
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተቻችለው ለሀገራቸው ሰላምና አንድነት የበኩላቸውን እንዲወጡ የአዲስቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተርና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ ጠየቁ።
አቶ ኦባንግ ሜቶ በሀገራዊ አንድነት ፣ ሰላምና መቻቻል ዙሪያ ትላንት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
“በሀገራችን በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋለ ያለው ግጭት ባለፉት 27 ዓመታት ለኢትዮጵያዊ አንድነት ትኩረት አለመስጠታችን ነው፣ ይህ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የነገይቱ ባለራዕዮችን እየተፈታተነ ይገኛል” ሲሉ ገልጸዋል።
ወደዚህች ምድር ብሔርን ምርጫ አድርጎ የመጣ ማንም እንደሌላ የተናገሩት አቶ ኦባንግ ሰው ማየት የሚገባው ሰው መሆኑ እንጂ በዘርና በብሔር መሆን እንደማገባም አመልክተዋል።
በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንጂ የዘር የበላይነት ሊኖር እንደማይገባ ጠቁመው ኢትዮጵያ እንድትለወጥ እያንዳንዱ ዜጋ ከብሔር አመለካከት ነፃ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
“በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች የኢትዮጵያ እንጂ ተዋጽኦ አይደሉም፣ ደግሞ አንዳችን ያለአንዳችን መኖር አንችልም ስለዚህ ተማሪዎች የጥላቻ ሳይሆን የአንድነት ነፀብራቅ ልሆኑ ያገባቸዋል” ብለዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ ግጭቶች ቢኖሩም የዴሞክራሲ መሠረት እየተጣለ መሆኑን የገለጹት አቶ ኦባንግ የተፈጠረው በነፃነት የመናገር ዕድል በመጠቀም ለሀገሪቱ አንድነት፣ ለሰላምና መቻቻል ሞጋቾች እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ባለቤት እንደመሆኗ ባለፉት ጊዜያት በአንድነት ሳይሆን በልዩነት ላይ ትኩረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
“ቀደምት አባቶቻችን በአንድነት ወግ ያደጉ በመሆናቸው የተለያዩ የሀገራችን ፈተናዎችን በድል ተወጥተው ለእኛ አስረክበዋል” ብለዋል።
ወደ ቀድሞ የአንድነት ታሪክ ለመመለስ የመሪነት ሚና መጫወት ያለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ መሆናችንን መዘንጋት እንደሌለባቸውም አመልክተዋል።
“ብሔራዊ መግባባትና አንድነት ላይ ባለመሠራቱ በክልል የታጠሩ ነፃ አዉጪ የፖለቲካ ድርጅቶች እየተፈጠሩ እንጂ ብሔራዊ አመለካከት ያላቸው ጥቂቶች ናቸው” ያለው ደግሞ በዩኒቨርስቲው የፕሮዳክሽን ምህንድስና የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ግሩም አጅሬ ነው።
ተማሪ ግሩም እንዳለው የዘር ፖለቲካ ባመጣው ጠባብ አመለካከት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተቻችሎ ለመኖር እየከበዳቸው ይገኛል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላምና መቻቻል አቶ ኦባንግ ገለፃ መስጠታቸው ራሱን እንዲያገኝ ያስቻለው መሆኑን ተናግሯል።
የኤሌክትሮኒክስ ምህንድስና የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሪሐና ኑሩ በበኩሏ “ሀገራችን በዘርና በብሔር በሽታ የታመመችው ከእኛ የተነሳ ነው” ብላለች።
ሆኖም አቶ ኦባንግ በአንድነትና ሰላም ዙሪያ ያደረጉት ገለጻ በካምፓስ ህይወታችን አንድነት በመፍጠር ተባብረው ለመኖር እንደሚያግዝ ተናግራለች።
ምንጭ፦ ኢዜአ
I am what I have said justice ,justice ,justice before everything , everything with out justice is nothing !!!!