* ግንቦት 20 ሲከበር
* አሸርጋጁ አደባባይ
* የግንቦት 20 ፍሬዎች
ልክ የዛሬ 25 ዓመት … የድሉ እወጃ!
በዚያች ቀን ነፍስ ያወቅን ሁላችንም የምናስታውሳት አዋጅ ተነገረች …”የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባ ሬዲዮ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲል ተቆጣጥሮታል፣ ግንቦት 20፣ 1983 ዓ.ም!”
ግንቦት 20፣ 2008 ዓ.ም ማለዳ …
25 ዓመት የድል ነጻነት ኢዮቤልዩ የድል በአላቸውን የሚያከብሩት የኢህአዴግና ሹማምንትና ደጋፊዎች በአደባባዩ ተገኝተዋል፣ በኢህአዴግ ከፍተኛ ሹማምንት፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ታድመውበታል … ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኋይለ ማርያም ደሳለኝ ድሮ ሀገሬው “ሰው በላ” እያለ ያወግዘው የነበረበትን ቃል ተጠቅመው ዛሬ እሳቸው “ሰው በላ” ያሉት ደርግ የተገረሰሰበትን የግንቦት 20 የኢህአዴግ የኢዩቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ ንግግር እያደረጉ ነው … የ25 ዓመቱ የሰመረ የልማት ትራንስፎርሜሽን ስኬት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተዘረዘረ ነው፣ በንግግራቸው ባይመስጥም በ25 ዓመታት ተደረጉ ያሏቸው እድገቶች፣ ልማቶች፣ የተፈጥሮ አደጋ ጋር የተደረገው ፈታኝ ግብግብ፣ ዲሞክራሲያዊ መንግስት፣ የመልካም አስተዳደር ግንባታ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማጥፋት እየተደረገ ስላለው ትግል ዘራዘሩ … እንዲህ የሚሏት ሀገር ሀገሬ ስለመሆኗ ተጠራጠርኩ፣ የሆነው እውነት ከሆነ መልካም ነው ስል በትዝብት አንገቴን ደፋ አድርጌ ቆዘምኩ …
ከ25 ዓመቱን የኢህአዴግ አገዛዝ 4 ያህሉን አመታት ብቻ በሀገር ቤት ሆኘ የማውቅ፣ ከ20 ዓመት በላይ በሳውዲ ስደት የከተምኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ! 25 ዓመቱን አገዛዝ፣ ኢትዮጵያውያንን እንደ መረጃ ተቀባይና አቀባይ ማሰብ በራሱ ያማል … እናም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያሉት እድገት እያለ ዛሬ ድረስ፣ ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ መልካም አስተዳደርና ፖለቲካው ገፍቶት ከሀገር የሚሰደደው ዜጋ እልፍ አእላፍ እየሆነ በመጣበት የታሪክ አጋጣሚ የጠቅላያችን ንግግር አልገባኝ አለ! የእድገት ትሩፋቱ ተጠቃሚዎች ከመላው ሀገሬ ምን ያህሉ ናቸው? በ25 ዓመቱ አገዛዝ መብታችን ይከበር ባሉ የተረገጡት፣ በጻፉና በተናገሩ ወጣትነታቸውን እድሜ የተቀሙ፣ ለአመታት ለእስር የተዳረጉ፣ በህገ መንግስቱ የተሰጠው መብት ይከበር ባሉ ወህኒ የወረዱ … እኒህኞቹስ? አልኩ … አዎ በአሉ የእነሱ ሊሆን አይችልም! ድፍን 20 ዓመት በአረብ ሀገር ስደት የተጎሳቆሉት፣ አሁን ድረስ የመብት አስከባሪ አጥተው ለሚንገላቱት “በአሉ በአላችን አይሆንም!” ቢሉ አልፈርድባቸውም፣ በአንጻሩ “በ25 ዓመቱ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ተጠቅመናል” ያሉ ሰንጋ አርደው በዓሉን ቢያከብሩት አይደንቀኝም፣ ተጠቅመዋልና! ለእኔ ቁም ነገሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብዛኛው ሀገሬ የመጣው ድል አብዛኛው ሀገሬ ተጠቃሚ ነው ወይ? የሚለው ነው! ታዲያ ተጠቃሚ ከሆነ ሰው ሞትን እየተጋፈጠ ለምን ስደትን ይመርጣል? ይህ አልገባኝ ብሏልና ዛሬም አጠይቃለሁ!
አሸርጋጁ አደባባይ …
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግን አብቅቶ ትርኢት መታየት ሲጀምር የመስቀል አደባባይ ትዝ አለኝ … አሸርጋጁ አደባባይ ያልኩትን የመስቀል አደባባይ “ይህ የተረገመ አደባባይ!” አልኩት በልቤ … መንግስት በሄደ በመጣ ቁጥር ሰው ተመርጦ፣ በደቦ ተጠርቶ፣ ይሰበሰብበታል፣ ሰው ተመርጦ ” … ይህን መፈክር በል፣ ይህን መፈክር ያዝ … በዚህ ሂድ … ” ይባልና እንደ እውነተኛ የህዝብ ስሜት ይነገርበታል … ይህ አደባባይ፣ ሀገሬው በኑሮ ውድነት፣ በፖለቲካው ግለት እየታመሰ መሪዎች የሚመሯት ሀገር እድገቷ የመጠቀ፣ መጻኤ ህይወቷ ብሩህ እንደሆነ የሚደሰኩሩባት አደባባይ በእርግጥም የመቀል አደባባይ መባል አልነበረበትም! ቢያንስ ለሰው ልጅ ድህነት ምልክት የሆነው የመስቀሉ በዓል የሚከበርበት ቦታ ከዘመነ ደርግ እስከ ኢህአዴግ የውሸት ዲስኩር መናገሪያ፣ የውሸት ሰልፍና ሽለላ ማሳያ አደባባይ ባልሆነ በመረጥኩ ስል ከራሴ ጋር ተሟገትኩ …
በአደባባዩ የብሔር ብሔረብ ብዝሃ ህዝብ …ትርኢቱ እንደ ቀጠለ ነው፣ በስደቱ አለም የ 20 ዓመት መብት ማስከበር ክሽፈት ምስክር ነኝና ጠባቂ ባጣው ስደተኛ የሆነው ሁሉ ከፊቴ ድቅን አለ …
ግንቦት 20 ሳስታሰውስ ደግሞ ደርግ ትዝ አለኝ፣ ደርግ ክፉ ነበር፣ እንኳንም ወደቀ! በደርግ ግፍና ጭቆና ተማርራችሁ ስለ እውነተኛ ዲሞክራሲ ደክማችሁ ላለፋችሁ፣ ጭቆናን ተጸይፋችሁ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ስትሉ ከአባገነኑ ደርግ ጋር ለተፋለማችሁ ክብር አለኝ ፣ እንኳን ደርግ ከወደቀበት 25 ዓመት አደረሳችሁ!
… ግን የታገላችሁበት፣ የመጣው ድል ከብዝሃነት እስኪደርስ የሆነው ያኮራል አልልም … ሌላው ቀርቶ ሀገር የተባለውን ያህል ካደገች ለምን ሰው ይሰደዳል? አልኩ፣ እንደሞኝ ነገር ደጋግሜ የጠቅላያችን የዛሬ ንግግር አስታውሸ … ከራሴ ጋር መጃጃሉን ተውኩት፣ ዝግጅቱን መከታተሉንም አቁሜ ራሴን አቀርቅሬ የአረብ ሀገሩ ስደትና የግንቦት 20 ፍሬዎች ስል በማለዳ ወጌን መሞነጫጨር ቀጠልኩ …! የግንቦት 20 ፍሬዎች … ይቀጥላል!
ቸር ያሰማን
ነቢዩ ሲራክ
ግንቦት 20 ቀን 2008 ዓም
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
ሸመልስይማም says
ጨካኙና አረመኔው ህወሀት ኢሀዴግ አባታቸው ሻቢያ ዘሬ Is Is የሚፈፅመውን ዘግነኝ ድርጊት በንፁሀን አትዮጵያን ላይ ፈፅመዉታል የኔ አንዲህ አንደ አሁኑ ቴክኖሎጂ ያልተስፋፋበተ ሰለነበር አለም አላወቃቸዉም ነበር አናም ከነዚ ገንጣይ አስገንጣይ ቡደኖቸ ልማተም ሆነ እድገት የለም