በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ መርጃ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ኦክቶበር 31 -2015 (ጥቅምት 20 – 2008 ዓ.ም) ተደረገ። በዝግጅቱ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ተገኝተዋል። በቦታው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ አበበ ቦጋለ የውጪ እንቢተኝነት ሊቀመንበር እና አቶ ቸኮል ጌታነህ የንቅናቄው ከፍተኛ አመራር ናቸው።
ዝግጅቱ ረፋዱን 14፡00 ሰዓት የተጀመረ ሲሆን አቶ ጌታሁን ማሬ የዝጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የስዊድን የአርበኞች ግንቦት ሰባት የስራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ዘለሌ ፀጋ ሥላሴን ስለዝግጅቱ ገለጻ እንዲያደርጉና ዝግጅቱንም እንዲመሩ ጋብዘዋል። አቶ ዘለሌ በበኩላቸው የከተማው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ያለበትን ሁኔታ ገልጸው እንግዶቹንም በማስተዋወቅ አቶ አበበ ቦጋለና አቶ ቸኮል ጌታሁን ንግግር እንዲያደሩ ጋብዘውል።
አቶ አበበ በአሁኑ ሰዓት አርበኞች ግንቦት ሰባት እየሰራ ስላለው የስራ ክንውን እቅድና አላማ እንዲሁም ደጋፊዎቹና አባላቶቹ እያደረጉ ስላሉት እንቅስቃሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ ቸኮል ጌታሁን በበኩላቸው በኤርትራ ቆይታቸው ወቅት ስለተመለከቱት የአርበኛው ቆራጥነትና የአላማ ጠንካራነት የገለጹ ሲሆን በአሁን ሰዓት የድሮ ጀግናችን ስም በመጥራት የምንቀመጥበት ጊዜ ሳይሆን እኛው እነሱን ተክተን በጀግንነት ስማችን ማስጠራት የሚገባን ጊዜ ነው በማለት ደጋፊውንና አባላትን የሚአበረታታና የሚነሳሳ መል ክት አስተላልፈዋል።
ከሁለቱ አመራሮች ንግግር በኋላ ተሰብሳቢው ሰው ጥያቄ እንዲያቀርብ ተጋብዞ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቷል። እንዲሁም ንቅናቄውን በተመለከተ ግልጽ ውይይት ተደርጓል። ከዚህ በመቀጠል «በደል ይረሳል ወይ?» የሚል ግጥም በማራኪና በወለላዬ ከቀረበ በኋላ የገቢ ማሰባሰቢያ ጨረታ ተደርጓል። ለጨረታ የቀረበው የንቅናቄው ሊቀመንበር የሆኑት የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ቆራጡ አርበኛ የአቶ
አንዳርጋቸው ጽጌ ከሚመሯቸው አርበኞች ጋር ሆነው የሚታዩበት «ላንቺ ነው ኢትዮጵያ» የተባለምስል ሲሆን ይሄው ምስል በግልና በቡድን ተጫርቶ ከፍተኛ ፉክክር ከተደረገ በኋላ በአንድ መቶ አራት ክሮነር (የስዊድን ገንዘብ) የስዊድን የስደተኞች ማህበር አሸንፎ ምስሉን የግሉ አድርጎታል። ከዚህ ከጨረታ ከተገኘው ገንዘብ ሌላ ሁለት የቃል ኪዳን ቀለበቶች የመግቢያ ገንዘብ ሦስት መቶ ዶላርና ከእጣ የተሰበሰበ ገቢ ተገኝቷል።
በወቅቱ በስደተኛ ማህበሩ አባላት ይደረግ የነበረው ተሳትፎ ዝግጅቱን አድምቆት አርፍዷል በጨረታው ጊዜም በማሃል እረፍት በሚደረግበት ወቅት የወ/ሪት ሙሉቀን አማረ «ኢትዮጵያዊት ነሽ አትበሉኝ» የሚል ግጥምና የ/ሮ ውቤ ማሞ እንዲሁም የአቶ መብራቱ ፀሐዩ ቀስቃሽ ግጥሞች ቀርበዋል።
(መግቢያው ፎቶ: አቶ ዘለሌ ፀጋ ስላሴ ዝግጅቱን ሲከፍቱ)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply