የዋቄፈታ እምነት ተከታዮች በማህበር ተደራጅተው እውቅና ጠየቁ!
ባለአወልያዎችም ተደራጅተዋል
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የዋቄፈታ እምነት ተከታዮች በማህበር ተደራጅተው ህጋዊ ፈቃድና የህጋዊነት ማረጋገጫ የምሰክር ወረቀት የጠየቁት “ይበራል ይከንፋል፣ አይሞትም ያርጋል” እየተባለ ሲመለክ የነበረው ታምራት ገለታ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ ነበር። የእምነቱ መሪዎች በ2002 ዓ ም ወልመራ ከተማ ቆቦ በምትባል ቀበሌ መስራች ስብሰባ አካሂደው እንደነበረ ያስታውሳሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት የወልመራ ወረዳ ከተማ በሆነችው ሆለታ የተደራጁት የዋቄፈታ ስርዓተ አምልኮ ተከታዮች የህጋዊነት ጥያቄ ያቀረቡት ለኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መሆኑን የሚጠቅሱት እነዚህ የእምነቱ ተከታዮች ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ እንደገለጹለት ከሆነ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል።
መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚለውና በህገመንግስቱ በግልጽ እንደተቀመጠው በኢትዮጵያ የእምነት ነጻነት የተከበረና ህጋዊ ከለላ ያለው መሆኑንን የሚናጉት ክፍሎች ቅሬታ አላቸው። ቅሬታቸውም ፈቃዱን እንዲሰጣቸው የጠየቁት ክፍል መደራጀታቸውን ተቀብሎ ህጋዊ የምስክር ወረቀት ስላልሰጣቸው ነው።
በኦሮሚያ የዋቄፈታ እምነት ተከታዮች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንን ቅሬታ አለን የሚሉት ክፍሎች ይናገራሉ። እምነቱ ፍቅርን፣ መታዘዝንና መከባበርን የሚያስተምር ከባህል ጋር የተዋሃደ በመሆኑ፣ መንግስት ለማህበራቸው አስቸኳይ እውቅና ሲሰጥ እንደ ማንኛውም እምነት ህጋዊ የምስክር ወረቀት ለመስጠት መዘግየቱ እምነቱን በውጪው ዓለም ለመስተማርና በክልሉ ውስጥም በዓለም ዙሪያ ትምህርቱን ለማስፋፋት መጠነኛ ችግር እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ዜና ባለ ኣወልያዋች ስድስት ኪሎ አካባቢ ማየት የተሳናቸው ማዕከል አካባቢ በሚገኘው አስተባባሪያቸው አማካይነት ተሰባስበው በመደራጀት ማህበር መመስረታቸው ተሰምቷል። ማህበሩን ለመሰረቱት ባለውቃቢዎች ቤተሰቦች ቅርብ የሆኑ እንደሚናገሩት መደራጀቱ የተፈለገው “አባባ ታምራት” የደረሰበት አይነት ችግር ቢያጋጥም ለመከራከርና የባለውቃቢዎቹ ተከታዮች በድብቅ የሚያካሂዱትን ስርዓት በግልጽ ለማካሄድ ይችሉ ዘንድ የግንዛቤ አድማስ ለማስፋት ታስቦ ነው።
ታዋቂ ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ነጋዴዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮች፣ ታዋቂ ስፖርተኞች የሃይማኖት ድርጅት መሪዎች ሳይቀሩ ባለ ውቃቢ በሰፈረባቸው ሰዎች መኖሪያ ቤት በድብቅ እንደሚሄዱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነገር የቆየ እውነት ነው።ታምራት ገለታ ሲታሰር ይፋ እንደተደረገው ባለስልጣናትና ሚስቶቻቸው፣ ዘፋኞች፣ሯጮችን ጨምሮ ጥረው ግረው የሰበሰቡትን በማስረከብ የበለጠ ለመፈለግ የባለ ውቃቢ ጀበና አጣቢና ካዳሚ ሆነው የቀሩ ምንተ እፍረታቸውን አደባባይ በመውጣት ራሳቸውን ምስክር አድርገው ነበር፡፡
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ድንጋጤ የገቡ ባለውቃቢዎችና የሚመለኩ ባለ ኣውልያዎች በተጠቀሰው መልኩ በመደራጀት መንግስት ህጋዊ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን የጎልጉል ዘጋቢ ለማረጋገጥ ችሏል። ፌደራል ፖሊስ እንዲታገሱ የመከራቸው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግን በየክልሉ ያሉት “ልማታዊ ሆነው” ባላቸው ተቀባይነት ህዝቡን ከረብሻና ከአመጽ በመመለስ መንግስትን አክብሮ እንዲኖር በማስተማር እንዲሰሩ በቅርብ ካድሬዎች መተማመኛ እንዲሰጣቸው በመደረጉ ቸል ብለውት የነበረውን የማህበር ምስረታ አሁን አጠንክረው እንደገፉበት ለመረዳት ተችሏል።
በደራ ወረዳ ክብረ ነክ ወንጀል ተፈጸመ
ኢህአዴግ የሚመራት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ሆና በተመረጠች ሳምንት እጅግ ዘግናኝ የተባለ ወንጀል መፈጸሙ ተሰማ። ወንጀሉን የፈጸሙት እስካሁን የቅጣት ፍርድ አልተበየነባቸውም። መንግስትም ዝምታን መርጧል፡፡
ህዳር 5 ቀን 2005 ዓ/ም በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በገብሮ ቀበሌ የወረዳው የአስተዳደርና ፍትህ ሀላፊ የቅርብ ዘመድ የሆነ አቶ አየለ የተባለ ከሌሎች ሁለት ግብረ አበር ፖሊሶች ጋር በመሆን በቀበሌው የሚኖርን አንድን ግለሰብ መሳሪያ ደብቀሀል በሚል ሰበብ ግለሰቡንና ባለቤታቸውን ልብሳቸውን በማስወለቅ እርቃናቸውን እንዲታሰሩ መደረጋቸውን የዘገበው ኢሳት ነው።
የሚሊሺያ ዘርፍ ሀላፊውና ፖሊሶች በመቀጠልም ባልየው ብልቱ በገመድ እንዲታሰር ካስደረጉ በኋላ ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ እርቃኗን የሆነቸው ባለቤቱ ብልቱን በገመድ እንድትስብ እንዲሁም ብልቱን እንድትስም አስደርገዋል። ነብሰ ጡር የነበረችው ባለቤትየው በእርግጫ በመመታትዋም የስድስት ወር ልጅ አስወርዳለች። ይህ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም አልሳቃችሁም የተባሉትም መደብደባቸውን ኢሳት በስፍራው የነበሩ ምስክሮችንና የቀበሌውን ሊቀመንበር በማነጋገር አጋልጧል።
ይህ አስነዋሪ ወንጀል በተለያዩ ደረጃዎች የቁጣ ስሜት የቀሰቀሰ ሲሆን፣ ኢሳት ያናገራቸው የአስተዳደር አካል ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ይቀርባል ከማለታቸው ውጪ መንግስት ስለ ጉዳዩ እስካሁን በይፋ ያስታወቀው ነገር የለም።
እስክንድር ነጋ አልከራከርም አለ
አቶ አንዱዓለም አራጌም ፍርድ ቤት ቀርበዋል
በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሶ በ18 ዓመታት ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ውሳኔ ያሳረፈበት ፍርደኛው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ዓቃቤ ሕግ እንዲወረስ ስለጠየቀበት የንብረት ጉዳይ ቤተሰቡም ሆነ እሱ መከራከር እንደማይፈልጉ ለፍርድ ቤቱ አስታወቀ፡፡ በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሽብርተኝነት አዋጁ በተቀመጠው አንቀጽ መሠረት፣ “በሽብር ወንጀል የተቀጣ ግለሰብ ንብረት መወረስ እንዳለበት ያዛል” በሚል ለፍርድ ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ንብረታቸው እንዲወረስ ከተጠየቀባቸው ፍርደኞች መካከል በዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ የተወሰነበት አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ትናንትና ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው የነበሩት የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌና ባለቤታቸው ዶክተር ሰላም አስቻለው፣ እንዲወረስባቸው የተጠየቀውን አንድ የቤት መኪና በሚመለከት ተቃውሞ እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
ሌላው ዓቃቤ ሕግ ንብረቱ እንዲወረስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ያቀረበበት፣ በሌለበት ጥፋተኛ ተብሎ በ15 ዓመታት ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ የተወሰነበትና ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው አበበ በለው ሲሆን፣ ባለድርሻ ይሆናሉ ያላቸውን የባለቤቱ አድራሻ ማግኘት አለመቻሉን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት አመልክቷል፡፡
በመቀጠል ጋዜጠኛ እስክንድር ከተቀመጠበት የተከሳሾች መቀመጫ ሳጥን ውስጥ ቆሞ የሚያቀርበው ሐሳብ እንዳለው በመግለጽ፣ “እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በንብረት ውርስ ምክንያት መከራከር አንፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ፍርድ ቤት ከዛሬ በኋላ እንዳልቀርብ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ይሰጥልኝ፤” በማለት አመልክቷል፡፡
የአቶ አንዱዓለም አራጌ ባለቤት ዶክተር ሰላም ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የተቃውሞ ደብዳቤ እንዲወረስባቸው የተጠየቀው የቤት መኪና፣ በዕድሜ ልክ የተቀጡት ባለቤታቸው ስንቅ ማመላለሻና ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ማድረሻና መመለሻ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁሉንም ወገኖች ሐሳብ ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ለአቶ አበበ በለው ባለቤትና ለጋዜጠኛ እስክንድር ባለቤት መጥርያ እንዲደርሳቸውና መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ በማዘዝ፣ የሚቀርበውን መቃወሚያ ለማየትና ውሳኔ ለማስተላለፍ ለኅዳር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
(የሪፖርተሩ ታምሩ ጽጌ እንደዘገበው)
አራቢካ ቡና በሰባ ዓመት ውስጥ ዝርያው ሊጠፋ ይችላል
“ኢትዮጵያ አራቢካ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው የቡና ዝርያ በሰባ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጠፋ እንደሚችል ተጠቆመ። ይህ ወፍ ዘራሽ የተፈጥሮ ቡና ዝርያ ከነአካቴው ሊጠፋ እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን ይፋ ያደረገው Eurekalert በመባል የሚታወቀው ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጽሁፎች በማቅረብ የሚታወቀው ድረገጽ ነው። ጥናቱ የተካሄደው የብሪታንያ ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ የሳይንስ ጠቢባን ከኢትዮጵያ የሳይንስ ምሁራን ጋር በጋራ ሲሆን ለአራቢካ ቡና ዝርያ መጥፋት በዋናነት የተጠቀሰው የአየር ንብረት ለውጥ ነው።
በአለም የቡና ተክሎች የሚበቅሉት የቡና ዝርያዎች በተፈጥሮ የሚይዙት የዘረ-መል አይነት ውሱን በመሆኑ የአየር ለውጥን፣ ተባይ፣ በሽታንና፣ ውርጭንና ሌሎች አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ብቃት እንደሌላቸው በጥናቱ ተገልጿል።
በቻይና ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ ሥልጠና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ
በዚህ በያዝነው የህዳር ወር የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በቻይና ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ መስጠት መጀመሩን አይጋፎረም የዩኒቨርሲቲውን የቋንቋዎች ዲን በመጥቀስ አስታውቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን እውቅና በዓለምአቀፍ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል የተባለው ይኸው ፕሮግራም ለመጀመሪያ ዲግሪ 20 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑንና በምስክር ወረቀት ደረጃም ተጨማሪ ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑ ታውቋል፡፡ በቀጣይም የማስተርስ ዲግሪና የነጻ ትምህርት ዕድል እንደሚመቻች ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ወደፊት ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ወደተለየ አቅጣጫ ለመውሰድና በበለጠ የአገዛዙን ማነቆ በታማኞቹ ለመቆጣጠር ጥቂቶች በልዩ ሁኔታ እየተመረጡ በቻይና ትምህርታቸውን እንዲከታሉ እየተደረገ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች በተበራከቱበት ባሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው የጀመረው ይህ አዲስ ፕሮግራም እጅግም የሚያስገርም እንዳልሆነ ተጠቁሟል፡፡ በተለይ የቻይና ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተበራከተ ባለበት ጊዜ በቻይና ቋንቋ የሚመረቁት እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ፣ … በመሳሰሉ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ባስተርጓሚነትና ሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ ተቀጥረው እንደሚሠሩ በዘገባው ላይ ተገልጾዋል፡፡
koster says
Woyane ethinic fascists are interested in looting and terrorizing and they do not care if arbica coffee disappears in 50 or 100 years. These home grown fascists do not consider the part of Ethiopia outside Tigrai their country. They sit in Menelik palace as long as they can loot and suck Ethiopian blood and resources and will retreat to great Tigrai when they are forced to give up power. Say no to state terrorism and ethnic cleansing in Ethiopia.
derje says
“እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በንብረት ውርስ ምክንያት መከራከር አንፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ፍርድ ቤት ከዛሬ በኋላ እንዳልቀርብ ለማረ