• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

አዲስ አበባን የተጫናት ፍልሰት

August 11, 2014 08:39 pm by Editor Leave a Comment

ዕቃ የጫኑ ታክሲዎችና ሌሎች መኪናዎች በሚያራግፉባቸው ማቆሚያዎች ሰብሰብ ብለው ሮጠው ዕቃ ማውረድ፣ ከሚጫንበት ስፍራም መጫን የለት ተዕለት ሥራቸው ነው፡፡

አሠሪዎች በተለይም በግንባታው ዘርፍ ያሉት የቀን ሠራተኞችን ከሚወስዱበት መገናኛ፣ ሃያሁለት፣ መሪ ሳሪስ አየር ጤናና ሌሎችም ሥፍራዎች በጠዋቱ ተሰባስበው መታየታቸው አመሻሽ ላይም በየሃይገሩና ባሱ ተጨናንቀው ወደየማደሪያቸው መጓዛቸውም እንዲሁ፡፡

ታዳጊ አዋቂ ሳይል በየገበያ ስፍራው የሸክም አገልግሎት ለመስጠት የሚሯሯጡትም ጥቂት አይደሉም፡፡ በመልካም አስተዳደር እጦትም ይሁን ከራስ በመነጨ ፍላጐት ትምህርት አቋርጠውና በእርሻውም ሆነ በሌላው የሚያግዙዋቸውን ቤተሰቦቻቸውን ትተው ወደ አዲስ አበባ የሚነጉዱት የየክልሉ ነዋሪዎች ተበራክተዋል፡፡

በዋና ዋና መንገዶች፣ በአደባባዮችና በትራፊክ መብራቶች፣ በእምነት ሥፍራዎች በማሳለጫ መንገዶችና ድልድዮች ከየአካባቢው የፈለሱና ጎዳና የሚያድሩ፣ የሚለምኑ እንዲሁም የንግድና የግንባታ እንቅስቃሴ ባሉባቸው ሥፍራዎች ሰብሰብ ብለው ቆመው ሥራ የሚጠባበቁ ኢትዮጵያውያንን ማየትም የአዲስ አበባ አንዱ ገጽታ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በከተማዋ በተጀመሩ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች የጉልበት ሥራ ለመሥራት እንዲሁም አዲስ አበባ ሥራ ይገኛል፣ የተሻለ መኖር ይቻላል በማለት ከየክልሉ የሚፈልሱ ዜጐች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበም መጥቷል፡፡ ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ ከሚፈልሱት በተለይ በመሥራት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ታዳጊዎችና ወጣቶች በአዲስ አበባ በግልም ይሁን በመንግሥት በሚሠሩ የግንባታ መሠረተ ልማቶችን የጉልበት ሥራ በአብዛኛው ሸፍነው የያዙ ናቸው፡፡ በመሠረተ ልማት ዝርጋታው የሚያበረክቱት የጉልበት አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ የከተማዋን የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻልና ለመቀየር፣ ትምህርት ለሁሉም ለማዳረስም ሆነ ጤናው የተጠበቀ ኅብረተሰብ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የራሳቸውን አሉታዊ ጫና ፈጥረዋል፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ ብሎም እስከ አዛውንት ወንድ ሴት ሳይል ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ኢትዮጵያውያን እንደፍላጎታቸው ተንቀሳቅሰው መሥራትና መኖር ሕገመንግሥታዊ መብታቸው ቢሆንም እነሱ የተመኙትን ያህል ከአዲስ አበባ ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡  በአዲስ አበባ  ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡

አቶ መሳፍንት አለባቸው በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቅኝትና አሰሳ ኦፊሰር፣ ፍልሰቱ አዲስ አበባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በምታደርገው እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ይላሉ፡፡

ቀድሞ የነበሩ ተላላፊና በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱና የማይከሰቱ ነገር ግን ኅብረተሰብን በክፉኛ የሚያጠቁ በሽታዎች ፍልሰቱ በሚያስከትለው ያልተመቻቸ ኑሮ ምክንያት ሊባባሱ ይችላሉ፡፡ ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ በሚደረገው ፍልሰት ከንፅህና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ በየቦታው መፀዳዳትና የምግብና መጠጥ መበከል ይኖራል፡፡ በዚህም የሆድ ትላትል፣ የቆዳ ችግሮች፣ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች በቀላሉ ይባባሳሉ፡፡

አቶ መሳፍንት እንደሚሉት ከሁለት ዓመት በፊት በቅማል አማካይነት የሚተላለፍ የትኩሳት ግርሻ በሽታ አዲስ አበባ ውስጥ ተከስቶ ነበር፡፡ ይህ የቀን ሥራ ለመሥራት ወይም ወቅታዊ ሥራ ለመሥራት ከየክልሉ የመጡ ሰዎች ካለባቸው የማደሪያ ችግር አንፃር አንድ ላይ ተሰባስበው በሚያድሩበት ሥፍራ በተፈጠረ ምቹ አጋጣሚ ምክንያት ነበር የተነሳው፡፡ በአብዛኛው የተጐዱትም እነሱው ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት በሁለት ክፍለ ከተሞች የተከሰተውን ወረርሽኝ ቤቶች ተቆጥረው አከራዮች ትምህርት ተሰጥቷቸው ቤቶች እንዲፀዱ መድኃኒቶች እንዲረጩ ተደርጐ በሽታውን መቆጣጠር ተችሏል፡፡ በ2001 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተከተሰው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትም የዚሁ ፍልሰት ጦስ ነው፡፡ ምግብ ወለድ በሽታዎችም በአብዛኛው ከፍልሰት ጋር ተያይዞ በሚኖረው ያልተመቻቸ የአኗኗር ዘይቤ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ከተማው ውስጥ ቋሚው ነዋሪ በሽታን ለማስፋፋት ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ከምግብ፣ ከአየርና ከውኃ መበከል ጋር የተያያዙ በሽታዎች ከሚባባሱበትና ቁጥራቸው ከሚጨምርባቸው ምክንያቶች አንዱ በፍልሰት ምክንያት ሰዎች በሚኖራቸው ንፅህናውን ያልጠበቀ የአመጋገብና የአኗኗር ሥርዓት ነው፡፡

ከተማዋ በቋሚ ነዋሪዎቿና በተለያዩ ግንባታዎች ምክንያት የተጫነባት ብክለት እንዳለ ሆኖ ወደ አዲስ አበባ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈልሱ ሰዎች ለመኖር በሚያደርጉት ግብ ግብ አቅማቸው የፈቀደውን ምግብ የሚያገኙት በየመንገዱና ንፁህ ባልሆነ በግላጭ ሥፍራ መሆኑም በከተማው የነበሩ ሆኖም የተመናመኑ በሽታዎች ቁጥራቸው እንዲጨምርና እንዲባባስ ምክንያት ይሆናል፡፡

እንደ አቶ መሳፍንት አዲስ አበባ ጤና ቢሮም በየሰዓቱና በየቀኑ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች አጠቃላይ ቅኝት ያደርጋል፡፡ በየጤና ማዕከላት ሪፖርት የተደረጉና የተለዩ ሕመሞች ወዲያው ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ በየትኛውም አካባቢ ተመሳሳይ ሆኖ ቁጥሩ የጨመረ ህመም ካለ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል ከጤና ጋር ተያይዞ የሚወጡ በሽታ ነክ ጭምጭምታዎች ሁሉ አይታለፉም፡፡

ፍልሰቱ በጤናው ዘርፍ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ በተጨማሪም በመማር የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው በትምህርት ሰዓት በየከተማዋ ጐዳናዎች ለሚታዩት ታዳጊዎችም ምክንያት ነው፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት በትምህርት ሰዓት ለምን ውጭ ይታያሉ በሚል በ2006 ዓ.ም. ሚያዝያ ላይ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ባደረገው ጥናት ከትምህርት ውጭ ሆነው የተገኙት ታዳጊዎች አብዛኞቹ በተለያየ ምክንያት ከየክልሉ የመጡ መሆናቸውን አሳይቷል፡፡ ዘመድ ሊያስተምር አምጥቷቸው ያላስተማራቸው፣ በቤተሰብ መፍረስ ምክንያት ያቋረጡ፣ ለሥራ ብለው ከክልል የመጡ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ከተማ መጥተው የተበተኑ እንዲሁም ሽመና ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን በሌላ በኩል እንማራለን ብለው መጥተው ያልተሳካላቸው መኖራቸውንም ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ብዙዎቹም ጎዳና ተዳዳሪ ናቸው፡፡ ይህም በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በመማር የዕድሜ ክልል ያሉ ሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት እንዳይቀሩ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት ያስተጓጉላል፣ ያዳክማል፡፡ ክፍተትም እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ትምህርት ለሁሉም በሚል አገሪቷ የጀመረችውን ፕሮግራምም ያሰናክላል፡፡

በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የጥናትና ምርምር ባለሙያ የሆኑት አቶ ኃይሉ ዲንቃ እንደሚሉት በመማር የዕድሜ ክልል ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች አዲስ አበባ ገብተው በመማር ላይ የማይገኙ ሕፃናትና ታዳጊዎች በትምህርቱ ዘርፍ ዕቅድ ከማቀድና ከመፈጸም አንፃር ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው፡፡ ጥናቱም 20,000 የሚጠጉ ሕፃናት ከትምህርት መስተጓጐላቸውን አሳይቷል፡፡

እንደ አቶ ኃይሉ ለታዳጊዎቹ ትምህርት ብቻ ማቅረብ ዋጋ የለውም፡፡ ቤት እናስገባ ቢባልም እገዛ የሚያደርግላቸው የለም፡፡ በመሆኑም መረጃ ተሰብስቦ ተማሪዎችን በመመገብ ሥርዓት አቅፎ ወደ ትምህርት እንዲገቡ ለማስቻል ታቅዷል፡፡ ክፍለ ከተሞችም ሕፃናቱን በትምህርት የሚያካትቱበት ሥርዓት እንዲዘረጉ ለማስቻል ጥናቱ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሆኖም ሌላ ችግር ከፊት አለ፡፡ በጥናቱ የተገኙት ወደ ትምህርት ሲገቡ ሌሎች ከየክልሉ ፈልሰው ይተካሉ፡፡

አዲስ አበባ የተሻለ ኑሮ ይኖርባታል በሚል ከየክልሉ በሚፈልሱ ሰዎች ከሚጨናነቁ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ አንድ ከተማ በሚፈልሱ ሰዎች ስትጨናነቅ፣ በሥራና በትምህርት ሰዓት ነዋሪዎቿ በየቦታው በብዛት ሲታዩ ለወንጀል የመጋለጥ ዕድል ያንኑ ያህል ከፍ ይላል፡፡ በአገርም ሆነ በከተማ ደረጃ ለወንጀል መንስዔ ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹም ሥራ አጥነት፣ ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ከተማ መፍለስና ቋሚ አድራሻ አለመኖር ነው፡፡ ከፍልሰት ጋር በተያያዘ በከተማዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ ፈልሰው በሚመጡ ብቻ ሳይሆን በከተማዋም ነዋሪዎች አነስተኛ የሚባሉ ወንጀሎች ይፈጸማሉ፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ ሰላማዊና ከባድ ወንጀል የማይፈጸምባት ከተማ ናት ይላሉ፡፡

በአጠቃላይ ወንጀልን ከመከላከል ጋር በተያያዘ በ116 ወረዳ በ808 የልማት ቀጣና ላይ ማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ማዕከላት የተቋቋሙ ሲሆን በዚህም እያንዳንዱ ነዋሪን በማሳተፍ ከሌላ ቦታ የመጡ፣ ማንነታቸው የማይታወቅ፣ የአዲስ አበባ አድራሻ የሌላቸው እንዲታወቁና ሕዝቡ ራሱ የመፍትሔ ባለቤት እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡

እንደ ኮማንደር ፋሲካ በማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊሲ ውስጥ ሥራ ያለው፣ ሥራ አጡ፣ ሊስትሮ፣ ቤት ተከራይቶ የሚኖር፣ ሱቅ በደረቴ ሳይቀር እንዲታቀፍ እየተደረገ ነው፡፡ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ቤት አልባውም ጭምር በማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊሲ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

እንደ ኮማንደር ፋሲካ ኮሚሽኑ ወንጀል መከላከል ብቻ ሳይሆን ሥራ የሌላቸው ከጥቃቅንና አነስተኛ ጋር እንዲሠሩ፣ ለሞራል የማይመጥንና ኅብረተሰቡ የማይቀበለውን ሥራ የሚሠሩት ዘርፍ አንዲቀይሩ እየሠራ ነው፡፡ ጐዳና ላይ ያሉትም ቢሆኑ ወደ ልማት እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ከፍልሰት ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ላይ ያለውን የጎዳና ተዳዳሪነት፣ የሥራ አጥነት እንዲሁም ትምህርትን ከማቋረጥና ለጥቃት ከመጋለጥ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም የአዲስ አበባን ገጽታ ለመቀየር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ቢሮ እየሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ከቢሮው የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በ1966 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ከአምስት ሺሕ በላይ ጐዳና ተዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1996 የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትና እናቶችን ለማቋቋም ያዘጋጀው ጽሑፍ በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር 150,000 እንደሚደርስ ከዚህ ውስጥ 100,000 ያህሉ በአዲስ አበባ እንደሚኖሩ አመልክቷል፡፡ ይህም የጐዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር በዓመት በአማካይ ከአምስት ሺሕ በላይ በሆነ ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ አሉታዊ ገጽታን ከማስፈን አልፎ ማኅበራዊ ቀውስን ያስከትላል፡፡ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተሃድሶና ልማት ንዑስ የሥራ ሒደት መሪ አቶ ባህሩ አበበ፤ ከሌላ ክልል ፈልሰውም ሆነ በከተማዋ የሚገኙ ጐዳና ተዳዳሪዎች እንደማንኛውም ሰው የኢኮኖሚው ተጠቃሚ መሆን አለባቸው በሚል እንደየዕድሜያቸውና አቅማቸው አረጋውያን በመጠለያ፣ ሕፃናትን በማሳደጊያ እንዲገቡ፤ መሥራት የሚችሉትን የሥነልቦና ተሃድሶ ትምህርት በመስጠትና ማኅበራዊ ድጋፍ በማድረግ ሥራ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ቢሮው በተለያዩ ጊዜያት አራት ጊዜ ከጎዳና የማንሳት ሥራም ሠርቷል፡፡ በዚህም ከ9,300 ሰዎች በላይ አቋቁመዋል፣ ሥራ አስገብተዋል፡፡ አቶ ባህሩ እንደሚሉት ከእነዚህ ውስጥ 85 በመቶ ያህሉም ከክልል የወጡ ናቸው፡፡

ከከተማ ፍልሰቱ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ላይ ያለውን ችግር በተለያዩ አጋጣሚዎች ለክልሎች ለማመልከት የተሞከረ መሆኑን፣ በቀጣይም ክልሎች ምንጩን እንዲያደርቁ ከየክልሉ የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሲዬሽን ጋር በመተባበርም ከኮብል ስቶን በተጨማሪ በብረታ ብረት፣ በልብስ ስፌት፣ በመኪና አሽከርካሪነትና በተለያዩ አሥር ዘርፎች ለማሠልጠንና ለማሰማራት ሥራው ተጀምሯል፡፡ ለዚህም ከሦስት ሺሕ በላይ ወጣቶች ተመዝግበዋል፡፡

አዲስ አበባ ያላት የቤት አቅርቦት ከነዋሪዎቿ ጋር ፍፁም ሊጣጣም አልቻለም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅጣጫዎችና አሠራሮች እየተቀያየሩ የትራንስፖርቱን ፍሰት ለማብዛትና የተጠቃሚውን ፍላጐት ለመድረስ ጥረት ቢደረግም እስካሁን መፍትሔ አልተገኘም፡፡ የከተማዋን የንፁህ ውኃ ፍላጐት ለማሟላት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ  ባለሥልጣን እየሠራሁ ነው ቢልም ያሉትን ቋሚ ነዋሪዎች በብቃት መድረስ አልቻለም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ ከአምስት ሺሕ በላይ በሆነ ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ ከየክልሉ ወደ ከተማዋ የሚፈልሱትን ዜጐች ታሳቢ ያደረገ የጤና፣ የትምህርት፣ የቤት፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርትና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች መዘርጋትና የተቀናጀ መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባታል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር ጋዜጣ)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Social Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የገዳ ሥርዓት እና የኦሮሞ ገዢ መደብ June 20, 2022 11:34 pm
  • “የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው” ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል June 12, 2022 07:09 pm
  • የሰሜን ምዕራብ ዕዝና የአማራ ልዩ ኃይል ተከዜ ክፍለ ጦር ዕውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው June 12, 2022 06:21 pm
  • ሀገር በቀል ባህላዊ የግጭት አፈታቶችን በተገቢው በመጠቀም ዘላቂ እርቅና ሰላምን ማምጣት ይቻላል June 12, 2022 05:40 pm
  • የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በገረጂና በቀበና ያስገነባቸውን የመኖሪያ አፓርትመንቶች አስመረቀ June 12, 2022 05:35 pm
  • በኦነግ ሸኔ ፈርሶ የነበረውና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀመረ June 10, 2022 09:13 am
  • ጃዋር በዳውድ ኢብሣ ቀይ መስመር ተሰመረለት June 8, 2022 12:59 pm
  • ወልቃይት: ቢመረንም ለመዋጥና ራሳችንን ለመመልከት እንሞክር June 8, 2022 11:53 am
  • እብድ ይሻለዋል እንጂ አይድንም፤ ሐጂ ጃዋር አሁን ለምን ብቅ አለ? June 8, 2022 05:59 am
  • ሕዝብ ድምፅ የነፈጋቸው “ፓርቲዎች” የሽግግር መንግሥት ይቋቋም አሉ June 7, 2022 01:11 am
  • “አድጌ እንደናንተ መሆን እፈልጋለሁ” June 5, 2022 06:58 pm
  • በሳምንት ለ100 ያህል ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ሥራ ጀመረ May 30, 2022 02:20 am
  • የጥቁር አንበሳ ዕጩ መኮንኖች (ካዴቶች) ተመረቁ May 29, 2022 04:01 pm
  • “ኢትዮጵያን መንካት አይቻልም!!” በሚል ቁጭት ነው እየሠራን ያለነው May 29, 2022 01:04 pm
  • “ከሞፈርና ቀንበር ወደ ትራክተር” በሚል መርህ ለአማራ ገበሬዎች የግብርና ሜካናይዜሽን ተሰጠ May 29, 2022 02:02 am
  • ኢትዮ 360 “የወያኔ፣ የጁንታ ሚዲያ ነው” – ባለከዘራው ጄኔራል May 27, 2022 02:51 am
  • “እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ የሚያጣሉን ፖለቲከኞች ናቸው” የአማራ ወዳጃቸውን አደራ ቤት የመለሱ የቅማንት ተወላጅ May 27, 2022 01:40 am
  • ትግራይን አገር እናደርጋለን፤ “በውይይት እና በጦርነት” ሁሉንም ጉዳይ እንቋጫለን – የወንበዴው መሪ ደብረጽዮን May 26, 2022 09:18 am
  • “ሁለቱ የምዕራብ ዕዝ ተዋጊ ዶክተሮች” May 26, 2022 08:19 am
  • ወደ ትህነግ ሊተላለፍ የነበረ አምስት ሚሊዮን ብር ከ20 ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ May 25, 2022 01:57 am
  • የጦርነቱ ስትራቴጂያዊ እውነታዎች May 19, 2022 09:37 am
  • በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም የሚውል የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የዓለም ባንክ May 16, 2022 10:22 am
  • በአዲስ አበባ 1 ሺህ 98 የብሬን እና 2 ሺህ 162 የክላሽ ጥይት ተያዘ May 16, 2022 10:10 am
  • በአዲስ አበባ ከተማ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ከ5 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላርና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች ተያዙ May 16, 2022 09:53 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2022 · Goolgule