በጅዳ መጠለያ አንዲት የኮንትራት ሰራተኛ በጅዳ ቆንስል በር ታንቃ ሞተች
በሪያድ “ኢትዮጵያዊቷ አሰሪዎቿን ለመበቀል የ6 አመት ህጻን ገደለች” የሳውዲ ጋዜጣ ዘገባ
ኮንትራት ስራ መጥተው ተፈናቅለው በጅዳ ቆንስል መጠለያ ከሚገኙት ቁጥራቸው ወደ 80 ከሚጠጉት እህቶች መካከል አንዷ እህት ከሁለት ቀናት በፊት እሁድ ጁን 23 ቀን 2013 በጅዳ ቆንስል ግቢ በር ራሷን አንቃ መግደሏ ታውቋል። ጉዳዩን ለማጣራት የዚህችው እህት ሬሳ ከቦታው ሲነሳ በቦታው ነበሩ ወደ ተባሉት በጅዳ ቆንስል የዲያስፖራና ተፈናቃይ ዜጎች ሃላፊ ወደ ሆኑት ቆንሰል ሙንትሃን በስልክ ለማግኘት ያደረግኩት ሙከራ አልተሳካም።
ስለተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት አካባቢው ከነበሩ የአይን እማኞች ለማጣራት ባደረግኩት ሙከራ ሟች በኮንትራት ስራ ከወሎ ወደ ሳውዲ አረቢያ መጥታ ከአመት በላይ ከሳውዲ አሰሪዎች ቤት ስትሰራ ከቆየች በኋላ በስራ ብዛት እግሯን ስላመማት ከስራ መፈናቀሏንና ወደ ጅዳ ቆንሰል መጠለያ መጠጋቷን ገልጸውልኛል። ያም ሆኖ በመጠለያው ትኖር የነበረች ይህችው እና የአእምሮ ሁከት ይስተዋልባት ያልነበረው እህት ባልታወቀ ምክንያት ሊነጋጋ ሲል ከቆንስሉ ግቢ በር ታንቃ መገኘቷን እንዳስደነገጣቸው እማኞች በእንባ እየታጠቡ አስረድተውኛል።
“መረጃ ለጋዜጠኛ ከሰጣችሁ ከመጠለያ ትባረራላችሁ!” የሚል ማስጠንቀቂያ ከመጠለያ ሃላፊዎች የተሰጣቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እኒሁ የአይን እማኝ ተፈናቃዮች “ታመው የሚሰቃዩት እና እያበዱ የሚመጡት አህቶች ሁከትና ረብሻ የቀረነውን ሊያሳብደን ነው” ሲሉ ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ ገልጸውልኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሟች ማንነትና ተዛማጅ መረጃዎችን ለማሰባስብ ባደረግኩት ሙከራ ሟች ከመሞቷ ከአስር ቀን በፊት ከቆንሰሉ በመጠለያ ስትጨናነተቅ ያገኟት አንድ ኢትዮጵያዊ በጉዳዩ ተቆጭተው በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ያነሱትን ምስል አግኝቼ ተመልክቸዋለሁ። በዚሁ ተንቀሳቃሽ ምሰል ቪዲዮ ላይ ሟች የመጣችው ከወሎ ሃይቅ አካባቢ መሆኑን ያስረዳች ሲሆን አንድ አመት ከሰባት ወር የሰራችበትን ደመወዝ አረቦች ሰጥተው ከመጠለያው ቢጥሏትም ገንዘቧ የት እንደ ገባ እንደማታውቅ በትካዜ ስትገልጽ ትታያለች። የምትፈልጊው ምንድን ነው ብለው ሲጠይቋትም ወደ ሃገሯን ለመግባት ብትፈልግም ሊሳካላት አለመቻሉን ተስፋ ቆርጣ ስታስረዳ የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል ያሳያል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ከበርካታ ወራት በፊት አንድ ወንድም ወደ ቆንሰሉ ግቢ እንዳይገባ ተከልከሎ በቆየበት በር ህይወቱ ማለፉ አይዘነጋም ። አንዲት የኮንትራት ሰራተኛ በቆንስሉ ግቢ አትገቢም ተብላ በመታገዷ ራሷን ስታ እንደነበር ይታወሳል። ይህችው እህት ከቆንሰሉ አካባቢ በሚገኝ ዛፍ ተንጠልጥላ ሶስት ቀናት ከቆየች በኋላ ያለቸበት ሁኔታ ታውቆ ከዛፉ እንድትወርድ ሲያግባቧት አሻፈረኝ በማለት ራሷን ከዛፉ ወደ መሬት ወርውራ መግደሏ ራሷን አጥፍታለች።
ከሳምንት በፊት ታዋቂው የሳውዲ እለታዊ ጋዜጣ ሳውዲ ጋዜጥ ተቡክ ተብሎ በሚታወቀው የሳውዲ ግዛት አንድ ኢትዮጵያዊት ራሷን መግደሏን ማስታወቁን በቁጥር 2 ዝንቅ መረጃየ ላይ ዘግቤው ነበር። በተመሳሳይ ዜና በዚያው ከሳምንት ካሚስ ምሽት ተብሎ በሚታወቅ አንድ የሳውዲ ግዛት አንዲት እህት “ራሷን ገድላለች” ተብሎ ሬሳዋን ወደ ሃገር ቤት ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኑንም መረጃውን አቀብየ እንደነበር አይዘነጋም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዋና ከተማዋ በሪያድ አንዲት ኢትዮጵያዊት የ26 አመት ወጣት የኮንትራት ሰራተኛ “በአሰሪዎቿ ደረሰብኝ የምትለውን አስከፊ እንግልት ለመበቀል የ6 አመት የአስሪዎቿን ሴት ህጻን መግደሏን አምናለች” የሚል አንገት ሰባሪ ዜና የተሰማው ትናንት ሲሆን ዛሬ የወጡት የሳውዲ ጋዜጦችም መረጃውን ይፋ አድረገዋል።
በኮንትራት ሰራተኞች ዙሪያ ሊሰሙት የሚዘገንን መረጃ መተላለፍ ከጀመረ አመታት የተቆጠረ ቢሆን መንግስት ትኩረት ስላልሰጠበት ችግሩ ሲባባስ ቆይቷል። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን በስደቱ እየሆነ ላለው በሚመለከት ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ ዘጋቢ ፊልም ከታየ ወዲህ መንግስት ጉዳዩን ለመቆጣጠር ቁርጠኛ አቋም እንደሚወስድ ቃል መገባቱ አይዘነጋም።
ከኮንትራት ስራ ጋር በተያያዘ በሳውዲ አረቢያና ኢትዮጵያ መካከል የኮንትራት ሰራተኛን በሚመለከት የሁለትዮሽ ስምምነት እንደሌለ የጅዳው ቆንስል አቶ ዘነበ ከበደ በጀርመን ራዲዮ “እንወያይ” ፕሮግራም ተጋብዘው ባደረጉት ውይይት ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ከሶስት አመት በፊት በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 120 ሺህ ገደማ ይገመት የነበረ ሲሆን የኮንትራት ሰራተኞች ያለ ሁለትዮሽ ሰምምነት መምጣት ከጀመሩበት ካሳለፍነው ሶስት አመት ወዲህ የኢትዮጵያውያኑ ቁጥር 500 ሺህ መድረሱ ይገመታል።
(ነቢዩ ሲራክ በፌስቡክ ገጹ “ከዝንቅ መረጃ” አምዱ ካቀረበው የተወሰደ)
Leave a Reply