በዛሬው ርዕስ ሥር የማነሳው ጉዳይ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቅርምትን ይመለከታል። በርግጥ ይህን ርዕሰ ጉዳይ በቅርቡ ከተቋቋመው የ EDF (Ethiopian Dialogue Forum) ድርጅት ዓባላት ጋር በነበረን ቴሌ ኮንፈረስ ላይ ለውይይት አቅርቤው ነበር። ዛሬ ደግሞ በቀለም ቀንድ ጋዜጣ በኩል ከሃገር ቤት ወገኖቼ ጋር ለውይይት ይሆነን ዘንድ መረጥኩት።
እንግዲህ በዓለም ላይ እጅግ ብዙዎቹ አገራት ወይ በባህል ወይም ደግሞ በሃይማኖት ብዙሃን ሆነው አንድ አገር መስርተው ይኖራሉ። አንዳንዶቹ ሃገራት እጅግ ብዙ ቋንቋና ባህል ያላቸው ቡድኖችን ይዘው በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ውስጥ ይኖራሉ። ለምሳሌ ናይጀሪያ ወደ 250 ብሄሮችን ይዛ እነዚህ ብሄሮች በአንድ ፌደራል ሪፐብሊክ ናይጀሪያ የፖለቲካ ጠገግ ስር ተጠልለው ይኖራሉ። ኢንዶኔሽያን የመሰረቱ ቡድኖች ደግሞ ወደ 300 ቡድን ናቸው። በርግጥ በዓለም ላይ ካሉ ብዙህ ሃገራት መካከል በጣም ብዙህ (Diverse) የሆኑት አገራት ቅድስት ምድር እስራዔልና የተባበረችው አሜሪካ ናቸው። በዓለም ላይ ነጠላ ወይም ሆሞጂኒየስ የሚባሉ አገሮች በጣም ውሱን ሲሆኑ ከአፍሪካ እንደ ቱኒዚያ አይነት ኣገሮችን ማለት ነው።
ታዲያ እነዚህ ብዙህ የሆኑ አገሮች የተለያየ ቋንቋና ባህል፣ ወይም ጎሳ፣ ወይም ሃይማኖት ይዘው አንድ አገር መስርተው የሚኖሩት አንዳንዶቹ በጦርነትና በተለያየ ሃይል ተገፍተው ዛሬ ራሳቸውን በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ስር ያገኙ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ምን አልባት አብረን ብንኖር ይሻላል በሚል ቡድኖች ተነጋግረው አንድ ሃገር መስርተው ይሆናል። ብቻ ግን እነዚህ አገራት በአሁኑ ጊዜ ዝንባሌያቸው በባለፈው ታሪካቸው ላይ ሳይሆን ቀጣዩን ህይወታቸውን እያዩ አገራቸውን አጠናክረው የሚኖሩበትን የፖለቲካ ጠገግ በሚገባ እያነጹ መኖር ላይ ነው። እነዚህ ብዙሃን አገራት አንድ አገር የሚሉትን ሰፊ አዳራሽ ሲመሰርቱ በመስዋእትነት ነው። አገርን የሚያህል ግዙፍ ነገር ዝም ብሎ ከንፋስ አይፈጠርም። መስዋእትነትን ይጠይቃል። መስዋእትነቱ ምንድን ነው? ካልን ቡድኖች ካላቸው ሃብትና እሴቶች ላይ የሆነውን ለዚህ አዲስ ለሚፈጥሩት አገር ለሚሉት ጠገግ መስዋእት ሲያደርጉ ነው። መቼም ይህ የጋራ ቤት ዝም ብሎ አይሰራም ብለናል። ይህ አዳራሽ ሲሰራ ቡድኖችን የሚጠይቀው ነገር አለ። በመሆኑም ቡድኖች ጎራ እየከለሉ ይኖሩበት የነበረውን መሬታቸውን እንዲሁም ደግሞ ፖለቲካዊ ማንነታቸውን ይሰውና አንድ አገር አለን ይላሉ። ቋንቋዎቻቸውንና ባህላቸውን ደግሞ በየመኖሪያቸው ይዘው እያሳደጉ ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ብዙ ብሄሮች በተለይ መሬታቸውንና ፖለቲካዊ ማንነታቸወን አደባልቀው አንድ ካርታ ከሰሩ በሁዋላ አንድነት የሚለውን ብሄራዊ ማንነት የሚባለውን ገነቡ ማለት ነው። በመሆኑም ብዙ ሆነው አንድ ነን ሲሉ በባህል የተለያየን ብንሆንም አደባልቀን መስዋዕት አድርገን የፈጠርነው ሌላ ብሄራዊ ማንነት አለንና ያ ነው አንድ ነን የሚያሰኘን ማለታቸው ነው። ቢያንስ ያደባለቁት መሬትና ፖለቲካዊ ስብእና ነው አንድነትን የሰራላቸው። በልዩነት አንድነት የሚባለውም ይህ መሆኑ ነው መሰለኝ። ግዛትንና ፖለቲካዊ ማንነትን በአንድ ገበታ ላይ ዘርግፈው አደባልቀው የእኔ…. የእኔ….. ቀርቶ የእኛ ሆኗልና ነው።
ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት አገር ናት። ይህቺ አገር እንደ ዓለም ወግ የተለያዩ ብሄሮች ሲመሰርቷት ግማሹ በቀላሉ ግማሹ በጦርነት የተሰባሰቡባት አገር ስትሆን በቁጥር ከሰማኒያ ሁለት በላይ ብሄሮች አሏት። እነዚህ ቡድኖች በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ውስጥ ሲኖሩ ሲኖሩ ቆዩ። ልክ ሌላው ዓለም እንዳለፈበት የህይወት ጎዳና የኢትዮጵያ ቡድኖችም አልፈው ሲያበቁ ሁዋላ በዘመናዊ ታሪካቸው ጊዜ ዘመናዊ አስተዳደር ሲመሰርቱ ቡድኖች ያላቸውን እዋጥተው አንድ ነን የሚለውን በተሻለ መረዳት ተቀብለውት ኖረዋል። ያለፈው ታሪካቸው ባይመች፣ የጋራ ታሪካቸው ብዙ ውጣ ውረድ ቢኖረውም በዚህች ዛሬ ራሳቸውን ባገኙባት አገር ግን ቂም የላቸውም በውነት። ይሁን እንጂ ድንገት አንድ ትውልድ ተነሳ። ይህ ትውልድ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው ያለስምምነት ስለሆነ፣ ቡድኖች ሳይጠየቁና “ዴሞክራሲያዊ” በሆነ መንገድ ያላችሁን ለኢትዮጵያ ማዋጣትና መስዋእት ማድረግ ትፈልጋላችሁ ወይ? ተብሎ ሳይጠየቅ የዛሬ ስንት መቶ ዓመት በሃይል ያለንን እሴት እንድናደባልቅ ስለተደረገ እንደገና እግዜር እንደፈጠረን የብሄር አስተዳደር መስርተን መኖር አለብን እንመለስ አለ። የብሄር ፖለቲካ የመጨረሻ ግብ ምን እንደሆነ የማይታወቅ ቢሆንም በጫና ሰማኒያ በላይ የሆኑ ብሄሮች በዘጠኝ ተከፈሉ። ይህቺ ኢትዮጵያ ስትፈጠር ዘጠኝ ናት ያለ የለም። ብቻ መንግስት እንዳሻው በዘጠኝ ሸነሸነና በዞንና በልዩ ወረዳ የብሄር ፌደራሊዝምን እውን ለማድረግ ተነሳ:: በዚህ መሰረት በ 1983 ዓ.ም አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ስልጣኑን ከያዘ በሁዋላ ኢትዮጵያ በብሄር ፌደራሊዝም የምትተዳደር አገር ሆና ታወጀባት።
ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ተፈጠረ? ስንል ሃገር የሚፈጥሩትን ዋና ዋና ጉዳዮች ብሄሮች እንዲቀራመቱ ተደረገ። ሃገር የሚባለውን ነገር የሚያቆሙት ካስማዎች እንደ ግዛት፣ ኔሽን፣ ፖለቲካዊ ማንነት፣ ታሪክ፣ የጋራ መግባቢያ እነዚህን ካስማዎች እየነቃቀልን በሙሉ በብሄሮች ዙሪያ ተከልን። በዚህም ኢትዮጵያን የመቀራመት ስራ በመደረጉ አንድነት የሚለው ጉዳይ ሜዳ ላይ ወደቀብን። ኢትዮጵያ አጨብጭቦ ባዶ እጆቿን ቀረች። ሃገር የሚመሰርተውን ኤለመንት ሁሉ ብሄሮች ሙልጭ አድርገው ወስዱ። እንደ ቅርጫ ስጋ ታሪክን፣ ግዛትን፣ እሴቶችን፣ ፖለቲካዊ ማንነትን፣ ሁሉ ተቃረጥን። ብሄሮችን ስስታም የሚያሰኝ ይህ የብሄር ፖለቲካ የወለደው አስተዳደር ሲመጣ ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ መስዋእት ኣድርገነው የነበረውን የመሬት አንድነትና ፖለቲካዊ ማንነት እየዘረፍን በየብሄራችን ውሰዱ ተባልን። በየብሄራችን የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመን ቁጭ አልን። ተፈርዶብን እንጂ ወደን አይደለም።
መሬታችንን ቋንቋዎቻችንን እየተከተልን ኮለኮልንና ከዚህ ወዲያ የእኔ ነው አልን። እኛ ራሳችን ኔሽን ነን አልን። ባንዲራዎች ሰራን። እነዚህን ሁሉ ተቀራመትንና የቀረንን ስናስብ ታሪክ ነው። የብሄር ፖለቲካው መሃንዲስ አቶ መለስ ዜናዊ የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው? በማለት የታሪክ ቅርምቱን በይፋ ገለጹ:: በሌላ አነጋገር ይሄ ሃውልት እኔ የመጣሁበት ብሄር ሲሆን ሌሎቻችሁ በየሰፈራችሁ የሚገኝ ቅርሳቅርስ ካለ ተቀራመቱ፣ ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ ነው የሚባል ነገር የለም እንደ ማለት ነው። እናም የታሪክ ቅርምት ጀምረንና ኢትዮጵያን ለመቀራመት እነሆ ተነሳን። የአሁኗ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት የት እንደገባ የጠፋብን ሚስጥሩ ለብሄራዊ ማንነት የተሰውትን መስዋእቶች መልሰን እንድንዘርፍ ስለተገደድንና ስለተቀራመትን ነው:: በዚህም ብሄራዊ ማንነት ከቦታው የጠፋብን።
ብሄራዊ ማንነት የጋራ ነገር ይሻል። ብሄራዊ ማንነት ህልው የሚኖረው ቡድኖች ጨክነውም በቸርነትም በሚሰዋቸው እሴቶች የሚገነባ ማንነት ሲሆን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ብሄራዊ ማንነት አለኝ ለማለት ያስቸግራታል። በርግጥ ህዝቡ ቃኪዳኑን በልቡ ይዟል። ከማተቡ ጋር ኣስሮ ቀን ይጠብቃል። ይሁን እንጂ ኦፊሺያሊ ብሄራዊ ማንነትና ኢትዮጵያዊነት ከነ ሙሉ ስልጣናቸው የሉም። በግልጽ ቡድኖች የተቀራመቷት አገር እንድትሆን መንግስት ስለፈረደባት እነሆ ዛሬ ኢትዮጵያ ይህ ቅርምት የተፈጸመባት አሳዛኝ አገር ናት። ያቺ ታላቅ አገር ኢትዮጵያ…….
አንድ እንደገና መሰመር ያለበት ጉዳይ ግን ይህ ቅርምት የኢትዮጵያን ቡድኖች ስነ-ልቡና በፍጹም አይወክልም። እኔ እራሴ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አየሁ….. ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቸሮች ናቸው። ደቡብ ውስጥ በቋንቋ የማንግባባ ሰዎች ቤት አምሽቼ ጠብ እርግፍ እያሉ አስተናገዱኝ። የቤቱ አባወራ ከመሃል አገር የመጣሁ መሆኔን ሲያውቁ ስለኢትዮጵያ ስለሃገራችን ታሪክ ሊያስረዱኝ ሞከሩ። ቋንቋ የሚገዛ ቢሆን ያን ቀን የኝህን ሰው ቋንቋ ገዝቼ ማዳመጥ በቻልኩ ኣስብሎኛል። ትንሽ ትንሽ እኔ የምናገረውን ቋንቋ በሚሞክረው ልጃቸው በኩል የሚነግሩኝ አንድነታችንን የኢትዮጵያውያንን ፍቅር ነበር። የኢትዮጵያዊነታችንን ወዙን ኣሳዮኝ። ድሬ ተጉዤ ከቤቴ ያልወጣሁ መስሎ ተሰማኝ። ብዙ ውየ ባድር እየተመኘሁ ተመለስኩ። ናዝሬትን ሳይ፣ ደሴን ሳይ፣ ወዘተ… ኢትዮጵያውያን የማይናወጥ የአንድነት የፍቅር መንፈስ እንደገዛቸው ተሰማኝ። የኢትዮጵያ ብሄሮች ቸሮች፣ እንግዳ ተቀባዮች፣ በአንድ ገበታ የሚበሉ ናቸው። ያላቸውን ለማዋጣት እምቢ ማለት የሚያሳፍራቸውና የማይወዱ ናቸው። እውቀታቸውን ቢሆን፣ ጥበባቸውን ቢሆን፣ መሬት ቢሆን፣ ቁሳዊ ቢሆን መንፈሳዊ ባህል ለሃገራቸው ለኢትዮጵያ ሰውቶ መልሶ ለመንከባከብ በጥብቅ የሚፈልጉ ናቸው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህን የህዝቡን ስነ-ልቡናና ባህል መሰረት ማድረግ አለበት። ይሁን እንጂ በተጽእኖ የተጫነባቸው የብሄር ፖላቲካ የሚወዷትን አገራቸውን እንዲቀራመቱ በማድረጉ ሃገራቸው ውስጣዊ ሉዓላዊነቷ ተሰነጣጠቀ።
መንግስት በዴሞክራሲ ዘመን፣ በግሎባላይዜሽን ዘመን፣ የሰባዊ መብት ጉዳይ በጣም ትኩረት ባገኘበት ዘመን አዲስ ነገር ተገልጦልኛልና ሁላችን በየቀያችን እንስፈር ሲልና የጋራ የማህበር ቋንቋ እንኳን ሲያሳጣን የተጎዳችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ኢትዮጵያዊነትም ወዙን አጣ። ለአንድ እናት ልጆች መግባቢያ ቋንቋ እንኳን የማይገደው መንግስት ገጠመን። የቋንቋ ሃብታሞች ሆነን የፍክክር ቤት እንደሚባለው አንድ የማህበር ቋንቋ እንኳን አጣን።
በዚህ ቅርምት ምክንያት ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሉዓላዊነቷ አደጋ ላይ ወድቆብናል። አንድ አገር ሉዓላዊ ነው የሚባለው በውስጡ የሚኖሩ ቡድኖች ቢያንስ በመሬት አንድነትና በፖለቲካ ማንነት ኣንድ ሲሆኑ ወይም ፖለቲካቸው በዚያ ባደባለቁት መሬት ካርታ ስር በአንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ሲቆም ነው። ኢትዮጵያ በቡድኖቿ ከፍተኛ ቅርምት የተካሄደባት አገር በመሆኗ ያለ ጥርጥር ውስጣዊ ሉዓላዊነቷ ተደፍሯልና ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያውያን ካሏቸው ልዩነቶች ሁሉ በላይ ጉልህ ጉዳይ ገጥሟቸዋል።
አንቀጽ 39 በራሱ የሚያሳየው ይህቺ አገር ቡድኖች በስስት የያዙትን ብጥስጣሽ መሬት ይዘው በፈለጉት ጊዜ ሽርፍ እያሉ መሄድ እንደሚችሉ ነው። ይህ ማለት ይህቺ አገር ሉዓላዊነቷ ዘላለማዊ ያልሆነ በየትኛውም ጊዜ እየተሸረፈች ልታልቅ የምትችል ተደርጋ የተፈረደባት ሆናለች ማለት ነው። ቡድኖች ያላቸውን እሴት ሁሉ በራሳቸው ስም አስመዝግበው መቆየታቸው የሚጠቅመው ለዚህ ለመሸረፍ ቀን ምቹ እንደሆነ መሪዎች ሳይሰቀጥጣቸው ኮራ ብለው ይናገራሉ። ይህንን እያነሱም አዲሲቱ ኢትዮጵያ ኣሁን ተራምዳለች ይላሉ። የብሄር ብሄረሰቦች መብት እስከ መገንጠል በሚል መሪ ቃል ዴሞክራሲን እውን ኣደረግን ብለው ያረፉ መሪዎች ያሉን እኛና እኛ ብቻ ነን። ደግሞ የሚያሳዝነው በዚህ በመለየት አንቀጽ ቡድኖች ተዝናንተዋል ይሉናል። ቡድኖች ይህ ኣንቀጽ ዋስትና ስለሆናቸው እፎይ ብለው ተኝተዋል ይሉናል። ይህበ እውነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ስድብ ነው። በባህላችንም ቢሆን እንኳን ኣብሮ የኖረ ሰው ሲለያይ ተላቅሶ መልካም እመኝልሃለሁ ተባብሎ ይሄዳል እንጂ ይሄን ያህል በመለያየት የሚዝናና ብሄር የለንም። ፍልስፍናው ራሱ የሰው ልጆችን ባህርይ አላገናዘበም። ብሄሮች በመገንጠል አንቀጽ የሚዝናኑ ከሆነ ለምን ኣብረው ይኖራሉ? እንዴት ሰው በመለያየት አንቀጽ እየዘለለ አብሮ ይኖራል? በዚህ ደረጃ መለየት ያዝናናቸው ቡድኖች በምን ያህል ፍቅርና መተማመንስ ይኖራሉና ነው እንዲህ የሚሉን?
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመባት ቅርምት በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ፈርክሶ የጣላባት ሲሆን ለጊዜው ግን አገሪቱ በወታደር ተጠርንፋ ትገኛለች። ይህ መንግስት ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ትልቁ ዘፈኑ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የራስን እድል በራስ መወሰን፣ የራስ ቋንቋ፣ ራስ… ራስ…. ራስ….። በመሰረቱ አገር በእኔ….. እኔ….. እኔ….. እኔ….. ኣይቆምም። ኣገር የሚቆመው በእኛ ነው። እኛ ህዝቦች (we the people….) በሚል ነው ኣገር የሚቆመው። ስለዚህ እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ህዝቦች ሁሉ ይህን በመስዋዕትነት የፈጠርነውን አገር እንዳናጣ ይህን እኔ… እኔ….. እኔ…. እናቁምና ወደ “እኛ” ምእራፍ እንሻገር።
ይህ ስስት የጥቂት የፖለቲካ መሪዎች ባህርይ እንጂ የኢትዮጵያ ብሄሮች አይደለም። የኢትዮጵያ ብሄሮች የገጠማቸው ክፉ ችግር ይሄ አይደለም። የኢትዮጵያ ብሄሮች የሚፈልጉት ዴሞክራሲን፣ መልካም ኣስተዳደርን፣ ከድህነት መውጣትን፣ ባህላቸውን መጠበቅን ነው። ስለዚህ ቡድኖች እንደገና ሊትክዙ ይገባ ይመስለኛል። ይህችን የምንወዳትን ኣገር መስዋእት ኣድርገን እንደገና ብሄራዊ ማንነታችንን ልንገነባው ይገባል የሚሉበት ዘመን ነው። ለሂቃኑ ሊቆጡ ሊነቁ የሚገባበት ዘመን ላይ ነን። ከፍ ሲል እንዳልኩት በዓለም ላይ ያሉ ብዙዎቹ ኣገራት የሚኖሩት ቡድኖች እያዋጡ መስዋእት እያደረጉ ነው። ለዓለም ይህ የቅርምት ኣስተዳደር የሚጠቅም ቢሆን ብዙ አገሮች በተከተሉት። ነገር ግን ይህን ጥለው ኣልፈው ሄደዋል። በቡድኖች መካከል ይሁን በግለሰብ ደረጃ የሰባዊ ጥሰት ሲገጥማቸው፣ ኣሰቸጋሪ ኣስተዳደር ሲገጥማቸው ለዴሞራሲና ለመልካም ኣስተዳደር ይጥራሉ እንጂ በቁጣ ሮጠው ኣገራቸውን ኣይቀራመቱም። በቃ ካልሆነ በየቤትህ እደር ብለው ወደ ልዩነት ፖለቲካ ኣይገቡም። በዓለም ዓቀፍ ህግም ቢሆን አገሮች ብሄራዊ ሉዓላዊነታቸውን ይጠብቁ ዘንድ ነው የሚበረታቱት። እንደ ኢትዮጵያ ኣይነት ኣስተዳደር በዓለም ቢሰፍን ዓለምን ሊያፈርሳት ይችላል። እሚገርመው ነገር የዓለም አገራት እንደ ኢትዮጵያ ያለ የብሄር ፖለቲካ የፈጠረውን የብሄር ፌደራሊዝም ቢከተሉ ፕላኔት መሬት ልትፈርስ ትችላለች። ለዚህ ነው በዓለም ህዝቦች ዘንድ የማይደገፈው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ከዴሞክራሲና ከመልካም ኣስተዳደር ጥያቄ ጎን ለጎን የሉኣላዊነታችን ጉዳይ ምን ላይ እንደሆነ ልናይ ይገባናል። የተቀራመትናትን ኢትዮጵያን እንደገና መስዋዕት ልናደርግ የሚገባንን ኣድርገን ልናንጻት ይገባል። አገር አምሮን፣ የጋራ ቤት አምሮን ግን ደግሞ ምንም መስዋእት ሳናደርግ ብሄራዊ ማንነት ሳንፈጥር መኖር አይቻልም። አሁን ያለው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቅርምት ኣስተዳደር ስልት ወደ ኮንፌደሬሽን የቀረበ ነው። አገሮች በኮንፌደሬሽን መተዳደር ካማራቸው ብዙ መስዋእት አይጠይቃቸውም። የጋራ ሚሊተሪና የተወሰኑ ጉዳዮች ኖሯቸው ራስን በራስ ማስተዳደር የሚባለውን እውን ሊያደርጉ ይችላሉ። ኢትዮጵያ እንደ ኮንፌደሬሽን ባለ የፖለቲካ እምነት ውስጥ ገብታ ግን ደግሞ በጣም ጠንካራ በሆነ ፈዴራል መንግስትና በጣም ደካማ በሆኑ የክልል መንግስታት ትተዳደራለች። ይህ ችግር ለሃገሪቱ ሶሺዮ ፖለቲካ ችግሮች ዋና መጋቢ ችግር ሆኖ እናያለን። የራስ በራስ ማስተዳደር የምንለው አሁን ባለው በብሄር ፖለቲካና በብሄር ፌደራሊዝም እውን ኣይሆንም። አሁን የምናያቸው የብሄሮች የፖለቲካ ኣሰላለፍ ግራ መጋባትና የህዝቡ የግልጽነት ጥያቄዎች በቀጥታ የሚያያዘው ኢትዮጵያ አየተከተለችው ካለው ግራ አጋቢ የፖለቲካ መዋቅር ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የማንነት ጥያቄዎቻችንን በአንድ በኩል ሊመልስ የሚችል መሆን ያለበት ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ በመዋጮ የሰራነው የጋራ ቤት ሊኖረን ያስፈልጋል። ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ወደ አዲስ ኪዳን ልንሻገር ይገባል። የተቀራመትናትን አገር እንደገና የወሰድንባትን ሁሉ ባስቸኳይ እንመልስ። እንዴውም ጨምረን ሰውተን የጋራውን ቤታችንን ደግመን ማነጽ አለብን። ኢትዮጵያን በአዲስ ኪዳን አንጸን ሰርተን ከዓለም ህዝቦች የመጨረሻ ያደረገንን ድህነት ልንዘምትበት ይገባል። ስለ አዲሲቱ ኢትዮጵያ የመንግስት ውቅር ጉዳይ አንድ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት የሚል ኣሳብ ጸሃፊው በመጽሃፍ መልክ እያዘጋጀ ስለሆነ ወደፊት መጽሃፉ ሲታተም በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ ይሰጣል እስከዚያው ግን ቅርምተ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የእኛ የኢትዮጵያውያን የመወያያ አጀንዳ ይሆን ዘንድ ይጋብዛል ።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
geletawzeleke@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Alemayehu says
I agree for your particpatio