ባለፈው ጽሑፌ ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ፤ ከልቤ ያማምንበትን በጥቅሉ አስፍሬ ነበር። በዚያ፤ ኢትዮጵያዊያንን መውደድ ማለት፤ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ መላ የኑሮ ሁኔታቸውን ጨምሮ ማለት ነው። ሀገራችንን ኢትዮጵያን ማፍቀር ደግሞ፤ ዳር ደንበሯ፣ የተፈጥሮ ሀብቷ፣ ወንዞችና ተራሮቿ፣ ደጋ፣ ወይነደጋና ቆላ ምድሯ፣ አራዊቷ፣ የሚለዋወጡ አራቱ የሀገራችን አየር ጠባይ ወቅቶችን ማለት ነው። ሀገር ያለ መንግሥት ችግር ነው። መንግሥት ደግሞ በዚህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን፤ በሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ኃላፊነቱ ተሠጥቶት የሚያስተዳደር ሀገራዊ ተቋም ነው። በዚህ ሂደት መንግሥት፤ ለመረጠው ሕዝብ ተንቆጥቁጦ ሥራውን ያከናውናል። በተገላቢጦሽ ሕዝብ መንግሥቱን ፈርቶ የሚኖርበት ሀገር፤ ለውጥ በሩን እያንኳኳ ነው። የዚህ አስፈላጊ ተቋምና የሕዝቡ ግንኙነት ይህ ነው። እናም ትክክል ሲሆን መደገፍ ሲሣሣት ደግሞ መቃወም፤ የዜጎቹ ግዴታ ነው። ይህን ነበር ያሳየሁ። በዚህ በክፍል ሁለት ደግሞ፤ በተጨባጭ አሁን በኢትዮጵያዊነታችን፤ የወገናችንን እና የሀገራችንን የፖለቲካ ሀቅ በመመርመር፤ ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን ኃላፊነታችን በግልፅ አስቀምጫለሁ። ለማንኛውም ክስተት፤ ፍዘት አይሎ መነቃንቅ እምቢ ሲል፤ ትኩረቱ መዞር ያለበት፤ መሠረታዊ የሆነውን ጉዳይ መፈተሽ ላይ ነው። ለኛ ፍዘት ደግሞ፤ መሠረታዊ ጉዳያችን፤ ያለንበትን ሀቅ መመርመር ነው። ይህን በደንብ መርምሮ የወደፊት ኃላፊነታችንን ማቀዱ፤ የቆምንበትን ማደላደል ይሆናል። የዚህ ምርመራና ኃላፊነት ትኩረቱ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሚያደርሰውን በደል ወይንም ለውድቀቱ ምኞታችንን መዘርዘር ሳይሆን፤ በውጭ ሀገር የምንገኝ የሕዝብ ወገን ኢትዮጵያዊያን (ካሁን በኋላ ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን) ያለንበት ሀቅ፣ የጎደሉን ነገሮችና ማድረግ የሉብን ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የሚለው ላይ ነው።
ያለንበት የፖለቲካ ሀቅ፤
- የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ፤ ከዕለት ዕለት እያሽቆለቆለ ወደ አዘቅት ወርዷል።
- ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን የትግል ድርጅቶች፤ በየግል ጥንካሬያቸው ተተብትበው፤ በአንድ ጎራ አልተሰባሰቡም።
- በውጭና በሀገር ውስጥ ያለን ታጋዮች፤ በድርጅት ያሉም የሌሉም፤ በአንድ የተሳሰርን አይደለንም።
- ሀገር ወዳድ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች፤ ቁጭ ብለው የሚመጣው የማይታወቅበትን ነገ ይጠብቃሉ።
- ግለሰቦች በሚታገሉት ድርጅቶች ላይ ኃላፊነቱን ጥለው ከትግሉ ርቀዋል።
- የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከፍተኛ የአጥቂ ዕቅድ ይዞ፤ በሙሉ ኃይሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር መዋቅሩን አጠንክሮ ዘምቷል፤ የእብሪት ጥቃቱን አስፋፍቷል።
የጎደለን፤
- በኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት አለ? ለሚለው ጥያቄ፤ በአንድነት የተስማማንበት መልስ የለንም።
- ለሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ፤ ምን ዓይነት ትግል መካሄድ አለበት? ለሚለው በአንድነት መልስ አልሠጠንበትም።
- ለትግሉ አንድ ትክክለኛ ኢትዮጵያዊ ማዕከል አላበጀንም።
- ለትግሉ ግልፅ፣ የጠራ ኢትዮጵያዊ ራዕይና ተልዕኮ በአንድነት አላወጣንም።
- የነገ፣ የተነገ ወዲያ፣ የሚቀጥለው ሳምንት፣ የሚቀጥለው ወር፣ የሚቀጥለው ዓመት ዕቅድ የለንም።
- መሪና ተመሪ፣ ታጋይና አታጋይ፣ ተለይቶ አልተቀመጠም።
- አሁን ካለንበት ሰዓት አንስቶ ሕዝባዊ ትግሉ ድል እስከሚያገኝበት ድረስ ላለው ወቅት ዝርዝር እቅድ የለንም።
- ከሕዝባዊ ድሉ በኋላ ለሚቀጥለው የሽግግር መንግሥት በጥናት የተደገፈ ለሂደቱ የተግባር እቅድ የለንም።
ማድረግ ያለብን፤
እንደ ኢትዮጵያዊያን ተቆርቋሪዎች፤ ታጋይ ምሁራንና የየድርጅቶቹ መሪዎች ልዩ ትኩረት ተሠጥተው፤ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥናቶች አሉ። እነዚህ ጥናቶች እስካሁን ሊደረጉ የሚገባቸው ነገር ግን ያላደረግናቸውን አስመልክቶ ነው። ለምን ማድረግ አልተቻለም? እንቅፋት የሆነው ምንድን ነው? እናስ ማስተካከል የሚገቡን ምንድን ናቸው? የሚሉትን መመለስ ነው። በዝርዝር
- አንድ ኢትዮጵያዊ የትግል ማዕከል ለመፍጠር ለምን አቃተን?
- ውጪሰው ኢትዮጵያዊያንን አነቃቅቶ ለተግባር በአንድነት የሚያነሳሳው ምንድን ነው?
- ውጪሰው ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት በአንድ ድርጅት ለማስተባብር ምንድን ነው ችግሩ?
- ውጪሰው ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ማዋቀርና ለትግል ማሠለፍ እንዴት ይቻላል? የመሳሰሉት ናቸው።
ከዚህ በተረፈ ግን፤ በትግሉ አኳያ በተጨባጭ ልናከናውናቸው የሚገቡ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው።
- አንድ ኢትዮጵያዊ የትግል ማዕከል ማበጀት።
- አጀንዳውን ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነጥቀን በመጨበጥ፤ እኛ አሽከርካሪ ነጂዎች መሆን።
- ሥራዬ ብለው ድርጅቶችን የሚያነጋግሩና ግለሰቦችን የሚያሰባስቡ ባለሙያተኞችን ማሠማራት።
- የትግሉን ምንነት አጥርተን በማውጣት፤ አብዛኛውን ውጪሰው ኢትዮጵያዊያ ባንድነት አካቶ፤ የኔ ብለው የሚቆሙለት ንቅናቄ፣ ሀገራዊ ራዕይና ተልዕኮዎችን ማዘጋጀት።
የኛ ቆራጥነትና ተግባራዊ ተልዕኮ በጃችን አለ። ያንን ይዘን ወደፊት የምንሄድ ከሆነ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሕልውና አጭር ነው። በአፍ ድንፋታችንና በማስፈራራታችን ልናገኘው የምንችለው ነገር ቢኖር፤ ላንቃችንን ማድረቅ ብቻ ነው። እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩት የማይታወቁ አዲስ ሃሳቦች አይደሉም። ከማንም ኢትዮጵያዊ የተሰወሩ አልነበሩም። ለተግባሩ ታታሪ ሆነው የሚጥሩና ከድርጅታቸው በላይ ሀገራቸውን ያስቀደሙ በማነሳቸው ነው። እናም እኒህን ጉዳዮች በደረጃ በደረጃ ማከናወን ይገባናል።
የመጀመሪያው ድረጃ፤ ( ፩ኛ )
- ትኩረቱ ውጪሰው ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ሁሉአቀፍ ሠፊ የኢትዮጵያዊያን ንቅናቄ ለማሰባሰብ ነው። እናም
- መድረኮችን በየቦታው እያዘጋጁ ውይይቶችን ማካሄድ
- ድረገፆች በተወሰኑ ርዕሶች አጥጋቢና ትምህርታዊ ጽሑፎችን እንዲያወጡ መጠቀም
- የፓልቶክ ክፍሎች፤ ተከታታይና ቀጣይነት ያላቸው የሀገር ጉዳዮችን እያነሱ እንዲወያዩባቸው ማቀድ
- የሬዲዮ ጣቢያ ትልልፎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ማበረታት
- በየከተማዎች ትንንሽ ከበቦችን መሥርቶ ቀጣይነት ባለው መንገድ ውይይቶችን ማካሄድ
- የስልክ ስብሰባዎችን በማድረግ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብዙዎች እንዲሳተፉ ማድረግ
መካከለኛው ደረጃ ( ፪ኛ )
- ትኩረቱ አንድ ኢትዮጵያዊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለመመሥረትና በመዋቅር ለመተሳሰር ነው። እናም
- ግልፅ የሆነ ኢትዮጵያዊ ራዕይ ማስፈር፤ በትክክል የሠፈረ ኢትዮጵያዊ ተልዕኮ መንደፍ
- በየወቅቱ ተግባራዊ የሚሆኑ የእንቅስቃሴ ዕቅዶችን በዝርዝር ማስቀመጥ
- ይኼኑ ተግባራዊ የሚያደርጉ ሙያቸው ሆኖ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን መመደብ
- በከተማ፣ በሀገር፤ በአህጉር መዋቅር መዘርጋትና የሰላማዊ እንቅስቃሴ አራማጆችን አሠልጥኖ ማሠማራት
የመጨረሻው ደረጃ ( ፫ኛ )
- ይህ ሰላማዊ ትግሉን በቀጥታ እስከስኬቱ ድረስ ማራመጃ ነው። እናም በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ
- በየቦታው ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች አብሮ አንግቦ በቦታው በመገኘት መሳተፍ
- እንዳስፈላጊነቱ ሰላማዊ ሰልፎችን ከሕዝቡ ጋር ተባብሮ መሳተፍና ማበረታታት
- የሥራ ማቆም አድማዎችን፤ የልጎማ ተግባሮችን መምራት
- መዋቅሮችን በየቦታው ማስፋፋት፤ እኒህ መተሳስሮች የትግሉ አውታር ስለሆኑ በትክክል ማካሄድ
- ማንኛውም ጥረት መደረግ ያለበት፤ ለዚህና ለዚህ ጉዳይ ብቻ ነው።
ማሣረጊያ
በያዝነው ሂደት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት አይወድቅም። በያዝነው ሂደት ሕዝቡ የሚመርጠው ኢትዮጵያዊ መንግሥት አይቋቋምም። ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ለሀገር አድኑ ንቅናቄ የሚያስፈልገን አንድ ሀገራዊ ሕዝባዊ ንቅናቄ መስርተን፤ የትግል ማዕከሉን በአንድነታችን በማጠናከር፤ ለወገናችን ትግል መድረስ ነው። መሰባሰቢያ የትግል ዕሴቶቻችን፤
፩. የኢትዮጵያዊያንን ሉዓላዊነትንና የትግሉ ባለቤትነት መቀበል፤
፪. የኢትዮጵያን አንድ ሀገርነትና አንድ ብሔርነት ማረጋገጥ፤
፫. በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትና ማስፈን፤
፬. የያንዳንዱ/ዷ ኢትዮጵያዊ/ት ዴሞክራሲያ መብት ማስከበር ናቸው።
Leave a Reply