• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

“የወደፊቷ ደቡብ አፍሪካ ከማንዴላ ጋር መያያዟን እጠራጠራለሁ” ፕሬዚዳንት መንግሥቱ

December 11, 2013 11:24 pm by Editor 1 Comment

የኔልሰን ማንዴላን ሕልፈት በማስመልከት አውስትራሊያ ከሚገኘው ኤቢኤስ ሬዲዮ የአማርኛ አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ መንግሥቱ ለሬዲዮው በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በእሳቸው በትረ ሥልጣን ወቅት ማንዴላ የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሽልማት ከመጎናፀፈቸውም ባሻገር፣ የአንድ መቶ ሺሕ ዶላር ገንዘብ ተበርክቶለቸዋል፡፡ ይህና ቀሪው ንግግራቸው እንዲህ ቀርቧል፡፡

‹‹ማንዴላና የተወሰኑ ተከታዮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ በስውር መጥተው፣ ወታደራዊ ሥልጠና አግኝተውና እግረ መንገዳቸውን ሞሮኮን ጐብኝተው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን ተገንዝቤያለሁ፡፡

‹‹በዚያን ጊዜ አሜሪካኖች በአማካሪነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበሩ፡፡ እስራኤሎችም ነበሩ፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በመሆኑ የማንዴላን ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘትና ወታደራዊ ሥልጠና በመከታተል እግር በእግር እየተከታተሉ መረጃ ሲሰበስቡ ስለሰነበቱ፣ ሰውየው አገራቸው እንደደረሱ ወዲያውኑ እጃቸው ተይዞ ወህኒ ቤት ገብተዋል፡፡

‹‹በሮቢን ደሴት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ጊዜ ከአንድም፣ ሁለት ሦስት ጊዜ ጆሃንስበርግ ውስጥ ታስረዋል፡፡ የመጨረሻውና ትልቁ ለ27 ዓመት የታሰሩበት ጊዜ ነው፡፡

‹‹እኔ ማንዴላን በስም እንጂ በገጽ አይቼ አላውቅም፡፡ ልጆች ሆነን በምንሰማው ሁሉ ስለአፓርታይድ ያለንን ጥላቻ በተለያየ መልኩ የምንገልጽ ሰዎች ነበርን፡፡ በኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ተለቅቀው በመጀመሪያ ደረጃ ዚምባቡዌ በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ በዚያን ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ በሚካሄድበት ጊዜ እሳቸውም የስብሰባው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ጤናቸው በጣም የተጐሳቆለና ብርድ ቢጤም መትቷቸው ታመው ስለነበር እኛ ዘንድ ከአንድ ሳምንት በላይ አስታምመናል፡፡ ጠና ያለ በሽታ ስለነበር ሐኪሞች ተሰባስበው የሚቻለውን ሕክምና ሁሉ አድርገው አስታምመናል፡፡

‹‹ስለታሪካቸው፣ ስለ ወህኒ ቤቱ፣ ስለሌላውም ሁሉ በሰፊው አነጋግሬያቸው አጫውተውኛል፡፡ በመጨረሻም የጠየቁኝ ነገር ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ ከእስር ቤት እንደወጡ ስለዓለም ወቅታዊ መረጃ ያላቸው ግንዛቤ ውስን ስለነበረ እንዴት ሆኖ ነው ሶቪየት ኅብረት እንዲህ ዓይነት ሥራ የሠራው? ለመሆኑ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ አልተደረገም ወይ? አልተነጋገራችሁም ወይ? በዚህ መልኩ እንዴት ነው አብዮት የተቀለበሰው፣ ወዘተ በማለት እነ ጐርባቾቭ ስለሠሩት ሥራ በመጸጸት፣ የእኔ አገር ለሶሻሊዝም በጣም የተመቻቸች (ፈርታይል) ነች፤ የምናራምደው ይኼንኑ ነው አሉኝ፡፡ አይ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ላይ ከመድረስዎ በፊት እስቲ ጊዜውንና ወቅቱን ይዩት፡፡ እርስዎ ዓለምን የሚያውቁበት ሁኔታ በእስር ቤቱ ምክንያት ምን እንደሚመስል ትንሽ ሰንብተው ይመልከቱና የሚወስዱትን ዕርምጃ ቢያመዛዝኑ ይሻላል፡፡ እኔ የምደግፈውና እናንተም ያነሳችሁት መፈክር ‹አንድ ሰው አንድ ድምፅ› (ዋን ማን፣ ዋን ቮት) ባላችሁት መርህ መሠረት የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ነፃነቱን ያግኝና ከዚያ በኋላ የትኛውን የዕድገት አቅጣጫ እንከተል የሚባለውን ነገር ልታዩት ትችላላችሁ አልኳቸው፡፡ ይህን ያህል ነው የተነጋገርነው፡፡

‹‹በእኛ በኩል ምን የምንረዳው ነገር ካለ ብንላቸው ምንም ነገር የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ ውሳኔ ነው የተፈታሁት፡፡ ነፃነታችንም በዚሁ መልኩ የተገኘ ስለሆነና ሌላ ትግል የሚጠይቅ ባለመሆኑ ምንም ዕርዳታ አያሻኝም አሉ፡፡ እኔ እንኳ ትጥቅ ወይም ሌላ ያስፈልግ ይሆን በሚል ነው የጠየቅኳቸው፡፡ ለሰውየው ትልቅ ክብር ስላለኝ በመሪ ደረጃ ያን ጊዜ ባይሆኑም አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሸኘኋቸው፡፡ የዚያን ጊዜ ኦሊቨር ታምቦ በፅኑ ታሞ ስለነበር እርሱን ስዊድን ሄጄ ልጠይቅና ህንድ ደርሼ ወደ አገሬ እመለሳለሁ አሉኝ፡፡

‹‹መቼም ከእስር ቤት ነው የወጡት፡፡ ምንም ነገር የላቸውም በሚል ግምት አንድ መቶ ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ቼክ ሰጠኋቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የተገናኘነው ዚምባቡዌ ነው፡፡ ዚምባቡዌ በዚያን ጊዜ የገለልተኛ ንቅናቄን ታስተናግድ ስለነበር በዚያን ጊዜ ነው የተገናኘነው፡፡

mengie and madiba‹‹ብዙ ሰዎች ሰውየውን ለማነጋገር ያስቸግሩ ስለነበርና የነበራቸውም ጊዜ በጣም ውስን ስለበር እኔም በዚያ ላይ ተጨምሬ ማስቸገር አልፈለግሁም፡፡ ማንዴላ እንደ ብርቅ ናቸው፡፡ ግማሹ ቀርቦ ለማነጋገር፣ ምን ዓይነት ሰው ነው፣ ምንስ ይመስላል በሚል ብዙዎች መሪዎች ከፍ ያለ ጉጉት ስለነበራቸውና የማነጋገር ጊዜ ስላነሰ፣ እኔ በዚህ ጊዜ ፕሮቶኮሌን ልኬ ሳነጋግራቸው፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ ሰው ናቸው፡፡ እንጃ ምን ያህል እንደሚያነጋግሩዎት አሉኝ፡፡ አይ እንግዲያውስ እግረ መንገዳችንን ስብሰባው ላይ እንዴት ነዎት? ተሻለዎት? ምን አዲስ ነገር አለ? አልኳቸው፡፡ አመሰግናለሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተደረገልኝ ሁሉ በሚል ተለያየን እንጂ የሰፋ ውይይት አላደረግንም፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ እንደሚታወሰው በከፍተኛ ክብርና ሥርዓት በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የኢትዮጵያን የክብር ኰርዶን ነው የሸለምናቸው፡፡ ስለተደረገው ትግልና ስለሳቸው ማንነትም ሰፋ ያለ ንግግር አድርጌያለሁኝ፡፡ በዚያው መሠረት እሳቸውም አንፃራዊ መልስ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያውቋት፣ ኢትዮጵያ ብቸኛ የነፃነት ኰከብ ሆና እንደኖረችና ከልጅነት ጀምሮ ኢትዮጵያን ሲያስቡ፣ እንደተስፋ ሲመለከቱ የኖሩ መሆናቸውን፣ በሒደትም ያዩትና የተገነዘቡት ይኼንኑ መሆኑን የሚገልጽ ታሪካቸውን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ተመልሼ መጥቼ መካከላችሁ ስቆም የሚሰማኝ እንደገና የመወለድ ዓይነት ነው በሚል በጣም ልብ የሚነካ ንግግር አድርገዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ዚምባቡዌ ከመገናኘታችን በቀር አላገኘኋቸውም፡፡ ከፕሬዚዳንትነት ወርደው ሌሎች ሥራውን በሚመሩበት ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን ችግር ይደርስባቸው ስለነበር ኢትዮጵያውያንን አትንኩ፣ አገራቸው ነው፣ ይኑሩ ተንከባከቧቸው ብለው በታቦ ምቤኪ ጊዜ በመናገራቸው ዛሬ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይኼ ነገር በከፍተኛ ደረጃ ይሰማቸዋል፡፡ የሰሞኑም ሐዘን በኢትዮጵያውያን ላይ ልዩ ስሜት እንደሚያሳድርባቸው አልጠራጠርም፡፡ ይኼን ነው የማውቀው፡፡ ሌላው ጽፈዋል፡፡ ‹ረጅሙ ጉዞ› የሚውን መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ እዚያ መጽሐፍ ውስጥ ስለኢትዮጵያ የሚያውቁትን፣ ያዩትንና የተደረገላቸውን ነገር አትተው በአክብሮትና በፍቅር ጽፈዋል፡፡ ይኼንን ነው ስለማንዴላ የማስታውሰው፡፡

በማንዴላ ሕልፈት ምን ተሰማቸው?

እዚህ በደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ የምንገኝ ሰዎች የሰውየውን የጤና ሁኔታ እናውቃለን፡፡ በየጊዜውም እንሰማለን፡፡ መሪዎች ወንድሞቼም ሁሉን ነገር ስለሚያውቁ ይነግሩኛል፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሰውየው ዕድሜያቸው ውስን እንደሆነ ስለምናውቅ፣ ሆስፒታልም ለመጀመሪያ ጊዜ በረጅሙ መቆየታቸው፣ ልባቸው በከፍተኛ ደረጃ መታወኩ ብሎም መናገር እንደተሳናቸውና እንዳይሞቱ ያህል ይጠበቁ ስለበር፣ ነገ ተነገወዲያ ከማለት ባሻገር ስለሰውየው በቂ ግንዛቤ ስለነበር፣ ሕልፈታቸው እንግዳ ወይም ያልተጠበቀ ነገር አልሆነም፡፡ ያዘንነው ቀድም ብሎ ስለሆነ ሞታቸው ለኔ በግሌ ልዩ ሁኔታ አልፈጠረም፡፡

ወደፊት እንዴት ያስታውሷቸዋል?

እኔ እዚህ ቁጭ ብዬ ስለደቡብ አፍሪካ መተንበይ ያስቸግረኛል፡፡ በውጪው ዓለም በብዙ እንደሚነገረው ለረዥም ጊዜ በእስር መማቀቃቸውና ለነፃነት መታገላቸው ብዙ ብዙ የሚደነቅ፣ የሚወደዱበት፣ የሚከበሩበትና ጀግና የሚያሰኛቸው ሥራ ቢኖርም በሌላ በኩል ደግሞ ውስጥ ያሉ የትግል አጋሮቻቸውንና ጓዶቻቸው በአንዳንድ ችግርና ድክመት ምክንያት ደስተኞች አይደሉም፡፡ ተቃዋሚም አላቸው፡፡ ይኼንን የውጭው ዓለም በውል የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ እስር ቤት በነበሩ ጊዜ ረዥምና ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነው እንለቃችኋለን ነፃነታችሁን ታገኛላችሁ፣ አመራርም ላይ ትቀመጣላችሁ፤ ነገር ግን በምንም ዓይነት ሁኔታ ደቡብ አፍሪካን ልትለውጡ አትችሉም፡፡ የነጩን ኅብረተሰብ ሀብት ንብረት ልትነኩ አትችሉም፤ ወይም የጊዜውን ሶሸሊዝም ወይም ማኅበራዊ ሥርዓት የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ በዚህና በዚያ ዓይነት ሁኔታ እንድንኖር ፈቃዳችሁ ከሆነ ነፃነታችሁን ለመስጠት በሚል መንገድ ከውስጥም ከውጭም ከፍተኛ ተፅዕኖ የተደረገባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ወጥተው ያለውን ሥርዓትና ኢኮኖሚ እንዳለ ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ምድር በጥቁር ሕዝብ ላይ ግፍ ተፈጽሞ እንደሆነ ደቡብ አፍሪካን የሚያክል የለም፡፡

መግደል፣ መግረፍ፣ ማሰቃየት፣ ማሰርና ማስራብ ብቻ ሳይሆን ወይም ኢሰብዓዊ የጉልበት ሥራ ማሠራት ብቻ ሳይሆን ጥቁሮች እንዳይራቡ፣ እንዳይወለዱ በየምክንያቱና በጤና ችግር ወደ ሆስፒታል በሚሄዱበት ጊዜ በሚስጥር እንዳይወልዱ እያመከኑ የኖሩ ናቸው የአፓርታይድ አራማጆች፣ ነጮቹ፡፡ ብዙዎቹ ጥቁሮች ለዚህ ያላቸው ጥላቻ ወሰን የለውም፤ መናገር ያቅታል፡፡ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ከእነሱ ጋር መኖር አለበት ወይ? የሀብት ክፍፍሉና የኑሮ ሁኔታም በእንዲህ ዓይነት መልኩ መቀጠል አለበት ወይ? የሚሉ ብዙ ተቃዋሚዎች አሉ፡፡ ማንዴላ የሚታሰቡበትና የሚከበሩበት የ27 ዓመት እስር ብሎም ደግሞ ነፃነት የማምጣቱ ጥረት አሁን ያለችውን ደቡብ አፍሪካ የመፍጠሩ ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የወደፊቷን ደቡብ አፍሪካ በሚመለከት አዲሱ ትውልድ ያለው ዓላማ ከእነማንዴላ የተለየ ነው፡፡ ዛሬ ነፃነት አለ ብለው ብዙዎች አያምኑም፡፡ የነፃነት ሰንደቅ ዓላማ ነው የምናውለበልበው እንጂ ሁሉም ነገር የነጮች በመሆኑ፡፡ ተወላጁ ቦታ የለውም ተብሎ ስለሚታመንና እውነትም ስለሆነ የወደፊቷ ደቡብ አፍሪካ ከማንዴላ ጋር መያያዟን እጠራጠራለሁ፡፡ (ሪፖርተር)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Politics Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. amanuel says

    December 15, 2013 07:54 pm at 7:54 pm

    Its good to know this tanx!
    But how much credible is this!

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm
  • ሃይማኖትን ለተራ የፖለቲካ ሸቀጥ ማዋል ውርደት ነው April 24, 2025 12:43 am
  •  የኬሪያ ኢብራሒም ኑዛዜ “ብትንትናችን ወጥቷል” April 22, 2025 12:08 am
  • ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጠ April 16, 2025 11:44 pm
  • ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው   April 15, 2025 12:32 am
  • “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” አበበ ጢሞ April 11, 2025 12:07 am
  • መለስ (ለገሰ) ዜናዊ – ተዋርዶ ያዋረደን! April 9, 2025 10:28 pm
  • የተከዜ ዘብ: የሉዓላዊነት መጠበቂያ April 8, 2025 11:49 pm
  • አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ April 8, 2025 10:06 pm
  • ሀሰተኛውን የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በጽኑ ተቃወመ፤ እርማትም ጠየቀ April 8, 2025 09:48 pm
  • “ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ነው ጌታቸው ረዳ April 7, 2025 10:22 pm
  • “TPLF’s belief in a strong federal government was always tied to its own dominance in Addis Ababa” April 7, 2025 10:15 pm
  • Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation March 31, 2025 02:36 am
  • የኤሊያስ መሠረትን ፌክ መረጃ ማን ያጋልጥ? February 19, 2025 06:00 pm
  • አዘርባጃን፡ የሻዕቢያን ሸምቀቆ ማጥበቂያ?! February 19, 2025 12:29 am
  • የአሜሪካ ድምፅ/ቪኦኤ ይዘጋ ተባለ  February 12, 2025 03:37 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule