዚህ አክራሪ ናሽናሊስቶችን ካበሳጫችሁ እንደ ኢርትራ ሊመጣ ይችላል የሚለው አመለካከት ዛሬ ምናልባት በጥቂት አክቲቪስቶችና የኦሮሞ መገንጠል በኦሮሞ ላይ ንጉስ ሊያደርገን ይችላል ብለው ለስልጣን ከሚቁዋምጡትና የወንድማማቾች ደም እንዲፈስ ከሚፈልጉት በስተቀር የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ለዚህም ምድር ላይ ከስርአቱ ጋር የሚፋለሙት ወጣቶች አንድነትን በደማቸው እየገነቡ መሆኑን እያየን ነው። ኢትዮጵያዊነት አብስትራክት አይደለም ትላንትም ዛሬም በህዝቦች ደም እየተገነባ ያለ ሃገራዊ ማንነት ነው። በዚሁ መስመር ላይ የተናገርከውና የምጋራህ የኢርትራውያንን መገንጠል ለዘመናት ሲያወግዙ የነበሩ እጅ ሰጥተው እርዳታቸውን እየለመኑ ነው የሚለው ነው። አዎ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሁለቱ ህዝቦች መቀራረብ የሚፈጠረው አምባገነኖች ከፍፋዮችና ገንጣዮች ሲወገዱ ብቻ መሆኑን የሚያምን ሲሆን ስልጣን በአቅዋራጭ የሚፈልጉ ኢሳይያስ ስር ቢልመጠመጡ አያስደንቅም።
በተራ ቁጥር 3 የምክር አስተያየትህ የብሄርተኞችን ልብና ቀልብ ለመሳብ ከጎንደርና ከባህር ዳር ወጣቶች ተማሩ “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የእኛም ደም ነው” የሚለው መፈክር ቅድመ ሁኔታ የሌለበት በንጹህ ሰብአዊነት ስሜት ላይ የተመረኮዘ ብሄረተኞችን ስጋት የማይከት አስተሳሰብ አዳብሩ ነው።
አቦ ልክ ነህ። ንጹህ ፍቅር የማይለውጠው ነገር የለም። በተንኮል እና ሸፍጥ ላይ የተመሰረተ ግለሰባዊ ህይወትም ሆነ ቡድናዊ አስተሳሰብ ራስንም ያጠፋል። ዛሬ ለፖለቲካ ጨዋታ ብቻ ሲባል በፖለቲከኖች ልባዊ ያልሆነ ወይም በዘላቂ ሃገራዊና ህዝባዊ ጥቅም ላይ ያልተመሰረተ የእንተባበር አካሄድ የትም አያደርስም። የአማራውም ሆነ የኦሮሞው ደም የሰው ልጅ ደም ነው። እንኳንስ በአንድ ጂዎግራፊያዊና ሃገራዊ ምድር ላይ በደምና በልዩ ልዩ የህብረተሰብ መተሳሰሪያ ገመዶች የተሳሰሩት የአማራና ኦሮሞ ልጆች ቀርቶ ቻይናም ይሁን ህንድ አፍጋኒስታንም ይሁን ጊምቢ የንጹሃን ደም ያለአግባብ ሲፈስ ውስጡን የማይሰማው ሰው ፖለቲከኛ ወይም አክቲቪስት ወይም ማንኛውም ዜጋ ተልእኮው በምድራዊ አጥፊነቱ ብቻ ሳይሆን በሰማይም ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ነው።
ሰብአዊነትና ቅንነት የጎደለው ሰው ነጻነትን አያውቅም። የነጻነት ምንጩ ለህይወት የምንሰጠው ግምትና አክብሮት ነው። ነጻነትን አብስትራክት አድርጎ የሚመለከትም የዚህ አይነት አስተሳሰብ ያለው ግለሰብ ወይም ቡድን ነው። ነጻነት ከያንዳንዱ ሰው ነጻ መሆን ይጀምራል። ስለዚህም ወንድሜ እንዳልከው በነጻነት ስም የሰውን ልጅ ነጻነትና የመኖር ህልውና ከሚያሳጡ አፋዊ የፖለቲካ መቀራረብ ታክቲኮች ተላቆ ዘለቂታና ሁሉንም ነጻ ሊያደርግ የሚችል ራእይ ላይ የተመሰረተ ትግል ማድረግ ነው። ለሁሉም ክፍል የሚበጀው ይህው ነው።
በ4ተኛ ተራ ቁጥር ምክርህ የፖለቲካ ጩሀት መንጫጫት ከመደራጀትና ህዝብን ከማንቀሳቀስ ውጭ ትርጉም የለውምና እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት ወይም የተወሰነ የፖለቲካ ቡድንን አስተሳሰብ ለመቀየር መደራጀት አስፈላጊነቱን ገልጸህ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነት ብለው ወይም የአንድነት ሃይሎች ነን ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ (unitarist Ethiopianist camp) በመሬት ላይ የሌሉ ናቸው በማለት ለማስረጃነትም አዲስ አበባን በመጥቀስ የነዚህ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ መሰረት የሆነችው ከተማ በተደጋጋሚ ጊዜ ለቀረበላት የምድር አንቀጥቅጥ ጥሪ ምላሽ አልሰጠችም ይህም አለመደራጀትን የሚያመለክት ነው የሚል ነው።
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ አዲስ አበባን በሚመለከት የተለያዩ ጸሃፊዎችና ተንታኞች የተለያዩ ምክንያቶችን የሰጡ በመሆኑ በበኩሌ በአጭሩ ለአዲስ አበባ በትግሉ ውስጥ ያለ መንቀሳቀስን በሚመለከት በአንድ አረፍተ ነገር ላጠቃለው። የአዲስ አበባ ህዝብ እንደሌሎቹ አካባቢዎች በደል ሳይደርስበት ቀርቶ ሳይሆን በደልን በማስወገድ ረገድ በደልን እናስወግዳለን ብለው የተነሱ ግለሰቦች ቡድኖች የፖለቲካ ድርጅቶች በፈጠሩበት ውዥንብርና አቅጣጫ በሌለው አካሄድ ውስጥ በተደጋጋሚ የገበረውን ህይወት መልሶ ላለመገበር ከመፈለግ ነው። በተለይም ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም ጭምር በመገናኛ አውታሮች በሚሰጧቸው የማይጨበጥ ተስፋ፣ ያልተማከለ ትግልና በህዝብ ልብ ውስጥ ገብቶ ስሜትን ሊያነሳሳ የማይችል የፖለቲካ ግብ ተጽእኖ አሳድሮአል።
በየትኛውም ሃገር እንደታየውና በሃገራችንም የለውጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ብሶትና ጭቆና መኖር ብቻውን ለውጥን አያመጣም። ጭቆናና ብሶት ህይወታቸውን በማንኛውም አይነት መንገድ የጎዳቸው፣ መንሰኤውንና መፍትሄውን ጭምር የተገነዘቡ፣ የአለምን አጠቃላይ ሁኔታ የህብረተሰብን እድገት ህግጋት የተረዱ፣ በአለም አቀፍና በአካባቢ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚያመነጩ ከሁሉም በላይ የቆሙለትን ማህበረሰብ ጠቃሚ እሴቶችን ቀጣይነትና በለውጡ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና የሚያገናዝቡ የተከፈተ አእምሮ ያላቸው ግለሰቦች መሰባሰብና አመራር መስጠት ወሳኝ ነው። እነዚህ የግለሰብ ስብስቦች ናቸው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ሲቪክ ማህበራት ወይም ለአንድ አላማ የሚንቀሳቀሱ አክቲቪስቶች ብለን የምንጠራቸው። ዋነኛ ተግባራቸውም ያሰቡትን ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ህዝባዊ መሰረት መፍጠር ነው። ዋና አስፈላጊነታቸውም ለውጥን ለማምጣት በሚከተሉት አቅጣጫ የሚከፈለውን መስዋእትነት በተለይም የህይወት ጥፋት በማሳነስና እያንዳንዷን ህይወት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደየሃገሩ ተጨባጭ ሁኔታና በስልጣን ላይ ያሉ መንግስታት ባህሪይ በማያመች መልኩ በተቀናጀ የትግል ስልት ህብረተሰቡን ማንቀሳቀስ ነው።
ወንድም ጀዋር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በፖለቲካ አደረጃጀት ረገድ ህዝብን በማደራጀትና በተለይም ወጣቱን በማንቀሳቀስ ረገድ እንደ ኢህአፓና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መኤሶን በሁዋላም ቅንጂት በኦሮሞ ትግል ውስጥ ኦነግ ጫካ በነበረበት ጊዘ የነበረውን ህዝብን ማንቀሳቅስ ምናልባት በታሪክም በደረስክበትም የምታውቀው ይመስለኛል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በፖለቲካ ድርጂት አንጻር አሁን ባለንበት ወቅት ያን የመሰለ የህዝብን ተነሳሽነትና በተለይም ወጣቱን የሚያንቀሳቅስ ድርጅት ዛሬ የለም ። እነዚያ ህዝብን ከዳር እስከዳር ያንቀሳቅሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ትላንትም ሆነ ዛሬ ለምን ላይሳካላቸው ቻለ? በኔ አስተያየት አበይት የምላቸው ምክንያቶች፤
- ይታገሉት የነበረው ከለየላቸው አምባገነኖችና እስከ እለተ ሞታቸው አጥፍቶ መጥፋትን መመሪያቸው ያደረጉ ጨካኞች በጉልበት ስላጠፏቸው፤
- እነዚህ ድርጅቶች ህዝብን ነጻነት ለማጎናጸፍ የጀመሩትን ጉዞ በጽናት መቀጠል አለመቻል ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው በሚፈጠሩ ችግሮች የሚቃወሙት ስርአት ላይ በጋራ ከመነሳት ይልቅ መጠፋፋትን መምረጣቸው (እራስን መግድል ሂደት)፤
- ሲነሱ የያዙትን የፖለቲካ አጀንዳና አላማ ከወቅቱ አለም አቀፍ አክባቢያዊና ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አለመጣጣም መቻልና ግትርነት፡ ማረም ወይም መታረም ሽንፈት ስለሚመስላቸው መሳሳታቸውን እያወቁ ጭምር በእልህ ፖለቲካ መቀጠላቸው ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው። በነገራችን ላይ ይህ ለሚታገሉት ክፍሎች ብቻ ሳይሆን ለወደቁትም መንግስታት ዛሬም በስልጣን ላይ ላሉት መገለጫ ነው።
እዚህ ላይ ዋናው ሃሳቤ በተለይም ወንድሜ ጀዋር የኢትዮጵያዊነት ሃይሎች የሚገባውን ያህል ተጠናክረው አለመታየታቸውን ማሳየትህ ተገቢ ቢሆንም ለዚህ መነሻ የሆነህ አንተም በምክርህ እንደገለጽከው ወይ ተደራጁ አልያም በአሁኑ ወቅት ህዝቡን በማንቀሳቀስ ላይ ላሉት ንቅናቄዎች ማለትም ለኦሮሞ ወይም ለአማራ አክቲቪስቶች ድጋፍ ስጡ የሚል ጥሪህን እንድታቀርብ አስገድዶሃል። ለዚህ መነሻ የሆነህ በርግጥም ባለፉት አንድ አመታት በመሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አካሄድ ተስፋ በመቁረጥ ወይም የኦሮሞ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የአማራ ተጋድሎ ንቅናቄ በተለይ ወጣቱን በማንቀሳቀስ ረገድ ያደረጉት ተጋድሎና በከፈሉት መስዋእትነት ላይ ተመስርቶ ነው። በአብዛኛው ንቅናቀዎቹ በወጣቱ የሚመሩ መሆኑ ደግሞ ግልጽ ነው።
ከላይ በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ወጣትነት አዲስ ነገር ለማየት ወይም ለለውጥ ጽኑ ፍላጎት መኖሩ አንዱ መገለጫ ባህሪይ ነው። ትላንት ወጣት በነበርኩበት ዘመን በታሪክ ለለውጥ መስዋእትነት የከፈሉ ብዙ የተጻፈላቸው ወጣቶች ባይኖሩም ሃገራቸውንና ህዝባቸውን የሚወዱ ወጣት ጀግኖች በጣሊያን ወረራ የፈጸሟቸውን አንዳንድ ታሪኮች አነብ ነበር። በተለይም እነ አብርሃ ደቦጭ ሞገስ አስገዶም ዘራይ ደረስ አብዲሳ አጋ በወጣትነት እድሜ ውስጥ የነበሩ መሆናቸውና በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄም እነ ጥላሁን ግዛው ማርታና ዋለልኝ መኮንን ባልዳበረው ጭንቅላቴ እነሱን መሆን እንደ ትልቅ ነገር እመለከት ነበር። ደርግ ስልጣን ላይ ሲወጣ ወጣት ስለነበርኩ በወቅቱ ገንነው የነበሩና በደርግ ፋሽስታዊ ተግባር በየአደባባዩ ወጣቶች ተገድለው ሲጣሉ ማየት ውስጤን ያንገበግበው ስለነበር ያ ስርአት እንዲቀየር ከሚታገሉት ጋር መወገንን መረጥኩ። ያ ውስጣዊ ስሜቴ ነበር። ውጫው ሁኔታዎችም ነበሩ። ኢህአፓ መሆን ክብር ነበር።
ኢህአፓ መሆን የሰለጠነ አስተሳሰብ ያለው ሰው መሆን መስሎ ይታየኝ ነበር። ኢህአፓን ማውገዝ ወይም በኢህአፓ ላይ የተለየ አስተሳሰብ ማቅረብ ከህብረተሰቡም ያገልህ ነበር። ሞትና እስራትም አይታይም ነበር። ወደ መታረጃው የሚሄድ ወጣት ኢህአፓ ያሽንፋል እያለ ለድርጅቱና ድርጅቱ ያነገባቸውን መፈክሮች እየዘመረ በተደፋበት ለዘላለም ያሸልብ ነበር። የአንድ ብሄረሰብ ወይም አካባቢ ብቻ ታሪክ አልነበረም። በብሄር ድርጂቶች ውስጥም የተሰለፉ ዛሬ በጥቂት አምባገነኖች አይን እይየን ከጫካ የመጡ እያልን የምንዘልፋቸው የዛሬን አያድርገውና የያኔዎቹ የትግራይ ወጣቶችና በአርሲ በባሌ በሃረርጌና በወለጋ በኦነግነት ያለቁት ወጣቶች አንድም በትግሉ አላማና ግብ የተሳቡ በሌላ በኩልም የወጣትነት እድሜ ባህርይ አስገዳጅ ሁኔታዎችም ነበር። የተወሰነ ወቅት ለውጥ መፈለግ ፋሽንም ጭምር የሚያመጣው ግፊት ነው። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የእኔነትን ስሚት ከፍ እያደረገ በርካታ ወጣት ለምን እንደሚታገል እንኳን በሚገባ ሳይረዳ የአምባገነኖች ሰለባ ሆነ። አንዳንድ መሪዎቹም በተክለ ሰውነት አበዱ።
በዚህ ሁኔታ በምንም የማንተካቸው ወንድሞቻችንን አጣን። አንዳንዴ ሳስበው እነዚያ ወገኖቻችን ዛሬ ቢኖሩና እንደኔ በአነስተኛ እውቀት ፖለቲካን በመተንተን የሚኖሩ ሳይሆን ምርጥ ሳይንቲስቶች ሆነው ሃገርን ብቻ ሳይሆን አለምንም በመቀየር ሂደት ከፍተኛ አስተዋጾ ሊያበረክቱ የሚችሉ እንደነበሩ መረዳት አዳጋች አይሆንም። ይህን ማንሳቴ ኢህአፓን ወይም ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችን በዛሬ መነጽር ተመልክቼ ልተች ሳይሆን የወጣት ስነልቦናና የፖለቲካ ለውጥ የነበራቸውን ወይም ወጣቱ የሚያደርገው ትግል ሁሉ በአግባቡ እስካልተያዘ ድረስ የሚያስከትለውን ጉዳት ለማሳየት ነው። ዛሬ በኦሮሞ በአማራ ህይወታቸውን ላጡ ጨቅላዎች የምናስብ ከሆነ የእያንዳንዱ ወጣት ደም ከፌስቡክና ከሚዲያ ማዳመቂያ በዘለለ በእውነትና በሃቅ ላይ ለተመሰረተ ዘላቂ ህብረትና መፍትሄ ሊያመጣ በሚችል ትግል ላይ እንዲሆን ማድረግ ከመሪዎች የሚጠበቅ ነው። አሁን ያለው ትውልድ የሚከፍለው መስዋእትነት ለሚቀጥለው ትውልድ መሆኑ ባይካድም የዚህን ትውልድ የመኖር እድል ባልተቀናጀ አመራር ለአምባገነኖች አሳልፈን እንዳንሰጥ መጠንቀቅ አስፈላጊ ይመስለኛል። ከትላንቱ ዛሬስ ተምረናል ወይ ብለን መጠየቅ ይገባናል። በተለይ ከሩቅ ሆነን የምንሰጠው አመራር እንደኛው በተሻለ አለም ውስጥ ለመኖር እኛ ያገኘነውን የ እውቀትም ሆነ ሌሎች እድሎችን ያገኝ እንደነበር ግምት ውስጥ ማስገባት ከሃላፊነት ጋር የሚጣጣም የፖለቲካ ስራ ነው። ይህን ስል ያለ መስዋእትነት ድል ይገኛል የሚል ንዝህላል የሆነ አመለካከት ተጠናውቶኝ አይደለም። አምባገነኖችንና በጥቅም ያበዱ ሃይሎችን በወሬ ብቻ ማውረድ ይቻላል ማለትም አይደለም። ድክመታችን ግልጽ ነው። ትግላችን አቅጣጫና ግብ የሊለው ቢኖረውም መተማመንና መነጋገር አለመቻል መጠራጠርና እራሳችንን የህዝብ ወኪሎች አድርገን በህዝብ ስም የህዝብን አቅጣጫ ለመወሰን በመፈለጋችንም ጭምር ነው።
አንዳንድ ነገሮችን ሰፋ አድርጌ ለአንተ ለፖለቲካ ተንታኙ ለማስረዳት ፈልጌ አይደለም። ፖለቲካ በእውቀት የተደገፈ ሲሆን የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን አምናለሁ። ነገር ግን ህብረተሰብ ከጭቆና እንዲወጣ በሚደረገው ትግል ወሳኙ የህዝብን ህይወት መኖር፣ ብሶቱን መረዳት፣ ህመሙን መታመም ደስታውን አብሮ መካፈል ባህሉን እሴቱን መገንዘብ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። የተወለድኩትም ያደግኩትም በኦሮሞ ህብረተሰብ ውስጥ ነው። ቋንቋውን ባህሉን ጠንቅቄ አውቃለሁ። በኔ የመማርና የማወቅ እድሜ ቁቤ ስላልነበረ የሚገባኘን ያህል አላወቅኩም ግን እሞክራለሁ። በኦሮሞ ወገኖቼ ላይ ይደርስ የነበረውን ኢፍትሃዊ ተግባር ልጅ ሆኝ ፖለቲካ ሳላውቅ ውስጣዊ ስሜቴ ይጸየፈው ነበር። ዛሬ ያ የልጅነት መንፈሴ በፖለቲካ ታጅቦ እውነታውን እያጠፋብኝ ያለ ይመስለኛል። ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ወይም ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ መሆኑ የጭቆናው መሰረት አለመሆኑን እገነዘባለሁ። ኢትዮጵያዊነትና አንድነትን መስበክስ ጸረ ኦሮሞ ያደርገኛል ብዬም እራሴን እጠይቃለሁ። የኢትዮጵያዊነት መንፈስና አንድነትን ማሰብ ያለፉ ስር አቶችን መናፈቅ ወይም መልሶ ለማምጣት ማሰብ ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ አብሰለስላለሁ።
በዚህ ጉዳይ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ወይም አክቲቪስቶች የወያኔ ኢሃዴግን ፕሮፓጋንዳ መልሰው ሲያስተጋቡ ይገርመኛል። ለመሆኑ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የህዝቦች እኩልነትን የማያስተናግድ የወያኔንም ሆነ የአለፉ ስርአቶችን በፈቃዱ ወይም በፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መልሶ ሊያስተናግድ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራልን? ከእንግዲህ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በራሳቸው ቁዋንቁዋ እንዳይጠቀሙ እንዳይዳኙ መሪያቸውን እንዳይመርጡ ባህላቸውን እንዳያዳብሩ ሊያደርግ የሚችል ምድራዊ የፖለቲካ ስርአት ይመጣልን? ታሪክና የህብረተሰብ እድገት ወደኋላ አይመለስም። ወደፊት የሚሄድበትን ከማሳየት ይልቅ ወደኋላ ልትመለስ ነው እና እኛ እናድንሃለን የሚሉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እራሳቸውን ከህዝብ ሃይል አግዝፈው ፈጣሪነታቸውን ለማሳየት ለምንድነው የሚሞክሩት? ምናልባት የዚህ አይነቱ በኋላ ታሪክ ወደፊቱን በስጋት ማሳየትና ማስፈራራት ወይም የነበረን እውነታ መቀበል አለመቻል ነው ህዝብም እንደህዝብ ሃገርም እንደሃገር እንዳይኖሩ ስጋት የሚፈጥረው።
ወንድሜ ጀዋር
በአሁኑ ወቅት በኦሮሞ ምሁራን በየአካባቢው የተጀመረው ውይይት ሊበረታታ እንደሚገባ አምናለሁ። በቅርቡም በአትላንታ ሰፊ ዝግጀት እንዳለ እይተነገረ ነው። በወንድማዊና አባታዊ ምክር አንተንና አንተን ለመሰሉ አክቲቪስቶች በመስጠት ላጠቃልል። ኢትዮጵያዊነት የኦሮሞነት ጸር አይደለም። ኦሮሞነትም የኢትዮጵያዊነት እንዳልሆነ ሁሉ። አንድነት ምንጊዜም በጎ ጎን ያለው ቃል ነው። የኦሮሞ ልጆችን ወደአንድነት ለማምጣት እየጣራችሁ ያላችሁት አንድነት በጎ ነገር ስለሆነ ነው። ወደአንድነት መምጣት የጋራ ችግራችንን ይፈታል ብለን ስለምናስብ ነው። ኦሮሞ ሁሉ በአንድ አይነት አስተሳሰብ የተጠመቀ አይደለም። እኔና መሰሎቼ ስለአንድነት ስናስብ በማንኛውም ህዝብ ላይ በደል ሊፈጽም የሚችል ሃይል ለመፍጠር አይደለም። ተባብረን እንድናድግ ነው። ተመካክረን ተፈቃቅረን የህዝብን ጥቅም ያስቀደመ ሃገር ለመመስረት ነው።
ከኦሮሞ አክቲቪስቶችም ሆነ ከኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ የምንጠብቀውም የጽንፍ አመለካከት ለማንኛውም ህብረተሰብ አጥፊ መሆኑን ተገንዝበን የእልህና የኔ ብቻ አስተሳሰብ የበላይ መሆን አለበት ከሚል አመለካከት መውጣት የሚያስችል የጠራ አስተሳሰብ እንዲወጣ ነው። ህዝብን ተክቶ በህዝብ ስም ውስኔ የሚሰጥ አስተሳሰብ አደገኛ ነው። ለኦሮሞ አንድነት የሚያስበው የኦሮሞ አክቲቪስት አንድነትን ለራሱ እንደሚያስበው ሁሉ ከሌላውም ጋር ሊኖረው የሚገባውን አንድነት ከፖለቲካ ታክቲክ በዘለለ እንዲያየው ነው። በዚህ ረገድ በርካታ የኦሮሞ ልጆች እያበቡ በመሆናቸው ደስ የሚለውን ያህል በየፓልቶኩ በፌስቡኩ በሌሎችም መገናኛዎች ያለምንም ገደብ ህዝብን ለማራርቅ ከሚሞክሩ ሃላፊነት የጎደላቸው ግለስቦች ወይም ቡድኖች ወጣ ብለው ለሰው ፍቅር የሌለው ነጻነትን ክሚሰብኩ ተለይተው እንዲወጡ ነው፡፡
በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እየታገለ ያለው ፍጹም አምባገነን ከሆነው የህወሃት ኢሃዴግ ስርአት ጋር ነው። ስርአቱ ሁሉንም በልቶአል። ሁሉን አስለቅሶአል። በየጊዜውም የተቃዋሚውን ደካማ ጎን ቦርቡሮ በመግባትና ስስ ብልቶቹን በማጥቃት እነሆ እድሜውን እያራዘመ ይገኛል። ከሁሉም እጅግ የሚያሳዝነው በየጊዜው ንጹሃን ዜጎች ህጻናት አሮጊቶች ወጣቶች ደም መገበር ለተቃዋሚው እንደ ባህል እየሆነ መጥቶአል። አንድ ሳምንት በጅምላ የሚሞቱ ወገኖቻችንን በሚዲያ ለቅሶ ስናለቅስላቸው ቆይተናል። ይህ ሁኔታ ሊያቆም የሚችለው የህዝብን ሰቆቃ ያስቀደመ የትግል አካሄድና የወደፊቱን የህዝባችንን አንድነት የሚያጎለብት ራእይ ነጥሮ ሲወጣ ነው። በፖለቲካ ዋስትና የሚባል ነገር የለም። ያለው አንድ ነገር ብቻ ነው። የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድም የፖለቲካ መፍትሔ ማምጣት። አንተን የመሰሉ ወጣት ኢትዮጵያውያን በታሪክ የሚኖራችሁ ተጠያቂነትም ሆነ ተቀባይነት በዘመናችሁ በምትሰሩት አፍራሽ ወይም ገንቢ ፖለቲካ ነው። አፍራሾች ምንጊዜም በታሪክ ሲወገዙ እንጂ ሲወደሱ አናውቅም። ለማፍረስም ብዙ እውቀት አይጠይቅም። በሆያ ሆየ ማፍረስ ይቻላል። መገንባት ግን ትልቅ ድካም አለው። ቅንነትን ትእግስትን አርቆ አሳቢነትን የዘመኑን ችግር ለመፍታት የሚያስችል እውቀትን መላበስ ያስፈልጋል። ጀዋርንና ሌሎች ወጣቶችን በዚህ ጎራ እንደምናያቸው ተስፋ አደርጋለሁ።
አቦ ገለቶሚ
ሽመልስ ወርቅነህ (Gishay)
Email: shimelisw@yahoo.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Mr. Jawhar is smart and ambitious young person. Anyone who strictly following him very well understand what he is doing and up to. It seems that he has his own personal agendas. Being controversial and naive is his manipulating strategy. He perverted history and manufacture historical incidents. Such individuals pick a grain of truth and magnify it as the whole truth that can stir emotion. He plays the emotional game upon honest and innocent youngsters. It the smartest skill to know what other individuals want to hear. Such individuals do not care what the consequence and outcome would be as long as they satisfy and boost their immediate nagging ego.
Such individuals have subtle manipulative skills and appeal. The average minds can not readily see and understand their true self. However dishonest, they look passionate and compassionate to cause of a certain group. If they stood up for the cause of the larger society — to humanity, they know their personal motive would be diminished and become like everybody else. Such individual love to be free like everybody else but equality is not in their agenda. They want to be seen unique and above everybody else even among equals. Such manipulative skill, however unique is short lived.
Instead of being a one time hero, it is wise to tame ones demeanour and become a national figure — all timer.