ዘግናኙ የስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ግፍ በሳዑዲ አረቢያዊያን እጅ፤ ከፊታችን ተደቅኗል። ሁላችን በያለንበት፤ “ለምን? ምን አደረግን? መጨረሻው ምንድን ነው? መቼ ነው ይኼ ሁሉ የሚያበቃው?” እያልን እርስ በርሳችን እየተጠያየቅን ነው። እኛ ወደ የምንፈልገው መንገድ ካልገባን፤ ሌላ ሊይስገባን የሚችል ኃይል የትም የለም። በሳዑዲ አረቢያ የተደረገውን ኢሰብዓዊ ድርጊት፤ ሁላችን ኢትዮጵያዊያን በግል በራሷና በራሱ እንደተደረገ በደል አድርገን ወሰደነዋል። ተገቢም ነው። ኢትዮጵያዊያን እንደ ትቢያ ተረገጥን፣ ተዋረድን፣ ተገደልን። እናም አንድ ነገር ማድረግ አለብን። ሀገራዊ መልስ ሠጪ መንግሥት የለንም፤ ሀገራችንን የሚወክል መንግሥት የለንምና። እኛ ግን በኢትዮጵያዊነታችን ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት አለብን። ኃላፊነታችን እስከምን ደረስ ነው? የሚለውን በዚህ ጽሑፍ እቃኛለሁ።
በሳዑዲ አረቢያ የተደረገውን፤ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥትና በኢትዮጵያ ያለው ወገንተኛ አምባገነን ሕገ ወጥ መንግሥት ባንድነት ሆነው የፈፀሙት ነው። ጥርጣሬ ያለው ካለ፤ በአዲስ አበባ ተቃውሞ ለማሰማት የወጡትን ወገን አፍቃሪና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ላይ፤ ወገንተኛው አምናገነን ሕገ ወጥ መንግሥት ያደረገውን መገንዘብ ይቻላል። ሀገራችን ለገጠማት አስቸጋሪ ሁኔታ ተጠያቂው ወገንተኛው አምባገነኑ ሕገወጥ መንግሥት ነው። በሳዑዲ ልዑላዊያንና በወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ገዥዎቻችን መካከል ስላለው ወዳጅነት እያንዳንዳችን በደንብ ማወቅ አለብን። ይኼ አዲስ አበባ ያለው መንግሥት ከኢትዮጵያዊያን ይልቅ ለሳዑዲ ልዑላዊያን ለምን ቆመ?
ይኼ በሳዑዲ አረቢያ የተደረገው ኢትዮጵያዊያንን የማጥቃትና የማጥፋት ጉዳይ፤ ብቻውን የቆመና ብቻውን የሚፈታ አይደለም። አዎ በሠልፍ እንውጣ፣ እንጩህ፣ ለዕርዳታ እንነሳ፤ የማታ ማታ ግን፤ አሁንም መሠረታዊው የኢትዮጵያዊያን ችግር፤ የራሳችን የአስተዳደር ችግር ነው። ይህ ደግሞ ወገንተኛ አንባገነኑ ሕገወጥ መንግሥት፤ በባለቤትነት የሚበላው ምግብ፣ የሚጠጣው ወሃ፤ ሥጋና ደሙ፤ አጥንትና ቆዳው ነው። ይህ መንግሥት እስካለ ድረስ፤ በተለያዬ መልክ እንዲህ ያሉ ተግባራት ይቀጥላሉ። እናም ዋናው ትኩረታችን ይኼን ሕገወጥ መንግሥት ማስወገድ መሆን አለበት። ይኼ ሕገወጥ መንግሥት የሚሠጠንን እያንዳንዱን ዕድል በደንብ መጠቀሙ የኛ ግዴታ ነው። እናም ይኼን የሳዑዲ አረቢያ ግፍ፤ ከዋናው ትኩረታችን ጋር ማስተሳሰር አለብን። ሰዎች እየተገደሉ ነው፤ በሀገር ቤትም በውጭም።
መነሳት ያለብን፤ ኢትዮጵያዊያን በያለንበት ምንድን ነው እየጠየቅን ያለነው? ከሚለው ነው። ኢትዮጵያዊያን ባሁኑ ሰዓት እየጠየቅን ያለነው የሞትና የሽረት ጉዳይ የሆነብንን የወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት መወገድና የኢትዮጵያዊያንን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስቀድም መንግሥት መቋቋምን ነው። ባሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት እንዲወገድ የምንፈልገው፤ ይህ መንግሥት ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ ኢትዮጵያዊነት ስለሆነ፣ ሀገሪቱን እያወደምና ሕዝቡን እየጨረሰ ስለሆነ፣ የሀገሪቱን ሀብት በመዝረፍ ባዶ ስላስቀራት፣ ኢትዮጵያዊያን እርስ በርሳችን እንድንጫረስ እያባላን ስለሆነና ለነገው ምፅዓት ከእግራችን ሥር ፈንጅ ስለጠመደብን ነው። ካገር ውስጥ አልፎ በየተሰደድንበት እጁን ሠዶ እያሰቃየን ነው። እናም ባሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያለው ዋናው ቅራኔ፤ በኢትዮጵያዊያን እና በወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት መካከል ያለው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው።
ይኼ ዋና ማሠሪያው ሆኖ፤ ከዚህ እንዲከተል የምንፈልገው ምንድን ነው? ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያዊያን በያለንበት በሀገራችን እንዲሆን የምንፈልገው፤ ኢትዮጵያዊያን አንድነታችን የተጠበቀ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ የተከበረ፣ የሕግ የበላይነት በሀገራችን የሠፈነና የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባት ሀገር እንድትሆን ነው።
ለኛ፤ የመጨረሻው ያማረ እንዲሆን ለምንፈልግ ሁሉ፤ በሀገርና በድርጅት መካከል ያለው ውዥንብር መገፈፍና መገለጥ አለበት። ባሁኑ ሰዓት አጀንዳችን ወገንን ማትረፍና ሀገር ማዳን ነው። ለዚህ የአንተ ወይም የአንቺ ድርጅት የተለዬ ተልዕኮ የለበትም። የኔ ድርጅት ከሁሉ በላይ ነው የሚለውን፤ ቦታ ማሣጣት አለብን። ሀገራችን ከማንኛችንም ድርጅት በላይ ነች። ሁላችንም አንድ ላይ አንድ ተልዕኮ ነው ያለን። ታዲያ የድርጅታችሁን ጋጋታ ለኋላ አቆዩትና በአንድ ላይ በዚህ አጀንዳ ዙሪያና አጀንዳው በሚጠይቀው የአደረጃጃት ጥሪ እንሰባሰብ። ይህ የሳዑዲ አረቢያ ግፍ ለዚህ ልባችንን ይክፈተው።
የምንሠለፈው በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ መሆን አለበት። በደላችን በኢትዮጵያዊነታችን ነው። መፍትሔውም በኢትዮጵያዊነታችን መምጣት አለበት። የሀገሪቱ ዜጎች በሙሉ በአንድ ተነስተን፤ የሀገሪቱ ተወላጅ በሙሉ እኩል የምንሳተፍበት የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር መሆን አለበት። በዚህ ላይ ስምነት ከሌለን፤ የነገው ሕልውናችን አስፈሪ ነው። በየክልላችን ተሰልፈን፣ በተለይ የፖለቲካ ማስተማመኛ ሳይኖር፣ ይኼ ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ትቶልን የሚሄደውን መርዛማ ውርስ አቅፈን፣ ፖለቲካውን የተላበስነው እንደሆነ፤ እያንዳንዱ ፖለቲከኛ ሲያኮርፍ ወደ ወገኖቹ እየሮጠ፤ የራሱን ጦር የሚቀሰቅስበት ሀቅ መፍጠራችን ነው። መዘንጋት የሌለብን፤ ወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥቱ ትቶልን የሚሄደው ሀቅ፤ ሀገራችን ታጣቂዎች እንዳፈር የሞሉባት፣ በጣም ደካማ የሆነ ማዕከላዊ መንግሥት፣ መተማመን ሀገር ጥሎ የኮበለለበት፣ ትምህርትና ሕክምና ባዶ የሆነባት፤ ድህነትና በሺታ የከተመባት ሀገር ናት። ይኼን መቀየር ያለብንና የምንችለው ኢትዮጵያዊያን ሆነን ስንነሳ ብቻ ነው።
ከዚህ ተነስተን አንድ ሀገራዊ ራዕይ እንፍጠር። የትግል ዕሴቶቻችን አንድ መሆን አለባቸው። ለዚህ ራዕይና ለነዚህ ዕሴቶቻችን፤ ተመጣጣኝ የሆነ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ይኑረን። የትግሉን ሞተር የሚያሽከረክረው ወገንተኛው አምባገነን ሕገወጡ መንግሥት መሆኑ ይብቃ። መሪውን እንንጠቅና እንዘውረው። የማልክደው ሀቅ አለ። እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን ዓላማ ለማራመድ፤ የተገኘውን አጀንዳ ሁሉ ወደዚያ ይጠመዝዘዋል። ይኼን በምንም ቀለም ኩለን ልናሳምረው የማንችል ጎጂ እውነታ ነው። አሁንም ይኼን የሳዑዲ አረቢያ ግፍ በሚመለከት፤ ለየራሳቸው ድርጅቶች የፖለቲካ ግኜታዎችን ለማስቆጠር ድርጅቶች ተኮልኩለዋል። በአነሳሽነትም ሆነ በተቀነባበረ መንገድ፤ የሳዑዲ አረቢያውን ግፍ በሚመለከት የሚቋቋሙት ማናቸውም አቀናባሪ አካል ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት። በዓለም ዙሪያ ካሉት ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ያካተተ መሆን አለበት። በተለያዩ የፖለቲካና የሕዝብ ተቆርቋሪ የድርጅቶች ሁሉ ያሉትን ያቀፈ መሆን አለበት። ከእህቶቻችን ሙሉ ተሳትፎ ያለበት መሆን አለበት። ከእስልምና ተከታዮች ማካተት አለበት። ወጣቶችን ያቀፈ መሆን አለበት። ባጠቃላይ አንድና አንድ ብቸኛ ድርጅት መሆን አለበት። ተልዕኮው ደግሞ የጀዳውን የተቀጣጠለ እሳት ማጥፋት ብቻ ሳይሆን፤ ለዚህና ለሌሎችም ተመሣሣይ ችግሮቻችን መንስዔ የሆነውን የወገንተኛ አምባገነኑን ሕገወጥ መንግሥት ለማስወገድ ኢትዮያዊያን በሀገርም ሆነ ከሀገር ውጪ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በተቀነባበረ መንገድ ማስተባበር ነው።
ይህ አቀናባሪ አካል፤ ከወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ክንድ የራቀ መሆን አለበት። ቀጣይነት ያለው ሆኖ፤ የተደራረበ አደረጃጀትን መሥርቶ፤ ሁሉን ክፍሎች የሚሰበስብበት እጆች አበጅቶና ዘርግቶ፤ መንቀሳቀስ አለበት። እዚህ ላይ ትሁትነት፣ ፈቃደኝነት፣ ፈጣሪነት እና አርቆ አሳቢነት ዋና መሣሪያችን መሆን አለባቸው። የግልና የቡድን አጀንዳ የሚያስቀድሙት ራቅ ማለት አለባቸው ወይንም መደረግ አለባቸው። ሁሉን ለሀገሬ ሁሉን ለወገኔ ባዮችን ማስቀደም አለብን። በተለያዩ ጎራዎች የተቋቋሙ ካሉ ይዋሃዱ። የተቋቋሙው ካንድ ወገን ብቻ ከሆነ፤ ለሌሎቹ ክፍሎች እኩል ዕድል በመሥጠት፤ ማካተቻ ቦታ በመክፈት፤ ሁሉን ማቀፍ አለበት። ይህ የሁላችን ጉዳይ ነው። ይህ የሀገራችን ጉዳይ ነው።
ይህ የሳዑዲ አርቢያ ግፍ፤ ከአውስትራሊያ በምዕራብ ተጉዞ እስከ ካናዳ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ስዊድን፣ ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ሀገር ኢትዮጵያዊያንን ያስለቀሰ ሰቆቃ ነው። ይኼ ግፍ የፈጠረውን ዕድል፤ እስከዛሬ እየመጡ እንዳሳለፍናቸው ዕድሎች ሁሉ ካሳለፍነው፤ ስቃያችን ይቀጥላል። ይህ በጃችን ያለ ፈተና ነው። ይህ ሁላችንን የቀሰቀሰ የሲቃ ጥሪ ነው። ይህን የተለመደ ካደረግነው፤ በጉሮሯችን ገብተው ልባችንን ዘንትለው እንዲያወጡ የፍቃድ ወረቀት ሠጠናቸው ማለት ነው። ከዚያ በድኑ ይታያል! ማን ይሆን?
አስከመቼ
Leave a Reply