“አስካውት!…”
“ምን ጊዜም ዝግጁ!!!”
ዱሮ ዱሮና በኛም ዘመን የቦይ እስካውት ክለብ (Boy Scout) እንቅስቃሴ ሞቅና ደመቅ ያለ ነበር፡፡ ሰላሌ ፍቼ፣ የአበራና አስፋው ወሰን የ1ኛ ደረጃና ወሊሶ የደጃዘማች ገረሱ ዱኪ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ እያለሁ (ከ1953-1960 ዓ.ም.) የቦይ እስካውት ክለብ አባል ነበርኩ፡፡ ፍቼ እያለን፣ የእስካውት ክለባችን ኃላፊ መምህር ወልዴ ይባሉ ነበር፡፡ በእግራችን ወደ ገጠር እየተጓዝን ድንኳንም ተክለን፣ ምግባችንን አብስለን፣ ሻይ አፍልተን እየተደሰትን አድረን እንመለስ ነበር፡፡ ማታ ማታም ደመራ ደምረን (Camp fire) ዙሪያውን ከበን እየጨፈርን፣ ግጥም የመግጠም ተሰጥኦ ያለን እየገጠምን ለጓደቾቻችን እያሰማን፣ አጫጭር የወዲያው ፈጠር ድራማም እያሳየን እንደሰት ነበር፡፡ ቀልዳ ቀልድም የሚያሰሙ ብዙዎች ነበሩ፡፡
በተለይም አንድ ጊዜ ከፍቼ ከተማ እስከ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ድረስ ታቹን በሽንኩርት ሚካዔል በኩል በእግራችን ተጉዘን፣ የጉር ወንዝን ጥንታዊ ጠባብ ድልድይ ተሻግረን ወደ ገዳሙ ዘለቅን፡፡ ይህ የጉር ወንዝ ድልድይ እጅግ ጠባብ የመሆኑን ያህል፣ እጅግ ወደታች ጥልቀትም አለው፡፡ ልጆች ሳለን አንድ ጊዜ የአበራና አስፋው ወሰን ት/ቤት ተማሪዎች፣ ላባባ ጃንሆይ አቤቱታ ለማቅረብ ከትምህርት ቤት ታላላቆቻችንና መምህራኖቻችን ጋር ሆነን ይህን ድልድይ ስንሻገር የሆነው ሁሉ ትዝ ይለኛል፡፡ ትንንሶቹ ልጆች ቆመን ደፍረን መሻገር ፈርተን እየተንፏቀቅን የተሻገርነው አይረሳኝም፡፡ ባንድ ጊዜ ካንድ ሰው በቀር አያሻግርም … ጎን ለጎን ተሁኖ፡፡ ይህን ጉደኛ ድልድይ ፖርቱጋል ሠራው ሲባል እንሰማዋለን፡፡ እውነቱን ግን የሚያስረግጥ መጣፍ ወይ እማኝ በግሌ አልገጠመኝም፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋልና ይህን ጉዳይ እግረ መንገዴን ባነሳው ደስ ይለኛል፡፡ የያኔው ላቤቱታ ወደ ጃንሆይ ያካሄዳችን ሰበብ ሚስተር ራፋት የሚባሉ ዝነኛ ግብጻዊ የትምህርት ቤታችን ዳይሬክተር ስለተቀየሩብን፣ እንዲመለሱልን ለጃንሆይ ለማመልከት ነበር፡፡ ያቤቱታው ሁናቴ የተመቻቸልን አባባ ጃንሆይ ልጃቸው ልዑል ሳህለ ሥላሴ ሙተውባችው ሊያስቀብሯቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ የመዝለቃቸው ዜና መሰማቱ ነው፡፡ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች አንድ ሳንቀር ከነመምህራኖቻችን ወደ ጫገል ገሰገስንና ባስፋልቱ ግራና ቀኝ ተሰልፈን ከቀብር እስኪመለሱ ድረስ ጠበቅን፡፡ ሲደርሱም አውቶሞቢላቸውን አስቁመው አቤቱታችንን በተወካያችን አማካኝነት በጽሑፍ ተቀበሉን፡፡
በተጨማሪም ተወካያችን ጉዳዩን ባጭሩ በቃልም አስረዳ፡፡ ”ዳይሬክተራችሁ እንዲመለሱላችሁ እናደርጋለን” ሲሉ ጃንሆይ ቃል ገቡ፡፡ ወዲያውም በክብር ዘበኞች አጃቢነት አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው አንዳች ከሚያህል የእጅ ቦርሳው ውስጥ ለያንዳንዳችን አንዳንድ አዳዲስ ብር እየመዠረጠ አደለን፡፡ ያላሰብነው ሲሳይ ስለነበረ፣ ላባባ ጃንሆይ እድሜና ጤና እተመኘን ድካም ሳይሰማን ወደ መጣንበት ወደ ፍቼ ገሰገስን፡፡ ግን ተወዳጁ ሚስተር ራፋት ሳይመለሱልን ቀሩ፡፡ ዘመኑ 1953 ዓ.ም. ነበር፡፡
ወደ ጀመርኩት የቦይ እስካውቶች የደብረ ሊባኖስ ገዳም ጉዞ ልመለስ፡፡ ጉዟችን ለተክለዬ ንግስ (ታህሳስ 24 ቀን) ለመገኘት ነበርና ድንኳናችንን ከገዳሙ ዝነኛ አምባዎች አንዱ በሆነው በውሻ ገደል ተክለን ከተምን፡፡ የገዳሙ ዙሪያ ገባ በደንና በቁጠጥቋጦ ተሸልሞ ያንን የልጅነት ዐይነ ልቡናችንን በፍቅር ስቦ የሚያማልለን እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ እዚያ እከተምንበት ጉብታ ስፍራ ላይ ውለን ስናድር፣ ሰዉ እየመጣ አሰፋፈራችንንና አኗኗራችንን እያደነቀ ሲመለከተን፣ ይሰማን የነበረው የደም ሞቅታ በእጅጉ ላቅ ያለ ነበር፡፡
ለምግባችን ፓስታና ሞኮሮኒ እየቀቀልን፣ ሻይ ከዩኒሴፍ ከተለገሰን የዱቄት ወተት ጋር እያፈላን እንደልባችን እራሳችንን እናስተናግድ ነበር፡፡
ታዲያ እዚህ ላይ ሳይነሳ የማይታለፈው፣ እያንዳንዱ የእስካውት አባል የሚሰጠውን የእስካውት መሠረታዊ የሥነ ምግባር ትምህርት የወሰደና ላፈጻጸሙም ቃለ መሃላ የፈጸመ መሆን አለበት፡፡ የእስካውት ዋናው መርሆ ላገርና ለሕዝብ ታማኝና አገልጋይ መሆንን ፋይዳዬ የሚል ነው፡፡ ያቅመ ደካሞችን ቤትና ንብረት መንከባከብ፣ የእንጨት ድልድዮችን መሥራትና መጠገን፣ ያካባቢ ጽዳትን በዘመቻ መልክ ማከናወን፣ የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ ማድረግ ወዘተ… እጅግ ከሚዘወተሩ ተግባራት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የቦይ እስካውት አለባበስ ደስ የሚል ነው፡፡ ባብዛኛው እጀ ጉርድ የካኪ ሸሚዝ ከቁምጣ ጋር ይለበሳል፡፡ አንዳንዶቻችን እጀ ሙሉ የካኪ ሸሚዝ ከቦላሌ ሱሪ ጋርም እንለብስ ነበር፡፡ በሱሪው ላይ ቁልቁል የሚወርድም በቀጭኑ የኢትዮጵያ ባንዲራ በእሰፒል እናያይዝ ነበር፡፡ በደረታችን ላይ ደሞ ትንሽ ሰፋ ያለ ያገራችንን ባንዲራ እናገለድም ነበር ፡፡ አንገት ላይ ሸብ የምትደረገዋ እስካርፍም ከቦይ እስካውት ኮፍያ ጋር ተስማምታ ስትታይ፣ የመታምርና የምታጓጓ ነበረች፡፡ የዚህችን ዓይነት ኮፍያ ማግኘት ካልተቻለ፣ የካውያ ቅርጽ ያለው ኮፍያ ወይም የሰሌን ባርኔጣም ስንጠቀም ነበር፡፡ ጩቤ ከነአፎቱ፣ ኮዳና በልዩ የተቋጨ ገመድ እጎን ላይ መታጠቅም ደምብ ነው፡፡
ያቺ ገመድ አሰተሳሰሯና ሙያዋ ሁሉ ልዩ ነው፡፡ አንድ የቦይ እስካውት አባል የገመዷን አስተሳሰርና በቀውጢ ሰዓት አጠቃቀም በብርቱ ሰልጥኖ ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ የጉዞ ፕሮግራም በሚኖርበት ጊዜ አንድ ደህና የእስካውት ዱላ (ሽመል) መያዝ ጥቅሙ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ልዩ ውበት ያለው የቦይ እስካውት አርማም የተከበረና በጥንቃቄ የሚያዝ ምልክታችን ነበርና፤ በክንዳችን ወይንም በደረታችን ላይ ለጥፈነው መታየት ልዩ ደስታን የሚሰጠን ነበር፡፡ የቦይ እስካውት መዝሙራችንም በልዩ ዜማና በጥልቅ አውደ ጉዳዮች የተኳሸ ነበር፡፡
የቦይ እስካውት ሰላምታ አሰጣጥም ለየት ያለ ነው፡፡ የቀኝ እጅ አውራ ጣት በትንሽዋ ጣት ላይ ያርፍና መሃል የቀሩት ሦስት ጣቶች ቀንተው እንደ ወታደር ያለ ሰላምታ ይሰጣል፡፡ ቦይ እሰካውቶች እርስ በእርስ የእጅ ሰላምታ ሲሰጣጡ በግራ እጃቸው ነው፡፡ እኔና አንድ ጓዴ እንዴት የእጅ ሰላምታ ስንሰጣጥ እንደነበር ከግርጌው ፎቶ ላይ ያስተውሉ፡፡
ወደ ወሊሶ የቦይ እስካውት ሕይወት ልምዴ ደሞ ላሸጋግራችሁ፡፡ ቀደም ሲል የራስ ጎበና ዳጨው አባ ጥጉ 2ኛ ደረጃ በኋላም የደጃዝማች ገረሡ ዱኪ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ እያለሁ፣ የቦይ እስካውት ክለብ አባልነቴን እስከ ትሩፕ ሊደር ማእርግ ደረጃ ደረስ ገፍቼበት ነበር፡፡ አሥረኛ ከፍል እያለሁ የቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርስቲ ያንድ ዓመት ብሄራዊ አገልግሎት መምህር ሁኖ ተመድቦ እኛ ዘንድ የመጣው አቶ ሲራክ በላይነህ የእስካውት ክለብ መሪያችን ነበር፡፡ ታዲያ ተተለያየን ተዚያ ሁሉ አጀብ ዘመን በኋላ (1962 ዓ.ም.) ያለሁበትን አፈላልጎ ከሚኖርበት ከአሜሪካ በስልክ ታነጋገረኝ በኋላ፣ በገባልኝ ቃል መሠረት ብዙ የዚያን ጊዜውን የቦይ እስካውትነት ዘመናችንን የሚያስታውሱ ፎቶገራፎች ልኮልኛል፡፡ እጅግ አጅጉን ምስጋናዬን አቀርብለታልሁ፡፡
መምህር ሲራክ፣ የቦይ እስካውት ክለብ ኃላፊ መምህር ሁኖ፣ እኔ ደሞ ትሩፕ ሊደር ሆኜ የመራነው አንድ አድካሚና አስቸጋሪ ጉዞ ሁሌም ይታወሰኛል፡፡ እቅዳችን በማለዳ ከጨቦና ጉራጌ አውራጃ ከወሊሶ ከተማ ተነስተን፣ በጅባትና ሜጫ አውራጃ ውስጥ የሚገኘውን የወንጪን ሃይቅ ለጥቂት ቀናት ጎብኝተን መመለስ ነበር፡፡ አንድ መምህርና 25 ተማሪዎች የተካተትንበት የቦይ እስካውት ቡድን ነበር፡፡ በወጣትነት መንፈስ ተነሳስተን የተያያዝነው የእግር ጉዞ እንዲህ በቀላሉ የሚበገር አልነበረም፡፡ በበጋው የፀሐይ ሐሩር ስንቀቀል የውሃ ጥሙ፣ የራቡና የድካሙ ዓይነት ፍርቅርቆሽ ትንፋሽ የሚሰብር ነበር፡፡ ተራራ መውጣት ቁልቁለት መውረድ የበዛበትም ጉዞ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ጓዛችን የዋዛ አልነበረም፡፡ ድንኳን፣ የማብሰያና የመመገቢያ እቃዎች፣ የግል አልባሳቶቻችንና የመሳሰሉትን ሁሉ ተሸክመን ነበር፡፡ እንዲያ እንዲያ ሁነን የማታ ማታ ከዝነኛውና በተፈጥሮ ጸጋ ከተዋበው የወንጪ ሀይቅ ደረስን፡፡
ድካማችንን አሽቀንጠረን፣ ያንን የወንጪ ሀይቅን ውበት ተበስተ ምሥራቅ ሁነን፣ ባመሻሽ ጀምበር ጥላ ስር እያጮለቅን እንደ መልካም ሲኒማ አጣጣምነው፡፡ ቀሪውን ለበነገታው ቆይታችን እይታ ብለን፣ እስትራቴጂክ ስፍራ ወደ መምረጡ አመራን፡፡
አዎን አመቺ ስፍራ ከተራራው ወገብ ላይ አግኝተን፣ ድንኳናችንን እዚያ ተከልን፡፡ የተለመደውን የቦይ እስካውት ደመራ ደምረን፣ ቀደም ሲል በወጣው የሥራ ድልድል መሠረት ምግብ አብሳዮች እራታችንን አዘጋጅተው ከተመገብን በኋላ፣ ጨዋታው ደራ፡፡ ሁሉም የራሱን የፈጠራ ችሎታ የሚያሳይበት እድል እየተሰጠው በመዝናናት ላይ እያለን፣ ኃላፊ መምህራችን አቶ ሲራክ ከጀማው መሃል ጠቅሶ ወሰደኝና በጆሮዬ አንድ ጉዳይ ያንሾካሽክልኝ ጀመር፡፡”አየህ አበራ አንተ ትሩፕ ሊደር ነህ፡፡ ይህን ደረጃ ያለው የቦይ እስካውት አባል ደሞ በሁሉም ተግባራዊ ነገር ቀዳሚ ሆኖ የመገኘት ግዴታ አለበት፡፡ አንተ አርአያ ከሆንክ በኋላ ነው ሌላው የሚተገብረው” አለኝ፡፡
”እና ምን እንድታዘዝ ፈለግህ?” አልኩት፤ አቀራረቡም ሹክሹክታውም ለመስማት ያለኝን ጉጉት አንሮብኝ፡፡ በእርግጥ የትሩፐ ሊደርን መብትና ግዴታ ቀደም ብዬም አውቅ ስለነበር ቀዳሚ መሆኑ እንግዳ አልሆነብኝም፡፡ ወንዝ ስንሻገር ቀድሜ ተሻግሬ የማሳየው እኔ ነኝ፡፡ ምግብንም አስቀድሜ የምቀምሰው እኔ ነኝ፡፡ ለብዙ ብዙ ተግባራት ቀዳሚው ትሩፕ ሊደሩ ነው፡፡
”አሁን ማንም ሰው ሳይይህ ትሰወራለህ፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ አበራ ጠፋ ብዬ አውጃለሁ፡፡”
”ተዚያስ?…” አልኩት ደንገጥ በዬ፡፡
”ተዚያማ ሁሉም ተነስቶ በዱር በገደሉ አንተን እንዲፈልግ አዛለሁ… ያደጋ ጊዜ ጥሪ ፊሽካም ሊነፋ ስለሚችል እያዳመጣችሁ ተንቀሳቀሱ እላቸዋለሁ…”
”ተዚያስ ?…”
”ተዚያማ አንተ ተተደበቅህበት ቦታ ሆነህ እስኪያገኙህ ደረስ ድምጽህን አጥፍተህ ትቆያለህ…”
”ሰው ወይ አውሬ ቢተናኮለኝስ?…” ስል ጠየኩት፡፡
”ጩቤህን ላደጋ ጊዜ መከላከያ ትይዛለህ… አንድ ባትሪና አንድ ፊሽካም ትይዛለሀ…”
”ተዚያስ ?…” መጨረሻውን የመስማት ጉጉቴ አሁንም እንዳየለ ነው፡፡
”ተዚያማ ሕይወትህን የሚፈታተን ማናቸውም ነገር ከመጣ የድረሱልኝ ጥሪ በፊሽካው አሰማ… ጩቤውም መከላከያህ መሆኑን አትርሳ… ባትሪው ግን እጅግ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ብቻ ብልጭ አድርገህ የምትጠቀምበት ነው… ተጠንቀቅ!…” አለኝ፡፡
ከዚህ በኋላ ጨርቄን ማቄን ሳልል ተዘገጃጀሁና ሹልክ ብዬ ለግዳጁ ተሰማራሁ፡፡ ጭለማው መርግ ነው፡፡ ድቅድቅ ብሎ እንኳን ከሰፈርንበት ተራራ ላይ ይቅርና እዚያው በዚያውም የሚያላውስ አልነበረም፡፡ ገደል ገብቼ እንዳልሰባበር እየፈራሁ በጥንቃቄ ተራራውን ወረድኩት፡፡ እታች ከሃይቁ ዳር ስደርስ በስተቀኝ ወደሚገኝ ግቢ አጥር ስር ሄድኩና ሽጉጥ ብዬ በተረከዜ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ግና አፍታም ሳልቆይ አንድ የግቢው ሰው (አባ ወራው መሆን አለበት) በበቆሎ የጓሮ እርሻው ውስጥ እየተሽሎከለከ መጥቶ ከጀርባዬ ላይ ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡ እጅግ እጅግ ደነገጥኩ፡፡ ትንፋሼ ተሰበረ፡፡ ላብ ባንዴ አሰመጠኝ፡፡ ምናልባትም ባቅራቢያው ያለ አንድ ገደልን ልሻገር ስል ባትሪውን ብልጭ አድርጌ ነበርና በእሱ ተመርቶ የመጣብኝ መስሎኛል፡፡ እጅግ እጅግ ከበደኝ፡፡ የጭንቀቴ ሃያልነት ልብ ተርታዬን እያፈጠነ ትንፋሽ ነሳኝ፡፡
አዎን ሰውዬው ያላንዳች እንቅስቃሴ እንደጅብራ ተገትሮ ቀረ፡፡ ምናልባትም እሱም እንደኔው ፈርቶ ይሆን?… እኔንጃ! ኮሽታ የለም፣ ንቅንቅ የለም… ተፋጠጥን፡፡ በመካከላችን ያለው የበቆሎ አገዳ አልባሌ እጥር ብጤ ነው፡፡ ደሞም በእጅጉ ያስፈራኝ፣ ቀን ያየናቸው ያካባቢው አባወራዎች ባለ ረዥም ዘንግ ጦር የሚይዙ መሆናቸው ትዝ ያለኝ መሆኑ ነው፡፡ እናም ጦር ይዞ ቢሆንና ተንጠራርቶ በዚያ ቢወጋኝ የሚለው ስጋት ነበር እንደውጋት ቀስፎ የያዘኝ፡፡ እናም ልቤ ”ተዚያ ክፉ ቦታ ተፈትልከህ ሽሽ! ሽሽ!…” ቢለኝም ወኔው ከዳኝና ቀዝቃዛ ነጭ ላቤን እያመነጨሁ ጭጭ አልኩ፡፡ እሱም ጭጭ እናዳለ ነው…. ከሩብ ሰዓት በላይ ተፋጠጥን፡፡
የኋላ ኋላ እንደምንም ትንፋሼን አሰባስቤ እንደ ድምቢጥ ከእግሩ ስር ቱር ብዬ አፈተለኩ፡፡ ከበስተኋላዬ ጆሮዬን አንቅቼ ሳዳምጥ አሁንም አንዳችም እንቅሰቃሴ ወይም ኮሽታ አልነበረም፡፡ ሰውዬውን ምን አገኝቶት ይሆን እያልኩ እስከዛሬ ውስጤን እጠይቃለሁ፡፡ የሆነውን ማን ያውቃል?…
ይህን አስፈሪ ስፍራ ከለቀቅሁ በኋላ አለፍ ብሎ ወዳለ ግቢ ገሰገስኩ፡፡ ጠጋ አልኩና ባጭሩ የበቆሎ አገዳ አጥር ላይ ዘልዬ ወደ ግቢው ስገባ፣ እርጭ ብሎ የነበረው ግቢ በሁለት ውሾች ጨኸት ተናጋ፡፡ ይሄኔ ፍጥኜ ተዚያ ግቢ ውስጥ ተፈትልኬ ወጣሁ፡፡ እኒያ ውሾች ሊዘነጥሉኝ ጥቂት ነበር የቀራቸው፡፡ ከዚህም ጉድ አወጣኝ፡፡ አሁን ቀጥዬ የሃይቁን ዳርቻ በጥንቃቄ ተከትዬ ወደሚቀጠለው ግቢ አመራሁ፡፡ አሁንም አጥር ሊባል የሚስቸግር አጭር ያገዳ ሽምጥ ተራመድኩና እግቢው ገብቼ እንሰቶች መሃል በተረከዜ ቁጢጥ አልኩ፡፡ አካባቢው ሰላም ነው፡፡ የውሻ ዘርም የለም፡፡ ግና የሲጥሲጥታ ድምጽ በያቅጣጫው ተደጋግሞ ክፉኛ ተሰማኝ፡፡ የእንሰቱ ተክል ንፋስ ሲታከከው ድምጽ ሊሰጥ ቢችልም ችላ ሊባል ሚችል አልነበረም፡፡ ”ሌላስ ነገር ቢሆን?…” የሚለው በውስጥ ነፍስ ውስጥ ያንቃጭላል፡፡ ደሞ ትኩር ብዬ ፊት ለፊት ሳስተውል ሁለቱም ዓይኖቼ ላይ ብርሃን ተግ ብሎ ይታየኝና አውሬ ያፈጠጠብኝ ይመስለኛል፡፡ ደሞም ቀን በሃይቁ ዙሪያ ባለ ጫካ ውስጥ የሚኖር ዘንዶ አለ የሚል ክፉ ዜና ካገሬው ሰው ሰምተነው የነበረውም ትዝ እያለኝ ፍርሃቴን አባባሰው፡፡ ጭንቀቱ የባሰ አቅሌን እያሳጣው እያለ፤ ወዲያው ካፋፍ ጀምሮ ”አበራ!… አበራ የት ነው ያለኸው?… ” የሚል የምጻኔ ጩኸት ተሰማኝ፡፡
የወንጪን ሀይቅ ዙሪያውን የከበበው ተራራ የገደል ማሚቶ ደሞ ያንን ጥሪ እያስተጋባ የስሜን ጥሪ ዙሪያ ገባውን አነገሠ፡፡ ለጓደኞቼ ጥሪ ምላሽ ሳልሰጥ ጭጭ አልኩ መመሪያው ተግባራዊ መሆን ስላለበት፡፡ ፍለጋቸውን ቀጥለው ወደኔ አቅጣጫ ሲመጡ፣ ድምጻቸው ሲቀርበኝ ልቤ በደስታ ሲፈነጥዝ፤ ደሞ ያ የሰማሁት የጓደኖቼ ድምጽ ሲርቀኝ ተመልሶ ፍርሃትና ሽብር ሲነግስብኝ ለግማሽ ሰዓት ያህል ተጉላላሁ፡፡ እናም ራቅ ሲሉኝ ፊሽካ መንፋት ጀመርኩኝ፡፡ ሁሎቹም ከመምህር ሲራክ በተሰጣችው መመሪያ መሠረት፣ የፊሽካ ደምጽ ወደ ሰሙበት መሯሯጥ ጀመሩ፡፡ ይሄኔ ነው ብዙ ጓደኞቼ መውደቅም፣ ከገድል ላይ መንከባልልም፣ መቁሰልም እንደተጠበቀ አደጋ ሁሉ የገጠማቸው፡፡ በደረሰባቸው ጉዳት ሁሉ ሲጯጯሁና ሲነጫነጩ ስሰማ ሆዴ አልቻለም፡፡ በደምብ እየቀረቡኝ መጥተው ” አገኘነው!…” እያሉ ተደስተው አቅፈውኝ እንዲሄዱ ፊሽካውን ደጋግሜ ነፋሁላቸው፡፡ አዎን እተቀመጥኩበት ሲደርሱ በሰላም አገኙኝ፡፡
በደስታ ፈንጥዘው፣ ” አያሆሆ ማታ ነው ድሌ!… ሜካዎ ያጉሮሌ!…” እያሉ እየጨፈሩ ሰፈር አደረሱኝ፡፡ ግዳያቸውንም ለመምህር ሲራክ ጣሉ፡፡ ትንሽ መረጋጋት ከተደረገ፣ የቆሳሰሉትም የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ፤ መምህር ሲራክ የኔ አጠፋፍ ምስጢርና የግዳጅ አወጣጥን ሥነ ስርዓት በዝርዝር አስረዳቸው፡፡ እኔም ስለአጠፋፌና ቆይታዬ ያሳለፍኩትን ገጠመኝ እንዳጫውታቸው ተጠየቅሁ፡፡ ጆሯቸውን ማመን አቃታቸው፡፡ አድናቆታቸውንም ለኔና ለመምህር ሲራክ በእጅጉ ለገሱን፡፡ በእርግጥም መምህር ሲራክ በቦይ እስካውትነት የረዥም ዘመን ልምድ የነበረው ብርቱ ሰው ነበር፡፡ ላካፈለን ልምዱና ለትምህርቱ ሁሉ በእርግጥም ምስጋና የሚበዛበት አልነበረም፡፡
በማግስቴው የወንጪን ሀይቅ በግላጭ ጎበኘነው፡፡ በታንኳ እየቀዘፍንም እንደትልቅ የገንፎ ዋደት አፉን ከፍቶ ከተቀመጠው የወንጪ ሃይቅ መሃል ላይ ጉብ ያለውንም ጥንታዊ ቤተ ክርሰቲያን ጎበኘን፡፡ ይሄ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ በሶስተኛው ቀን ወደ መጣንበት ወደ ወሊሶ ለመመለስ ቡደኑ ይዘጋጅ ዘንድ ጋሼ ሲራክና እኔ ቡደኑን ጠየቅን፡፡ ግን አንድም ሰው ፈቃደኛ አልነበረም፡፡
የቦይ እስካውቱ አባላት ከትናንት በስቲያ ስንምጣ የወጣን የወረድንበትን አድካሚ ጉዞ እያሰቡ ሀሞታቸው ፈሰሰ፡፡ በዚህ በመጣንበት መንገድ በጭራሽ ለመመለስ ፈቃደኞች እንዳልሆኑ አቋማቸውን ገለጹ፡፡ እናም እንዳማራጭ ወደ አምቦ ከተማ ተጉዘን ከዚያም ባዲስ አበባ በኩል ዙረን ወደ ወሊሶ ለመመለስ ቁርጥ ሃሳብ አቀረቡ፡፡ መሪዎቹ በዲሞክራሲያዊው አብላጫ ድምጽ መገዛት እንጂ ምርጫ ስላልነበረን፣ ጉዞ ወደ አምቦ ሆነ፡፡ መቼም መምህራችን ላይ ጭነንበት የነበረው ይህ ያልተጠበቀ ዓይነት አማራጭ ውሳኔና ተመሳሳዩ ሁሉ ቀላል አልነበረም፡፡ በትእግስትና በዘዴ የብዙሃኑን ፍቃድ ሞልቶ አምቦ ከደረስን በኋላ፣ በቀ.ኃ.ሥ. ማእረገ ሕይወት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አረፍን፡፡
አምቦ ስንደርሰ እንደገና መፋጠጥ ሆነ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ብሎም ወደ ወሊሶ ልንሳፈርበት የሚያስችለን ገንዘብ አልነበረንም፡፡ መምህር ሲራክና እኔ እንደገና ፈተና ላይ ወደቅን፡፡ መሳፈሪያ ገንዘብ እንድናፈላልግላቸው ጓደኞቻችን ወጥረው ያዙን፡፡ አንድ ብልሃት አገኘን… የማታ ማታ፡፡ የማእረገ ሕይወት 2ኛ ደረጃንና የአምቦ እርሻ ኮሌጅ መምህራንን እርዳታ መጠየቅ፡፡ አዎን ሠራ፡፡ የሚቻላቸውን ረድተውን ተሳፍረን ሄድን፡፡
የቦይ እስካውት ሕይወት እንዲህ እንዲህ የመሳሰሉ ወጣ ውረዶች ቢኖሩበትም፣ ብዙ ደስታና እውቀትም የሚሸመትበት ነበር፡፡ ላገርና ለወገን ተቆርቋሪነት፣ ወንድማማችነት፣ የጨዋ ዜግነት ባሕሪይ ባለቤትነትና ብዙ ብዙ ደጋግ እሴቶች ከቦይ እስካውትነት ሕይወት
ይመነጫል፡፡ የድንቁ ኢትዮጵያዊ አትሌት የሻምበል አበበ ቢቂላ ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካንን ቦይ እስካውትን ባገራችን በማስፋፋት ረገድ ከሚጠቀሱት ስመ ጥሮች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
የዚያን ዘመኑ የጃን ሜዳው የጃምቡሬ ሰልፈኛው ትዝታ ለትናንት ትናንትናው ልጆች ሁሉ ልዩ ቃና ነበረው፡፡ በዘመነ ደርግ የቦይ እስካውት እንቅሰቃሴ አልነበረም፡፡ ዛሬስ እንዴት ይሆን?… የሚያውቁ ሀሳባቸውን ቢያካፍሉን መማማሩ ብርታት ያገኛል እላለሁ፡፡
”አስካውት!…”
”ምን ጊዜም ዝግጁ!!!”
ትናንትም ነበረ፣ ዛሬም ይኖራል፣ ወደፊትም….
ablemma@gmail.com
******************************
ማሳሰቢያ: ይህንን ጽሁፍ ካተምነው በኋላ አቶ አበራ ለማ ተጨማሪ ፎቶዎችና መረጃ አክለውበት የላኩትን የስካውት ትዝታቸውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡
Leave a Reply