በድሉ ዋቅጅራ ‹የሌላቸው ባለቤቶች› የሚል ቅራኔ ውስጥ የገባው ከተጨባጭ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታ ተነሥቶ ነው፤ አንዳንዴ ሁኔታዎች እያስገደዱን ቅራኔዎችን እንቀበላለን፤ አንድ ጌታ አሽከራቸውን ይጠሩና ባላገር ወደሚኖሩ እናታቸው ዘንድ ይልኩታል፤ ነገር ግን ‹ሞተው ከሆነ እንዳትነግረኝ› ብለው አስጠንቅቀውት ይሄዳል፤ ሴትዮዋ ሞተው ይደርሳል፤ ምን እንደሚያደርግ ግራ ገባው፤ ሲያንሰላስል ብዙ ቀናት ከቆየ በኋላ ጎፈሬውን ለሁለት ከፍሎ ግማሹን ይላጭና ግማሹን ብን አድርጎ ያበጥርና ጌታው ዘንድ ይቀርባል፤ አንዴ ጎፈሬውን እየነካካ፣ አንዴ የተላጨውን እየዳበሰ ጥያቄዎቻቸውን ሲመልስ፣ ጌታው ተቆጡና ‹ምንድን ነው የምታድበሰብሰው አርፈው እንደሁ በወጉ አትነግረኝም!› ብለው ሲጮሁበት ‹አዬ ጌታዬ አርስዎ መቼ በወጉ ላኩኝና!› ብሎ መለሰላቸው።
የበድሉ ‹የሌላቸው› በግማሽ እንደተላጨው ጸጉር ነው፤ ‹ባለቤቶች› ደግሞ እንደግማሽ ጎፈሬው ነው፤ የሌላቸው አላቸው፤ የአላቸው የላቸውም፤ እንደዚህ ያለውን ጉደኛ ሁኔታ እዚያው ጉደኛ ሁኔታ ውስጥ ካለው በቀር ሌላ ሰው አይገባውም፤ መብት ከግዴታ ሲገነጠል መብትም ግዴታም ባሕርያቸውን ለውጠው ሌላ ነገር ይሆናሉ፤ መብትም መሸጦ፣ ግዴታም መሸጦ ሲሆን ከራሱ በቀር ማን ለማን፣ ማን ለምን ኃላፊነት አለበት? መሬቱ ለሙስና ለምለም የሚሆነው እንዲህ እየሆነ ነው፤ ትንሽ መንደር ለትልቅ አገር መመሪያ ሲያወጣና የማንነት ምንጭ ሲሆን ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› ብሎ በአደባባይ መናገር ይቻላል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያዊ በሚባል ጋዜጣ ላይ ሀሳቡን እየጻፈ፣ ኢትዮጵያዊ የሚባል ብር እየተቀበለ (በጎን ሊሬም፣ ዶላርም ሊኖር ይችላል፤) ኢትዮጵያዊ የሚባል ምግብ (ማካሮኒም ሊሆን ይችላል) እየበላ፣ ኢትዮጵያ ከምትባል አገር የሚያገኘውን ጥቅም ሁሉ እያግበሰበሰ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› ማለት ይችላል፤ ሀሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፤ ግን ‹ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም› ብሎ የሚናገረው ለማን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፤ ለኤርትራውያን ነው? ለኢትዮጵያ ወጣቶች ነው? አንዱ የክህደት ትምህርቱ የገባው ወጣት ኢትዮጵያዊነት ዜግነት እንጂ ማንነት አይደለም ብሎ ጻፈልኝ፤ ፊደልን ተምረው ማንበብና መጻፍ ሲጀምሩ ድንቁርናን የሚያነግሡ ሰዎች በተፈጥሮ ያገኙትን ደመ-ነፍሳቸውን እውቀት ያደርጉታል፤ ፊደሉ የእውቀትን በር መክፈቻ መሆኑ ሳይገባቸው ይቀርና ፊደሉን የእውቀት መጨረሻ ያደርጉታል።
‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› ማለት ኢትዮጵያ ባለቤት የላትም ማለት አይደለም? ይህንን የሚለው ከሌላቸው ‹‹ባለቤቶች›› አንዱ መሆኑ አይደለም? ባለቤቶች ነን የሚሉትንስ ወደባዶነት መለወጥ አይደለም (ሁሉም ዜሮ)? ባለቤት ለመሆን መጀመሪያ ቤቱ ባዶ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ አይደለም? ኢጣልያኑ ቅኝ ገዢ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁን ሲያይ ለዓይኑ አልሞላ አሉትና ‹‹ለካ ቤት ባዶ ሲሆን ቁንጫ ያፈራል የሚባለው እውነት ነው!›› አላቸው፤ ሌላው ቢቀር ኢጣልያኑ የተረተው በአማርኛ ነው!
‹‹ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤›› ያለው ሰው ዓላማ አለው፤ ዓላማው ኢትዮጵያን በቁንጫ መሙላት ነው፤ ኢትዮጵያዊ ማንነት ሁሉ ወደቁንጫነት ሲለወጥ እሱ አንድ ቆርቆሮ ፍሊት ይዞ የቁንጫዎች የበላይ ይሆናል፤ ይህንን የሂትለርና የናዚን ፍልስፍና የሚያረጋግጥ ሌላም ነገር አለ፤ ‹‹ትግራዋይነት ዝበሃል ንጹሕ መንነት አለና፤››! ‹‹ትግራዋይነት የሚባል ንጹሕ ማንነት አለን፤›› ማለት ነው፤ ዘረኛነትና ድንቁርና የማይለያዩ መሆናቸውን ማረጋጋጫ ነው፤ እንኳን የትግራይን ሕዝብና ራሱንም አጥርቶ የማያውቅ ሰው ስለ‹‹ንጹሕ›› ማንነት ያወራል፤ እስቲ ‹‹ንጹሕ›› ትግራዋይ የሆኑ ሰዎችን ስም ዘርዝር ቢባል እነማንን አንደሚጠራ አላውቅም፤ የጀርመን ናዚዎች ስለንጹህ የአርያን ዘር የጻፉትን በጥራዝ-ነጠቅነት በዓይኑ ዳብሶት ይሆናል፡፡
ይህንን ዘረኛ ብቻ ሳይሆን ጸረ-ኢትዮጵያ አመለካከት በአደባባይ ያወጣው አንድ የሪፖርተር ጋዜጠኛ ቢሆንም ምንጩ ያው ጋዜጠኛ ብቻ ነው ለማለት ይከብዳል፤ ሰውዬው እንደቧንቧ ከማስተላለፍ ባለፈ ይህንን ሸክም የሚችል አይደለም፤ እንክርዳድን ያበቀለችው መንደር ኢትዮጵያ ውስጥ ናት፤ ሆኖም በዚያች አንድ እንክርዳድን ካበቀለች መንደር ውስጥ ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ለኢትዮጵያ ክብር የመጨረሻውን መስዋእትነት የከፈሉ ኢትዮጵያውያን የምንላቸው የሉም? እንደምናውቀው ትግራይ የኢትዮጵያ ማኅጸን ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› የሚለው ጉድ ከዚህ ማኅጸን እንዴት በቀለ? የእናት ሆድ ዥጉርጉር ነው ብለን እንዳንተወው የሚቀጥለው ትውልድ ይጎዳል።
አሁን አንድ ጥያቄ ይቀራል፤ ኢትዮጵያዊነት ዜግነት አንጂ ማንነት አይደለም ተብሏል፤ በእውነት ዜግነት ማንነት አይደለም? ጋዜጠኛነት ማንነት አይደለም? እናትነት ማንነት አይደለም? ሚስትነት ማንነት አይደለም? … ማንነትን በጨርቅ ቋጥሮ ከጎሣ ጋር ያቆራኘው ማን ነው? ጎሣም ያለጥርጥር ማንነት ነው፤ ነገር ግን አንዚህን የጠቀስኋቸውንና ሌሎችንም ማንነቶች የሚያጠቃልል ማንነት የለም? ዜግነት አጠቃላይ ማንነት አይባልም? እንዲያውም ከዜግነት በላይ የሆነ ማንነት የለም? ሰውነት ከዜግነት በላይ የሆነ ማንነት አይደለም? ህንድ ከሁለት መቶ በላይ ቋንቋዎች አሉት፤ ከነዚህም ከሀያ እስከሠላሳ የሚሆኑት የራሳቸው ፊደል ያላቸው ናቸው፤ ይህም ሆኖ ማንነታቸው ህንድ መሆኑን ጥያቄ ውስጥ አላስገባባቸውም፤ እንዲሁም ስዊትዘርላንድ አራት የራሳቸው ፊደሎች ያሏቸው ቋንቋዎች ቢኖራቸውም ማንነታቸውን ከስዊስነት አልቀየረውም።
የጎደለ መብት ካለ ያንን ለማሟላት መታገል አንድ ነገር ነው፤ የሁሉም የዜግነት ግዴታ ይሆናል፤ ነገር ግን የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ማፍረስ ወይም መሸርሸር ሌላ ነገር ነው፤ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ብዙ የጎደሉና ያልተስተካከሉ ነገሮች ይኖራሉ፤ ኃይላችንን እነዚህን ጉድለቶች ለመንቀስና ለማስተካከል መሞከሩ ከማፈራረሱ የተሻለ አማራጭ ነው።
ባለቤቶች የሌላቸው ከመሆን ወጥተው ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ይቻላል።
Leave a Reply