እውኑን ቀርቶ ምስሉንም እንኳን አይቸው የማላውቀው[1] በዓሉ ግርማን አውቀዋለሁ። ህይወትን እና ሰውን የሚወደውን፣ ውብ ሰብዕና ያለውን በዓሉ ግርማን አውቀዋለሁ። በዓሉን፣ ሰብዓዊ እና ሞራላዊ ማንነቱን በጽሁፎቹ ውስጥ አይቻለሁ። በዓሉን አውቀዋለሁ።
እናት አባት አያት፣ ቅማያት እና ቅንዝላቶቼ ሁሉ መጣፍ ቅዱስ ዳዊቱን፣ ቁራን ኪታቡን በነጋ በመሸ ቁጥር እየደገሙ እና እያነበቡ የኖሩትን ያህል፣ እኔ ደግሞ በዓሉን አንብቤያለሁ። በተለይ ኦሮማይን፣ ቢያንስ ከእጄ ከገባበት (ከ1978 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ) ምናልባትም ከሶስት እና አራት ጊዜ በላይ ደጋግሜ ሙሉውን ያነበብኩትን ያህል፣ ለአምስት ወይም ስድስት አመት አካባቢ ደግሞ፣ ጧት ጧት ከእንቅልፌ ነቅቼ ከምኝታዬ በተነሳሁ እና ቤት ውስጥ በገባሁ በወጣሁ ቁጥር እንደሥሥት ልጅ ደጋግሜ እያነሳሁ በየቀኑ፣ ከጄ የገባውን አንድ ሁለት ገጽ ወይም አንቀጽ ሳላነብ የዋልኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የኦሮማይን አንዱን አረፍተ ነገር መዝዘህ ብታነብልኝ፣ ገጹን እና ምዕራፉን መናገር እችል ነበር። በዓሉን በጣም አንብቤዋለሁ።
ከሁሉም የሰነ-ጽሁፍ አላባዎች አንጻር ሲታይ፣ የበዓሉ ግርማ ስራዎች ገና ያልተነካ ድንግል መሬት ማለት ናቸው። እኔ በሽንኩርት ነው የምመስለው። ዛሬ ያነበብኩትን አንዱን አንቀጽ እንደ ነገ ሳነበው የማገኘው ከሌላ የስነ-ጽሁፍ ጥበብ፣ ውበት እና ለዛ ጋር ነው። መጽሃፍቶቹ የያዙት ጥሪት (ረሶርስ)፣ በተለይ በአጻጻፍ ቴክኒክ፣ ቋንቋ እና በባህል አብዬት አኳያ፣ ተዝቆ የሚያልቅ አይደለም። የበዓሉን የህይወት ፍልስፍና እና “ሌጋሲ”፣ ያቅሜን ያህል፣ ትንሽ ለማጉላት እና ለማውጣት እታደል ይሆን?
ደራሲ የሚጽፈው፣ የፈጠራ ድርሰት ቢሆንም እንኳን፣ ስለሚያውቀው ጉዳይ እና የራሱን እይታ በገጸ-ባህሪያቱ አማካይነት እየነገረ ነው። የበዓሉ ሰብዕና እና ማንነት ጽሁፎቹ ውስጥ ይገለጻሉ። ኦሮማይን አንዳንድ ጊዜ እንዲሁ አንዳንድ አንቀጾቹን ባነበብኩ እና የበዓሉን ሰብዕና ባሰብኩ ቁጥር አይኔ እንባ ያቀርር ነበር። አሁንም ይህን ጽሁፍ ስጽፍ የተሰማኝ ያው ነው። ግን አይኔ እንባ ያቀረረው ለበዓሉ አይመስለኝም። ይልቁንም በበዓሉ ምናባዊ ምስል ውስጥ ለሚታየኝ–ለራሴ፣ ለእኛ (ህዝብ)–ማንነት ነበር የማለቅሰው።
እንደ በዓሉ ያሉ ውብ ሰብዕና ያላቸውን ሰዎች በሰው ጅቦች እያስበላን ዝም የምንል ሰዎች እየበዛን በሄድን ቁጥር፣ እኛም ራሳችን ወደዚያው የሰው ጅብነት እየተቀየርን የምንሄደው “ሰዎች” ቁጥር እየበዛን መሄዳችንን አለማወቃችንን ነው። አንድ ማህበረሰብ፣ አንድ አባሉ ወይም አባላቱ ላይ የደረሰ በደል እና ግፍ ካልቆረቆረው፣ እናም ፍትህ እንዲሆን ካልሰራ ወይም ካልጣረ፣ በተለይም ሊሾሙ እና ሊሸለሙ የሚገባቸው ዜጎች በእስር ሲጋዙ፣ እልፍም ሲል ሲገደሉ እያየ ዝምታ ባበዛ ቁጥር፣ ያኔ ማህበረሰባዊ ሞራሊቲ ሞተ ማለት ነው። ያ ማህበረሰብ ራሱ ፍትህ እንዳጣ ይኖራል፤ አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።
ታሪኩ አባዳማ እንዳሉት ሳይሆን፣ በዓሉ ሞት እንደሚጠብቀው እያወቀ ኦሮማይን የጻፈ አይመስለኝም። በዓሉ ህይወትን እና ሰውን ይወዳል። ውብ ሰብዕና ያለው ሰው የውብ ሰብዕናው መገለጫ የሆነውን እውነትን፣ ፍትህን፣ ሰላምን ይሰራል። ውብ ሰብዕና ያለው ደራሲ እና ጋዜጠኛም እውነትን እና ሰብዓዊነትን ያነግሳል። በቅርብ የሚያውቀው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር “… በአሉ እንደሚሞት እያወቀ ኦሮማይን ጻፈ ለማለት ይከብደኛል…” አይነት አስተያየት እንደሰጠ ትዝ ይለኛል። በዓሉ ‘… እውነትን እና ሃቅን መናገር እንዲህ ለሞት ይዳርጋል? ወይስ አይዳርግም?’ ብሎ የሚያስብም አይመስለኝም። እሱ የጻፈው እውነት ነው። ውብ ሰብዕና ያለው ሰው የሚሰራው ማንኛውም ስራ ያስገድላል ወይስ አያስገድልም ብሎ ለመስጋት ቀርቶ ለማሰብም ጊዜ የለውም። ሞት ያስከትልብኛል ወይስ አያስከትልብኝም ብሎ ከማሰቡ በፊት እውነትን ይናገራል። ይጽፋል። በዓሉም ያደረገው ይኸንኑ ይመስለኛል።
በሰለጠነው አለም፣ ወንጀለኛነቱ ከተረጋገጠ አስከሬንም ይቀጣል። የድርጅት (ተቋም) አስከሬን ሲቀጣ ግን አይቼም ሰምቼም አላውቅ። የሰዎች ስብስብ መጠሪያ የሆነው ተቋም (ደርግ) ዛሬ የለም። አይናገር አይጋገር… ሞቶ ተቀብሯል። አሁን ለፍርድ የሚቀርብም ሆነ በህግ የሚቀጣ ደርግ የለም። መንግስቱ ሃ/ማርያም ደሞ ቃታ ስቦ በዓሉን ገደለ ቢባልም ለማመን ያስቸግረኛል። መንግስቱ ገና ደርግ ሲመሰረት አካባቢ በስሩ ያሰለፋቸውን የአንጃውን ደጋፊዎች እያዘዘ፣ አጠገቡ የነበሩትን ሁሉ እንዳስወገደው አይነት፣ በዓሉንም አንዱን “አስር አለቃውን” ብቻ ነግሮ አሰገደለው ብሎ ለማሰብም ይከብደኛል። በዓሉ ከጎኑ፣ ከበታቹም ሆነ ከበላዩ ካሉ ሰዎች ውስጥ አንድም ሰው ባላወቀው ሁኔታ ተገደለ ቢባልም ለማመን ይከብደኛል። አበራ እንዳለው አጠገቡ የነበሩ ሰዎች፣ እሱ ሲሞት ሹመት እና ሽልማት እናገኛለን ብለው አስበው አስገደሉት ለማለትም አልደፍርም። ምናልባትም ህይወቱን ሊያሳጣ እንከሚችል ደረጃ ይደርሳል ብለው ባልጠበቁት መልኩ አሲረውበት ሊሆን ግን ይችላል። ያደግንበትን ማህበረሰብ እናውቀዋለን። አሁንስ እየሆነ ያለው ምንድን ነው?
መንግስቱ ሃ/ማርያም ስለ በዓሉ አሟሟት አለማወቁ “ማፈሪያ ነው” ብዬ የማልፈው አይደለም። በሚ/ር ማዕረግ አጠገቡ ያለ ሰው እንዴት እንደተሰወረ ያላወቀ መሪ፣ 70/80 ሚልዬን ህዝብ እንዴት እንደኖረ ምንም ባያውቅ እና አሁን ለገባንበት አዘቅት ቢያበቃን አይገርመኝም ብዬ የማልፈውም አይደለም። ምክንያቱም መንግስቱ ስለ በዓሉ አሟሟት አያውቅም ቢባል ጨርሶ አይገባኝም። የመንግስቱ ሃ/ማሪያም ሃሳብ (ትዕዛዝ?) ሳይኖርበት በሚ/ር ደረጃ ማዕረግ የነበረውን በዓሉን፣ አንድ ተራ የደህንነት ሰው ቀርቶ፣ የደህንነቱ ሹም ተስፋዬ ወ/ስላሴ ራሱ ብቻውን ወስኖ አስገደለው ቢባል እንኳን አይገባኝም።
እንኳንስ መንግስቱ ሃ/ማርያም፣ ያሁኑም መንግስት አንድም ስለበአሉ አሟሟት ላለማወቅ እና ላለማየት አውቆ አይኑን ጨፍኗል፣ አለያም እያወቀ ላለመናገር አፉን የዘጋ ይመስለኛል። ማን ይሙት አሁን ያገሪቱን ቁንጮ የደህንነት ስው (ተስፋዬ ወ/ስላሴን) ጨምሮ፣ አንድ አገር ሙሉ የደህንነት እና የደርግ ሹሞችን እንዳለ በእጁ ይዞ የኖረው ያሁኑ መንግስት ስለ በዓሉ አሟሟት እና ገዳይ አስገዳዮች አጣርቶ ማወቅ እና አደባባይ ማውጣት ተሳነው? ወይስ ይኸም መንግስት የሚፈራው ጉዳይ አለው?
የታሪኩ አባ ዳማ፦ “… በደርግ ዘመን በጸረ-አብዮተኛነት ከተጠረጠረ ሰው ጋር ቡና መጠጣት ያቆሙ የቅርብ ጓደኞች እጅግ ብዙ ናቸው።…”፣ “… በዓሉ በደህንነት ታፍኖ ሲወሰድ አስፋው ዳምጤ አይቶ ነበር ብንል እንኳ- የተፈጸመውን ስውር አፈና ለሌላ ቢናገር ተመሳሳይ ዕጣ ሊደርስበት እንደሚችል በመፍራት ቤቱ ገብቶ ዝም ቢል የሚፈረድበት አይሆንም። በደርግ ዘመን ለነፍስህ ብትፈራ ይፈረድብሃል? ለማንስ ምን ይነገራል? … አስፋው ዳምጤ ጣጣ ውስጥ ሊገባ ነው። …”፣ “… ይሁን እና ምሽቱን ባየው ነገር (አስፋው ዳምጤ) ደንግጧል። ለራሱ ፈርቷል። ይህስ ሆኖ ቢሆን ይፈረድበታል? …” የሚሉት ጽሁፎቹ፣ ደንበኛ የኛ (የሃበሻ) ማንነት (የማህበረሰባዊ ሞራል ቀውስ) መገለጫዎቻችን ናቸው።
አስፋው ዳምጤ (እኔም “… አይቶ ነበር ብንል እንኳ…” እያልኩ እንደሆነ ይያዝልኝ) በደርግ ጊዜስ ይፍራ። ይሁን። ዛሬስ? የደርግ ሙት መንፈስ እያስፈራራው ነው? ወይስ መንግስቱ ሃ/ማሪያም ሃራሬ ላይ ሆኖ አይኑን አጉረጠረጠበት? በዓሉ ጋር ስላሳለፈው ምሽት አስፋው ባደባባይ የጻፈው ወይም የተናገረው አለ? እንካሁን ከሌለ ለምን አሁን አያደርገውም?
በአንድ ግለ-ሰብ ላይ የተሰራ ህገ-ወጥ ስራ ሌላው በራሱ ላይ እንደደረሰ ቆጥሮ (አብዛኛው ሰው) ለፍትህ በሚቆምበት፣ በዚህ በምዕራቡ አለም ለመሆኑ ታሪኩ አባዳማ ምን ያህል ጊዜ ኖረዋል? የትስ ነው የሚኖሩት?
እኔ አስፋውም ሆነ ሙሉጌታ በበዓሉ ሞት እጃቸው አለበት እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። በልጅነቴ በኖርኩበት መንደር ውስጥ የነበሩ አንዲት ሴትዮ፣ እንደ አብዛኛው ጎረቤቶቻችን ይሉኝታ የሚያጠቃቸው አልነበሩም። ልጆች ሆነን ሰፈር ውስጥ ስናጠፋ፣ ይሉኝታ ሳይፈሩ ለየቤተሰቦቻችን ስሞታ ይናገሩ ነበር። ከመሰላቸውም በቁንጥጫ ያበግኑን ነበር። አንዳንዱ ወላጅ ታዲያ፣ “ልጄ ለምን ስሙ ተነሳ…?” አይነት ሴትዮዋን ይጠምዷቸዋል ወይም የምር ጠብ ይገቡና መልሰው ሴትዮዋን አምርረው ሲወነጅሏቸው “አሁንስ ኩት አትበሉኝ የሹም ዶሮ ሆንሽብኝ” ይሉ ነበር። (“ኩት” ዶሮ ስጥ እንዳትበላ ወይም እንዳትበትን የማባረሪያ አጠራር ነው።) አበራ ከራሱ የስራ ልምድ እና ከሚያውቀው፣ እንዲሁም ባደባባይ ታትሞ ከተሰራጨ መጽሃፍ ላይ ምንጭ እያጣቀሰ የራሱን ግንዛቤ አክሎበት ጽፏል። አስፋው እና ሙሉጌታ ለምን በበዓሉ ጉዳይ ስማቸው ተነሳ በሚያስብል ደረጃ ይህን ያህል በአበራ ላይ ውርጅብኝ እና ስድብ ማውረድ ተገቢ አይመስለኝም።
በተለይም ይህን ጽሁፍ እየጻፍኩ ባለሁበት ሰአት የወጣው የተስፋዬ ተሰማ ጽሁፍ ከርዕሱ ጀምሮ “በዓሉ ግርማን ለመግደል ሴራ ያስፈልግ ነበር ወይ?” የሚለው ራሱ ችግር አለበት። ሴራ ማለት ሁለት እና ከዚያ በላይ ሰዎች ተሰብስበው፣ “እንዴት እናድርገው …” ብለው መክረው ዘክረው የሚያደርጉት ነው። በዓሉ እንዲሁ፣ የወቅቱ የደህንነት ቢሮ ሳያውቀው፣ ሴራ ሳይጠነሰስበት ተሰወረ ቢባል ጨርሶ የማይመስል ጉዳይ ነው። በዓሉ በአንድ ተራ ሰካራም እንደተገደለ አድርጎ ለማሳየት የመሞከር ያህል ነው።
አበራ ከአሁኑ መንግስት ጋር ስለመስራቱ እዚህ ከበዓሉ ጉዳይ ውስጥ መሰንቀሩም አግባብ አይመስለኝም። በሌላ ራሱን በቻለ ጉዳይ አንስቶ መከራከር ነው:: የሌላውን ሰው መጥፎ ምግባር (አንዳንዴ የፈጠራም ሊሆን ይችላል) አጉልቶ በማሳየት፣ የራስን ጥሩ ሰውነት ለማሳየት መሞከር (ምንም ጥሩ ስራ ሳይሰሩ) አንዱና መጥፎ “ባህላችን?” ነው።
ቢያንስ የአበራን ብቻ ሳይሆን፣ የበዓሉን ቤተሰቦች ስሜት ላለመጉዳት መጠንቀቅ የነበረብን ይመስለኛል። “… እንኳን እሱን (አስፋውን) ባለቤቱንም…” በሚል፣ አንቀጽ 28 ላይ ተስፋዬ ተሰማ ያነሱት ጉዳይ፣ አንድም ገና “ይኸ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ … ባይሆን ኖሮ…” የሚሉ ምናባዊ ጉዳዮችን እያነሱ፣ የሰውን ስሜት መጉዳት፣ ሰው እንዳይናገር እና እንዳይተነፍስ ማሸማቀቅ በጣም የወረደ ስራ ነው።
በተለይ በበዓሉ ጉዳይ ላይ ማንኛውም ጸሃፊ በብዕር ስም ተሸሽጎ መጻፍ ያለበት አይመስለኝም። የቤተሰብ ወዳጅ ዘመዶቹን ስሜት ላለመጉዳት መጠንቀቅ ያለብን ይመስለኛል፣ እያንዳንዱ ጸሃፊ ማንነቱን ባደባባይ ማውጣት ያለበትም ይመስለኛል።
በበአሉ መሰወር እጃቸው ያለበት ሰዎችን ለፍትህ የማቅረብ ስራ የቅርብ ቤተሰቦቹ ብቻ አይደለም። በዓሉ የኢትዮጵያ፣ እልፍ ሲልም የዓለም ማህበረሰብ፣ ሃብት እና ቅርስ ነው። ስለዚህ የበዓሉን አሟሟት የሚያጣራ አንድ ኢንተርናሽናል ኮሚቴ (ኢንቬስቲጌቲቨ ኮሚቴ) ቢቋቋም መልካም ይመስለኛል።
የቪኦኤዋ ጋዜጠኛ (አዳነች ፍስሃዬ?) ካንድ ሁለት አመት በፊት አካባቢ ስለ በዓሉ አሟሟት የተናገረችውን የሰማልኝ ሰው አለ? ወይስ ጆሮየን መጠራጠር አለብኝ? ምነው እነ ታሪኩ አባዳማ እና ተስፋዬ ተሰማ ስለ በዓሉ አሟሟት ካሁን ቀደም ባደባባይ ስለተጻፈው (በበዓሉ ሞት እጁ አለበት የተባለ አንድ አሁንም በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ እያገለገለ ያለ ሰው እንዳለ ባደባባይ ተጽፏል) እና በሬዲዮ ስለተባለው ነገር አንድም ሳይገልጹ ፍርድ ቤት ሊቀርብ በማይችለው ደርግ ላይ እንዲህ በረቱ?
ታሪኩ አባዳማ፦ “… አበራ ሆይ! ታላቁን ሰው በዓሉን የበላው ደርግ ነው…”።
እኔ፦ “ታሪኩ አባዳማ ሆይ! “ደርግ” ተቋማዊ ስም ነው። ቃታ የሚስብበት ጣት የለውም። በዓሉን የበላው (የበሉት) ጅብ (ቦች) በጥርሳቸውም ይሁን በጥፍራቸው እንደኔና እንዳንተ፣ እንደ ሙሉጌታ ሉሌ እና አስፋው ዳምጤ … ጥርስ እና ጥፍር ያላቸው ሰዎች ናቸው። ደርግ አይናገር አይጋገር፣ ስም ነው። ደርግ ለሰራው ጥፋት ሲታሰር እና ሲቀጣ አላየንም። የታሰረው በደርግ ውስጥ የነበረው (ለምሳሌ የቀድሞው ጠ/ሚ ፍቅረ-ስላሴ ወ/ደረስ….) ሰው ነው። በዓሉንም ተናግረውም ሆነ አናግረው፣ ጎትተው ወስደውም ሆነ አስወስደው ያስገደሉት እንደኔና እንዳንተ የሚናገሩ ሰዎች ናቸው። “በዓሉን ደርግ በላው” ብሎ አድበስብሶ ማለፍ ፍትህ እንዳይሰፍን መስራት ነው።
በዓሉ ግርማ በህይወት ካሉትም ሁሉ በላይ ግዙፍ ነው! ደራሲ እና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ገና ገና ይኖራል!
(segel143@gmail.com)
Hiwot says
Well done Golgul as usual!… Mezgebe’s article is very impressive and well articulated on exposing the evil role of Tariku Abadama and Yussuf Yassin aka Tesfaye Tessema.
Hiwot
aradaw says
he will live forever in the memories and mind of all Ethiopian current and future generations. Great writer and great books live forever.