
ለወራት በኦሮሞ ወጣቶች ሲካሄድ የቆየው ለዴሞክራሲ የሚደረገው ህዝባዊ ትግል ሳያቋርጥና እየሰፋም እየሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እየደጋገሙ ሲታገሉለት የቆየው የህዝቦች ወንድማማችነትና የትግል አንድነት ጥያቄም ባለፉት ሳምንታት በአማራውና በኦሮሞ ክልሎች በሚካሄዱት ሰላማዊና ህዝባዊ ትግሎች አማካኝነት ስር እየሰደደ መሆኑን እየታዘብን
ነው፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ በትግሉ ማየልና መስፋት ብርክ የያዛቸው የወያኔ/ ኢህአዴግ መሪዎች ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ለመስጠት የሚሞክሩት አጸፋ በለየለት ጸረ ህዝብ አመጽ መሰማራት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ መልክ ባለፉት ወራት በኦሮሞ ታጋዮች ላይ ያወረዱትና በመቶ የሚቆጠሩ ንጹህ ዜጎችን መግደልና በሽህ የሚቆጠሩ ሌሎችን ለእስር መዳረግ ሳይበቃቸው አሁን ደግሞ በኦሮሞም በአማራም ታጋዮች ላይ ይህንኑ የጥፋት ሂደት እየተከተሉ ይታያሉ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ድርጅታችን ይህንን የአፈና ውርጅብኝ ሙሉ በሙሉ እያወገዘና ለተሰውት ወገኖች ዘመዶችና ወዳጆች መጽናናትን እየተመኘ በእስር በመንገላታት ላይ ካሉት ታጋዮቻችን ጋር አንድነቱን ለመግለጽ ይፈልጋል፡፡
በጎንደርም ሆነ እንደ ባህር ዳር ባሉ ሌሎች ከተሞች የሚካሄዱት የአካባቢውን ህዝብ በሙሉ ያካተቱ ትግሎች ሰላማዊ ከመሆናቸው ባሻገር የወያኔን የከፋፍለህ ገዛ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ በማክሸፍ በኦሮሚያ ከሚካሄደው ህዝባዊ ትግል ጋር አንድነትን እያነጸባረቁ ናቸው፡፡ የጎንደር ሰልፈኞች ‘በኦሮምያ የሚፈሰው የወንድሞቻችን ደም የኛም ደም ነው’sሲሉ በባህር ዳር በተካሄደው ሰልፍ ደግሞ የአቶ በቀለ ገርባን ፎቶግራፍ በመያዝ ‘በቀለ ገርባ መሪያችን ነው’s ‘በቀለ ገርባ አሸባሪ አይደለም’ በሚሉ መፈክሮች አማካኝነት የአማራው ህዝብ ከኦሮሞ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ያለውን ትስስርና የትግል አንድነት በይፋ ሲያስተጋባ ተስተውሏል፡፡ በአምቦ፣ ሻሻመኔ፣ ነቀምቴ ጉደር ወዘተ ደግሞ የኦሮሞ ታጋዮች በበኩላቸው ‘አማራ የኛ ነው’ ‘እነ በቀለ ገርባ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በመላ በሃገሪቱ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ’sወዘተ በሚሉ መፈክሮች የታጀቡ ሰላማዊ ሰልፎች አካሂደዋል፡፡ እያካሄዱም ነው፡፡
በዚህ በጎ ሂደት ክፉኛ የተደናገጡት የወያኔ-ኢህአዴግ መሪዎች ለተፈጠረው አዲስ ሁኔታ በመሞከር ላይ ያሉት አጸፋ ከዚያው ካረጀ ካፈጀ ስትራቴጂያቸው የተለየ ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ መጀመሪያ ነገር በኦሮምያም ሆነ በአማራው ክልል ከግንቦት 97 ወዲህ ባልታያ ሁኔታ ህዝብ ከዳር እስከዳር የሚሳተፍበትን እንቅስቃሴ ‘‘በጥቂት አክራሪና ሽብርተኛ ግለሰቦች’’ የተጠነሰሰ ጸረ ህዝብና ጸረ ህገመንግስት ትግል አድርጎ የሚያቀርብ ግልጽ የሆነ ቅስቀሳ ይታያል፡፡ ከዚህ አንጻር የወልቃይት ጠገዴን ጉዳይ ‘የህዝብ ሳየሆን የጥቂት አመራሮች ችግር ነው’ በማለት ሃይለ ማርያም ደሳለኝ መግለጫ ሲሰጥ እነ ሬድዮ ፋናና ሌሎች የወያኔ አፈ ቀላጤዎች በዚሁ መልክ ንቅናቄውን ህዝቡ ጨርሶ የማይቀበለው የጥቂት አክራሪዎች ሴራ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ የጎንደር ህዝብ በማያሻማ ሁኔታ ‘የሻብያ ተላላኪ እኛ ሳንሆን ወያኔ ነው’s ብሎ በግልጽ ያስቀመጠውን ሃቅ ጨርሶ በመካድ ይህንን ህዝባዊ ትግል የሻብያ ተላላኪዎች ሴራ አድርጎ ለማቅረብ የሚደረገው ከንቱ ሙከራ አገዛዙ ምንኛ ውጥረት ላይ እንደወደቀ የሚያሳይ አካሄድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የወያኔ ኢህአዴግ መሪዎች እስከዛሬ የህዝብን ትግል ለማክሸፍ ይጠቀሙበት የነበረው የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ በዚህ መልክ በህዝቦች ወንድማማችነትና የትግል አንድነት መንፈስ እየከሸፈ መሄዱ ትልቅ ህዝባዊ ድል ቢሆንም ይህ በጎ ሂደት በአማራና ኦሮሞ ህዝቦች የወንድማማችነት መንፈስ መጎልበት ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ የወያኔ መሪዎች ለህልውናቸው አለን የሚሏቸውን ሁለት ሌሎች ከፋፋይ ስትራጂዎቻቸውንም ከማገዝ ይልቅ ለማክሸፍ መስራት ያስፈልጋል፡፡
አንደኛው የከፋፍለህ ግዛ ስትራጂያቸው ዘርፍ ለትግራይ ህዝብ ይህ ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ ተጋድሎ በሱም ህልውና ላያ ያነጣጠረ ሴራ አድርጎ ማቅረብ እንደሆነ ባለፉት አመታት በተደጋጋሚ ያየነው ነው፡፡ በተያያዝነው ትግል ከተቃዋሚዎች ጎራ የሚሰነዘር ማንኛውም ጸረ ትግራይ ህዝብ ልፈፋ ይህንን የወያኔ ስትራቴጂ የሚያግዝ እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ከዚህ ይልቅ ይህ ለዴሞክራሲ የሚደረገው ታሪካዊ ተጋድሎ በምንም አይነት ጸረ ትግራይ ህዝብ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም አንዱ አላማው የትግራይም ህዝብ ከዚህ አፋኝ አመራር ነጻ ወጥቶ በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እሱም ተገቢ ቦታውን ይዞ ከቀሩት ወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላምና በነጻነት የሚኖርበት ህብረተሰብ የመፍጠር አላማ መሆኑን እያበሰሩ በአላሰለሰ ሁኔታ ለትግራይም ህዝብ የትግል አንድነት ጥሪ ማስተላለፍ ያስፈልጋል፡፡
እየሰፈነ በመሄድ ላይ ባለው የህዝቦች ወንድማማችነት መንፈስ ብርክ የያዛቸው የወያኔ/ኢህአዴግ መሪዎች የሚቀራቸው አንድ መውጫ ዘዴ የህዝቡን ትግል በለየለት አመጽና በደም ባህር የማስመጥ ርኩስ ስትራቴጂ እንደሆነ ሰሞኑን በይፋ እያሳዩን ነው፡፡ ይህ እንዲሳካላቸው ደግሞ የማይቀረው አካሄዳቸው ለኢህአዴግ አባላትና ለሰራዊቱም ሆነ ለፖሊሱና ለደህንነቱ ይህንን ህዝባዊ ንቅናቄ በነሱም ህልውና ላይ ያነጣጠረ አድርጎ በማቅረብ እነዚህ ወገኖች በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ስሜት እስከመጨረሻው ከአገዛዙ ጎን ጸንተው እንዲቆሙ መሞከር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን አካሄዳቸውን ለማክሸፍ ደግሞ ባላሰለሰ ቅስቀሳ ህዝባዊው ትግል ከነዚህ ወገኖች ጋር ምንም ጸብ እንደሌለው፣ አላማው ብሄራዊ እርቅ የሰፈነባትና ለእነሱም የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት መሆኑን ለማስጨበጥ መሞከርና በምንም አይነት የወያኔ/ኢህአዴግን መሪዎች ርኩስ ስትራቴጂ ሊያግዙ ከሚችሉ ቅስቀሳዎች መቆጠብ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
እንዲህ አይነቱ አካሄድ ፖሊሱና ሰራዊቱ በደመ ነፍስ ከሚወስዷቸው ጸረ ህዝብ እርምጃዎች እንዲቆጠቡ፣ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎችና አባላት ደግሞ በድርጅታቸው ውስጥ የህንን የጥቂቶች ጸረ ህዝብ ፖለቲካ ለመቃወምና ለማክሸፍ እንዲበራቱና ይህ ካልተሳካላቸው ደግሞ የህንን የጥፋት ድርጅት እየለቀቁ ከህዝቡ ትግል እንዲቀላቀሉ በሩን የሚከፍት አካሄድ በመሆኑ እንደ ትግልችን አንድ የማይናቅ ገጽታ አድርገን መውሰድ ይኖርብናል፡፡
ከዚህ ሁሉ አንጻር ሰሞኑን በሃገራችን የታዩት በጎ ክስተቶች ማንም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ሳይመራቸው ‘ከታች’ ከህዝቡ ከራሱ በፈለቁና በያሉበት ‘ለትግል ተነስ’ የሚሉትን ህዝብ የህልውናም ሆነ የመብትና የማንነት ጥያቄዎች ጠንቅቀው በሚያውቁ በያሉበት የህዝቡን ችግርም ሆነ ህልም በሚጋሩ ዜጎች የሚቀነባበሩ ትግሎች ናቸው፡፡ በዚህ መልክ እየተከሰተ ያለውን በጎ ሂደት ለማገዝና ገፍቶ ለድል እንዲበቃ ለማድረግ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ስብስቦችና ሃገር ወዳድ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ሚና ከሁለት አንጻር መጠቆም ይቻላል፡፡
አንደኛ በሰሞኑ ትግል ለተፈጠረው አዲስ ሁኔታ በሚመጥን መልክ ህዝባችን የቀደደውን ፈር በመከተል በውስጥም በውጭም ሃገር ወዳድና ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ሃይሎች የወያኔን መሪዎች ቅስም የሰበረውን የህዝቦች ወንድማማችነት መንፈስ ለማገዝና ለማጎልበት በይፋ በአንድነት ቆመው ትግሉን ሲደግፉ መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በውጭ በብሄርና በህብረ በብሄር ደረጃ የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች ስብስቦች የህዝቡን ትግል በመደገፍ ብቻ ሳይሆን በመካሄድ ላይ ያለውን አፈናና ግድያ በመቃወም የጋራ ሰላማዊ ሰልፎች ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሲደረግ ደግሞ በተቃዋሚው ጎራ አንዳንዶች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በሚነዟቸው ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩና ብሎም የወያኔ መሪዎችን የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ በሚያግዙ ቅስቀሳዎች ሲሰማሩ እነዚህን አፍራሽ አካሄዶች በግልጽና በጋራ አውግዞ መውጣት ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛ ሁሉም የሚንቀሳቀስባቸው የህልውና፣ የማንነትም ሆኑ የመብት ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙት የስርአት ለውጥ ተደርጎ ዴሞክራሲና ተጠያቂነት የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን ስትሆን ብቻ ስለሆነ የህዝቡ ትግል ወደዚህ አገራዊ ግብ ለመድረስ ስለሚከተለው ቅደም ተከተል ወይም ሮድ ማፕና የሂደቱን መቋጠሪያ በተመለከተ አንድ የጋራ ስትራቴጂ ነድፎ ይህንን በትግል ላይ ላለው ህዝብ ማስጨበጥና አሁን በሚያሳየው ቆራጥነትና ብስለት ለዚህ ዘላቂና የጋራ አጀንዳ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ በአንድ አቅጣጫ እንዲታገል መቀስቀስ ያስፈልጋል፡፡
የህዝቦች ወንድማማችነት ይለምለም!!!
መላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)
ነሃሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም.
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply