
ከአመታት በፊት በምርጫ ዘጠና ሰባት አካባቢ አዋሳ ከተማ ውስጥ የገጠመኝ ነገር ትዝ ይለኛል። በአዋሳ ከተማ ቆይታየ ጊዜ ከአንድ ታዋቂ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ እሳተፍ ነበር። በዚህ ድርጅት መሳተፍ እንደጀመርኩ ብዙም ሳልቆይ የወጣቶች ጉዳይና የድርጅት ጉዳይ ሆኘ ተመደብኩ።ታዲያ በዚያ አጭር ጊዜ ቆይታየ የመንግስትን የስለላ ስራና ተፈጥሮ እንድረዳ እድል ስለሰጠኝ ያ ጊዜ አስተማሪየ ሆኖ ይሰማኛል። በውነት ለመናገር ያ የአዋሳ ቆይታየ ስለ ወያኔ ያለኝን መረዳት አራምዶት ነበር።
ዛሬ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (TPDM) መሪ የነበረው ሞላ የተወሰኑ ታጋዮችን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገባ የሚለው ዜና ከተሰማ በሁዋላ ያ የአዋሳው ትዝታየ የኋሊት በምናብ ታወሰኝ። በተለይም የሞላ አስገዶምን ኢንተርቪው ሳይ “እኛ ከመንግስት ጋር ስንሰራ ቆይተናል። ግንኙነት ነበረን” ሲሉ የአዋሳ ገጠመኘን በጣም አጉልቶ አሳየኝ።
እስቲ አዋሳ የሆነውን ላውጋችሁ። አዋሳ ከተማ ውስጥ እሳተፍበት በነበረው የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ከኮሚቴዎቹ መካከል አንዱ ማለትም የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊው በጣም ይቀርበኝ ነበር። አቶ ኤልያስ ይባላል። ይህ ሰው ትሁት፣ ተቆርቋሪ፣ ለአገር አሳቢ ነው። ሞላን ይመስላል። በስብሰባዎች ወቅት ማስታወሻ መያዝ ይወዳል። ስብሰባዎችን ስንጨርስ አቀፍ እያደረገ ወደ ጎን ወሰድ ያደርገንና ለድርጅቱ ያለውን ፍቅር፣ የእኛን አስተዋጾ ያደንቃል። እኔም እውነቱን ለመናገር አመንኩት። ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን የተለመደውን ስብሰባችንን አጠናቀን ስንጨርስ “የማወራህ ብርቱ ሚስጥር አለኝና አብረን ወጣ እንበል” አለኝ ለስላሳው አቶ ኤልያስ፣
“በደስታ። እንዴውም እኔም ዛሬ የማካፍልህ አሳብ አለኝ” አልኩት
በተለይ በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ልዘረጋው ያሰብኩትን መዋቅርና ፕላን ለማሳየት ፋይሌን ከፈትኩና አንድ ገጽ ወረቀቴን ይዤ ወጣሁ። እንደተለመደው አቶ ኤልያስ አቀፍ አርጎኝ እየመራኝ ከጽህፈት ቤቱ ግቢ ወጥተን ጉዞ ጀምረናል። ወደየት እንደምናመራ አልገባኝም፣ አልጠይቅምም። የአዋሳው ዩኒቨርሲቲ ፕላኔ መስጦኝ ስለነበር በዚያ ዙሪያ አንዳንድ አሳብ እያነሳሁለት እንጓዛለን። ከጥቂት ጉዞ በኋላ ወደ አንድ የማይመች አጣብቂኝ ቦታ ይዞኝ ገባ።
“ወደ ተሻለ ቦታ ሄደን ሻይ ቡና እያልን ብናወራ አይሻልም አቶ ኤልያስ?”
አንድ ርምጃ ፈንጠር ብሎ ቆመና ጥቂት ዝም አለ። ግብዣየን እያሰበበት መስሎኝ ደግሜ ጠየኩት።
አቶ ኤልያስ ቀና አለና “አይ! ሌላ ጊዜ ይሻላል አሁን ግን የማጫውትህ ብርቱ ምስጢር አለኝ”
“አጫውተኝ፣ ምን ችግር አለ….” ፈርጠም ብየ። የመሰለኝ ያው ከድርጅቱ እቅድ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነውና።
“ችግር ገጥሞኛል እባክህ” አለ አቶ ኤልያስ ተስፋ እንደቆረጠ ሰው ፊቱን አቀጭሞ።
“ምን ችግር ገጠመህ?” መልሱን ሁሉ በኪሱ እንደሞላ ሰው ዘና ብየ
“ተይዣለሁ”
“ማን ነው የያዘህ? …. ማለቴ አልገባኝም??…..”
“ይዘውኛል”
እነማን ናቸው የያዙህ አቶ ኤልያስ?
“ደህንነት ይዞኛል”
“አልገባኝም?”
“የመንግስት ደህንነት ይዞኝ ለነሱ እየሰራሁ እገኛለሁ”
ግራ ገባኝ በውነት።
“ለነሱ እየሰራሁ ነው ስትለኝ ምን ማለት ነው?”
“በቃ የደህንነቱ ዋና ሃላፊ ይዞኝ ለኛ ሰላይ ሁን አለኝ፣ ለኛ የማትሰልል ከሆነ በአንተና በቤተሰብህ ላይ ፍረድ ስላለኝ ለነሱ እየሰራሁ እገኛለሁ። ቀን ቀን ከናንተ ጋር ተሰብስቤ ማስታወሻ ስይዝ እቆይና ማታ ማታ በሚኖረን ስብሰባ ላይ ሪፖርት አደርጋለሁ። በተለይ አንተ ወደዚህ ከመጣህ በሁዋላ የአንተን ንግግሮች በሚገባ ማስታወሻ ይዤ ሪፖርት እንዳደርግ ታዝዤ ይህንን በማድረግ ላይ እገኛለሁ። ደህንነቱ ይከታተልሃል።”
“ስንት ጊዜ ሆነህ እንዲህ ስታደርግ?”
“ከዓመት በላይ ይሆነኛል” ልክ ሞላ አስገዶም ከዓመት በላይ ከመንግስት ጋር ስሰራ ነበር እንዳለው::
“ይህንን ጉዳይ ለድርጅቱ መሪዎች አሳውቀሃል?”
“በፍጹም:!” ምላሱን ጎልጉሎ
አቶ ኤልያስ ቀጠለ …. “ላንተ ብቻ ነው የምነግርህ …. ላንተ የምነግርህም በተለይ ስብሰባዎች ላይ የምትናገረውን እንድትጠነቀቅ፣ ይህንን የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ እቅድህን እንድታዘገየው ነው።”
እውነቱን ለመናገር በጣም ግራ ተጋብቼ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሰው አሁን ይህን የሚነግረኝ ለእኔ አሳቢ ስለሆነ ነው ብየም አሰብኩ። ሁለታችንም መሬት መሬት እያየን ነገሮችን በማላመጥ ላይ እያለን። አንድ የቸኮለ ሰው የሚመስል በጎናችን ሲያልፍ “ሰላም ኤልያስ” አለ።
ሰውየው በጎኔ ሲያልፍ አየሩን ቀዝፎት ነበር። ለምን በዚያ መጠጋጋት በስራችን እንዳለፈ አላውቅም። ለማስፈራርትም ሊሆን ይችላል።
የአየር ላይ ሰላምታ ተለዋውጠው ሲያበቁ ኤልያስ ጠበብ ያለ ሳቅ ጀመረ።“ይሄም የኛ ሰው ነው…. ሰላይ ነው…ማታ ማታ ሁሌ እንገናኛለን”
አሁን ጨዋታ በቃኝ። ብቻየን መሆንና ማሰብን መረጥኩ።
“ጥሩ አቶ ኤልያስ ስለ ሰጠኸኝ መረጃ አመሰግናለሁ። ሌላ ጊዜ እንጫወታለን።” እጄን ዘረጋሁ። ለሰላምታ።
“አንተንም በቅርቡ ሊያነጋግሩህ ሊጠሩህ እንደሚችሉ እገምታለሁ።”
“እኔን?”
“አዎ!” ደሞ ይስቃል
ውስጤ በሸቀ። “ዛሬ ማታ ደህንነቱን ስታገኘው ወደኔ አትምጡ በልልኝ” ብየ የማመናጨቅ ያህል ሰላም ብየው ተለየሁ።
ጉዳዩን ሮጦ ለሌሎች ከመናገር በፊት መመርመር መረጥኩና ጋሪ ተሳፍሬ ወትሮም ወደምወደው የአዋሳ ሃይቅ ዳር አመራሁ። በዛ ቁጭ ብሎ የአዋሳን ግርማ እያዩ ማሰቡ ይረዳል።
አዋሳ ሃይቅ ዳር ቁጭ ብየ ማሳብ ጀመርኩ።
ይህ ሰው እንዴት ይህን ብርቱ ምስጢር ሊነግረኝ ቻለ?
ለምንስ እኛን ሰላማዊ ታጋዮችን በዚህ ደረጃ መሰለል አስፈለገ?
ምን የተደበቀ ነገር አለን?
ምን ስለላ ያስፈልገናል? ብዙ ጥያቄዎች ያለ ወረፋ በአይምሮየ በፍጥነት ይጎርፋሉ። አንድ ደረጃ ከፍ ብየ ማሰብ እንዳለብኝ ተሰማኝ።
ያኔ አገሩ አንጻራዊ የሆነ ሰላም ነው። ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች በተሻለ አንጻራዊ ነጻነት ይሰራሉ ፣ ምንድነው ይሄ ነገር? …. አሳብ ሳወጣ ሳወርድ ከቆየሁ በሁዋላ የወያኔን ዘዴ ለመረዳት ብዙ አልተቸገርኩም። የአዋሳ ጀምበር ደህና እደር አዋሳ ስትል፣ የሃይቁ ፍጡራን እነ ጉማሬ በውሃ ሲጫውቱ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ። ከሃይቁ ዳር ዳር ቀጥፌ የነበረውን ሳር ወደ ውሃው ወረወርኩና ሽቅብ ወደ ማረፊያየ አቀናሁ።
ግምቴን ይዤው ጥቂት ቀን ቆየሁና የሚቀጥለው የኮሚቴው ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ስብሰባው ቅዝቅዝ ብሏል። አዲስ አሳብ አይሰነዘርም። ጥቂት የኮሚቴው አባላት ላይ ምክንያት የለሽ ደረቅ ፈገግታ አያለሁ። እርስ በርስ መተያየት ተያይቶ ሲያበቁ ፈገግ ማለት ሆነ ስራችን። እንዲሁ የሆነ ያልሆነውን ጥቂት አወራንና የመለያያ ጊዜ ደረሰ። አቶ ኤልያስን ሰረቅ እያደረኩ አይ ነበር:: ለሌሎችም ተመሳሳይ ነገር ነግረው እንደሆነ ከአይምሮአቸው መረጃ ለመስረቅ ጥረት አደረኩ። ለማናቸውም አንዱን የኮሚቴ አባል መጨረሻ ላይ በጎን በጎን አድርጌ በማውራት ለሌሎችም ይህን ለኔ የነገረኝን መንገሩን ለመረዳት አስቤ ጠየኩት። በርግጥም ለእኔ የደረሰኝን አይነት መረጃ ለዚህ ሰውም እንደደረሰው ገባኝ።
ነገሩ እያደር እየበራልኝ መጣ። አቶ ኤልያስ በርግጥ የስለላ ስራ ይሰራል። የስለላ ስራውን የሚሰራው ግን እንገልሃለን ስለተባለ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የወያኔ አባል ነው። አሁን የተሰጠው ሚሽን በዚህ እኔ በምሳተፍበት የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በሃላፊነት ቦታ ሰርጎ በመግባት በዚህ ቀጣና ያለውን ሰላማዊ ትግል ማፍረስ ነው። አቶ ኤልያስ ደምበኛ ወያኔ ሲሆን ለእኔ ያንን ምክር መሳይ ማስፈራሪያ የሚነግረኝ በስብሰባዎች ላይ አሳብ እንዳላቀርብ፣ ፈርቼ ቶሎ ከዚያ ድርጅት እንድወጣ ነው። ይህ ሰው ተልእኮው ይሀ ነው። አቶ ኤልያስ ጥሩ ሰው ይምሰል እንጂ እየተቅለሰለሰ ስራ ይጎትት እንደነበር ኋላ ላይ መገምገም ችየ ነበር።
ወያኔ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ለመምታት የሚጠቀማቸው ስልቶች ብዙ እንደሆኑ ይህ ጉዳይ ያሳየኝ ጀመር። ተገረምኩ። አብሪ ጉዳይ ሆኖ ታየኝ። ጉዳዩ አገራዊ ሆኖ ገዝፎ ታየኝ። በርግጥ በማእከላዊ ደረጃ፣ በሁሉም ፓርቲዎች ዘንድ ይህ አይነቱ የወያኔ አሰራር ወጥነት ሊኖረው እንደሚችል አመንኩ። በውነት ኢትዮጵያ ያሳዘነችኝ ያን ቀን ነው። አሳዘነችኝ። ሚናው ያለየለት ትግል ውስጥ ሆና ግራ ተጋብታ ታየችኝ። ወያኔ ትግሉን እንዴት እንዳወሳሰበው ሳይ ኢትዮጵያን ለቆ የመውጣቱ ጉዳይና የታጠቁ ሃይሎችን የመቀላቀሉ ጉዳይ በውስጤ ሲደምቅ ይሰማኝ ነበር። የታጠቁት ሃቀኛ ናቸው፣ ወያኔ ሰርጎ አልገባባቸውም የሚለውን እምነት ከየት እንዳፈስኩት ባላውቅም የተሻለ አማራጭ መስሎ ግን ታየኝ።
ከሁሉ በላይ ግን የወያኔ ስርዓት በምን ላይ እንደቆመ የመመርመሩ ጉዳይ ዝንባሌየን ሳበው። ይህ ጥያቄየም የሃገሬን የፖለቲካ ችግር የሚያስረዳኝ ለወደፊት ተሳትፎየም በመረዳት ላይ ያተኮረ ድጋፍ ለመስጠት የሚረዳኝ መሰለኝ።
ብዙ ሰው እንደሚረዳው የወያኔ መራሹ መንግስት በትግል ሂደቱም ሆነ አሁን ስልጣን ከያዘ በሁዋላ የሚጠቀምበት ስልት ጠለፋ (hijacking) መሆኑ በመረጃ ተደግፎ ገባኝ። በሰፊው አገራዊ ችግርም ሆኖ ስለታየኝ አዲስ ነገር መሰለኝ።
ህወሃት ራሱ “ኢሃዴግ” ብሎ የሚጠራውን ካባ ለመልበስ ሲል የተለያዩ የብሄር ድርጅቶችን የፈጠረ ሲሆን እነዚህ ድርጅቶች በወያኔ ሙሉ በሙሉ የተጠለፉ ናቸው። እንቅሳቃሴዎቻቸው ሁሉ በህወሃት የተጠለፈ፣ መጠለፍ ብቻ ሳይሆን በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው። ህወሃት እነዚህን ድርጅቶች ጠልፎ ጠልፎ አንድ “ኢሃዴግ” የሚባል ካባ ይለብስና መንግስት ሲመሰርት ደግሞ መንግስትን ራሱን በሙሉ ሲጠልፈው እናያለን። ሰኪዩሪቲው፣ ወታደሩ፣ ሲቪል ሰርቪሱ በሙሉ የመንግስት ተቋማት በህወሃት ተጠልፈው እናያለን።
ይህ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚውን ክፍል ሰላማዊውን ትግልና የትጥቅ ትግሉንም መጥለፍ ለዘላቂ ስልጣን ይጠቅመኛል ብሎ ስለሚያስብ አንዳንዴ ራሱ መንግስት ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶችን እየፈጠረ አንዳንዴ በእውነተኛ ተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥ እስከ ሃላፊነት ደረጃ የሚደርሱ አስመሳይ ወያኔዎችን እየሰገሰገ የጠለፋውን ስራ ሲሰራ እናያለን። ይህ የሚያሳየው ራሱ መንግስት በጠለፋ ላይ የተዋቀረ መሆኑን ነው። ይህ የህወሃት መሰረታዊ በስልጣን ላይ የመቆያ እምነትና ዘዴ ነው።
ህወሃት ወደ ስልጣን ሲመጣም ከመጣም በሁዋላ የማይለወጥ ይህ የጠለፋ ዘዴው በዜጎች ሁሉ ዘንድ መታወቅና መጋለጥ አለበት። እውነተኛ የተቃዋሚ ድርጅቶችም በተለይ አመራር አካባቢ ያሉ ሰዎች ትግሉ እንዳይሄድ ሲያደርጉ ይህን የወያኔን የጠለፋ ተፈጥሮ በመገንዘብ አባላት አመራሮቹን ወጥሮ ሊይዝ ይገባል። በየጊዜው ትግሉ የት ደረሰ? ብሎ ወጥሮ ሊይዝ ይገባል። የየፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ንጹሃን አመራሮች ድርጅታቸው ወደ አንድነት የማያመራበትን ምክንያት አጥብቀው መጠየቅ ወደ አንድነት የማያመራ ከሆነ መልቀቅና ማጋለጥ ያስፈልጋል።
ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ ወደ ሆነኝ ጉዳይ ልመለስና በትህዴን ሊቀመንበሩ በሞላ አስገዶም ጉዳይ ልንደነቅ አይገባም ለማለት ነው የቆምኩት። ይህ ጉዳይ የስርዓቱ መሰረት መገለጫ ነው ለማለት ነው። ሞላ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ የሚነግሩን ከመንግስት ጋር ስንሰራ አንድ አመት አልፎናል ረዘም ላለ ጊዜ ስንሰራ ነበር ይላል። ይህ ማለት አቶ አንዳርጋቸውንም ያሳፈኑት እነሱ ናቸው ማለት ነው። አንዳርጋቸውን ሲያታልሉ ሲሰልሉ ነው የከረሙት። ያሳዝናል።
ሲሰልሉ የቆዩበት ጊዜ ግን ውሸት ነው። ወያኔ በጣም ይፈራ የነበረው የታጠቁ ሃይሎችን ሲሆን እነዚህን ሃይላት ለመጥለፍ እንደ ትህዴን አይነቱን መጥለፍ ወሳኝ መስሎ ነው ይሚታየውነው። ከስልጣን የሚያስለቅቀው ሃይል ሲፈጠር ደግሞ ለመጨረሻ ጊዜ አማራጭ (worst case scenario) የሚያገለግል ሃይል አድርጎም ነበር የሚያየው።
በመሆኑም በዚህ ድርጅት ውስጥ ከመሪው ጀምሮ እንደ አዋሳው አቶ ኤልያስ አይነት ሰው አስቀምጦ የትጥቅ ትግሉ እንዳይራመድ ማድረግ፣ የትጥቅ ትግሉ እንዳይራመድ ብቻ ሳይሆን በስርዓቱ ተማረው በትጥቅ ትግል ወያኔን ለመጣል ከኢትዮጵያ የሚመጡትን ኢትዮጵያዊያንን ይዞ በማቆየት፣ ወይም በማጥፋት ወይም አሳልፎ በመስጠት ስራቸውን ሲሰሩ ቆይተዋል። አቶ አንዳርጋቸው አንዱ ሰለባ ናቸው።
ልብ በሉ …. ትህዴን ከተቋቋመ ረጅም ጊዜው ሲሆን ብዙ ወታደር አለው ተብሎ ይወራል። የሚገርመው ግን አንድ ቀበሌ እንኳን ሲይዙ የትጥቅ ትግሉን ሲያጠናክሩ አይታይም። ህወሃት በተቋቋመ በስድስት ወሩ ከፍተኛ ውጊያዎችን አድርጎ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነጻ መሬት እያሰፋ ነበር የሄደው። እነ ሞላ ኤርትራ ቁጭ ብለው ሌሎች ተቃዋሚ ሃይላትን እያዳከሙ የወያኔ ደጀን ሆነው ቆይተዋል። እነዚህ ሃይሎች የትጥቅ ትግሉን የሚጠልፉ ቡድኖች ናቸው። ይህ ማለት ግን አብዛኛውን የዋህ የትህዴንን አባል አይወክልም። በየትኛውም የተቃዋሚ ድርጅት ውስጥ ወያኔ ግዙፉን ህዝባዊ ድጋፍ አያገኝም። ህዝቡ ተቃዋሚዎች አለን የሚሉትን መርህ ስለሆነ የሚደግፈው ወያኔ ይህን ሃይል መቼም ቢሆን ሊጠልፈው አይችልም። ይሁን እንጂ አመራር ላይ ያሉትን አንዳንዶችን እንዲህ እየጠለፈ ትግሉን ማጓተቱ አንዱ የስርዓቱ እምነትና መሰረት መሆኑን መረዳት አለብን። ለዚህ ነው ሰፊው ህዝብና አባላቱ ድርጅቶቹን ውጤት ተኮር ግምገማ ሊያደርግባቸው ይገባል የሚያስብለን።
ወያኔን ከጠለፋ ስራው የምናጋልጠውና ትግሉ የሚጠናከረው ፓርቲዎችን ወደ ተግባር በምንገፋው የግፊት መጠን ነው። የወያኔ መርህ የሆነው ጠለፋ በመንግስት፣ በተቃዋሚዎች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ተቋማት አካባቢ የሚቃወሙትን፣ የሰባዊ መብት ረገጣውን በሚያጋልጡ ድርጅቶች ሁሉ ላይ ያነጣጠረ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጠብቀው ሲያጋልጡትና ርዳታ ሲያስቀሩበት ወያኔ ዝም ይላል ብሎ ማሰብ የወያኔን ቂመኛ ባህሪ ያለማወቅና የዋህነት ነው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን ለነዚህ ተቋማትና ለለጋሽ አገራት የወያኔን የህዝብ ግንኙነት ስራና ተንኮል ማጋለጥ አለብን።
ኢትዮጵያውያን የወያኔን ስርዓት አወቃቀር በሚገባ ልንረዳ ይገባናል የሚያስብለን ትግሉን ወደፊት ለማራመድ ዘዴኛ እንድንሆን እንጂ ሁሉን እንድንጠረጥርና ተስፋ እንድንቆርጥ አይደለም። ስርዓቱ የቆመበት ይህ የማታለልና የጠለፋ ድርጊት መፍረስ አለበት። በሌላ በኩል ስለ ወያኔ ተፈጥሮ ስናወራ መርሳት የሌለብን ወያኔ ራሱ ድርጅቱ እንደ ፖለቲካ ድርጅት የሚታይ አይደለም። ህወሃት የማህበራዊ ኢኮኖሚ ተቋም ሲሆን ይህ ተቋም መንግስትን በተለይም ወታደሩንና ሰኪዩሪቲውን ጠልፎ የሚኖር ነው። የህወሃት ውስጣዊ ማንነት ኤፈርት ነው። ምንም አይነት የጠራ የፖለቲካ ርእዮት የማናየው፣ አገሪቱ ወደ ተሻለ መድብለ ፓርቲ ስርዓት የማትራመደው የወያኔ ተፈጥሮ ፖለቲካዊ ዝንባሌ ያለው ሳይሆን የሶሺዮ ኢኮኖሚክ ተቋምነት ባህርይ ያለው በመሆኑ ነው። ይህንን ስርዓት የሚቃወሙ ሃይላት በፍጹም በጎሳ ላይ መደራጀት የለባቸውም። ጎሳ ተኮር የሆነ ትግል በመርህ ደረጃ ከወያኔ አይለይም።
ምን አልባት በየዋህነት ለውጥ በዚህ መንገድ ይመጣል ብለው የተነሱ ሃይለት አሁን የሚረዱበት ዘመን ይመስላል። ከመጣመድ ከግንባር ወጥተው መዋሃድ አለባቸው። ጎሳዊ ስም ይዞ በአንድ በኩል በኢትዮጵያ አንድነት አምናለሁ የሚለው ፍልስፍና በሚገባ መጤንና ስህተትነቱ ሊገባን ይገባል። ሚናው የለየለት ትግል ውስጥ ካልገባን ወያኔ ለጠለፋ ስራው የሚጠቅመውን ሁኔታ እናመቻቻለን።
የሞላ መኮብለል የሚያሳየው ሃቀኛ ትግል እያየለ መምጣቱን ሲሆን አሁንም ቢሆን ፓርቲዎች እያጠሩ ቶሎ ወደ ውህደት መራመድ አለባቸው። ውህደት በራሱ የሚያፈርሰው ብዙ የወያኔ ሴራ አለ። በሌላ በኩል ወያኔ አደገኛነቱ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለኤርትራውያንም ነው። አጠቃላይ የሃበሾችን መጻኢ እድል እያወሳሰበ ያለ መጥፎ ሰርዓት ነው።
እዚህ ላይ አንድ ነገር በግልጽ መናገር ጥሩ ነው። ይሄ “ወያኔ” የሚለው አጠራር ትርጉሙ ፈጽሞ ከትግራይ ተወላጆች ጋር መያያዝ የለበትም። የትግራይ ወጣቶችም ይህን ስያሜ ከባህላዊ ቡድናቸው ማንነት ጋር ማያያዝ የለባቸውም። ወያኔ የብሄር መጠሪያ አይደለም። ወያኔ ማለት ራሱ ስርዓቱና የስርዓቱን ተዋንያን የሚያሳይ ሲሆን አዲሱ ለገሰም፣ በረከት ስምዖንም፣ አባዱላ ገመዳም፣ ሃይለማርያም ደሳለኝም፣ ቴድሮስ አድሃኖምም፣ ወያኔዎች ናቸው። እነሱም ሁላችንም ወያኔዎች ነን ብለዋል። የትግራይ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ከዚህ ከማንነት ፖለቲካ መራቅ አለብን። ሃበሾች ለነጻነታችን ስንል ከዚህ ከፋፋይ አስተሳሰብ ጋር መታገል አለብን። የተባበረችውን ኢትዮጵያን የምንገነባው ወጣ ባለ አሳብ ነው። ከሁሉ በላይ የወያኔን የጠለፋ ስርዓት ስንረዳው በየጊዜው የሚከዱ፣ ትግሉን ሲጎትቱ የሚያዙ የተቃዋሚ መሪዎችን ነገር ግን የወያኔ ሰላዮችን ስናይ ግራ ሳንጋባ የበለጠ የዴሞክራሲ ትግላችንን እናቀጣጥላለን። ጉዳያችን ከመርህ ጋር የተጣበቀ፣ ከኢትዮጵያ አንድነት ጋር የተጣበቀ ይሁን። ሚናው የለየለት ህብረት እንመስርት። ሚናው የለየለት የትግል አውድማ ውስጥ እንግባ። ከዚያ ብዙ ህዝብ የሚጠብቀው የትግል ፍሬ ይታያል።
የተባበረችውን ኢትዮጵያን እንገንባ
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply