
. . . ነፍሱን አይማርና! ያ! ቀጣፊ ከንቱ – የሂትለሩ ጉብልስ፣
አሳልፎ ሄደ፤ መሰሪ ትምህርቱን – ለበረከትና…ለነ አቶ ሽመልስ፤
እነሱም በተራ፣ ለታችኛው አሽከር ነጭ ውሸቱን ዘርተው፣
አጨዱት. . .፣ ከመሩት. . .፣ ማተብ-አልባ አድርገው፤
ከወያኔ ካድሬ፣ የውሸት ፋብሪካ፣ ተመርታ የወጣች፣
የዘረኞች ቋንቋ፣ “ትግሬ ትጠላለህ” የሚሏት ቃል አለች፤
ያገር ወዳዶችን ተቃውሞ ማስቆሚያ፣
በይሉኝታ ገመድ ሸብቦ ማሰሪያ. . .፣
ሆና ታገለግል ዘንዳ የተቃኘች፣
የጥላቻ ዜማ፣ ለጆሮ እምትቀፍ፣ ጩኸት የቁራዎች።
. . . እዩትማ እንግዲህ፣ ወደ ውስጥ ሲሰምጥ፣
መብሰሉን ሲያቅተው፣ ሲላወስ እንደ ሊጥ፣
ራሱ በፈጠረው፣ ራሱን አስጨንቆ፣ ጭቃ ሲንከባለል፣
እኩዮቹን ክዶ፣ ራሱን አሳንሶ፣ ሚጢጢዋን ሲያክል፤
ስልጣኑ አስክሮት፣ የግፍ ሃብት ቆዝሮት፣
ንቀት አሳውሮት፣ ህሊናውን ደፍኖት. . .፣
ደግሞ ከእሱ ብሶ፣ “ጅራፍ ገርፎ ሲጮኽ. . .፡
ይለኛላ እኔኑ፣ “ትግሬ ትጠላለህ”¡
. . .ንገረኝ ካልክማ፣ አንተ ነህ ጥላቻ፣ የጥላቻ ምንጩ፣ ህዝብ የምትጠላ፣
የይሉኝታ ደሃ፣ ምግባረ-ብልሹ፣ የዘመን አሽክላ!
አይገባህም እንጂ፣ ለመቻቻል ብሂል ስንት ዋጋ ከፈልኩ፣
ይኸው አንተን እንኳን፣ ሁለት አስርት ታገስኩ፤
ከያዘህ አባዜ ብትላቀቅ ብዬ፣
ታጥቦ ጭቃነትህን ሲያውቀው ልቦናዬ፤
እኔማ እንዴት ልጥላ! አብሮ አደጎቼን፣
እህት ወንድሞቼን፣ እናት አባቶቼን፣ ዘመድ ስጋዎቼን፣
ወዳጅ ጎረቤቴን. . . የሃገሬን ልጆች፣
የአጥንቴን ክፋይ፣ የደሜን ቅጅዎች፤
እንዴት ብዬ ልጥላ?!
. . . ይጠየቃ አክሱም፣ የቆመው ሐውልቱ፣
የዘመናት ታሪክ፣ ስረ-መሰረቱ፤
ትጠየቅ እምዬ፣ ወላዲት ማሪያሟ፣
የጽላተ-ሙሴ፣ ማደሪያ ጽዮኗ፤
ትጠየቅ ማይጨው፣ ትመስክር አድዋ፣ የታሪክ ማማዋ፣
ያያቶቼ. . . አጥንት ታዛ ከለላዋ፤
ካሻህም ላስመስክር፣ የሰው እማኝ ልጥራ፣ ለማተብ የቆሙ፣
ከዘመናት ታሪክ..እስካለንበቱ . . . በክብር የታደሙ፤
ሲዘከር፣ ሲተረክ፣ ሲጠራ፣ ሲወሳ . . . ዝነኛ ስማቸው፣
ምንኛ እንደምከንፍ፣ ለወገን ፍቅራቸው!
. . . አሉላ፣ ዮሃንስ፣ ዘርዓይ፣ አብርሃ፣ አውዓሎም፣ ሐጎስ፣
ገ/ሕይወት፣ አስገዶም፣ ባህታ፣ አሰገድ፣ ገ/መድኅን፣ ኪሮስ፣
ጋይም፣ አረጋዊ፣ ዘርዑ፣ ደበሳይ. . .፣
አቤሰሎም፣ አርዓያ፣ ግደይ፣ ገብረ-ተንሣይ. . .፤
አደይ፣ አታክልቲ፣ ጸሐይቱ፣ ሐዳስ. . .፣
ጽዮን፣ ትብለጽ፣ ምጽላል፣ አብርኸት፣ ትርሃስ. . .፤
ይልቁን ልምከርህ፣ ያገር ልጅ ወንድሜ፣
እኔስ ተስፋ አልቆርጥም፣ አሁንም ደግሜ፤
የቁማር ገድ-አልባ፣ የዘረኞች “አኪር”፣
ያለፈባት ካርታ፣ የነተበች “ጆከር”. . .
መምዘዙን አቁመህ፣
መስሎህም ከሆነ፣ ባገር የተጠላህ፣
ዘለህ የሕዝብ ስም ማንጠልጠሉን ትተህ፣
ራስህን ቻልና፣ ጠመንጃህን ጥለህ፣
“እኔን ትጠላለህ?” በልና ጠይቀው፣
ዞረህ ያገሬን ሰው፤
ተጠልተህ ከሆነም. . .፣
“ለምን እጠላለሁ?” ብለህ ራስህን ጠይቅ፣
ከዚያም መለስ ብለህ፣ ከህሊናህ ታረቅ፤
ያኔ! ዙሪያህን ስትቃኝ፣ ውስጥህን ስትመረምር፣
ይከሰትልሃል፤ እውነተኛው ምስጢር!
እስኪ ምክር ስማ፣ አያዋጣም ከንቱ ይኼ ነውረኝነት፣
ልቦናህ እያወቀው፣ ለፍርፋሪ አድረህ፣ በእሳት አትጫወት፤
እየለበለበ፣ መልሶ አንተኑ፣ ሊያቃጥል በቀኑ፣
ፈጥነህ ልብ ግዛ፤ ከእኩይ መንፈስ ታቀብ፤ ሳይብስ ሰቀቀኑ!
ልምከርህ ደግሜ፤ ያገር-ልጅ ወገኔ!
መልካም በመከወን፣ ደፍረህ በመጠመቅ፣ በሕዝብ ፍቅር ጸበል፣
“ይጠሉኛል” ብለህ ራስህን ከማስጨነቅ፣ ህመም ተገላገል!!
መስከረም 2007 ዓ/ም
(ኦክቶበር 2014)
ማር አይጣፍጣትም ለአህያ ለዶሮ
ምክርም እንዲህ ነች ለደደብ ወያኔ ለልበ ድንቆሮ።
ምን ያረጋል ወንድሜ ምክርህ ቆንጆ ነበር። ግን አሁን ኢትዮጵያን
አንቀጥቅጦ ለሚገዛት ሻዕቢያ ይህ አባባልህ ፍፁም
አይገባውም።ያ ሁሉ ትግላችንንና ደማችን
ህወሀት ለሻዕቢያ እንደዋዛ እንደሸጠው ደስ በሚለው
መጣጥፍህ ለየዋሁና ለምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ግለፅልኝ።
መርሻ ዘ ዐዲግራት።