ጠይም ፊትሽ መጥቆሩን፣
ትንፋሽሽ፣ ጥሎሽ መሸሹን፣
የፊትሽ ወዝ ማጠፈፉን
አካል ቁመናሽ መርገፉን
ሰማሁ እናቴ ሰማሁ፣
አይቻል የለ ችያለሁ።
በዝምታ ተውበሽ
በሰው ሸክም ተሞሽረሽ
በኡኡታ …
በዋይታ…
መሸኘትሽን ሰማሁት
አይቻል የለ ቻል አ’ረኩት
የሆንሽውን ሳልጠይቅሽ ሳትነግሪኝ
ጎንሽ ሆኜ ሳላዋይሽ ሳታዋይኝ
ሞተሽ ቀብርሽ ሳልቆምልሽ ከቀረሁኝ
እናቴ ሆይ! ፍረጂልኝ ፍረጂብኝ
ምን ላድረገው? ምን ታረጊኝ?
ስደት ዶጋ አመድ ያድርግህ!
እንደ እናቴ ትንፋሽ ይንሳህ!
ምንስ ብትነፍግ ብታሳጣ
ካገር ወጪ ብታውጣ
የናቴን! የናቴን እንኳን
የመጨረሽ ሽኝቷን
እንዴት! ከዓይኔ ታርቅ
እንዴት! ከእግሬ ትነጥቅ
አዎን! ግድየለም!
ሞት መቼም ለኛ አዲስ አይደለም
ግን! እናትን ያህል ነገር
እንዴት ታሳጣኝ ቀብር?
ምነው እናቴ አንችስ!
ናፍቆትሽን እስክወጣ
ከሄድኩበት እስክመጣ
ዓይንሽ ከዓይኔ እስኪተያይ
ሞትሽን እንደ ተዋናይ
ገትረሽው በራፍሽ ላይ
ምነው? ነበር በጠበቅሽኝ
እስከማይሽ በቆየሽኝ
አንቺስ! ምነው ሀገሬ
ውለታትሽን ደፍሬ
እርግፍ አድርጌሽ ስወጣ
እናቴን ጭምር እንደማጣ
እያወቅሽው እያየሽኝ
በዝምታ ሸኝተሽኝ
ለትዝብትሽ ምነው ጣልሽኝ
የሀገሬ ጥቁር ምድር
ፍረጅልኝ! ይሄን ነገር
ልብ በይው፣ እስቲ ፀሀይ
ከናቴ ጋር ሳንተያይ
ተገናኝተን ሳንወያይ
ሞት ሊነጥል ይችላል ወይ?
አንተ! ጨካኝ ሞት ራስህ
አፈር ግባ! ድብን ያርግህ!
አንድ እናቴን ሰርቀህ ስትሄድ
ያንጠልጥልህ ሞት ከመንገድ
ብቻ ሞትስ ምን ያድርገኝ
ስንት ዘመን ይጠብቀኝ
ምንታደርጊ አንቺ ራስሽ
ልታገኚኝ በጸሎትሽ
ብዙ ለፋሽ ብዙ አነባሽ
መጨረሻ ደክሞሽ አረፍሽ
ይልቅስ እናት ዓለም
ባይጠቅምሽም
ባይጠቅመኝም
ያየሁትን ልንገርሽ ህልም
በሀገራችን፣ በግቢያችን ገብቶ ነፋስ
ህዝብ ሀገሩን ሲያተራምስ
ጉልበት አጥተሽ
አቅም አንሶሽ…
ንፋስ መሀል ስዳክሪ
ድምጽ አውጥተሽ ስትጣሪ
እየሰማሁ እያየሁኝ
ዝም ብዬሽ ትቸሽ ሄድኩኝ
ይሄን አየሁ ይሄውልሽ
ቀደም ብዬ ከመሞትሽ
ህልም…እልም…
ብዬ ብልም
ያንቺ ነገር ህልም አልሆነም
ይሄው! ጠይም ፊትሽ መጥቆሩን
ትንፋሽሽ ጥሎሽ መሸሹን
የፊትሽ ወዝ ማጠፈፉን
አካል ቁመናሽ መርገፉን
ሰማሁ እናቴ ሰማሁ
አይቻል የለ ችያለሁ።
ለናቴና በስደት ዓለም ሆነው እናት አባት ወይም የሚወዱት ዘመድ በሞት ለተለያቸው ቤተሰቦች ጭምር መታሰቢያ ይሁን
Tefera Tesfaye Gebresilasse says
…….. በሀገራችን፣ በግቢያችን ገብቶ ነፋስ
ህዝብ ሀገሩን ሲያተራምስ
ጉልበት አጥተሽ
አቅም አንሶሽ…
ንፋስ መሀል ስዳክሪ
ድምጽ አውጥተሽ ስትጣሪ
እየሰማሁ እያየሁኝ
ዝም ብዬሽ ትቸሽ ሄድኩኝ
ይሄን አየሁ ይሄውልሽ
ቀደም ብዬ ከመሞትሽ
ህልም…እልም…
ብዬ ብልም
ያንቺ ነገር ህልም አልሆነም//
Nefes yemar Welelaye geta yatsenah
Bombu says
አዎ ያገሬ ልጅ ስሜትህ
ገባ ከሆዴ ቁጭትህ
የናትን ነገር ሚሥጥሩን
የፍጥረት መሠረት መሆኑን
ምን ይጨመር ምን ይቀነስ?
ከናት ፍቅር ካባት መንፈሥ
የፍቅር ሁሉ መገለጫ
ከሁሉም በላይ በአብላጫ
የቤተስብ ዋልታ ማገሩ
የናት ያባት ያገር ክብሩ
የተሣሰረ የተቆራኘ
ዕውነት በውነት የተገኘ
አይጣመም አይሰበር
የማጠፋ የማይሻር
ጊዜ ቦታ አያግደው
ጸንቶ የሚኖር እስከዛኛው
ምን ይጨመር? ምን ይቀነስ?
ከናት ፍቅር ካባት መንፈሥ
ሲኖር ብቻ ያለው ትርጉም
ከጎደለ ያለም ዕርጉም
ምን ይጨመር? ምን ይቀነስ?
ከናት ፍቅር ካባት መንፈሥ
በለው ! says
************************
የአርስበእርስ መጠፋፋት በበዛባት ሀገር
እናት አባት ተጨንቆ ሂዱ ብሎ ልጅ ሲያበር
ልጅ ሲጓጓ ከአብሮ አደግ በሀገሩ መቦረቅ መጫወት
ወደ ሰው ሀገር አግሬ አውጭኝ ማንነትን ማጣት
ዘመን አልፎ ዘመን ሲመጣ መልካም ምኞት
ሀገሬን ወገኔን አባቴን እናቴንስ መቼ ነው የማያት?
ካለፈው ቀን ዛሬ ተሽሎ ነገን ይበልጥ መጓጓት
ጭራሽ ባሰ አልሞላም አለ ፍቃዱ የእግዜር
ያለወገን ያለዘር እያስቅረ በሰው ሀገር
ሁሉ ሲፈራርስ የነበረው እንዳልነበር
ፀሐይ ጠልቃ መውጣቷ ሲያጠራጥር
ወለላ የመሳሰሉ በንዴት ከስተው ጥቁር
ሰማይ ሁሉ ኮከብ አድማቂው ጨረቃ
ወንድም ለኩራት አህት ለመፅናኛ አባት ለጠበቃ
አግዜሩም አትንፈገን ምሕረትህን በቃ በል ሁሉን ነጠቃ
ለሞቱትም ነፍስ ይማር ያለነውንም ከቁም ሞት እንንቃ
ስቃይ ቸነፈር ንፋስ ትርምስ ሽብር በዚሁ ይብቃ!!
***********************
ስለመልካም ወንድሜ ጓደኛዬ አባቴም እንዲሁ በእየግላችሁ ለተነጠቃችሁ ጥናቱን ይስጣችሁ። የሀዘን መጨረሻ ሠላም ለሁሉም ይሁን በለው!